Saturday, 16 May 2020 12:04

ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ - በምርጫ ማራዘምና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

     • የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ ሕገ መንግሥታዊ ድጋፍ አለው
            • ብሔራዊ አደጋዎችን በመግባባት ልንሻገራቸው ይገባል      
           • የራሱ ጽ/ቤት የሌለው ፓርቲ አገር ለመምራት ማሰብ የለበትም

         ከተመሰረተ የአንድ ዓመት ተኩል ብቻ ዕድሜ ያለው ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ፤ በነሐሴ ወር ይካሄዳል ተብሎ ታቅዶ ለነበረው አገራዊ ምርጫ ራሱን ለማዘጋጀት የተቻለውን ሁሉ ሲያደርግ እንደነበር ይገልጻል፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለምም ጭምር የተከሰተው የኮቪድ ወረርሽኝ ግን ከቀድሞው የተሻለ የምርጫ ዝግጅት እንዲያደርጉ እድል እንደሰጣቸው የፓርቲው ሊቀመንበር ያስረዳሉ፡፡ አገሪቱ ከኮቪድ - 19 በተጨማሪ ሌሎች ብሄራዊ አደጋዎች ተደቅኖባታል በሚለው የመንግሥት ሀሳብ ላይ እንደሚስማማ የሚገልፀው ፓርቲው፤ እነዚህን አደጋዎች በአንድነትና በጋራ መሻገር እንደሚገባ ያምናል፡፡
ከተቋቋመ ዓመት ከ6 ወር ብቻ ያስቆጠረው ‹‹ነፃነትና እኩልነት›› ፓርቲ፤ ፓርቲው እስካሁን ሰነዶች ካዘጋጀላቸው አበይት ጉዳዮች መካከልም ብሄራዊ መግባባትና እርቅ እንዲሁም ከሰሞኑ አወዛጋቢ ሆኖ የዘለቀው የሕገ መንግሥት ችግርና የመውጫ መንገዶችን ያመላከተበት ሰነድ ተጠቃሽ ነው፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የፓርቲውን ሊቀ መንበር ዶ/ር አብዱል ቃድር አደምን በወቅታዊ ጉዳዮችና በፓርቲው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡


             የራሳችሁን የሕገ መንግሥቱን ችግር መፍቻ ምክረ ሀሳብ ቀድማችሁ አቅርባችሁ ነበር?
ኮቪድ 19 ከመምጣቱ በፊት ጀምሮ ምርጫው ይካሄድ አይካሄድ በሚል ብዙ ክርክሮች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ በኋላ ምርጫው እንዲካሄድ መንግሥትና የምርጫ ቦርድ ወስነው ወደ ዝግጅት ተገብቶ ነበር:: በመጨረሻ ግን ከሁላችንም ቁጥጥር ውጪ የሆነው ወረርሽኝ መጣ፡፡ በዚህም ምርጫውን ማካሄድ እንደማይቻል ሁሉም ከስምምነት ላይ ደረሰ፡፡ ምርጫ ቦርድም በዚህ ጉዳይ ፓርቲዎችን ሰብስቦ ሀሳብ እንድንሰጥ ጠይቆን ነበር፡፡ በጊዜው እኛም ተገኝተን ምርጫውን ማካሄድ አይቻልም፤ የዜጎችን ሕይወት አደጋ ውስጥ ማስገባት ይሆናል የሚል ውሳኔ ላይ ሁላችንም ፓርቲዎች ደርሰናል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው የሕገ መንግሥት ችግር የተፈጠረው። እኛም እንደ ፓርቲ ወዲያው ጉዳዩን በጥሞና ተመልክተን፣ ባለሙያዎችም ጭምር አማክረን፣ ይሄ ጉዳይ እንዴት ነው መፍትሄ የሚያገኘው ብለን ውይይት አደረግን፡፡ በዚህ መነሻ በባለሙያዎች የታገዘ ዝርዝር አማራጮችን የያዘ ሰነድ አዘጋጀን፡፡ ምናልባትም ከመንግሥትም በፊት አራት አማራጮችን ይዘን የመጣነው እኛ ነን ማለት ይቻላል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ገዥው ፓርቲ የራሱን አራት አማራጮች ይዞ የመጣው። ገዥው ፓርቲ ይዞ ከቀረባቸው አራት አማራጮች ሶስቱ ከኛ ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡ የምንለያይበት አንደኛው አማራጭ የሽግግር መንግሥት ነው፡፡ እኛ የሽግግር መንግሥት ተመራጭ ነው ባንልም፣ እንደ አማራጭ ከእነ ችግሮቹ አቅርበን ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ሌሎች ፓርቲዎች ተመሳሳይ አማራጮችን ይዘው ቀርበዋል፡፡ እኛ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ የተሻለ አማራጭ ነው ብለን ነው የመረጥነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ከዚህ ብዙም ባልራቀ ሁኔታ የሕገ መንግሥት ትርጉምን አማራጭ አድርጎ ተቀብሏል። በቀጣይ የመጨረሻ ውሳኔ ሲሰጥበት የምናየው ነው የሚሆነው፡፡
ምርጫው በኮቪድ - 19 ምክንያት ከመራዘሙ በፊት እናንተ ለምርጫው ምን ያህል ዝግጁ ነበራችሁ?
