Monday, 18 May 2020 00:00

ኢትዮጵያ እጇን መስጠት የለባትም!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)

 ግብፆች የአሜሪካንን መንግሥትና የዓለም ባንክን ወደ ሕዳሴው ግድብ ድርድር እንዲገቡ የፈለጉትና ያደረጉትም ሁለቱ ለእነሱ ፍላጎት መሳካት ያላቸውን ታማኝነት አይተው መሆኑ በተግባር ተረጋግጧል፡፡
በሞኝ ክንድ የዘንዶ ጉድጓድ ይለካል እንዲሉ፣ በቅንነት በገባበት ድርድር በእባቦች የተነደፈው የኢትዮጵያ መንግሥት፤ አሜሪካና የዓለም ባንክ ከታዛቢነት ወንበር አልፈው እንደ ጀመሩት አደራዳሪነትና ውል አርቃቂነት ለመግባት ከፈለጉ እና ውል የማርቀቁ ሥራ ለሦስቱ ተደራዳሪዎች ብቻ እስከ አልተው ድረስም ወደ ድርድሩ እንደማይመለስ አሳውቋል፡፡ ይህ ተገቢና የሚመሰገን እርምጃ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በአሜሪካ ይካሄድ የነበረውን ድርድር ጥሎ ሲወጣ የራሱን የመደራደሪያ ሀሳብ እንደሚያቀርብ በገለጠው መሠረት የድርድር ሀሳቡን ሰሞኑን አቅርቧል፡፡ መደራደሪያው የቀረበው ግብፅ አንድ አይነት ስምምነት ሳይደረግ ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብ መሙላት ብትጀምር የአካባቢውን ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታ ሊያናጋው ይችላል የሚል ምክንያት በመደርደር፣ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የፀጥታው ምክር ቤት ጥያቄ ባቀረበችበት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡
የግብፅ አቋም ሳይታለም የተፈታ ቢሆንም፣ ዓለም ባንክና የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ያረቀቁትን ስምምነት ለማውገዝ በተሰበሰበው የአረብ ሊግ ስብሰባ ላይ ተቃውሞ ያሰማችውና ስሟ ከአውጋዦች ዝርዝር ውስጥ እንዳይገባ ያደረገችው ሱዳን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረበውን አዲስ የስምምነት ሀሳብ እንደማትቀበል ገልጻለች፡፡ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶኪ የቀረበውን ረቂቅ ስምምነት ውድቅ ያደረጉት የሕግ ጥያቄዎችን አይመልስም፤ ግድቡ ስለሚያስከትለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ አይገልፅም በማለት መሆኑን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ይህ ጉዳይ ግን ያልታሰበበት ሳይሆን ታስቦ የተሰራበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከሶስቱ አገሮች ተውጣጥቶ ለተቋቋመው የሙያተኞች (ኤክስፐርቶች) ቡድን ካቀረበቻቸው 153 ሰነዶች ውስጥ የተካተተ ጉዳይ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ለሁለቱ አገሮች ሙያተኞች ከተጠቀሱት ሰነዶች በተጨማሪ 103 ንድፎችና ሰባት ካርታዎች እንዲመረምሩ የሰጠችው በሳለችው ቢላዋ ለመታረድ ሳይሆን አብሮ ለመሥራትና አብሮ ለመልማት ካላት ትልቅ ፍላጎት መሆኑ ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባል፡፡
አሁን ኢትዮጵያ ይበልጥ ልታስብበት የሚገባው ከሱዳን ድጋፍ ማጣቷን ሳይሆን የላይኛውን የዓባይ ተፋሰስ አባል አገራት ድጋፍ መልሶ በማሰባሰብና ከጎኗ እንዲቆሙ በማድረግ ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ድርድር ተሸነፈች ማለት የእርሷ የመልማት እድል ብቻ ሳይሆን የሚበላሸው የላይኛዎቹም የተፋሰሱ አባል አገራት መሆኑ በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡
አልጄዚራ፤ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የመደራደሪያ ሀሳብ አለመቀበሏን መነሻ በማድረግ አሠራሁት ያለውን የጥናት ውጤት አቅርቧል፡፡ በጥናቱ መሠረት፤ ኢትዮጵያ በሃያ አንድ ዓመት ውስጥ የሕዳሴውን ግድብ ለመሙላት ብትነሳ፣ በየዓመቱ ግብፅ ከምታገኘው ውኃ 5%  በመቶ እንደምታጣና የእርሻ ምርቷም 2.5% እንደሚቀንስ ያስረዳል፡፡ የግድቡ ሙሌት በአስር ዓመት ውስጥ ቢከናወን ደግሞ ግብጽ በየዓመቱ 8 ቢሊዮን ሜትር ኩዩብ ውኃ እንደማታገኝና የእርሻ ምርቷም 18 በመቶ እንደሚያዘቀዝቅ ያስረዳል:: ግድቡ በአምስት ዓመት ውስጥ ይሞላ ከተባለ፣ ግብፅ በየዓመቱ 20 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ ሊደርሳት እንደማይችልና የእርሻ ምርቷ 36% በመቶ እንደሚያሽቆለቁል አልጄዚራ ይተነትናል፡፡