ጊዜው በጣም ጠባብ ነበር፡፡ ሆኖም ማድረግ የምንችለውን ያህል ዝግጅት ስናደርግ ነው የቆየነው፡፡ ከ20 የሚበልጡ የፖሊሲ ሰነዶችን እንዲሁም የምርጫ ማኒፌስቶ ማዘጋጀት፣ አደረጃጀቱን የማስፋትና በየክልሉ ቢሮ የመክፈት ስራዎችን እየሰራን ነበር፡፡ ወደ እጩ ምልመላም ለመግባት እየተንቀሳቀስን ነበር:: ለምርጫው በሙሉ አቅማችን እየሰራን ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን መራዘሙ ደግሞ ያልሰራናቸውን እንድንሰራ ተጨማሪ ጊዜ ሰጥቶናል፡፡ አገሪቷም የተረጋጋ የሽግግርና የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የምታደርግበት ዕድል አግኝታለች፡፡
መንግሥት ከኮሮና በተጨማሪ ሌሎች ብሄራዊ አደጋዎች እንደተደቀኑበት ገልጿል:: ፓርቲያችሁ አገሪቱ ከሌሎች ብሄራዊ አደጋዎች ተደቅኖባታል ብሎ ያምናል?
እንደ አደጋ የሚገለጽ ነገር ካለ ከኮቪድ 19 ቀጥሎ የምናየው የአደጋ ስጋት ከህዳሴ ግድቡ ጋር በተያያዘ ያለው ነገር ነው፡፡ በተለይ ከግብፅ ጋር የገባነው ፍጥጫ አንድ ትልቅ ብሄራዊ አንድነታችን የሚፈልግ አደጋ ነው፡፡ ይሄን አጣብቂኝ ለመፍታት በኛ በኩል እንደ አንድ መፍትሄ የምናስቀምጠው፣ በማንኛውም መንገድ ቢሆን፣ አንድ ጠንካራ መንግሥት መኖር አለበት የሚል ነው፡፡ ይሄ ለድርድር መቅረብ የለበትም። ምክንያቱም እንደ ህዳሴው ግድብ ያሉ ትልቅ አጀንዳዎችን በብቃት በትኩረት ሊመራ የሚችል መንግሥት ከሌለ ችግር ውስጥ እንገባለን የሚል እሳቤ ነው ያለን፡፡ በተለይ ከግብፅ በኩል የምንሰማው ዛቻና ማስፈራራት ጉዳዩ ትልቅ ዝግጅትና ህብረትን የሚፈልግ ብሄራዊ አደጋ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ብለን መውሰድ እንችላለን፡፡ ሌላው አሁን ላይ ቢቀንስም የአንበጣ ወረርሽኝ ትልቁ አደጋ ነው፡፡ ይሄም ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ የምግብ ዋስትናን አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ነው፡፡ እነዚህ ብሄራዊ ስጋቶች ምንም ጥርጥር በሌለው ሁኔታ በመግባባት ልንሻገራቸው የሚገቡ ናቸው፡፡
ከምርጫው ጋር ተያይዞ መንግሥት የሕገ መንግሥት ትርጉምን እንደ መፍትሄ ወስዷል፡፡ በዚህ ላይ የፓርቲያችሁ አቋም ምንድን ነው?
እኛ አቅርበነው የነበረው መፍትሄ፣ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 58 (3) ማሻሻል የሚል ነው፡፡ ሌሎች ያቀረብናቸው ፓርላማ መበተን የሽግግር መንግሥት መመስረትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚሉ ነበሩ፡፡ እነዚህን በዝርዝር ከእነ ጉድለታቸው አቅርበናል፡፡ ነገር ግን ከሁሉም ተመራጭ ሆኖ ያገኘነው አንቀጽ 58(3) ስለ ምርጫ የሚደነግገውን ማሻሻል የሚለውን ነበር፡፡ ይህ ከአተገባበር አንፃርም ቀላል ነው፡፡ አሁን በመንግሥት ወይም ገዥው ፓርቲ በኩል የተመረጠው መፍትሄ ትርጉም መጠየቅ ነው፡፡ ይሄን እኛም ሀሳቡን እናደንቃለን፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እኛ የምንጠይቀው ሂደቶች በሙሉ ግልጽና አሳታፊ እንዲሆኑ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ግን አማራጩ ሕገ መንግሥታዊ ድጋፍ አለው፡፡ በሌላ በኩል፤የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ ማለት የሕገ መንግሥት ማሻሻያ አንዱ አካል ነው፡፡ የሕገ መንግሥት ባለሙያዎች እንደሚሉት ትርጉም መጠየቅ ራሱ አንድ የማሻሻያ አካል ነው፡፡
ምርጫው እንዴትና መቼ ቢካሄድ ተመራጭ ይሆናል ትላላችሁ? በሕገ መንግሥት ትርጉም ወቅትስ የእናንተ ተሳትፎ ምን ይመስላል?
የሕገ መንግሥት ትርጉሙን በተመለከተ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤው በጉዳዩ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ የተለያዩ አካላትን ሀሳብ እንዲወስድ ሀሳብ አቅርበናል:: የምርጫው ወቅትም በጊዜ ገደብ መታሰር አለበት፡፡ የኮሮና ስጋት ከቆመበት ጊዜ ጀምሮ ቢበዛ ከአንድ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ምርጫ እንዲካሄድ ነው የጠየቅነው፡፡ የኮሮና ችግር መቼ እንደሚወገድ ማንም ዛሬ ላይ ቆሞ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይችልም:: እኛ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይቆማል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ስጋቱ ከቆመበት ጊዜ ጀምሮ ግን ወደ ምርጫ መገባትና በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ አለበት፡፡
በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እየተፈጠረ ያለው የፍላጎት መራራቅ ብሄራዊ ስጋቶችን ያባብሳል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እናንተስ ምን ስጋት ትጋሩታላችሁ?
የሁሉም ፓርቲዎች አቋም በማንኛውም ጉዳይ አንድ አይነት እንዲሆን አይጠበቅም፡፡ በብሄራዊ ጥቅም ጉዳይ ግን እስካሁን የተለየ ያፈነገጠ ሀሳብ ያለው ፓርቲ አላጋጠመንም:: በተለይ ብሄራዊ የምንለው አንዱ የዓባይ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ሁሉም ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ከኮቪድ ጋር በተያያዘም ምርጫው መራዘሙን ሁሉም ይደግፋል:: ይሄ አንድ ብሄራዊ ጉዳይ ነው፡፡ ችግሩ ያለው ምርጫው ከተራዘመ በኋላ ያለውን የሥልጣን ክፍተት እንዴት እንሙላው በሚለው ላይ ነው፡፡ ያሉት ልዩነቶች ግን ያን ያህል የሚጋነኑ አይደሉም፡፡ ብሄራዊ ጥቅምን አደጋ ላይ የሚጥሉም አይደሉም:: በሰለጠነ መንገድ ተወያይተን ልንፈታቸው የምንችላቸው ናቸው፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት አለ፡፡ እሱ ያወጣው መግለጫም ውይይት መደረግ እንዳለበት ነው ያመላከተው፡፡ ስለዚህ ተነጋግሮ መፍታት የሚቻል ጉዳይ ነው፡፡
ለምርጫው መራዘም ምክንያት ለሆነው የኮቪድ - 19 ወረርሽኝ መንግሥት እየሰጠ ያለውን ምላሽ እንዴት ታዩታላችሁ?