የሚያሳዝነው አንድም ቦታ አልጄዚራ፣ ኢትዮጵያ ከሕዳሴው ግድብ ልታገኝ የምትችለውን ጥቅም ለመጥቀስ አለመቻሉ ወይም አለመፈለጉ ብቻ ሳይሆን ወደ ግድቡ የሚገባው ውሃ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጭቶ የሚወጣ መሆኑንም ለመናገር አለመፍቀዱ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ግድቡን በአምስት ዓመት ውስጥ ለመሙላት ከፈለገች፣ የግድቡ የውኃ መቋጠር መጠን 74 ቢሊዮን ሜትር ኩዩብ በመሆኑ፣ በአመት ለመያዝ የምትገደደው ወይም የሚያስፈልጋት 15 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ሲሆን አልጀዚራ ግን ለግብፅ ባለው አድሏዊነት የሌለውን ፍላጎት እንዳለ አድርጎ አቅርቧል፡፡  
በመላው ዓለም እንዲህ እየተካሄደ ያለው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ መመከት እንዳለበት ሊታመን ይገባል፡፡ የአዲስ አበባው የአልጄዚራ ቢሮ ሊጠየቅና መልስ ሊሰጥበት ያስፈልጋል፡፡ መልስ መስጠት ባይገደድ እንኳ 40% በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በዓባይ ገባር ወንዞች ተፋሰስ ስር እንደሚኖርና ይህ ሕዝብ የመልማትና የማደግ መብት እንዳለው፣ የአካባቢው የተፈጥሮ ሀብት እጅግ የተራቆተ በመሆኑ የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ሊካሄድለት እንደሚገባና በምግብ ራሱን ያልቻለ በመሆኑም በአካባቢው የሚገኝን መሬት በመስኖ ማልማትና ራሱን ከተረጅነት መታደግ መቻል እንዳለበት አመዛዛኝ ሪፖርት እንዲሰራ መገፋፋት ይኖርበታል፡፡
በዚህ ሰዓት የግብጽ ሱሪያችሁን ካልፈታችሁ ወይም ካላስፈታችኋችሁ ጥያቄና ግብ ግቡ ለምን መጣ?
ከአምስት ወር በፊት በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ውስጥ ዋናው መነጋገሪያ በ2012 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው አገር አቀፍ ምርጫ ነበር፡፡ በሕዝቡ መካከል ለ27 ዓመት የተዘራው ዘረኝነት፣ አንዱ በሌላው ላይ ያሳደረው ጥላቻና መጠራጠር ሳይወገድ፣ አልፎም በየአካባቢው የተቀሰቀሰው ግጭት ሳይበርድና ሰዎች ወደ መኖሪያቸው ሳይመለሱ እንዴት ሆኖ አገር አቀፍ ምርጫ ይካሄዳል የሚሉትም እና በአካባቢያቸው ብሔራቸውን የሥልጣን ባለቤት ማድረግ በሚፈልጉ መካከል የጦፈ ክርክር ነበር፡፡ ምርጫው ከግንቦት ወር ወደ ነሐሴ ተገፋ፡፡
በቻይና በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ የተቀሰቀሰው ኮሮና፣ በመጋቢት 2012 መጀመሪያ ላይ ወደ አገራችን ገባ፡፡ የነሐሴውን ምርጫ የማይታሰብ አደረገው:: አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከመስከረም 30 ቀን 2013 በኋላ የምርጫ ዘመኑ ስለሚያልቅ፣ አገር መንግሥት አልባ ትሆናለች፤ መላ ይፈለግ የሚል ጥያቄ ተቀጣጠለ፡፡ ወትሮም ለችግሮች በራሱ መንገድ መፍትሔ የሚፈልገው መንግሥት፤ የራሱን የመፍትሔ ሀሳብ ማለትም ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም መጠየቅ የሚል ሀሳብ ይዞ መጣ፡፡ ሀሳቡን የሚቀበለው እምብዛም ሆነ፡፡ እሱም ችግሩን መፍታት ባለመቻሉ፣ አሁን መንግሥትና ተቃዋሚዎች እርስበርስ እየተካሰሱ ናቸው፡፡
አገር የመምራት ኃላፊነት ይዞ የሚገኘው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት፣ በሶስቱ ጉልቻዎች ማለትም የኮቪድ 19 በሽታ፣ ከግብፅ ጋር እየተካሄደ ያለው የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሌት ድርድር እንዲሁም መቼ እንደሚሆን ባይታወቅም ምርጫ ተደርጎ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ሥልጣን እስከሚይዝበት ጊዜ ድረስ የመንግሥትን ሥልጣን ከእነ ሙሉ ጉልበቱ ማቆየት ጥያቄ ላይ ተጥዶ ይገኛል፡፡
ድሮም ቢሆን ተደራድረው ተግባብተው፣ አንዱ የሌላውን ሀሳብ ተቀብሎ ከአንድ ግብ ከማያደርሱ ተቃዋሚዎች፣ ሕዝብ ምንም በጎ ነገር ሊጠብቅ እንደማይችል የታወቀ ነው፡፡
መንግሥት ግን ሕዝብንና አገርን ማዳን አለበት፡፡ ሕዝብን ማዳን ማለት ኮቪድ-19ን መከላከል ሲሆን አገር ማዳን ማለት ደግሞ የሕዳሴ ግድብ ድርድርን በአሸናፊነት መወጣት ማለት ነው፡፡
አንድ ራሱን ቆሞ እንኳን ቢሆን መሟገት እንጂ እጁን ለግብፅ መስጠት የለበትም፡፡
ተቃዋሚዎችም ቢሆኑ የሚፈጥሩት የአገር ውስጥ ሁከት የሚጠቅመው ለግብፅ መሆኑን መረዳት አለባቸው፡፡ የወርቅ እንቁላል የምትጥል ዶሮ ማረድ ወርቅ አያስገኝም፡፡
የግብፆች አንዱ ኢትዮጵያን የማዳከም ሥልት ደግሞ የውስጥ ችግሮችን ማባባስ ነው፡፡ መንግሥት ሆይ፤ ብልህ ሁን፡፡       


Read 1942 times