ከሞላ ጎደል መንግሥት የሚቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው ብለን እናስባለን:: ይሄ ወረርሽኝ አለማቀፍ ነው፡፡ በዚህ መጠን ወረርሽኝ የተከሰተበት ተሞክሮ በአለም የለም:: በአገርም ደረጃ ተመሳሳይ ነው፡፡ በዚያ ላይ የኛ መሠረተ ልማት፣ ኢኮኖሚያችን ደካማ ነው፡፡ ከሌሎች የበለፀጉ አገራት አንፃር ስናየው፤ መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች የሚደገፉ ናቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችም መንግሥትን መደገፍ አለብን:: በዚህ ጉዳይ የጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት አንድ ስብሰባ ጠርቶን ነበር፡፡ ሁላችንም ተገኝተን ተነጋግረን በጋራ እንሰራለን የሚል ድምዳሜ ላይ ነበር የደረስነው። ከዚያም አልፎ ከየፓርቲዎቹ ተወካዮችን ለጠ/ሚሩ ቢሮ እንድንልክ ተጠይቀን ዝርዝር ልከን ነበር:: ነገር ግን ከዚያ በኋላ እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ግንኙነት የለንም፡፡ በድጋሚ ተወካዮቹ አልተጠሩም፡፡ በጋራ ተወያይቶ እቅድ ነድፎ እንቅስቃሴ ይደረጋል የሚል ግምት ነበረን:: ነገር ግን ይሄ አልተደረገም፡፡ ያ ስብሰባም ከሚዲያ ግብዓትነት ያለፈ ትርጉም አልነበረውም፡፡ መንግሥት አሁንም ቢሆን ፓርቲዎችንም ሆነ ሌሎች አካላትን በዚህ ጉዳይ ለማሳተፍ ቁርጠኛ መሆን አለበት፡፡
ፓርቲያችሁ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን ከሰጣችኋቸው መግለጫዎች መረዳት ይቻላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ድጋፍ በፓርቲ ደረጃ ብዙም የተለመደ አይደለምና እንዴት አሰባችሁት?
እርግጥ ነው ሀሳባችን የነበረው ሁሉም አካል የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ አርአያ ለመሆን እንጂ ያደረግነው ድጋፍ ያን ያህል ብዙ አይደለም፡፡ ድጋፍ እናድርግ ብንልም የሚቻል አይደለም፡፡ የገንዘብ አቅም ውስንነት አለ፡፡ ግን አንድ መልዕክት ማስተላለፍ ነበር የፈለግነው፤ ይኸውም የአደጋውን ግዙፍነትና የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፈልገው ለማሳየት ነው፡፡ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን የሕብረተሰቡ ለሕክምና ባለሙያዎች ሰጥተናል:: ለወደፊትም ይሄን ለማድረግ በዋና ቢሯችንም ሆነ በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶቻችን በኩል ዝግጅቶች እያደረግን ነው፡፡
በትግራይ ክልል መንግሥትና በፌደራሉ መካከል ያለው የፖለቲካ መካረር እንዴት መፍትሄ ሊያገኝ ይችላል ብላችሁ ታስባላችሁ?
የትግራይ ክልል ከምርጫው ጋር በተያያዘ ያለው አቋም ግልፅ አይደለም:: በትግራይም ሆነ በሌላውም ክልል በዚህ ሰዓት ምርጫ ማካሄድ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው፡፡ ይሄ አካሄድ ግጭት ውስጥ እንዳያስገባ እኛም ስጋት አለን፡፡ እኛ የምንመክረው ክልሉ የያዘውን አቋም እንደገና እንዲፈተሽ ነው፡፡ ትግራይም ሆነ ሌላው ክልል ከእንዲህ ያሉ አቋሞች እንዲቆጠቡ ነው የምንጠይቀው፤ ምክንያቱም ጉዳዩ ሄዶ ሄዶ በጎ ውጤት የለውም፡፡
ብዙ ጊዜ የሌሎች ፓርቲዎች ጽ/ቤቶችንና የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን እየዞራችሁ ትጎበኛላችሁ፡፡ ይሄም ብዙ የተለመደ አይደለም?
የኛ አገር ፖለቲካ እንደሚታወቀው በርካታ ችግሮች አሉበት፡፡ አንደኛው ግልጽነትና አብሮ የመስራት ባህል ብዙም የለንም፡፡ ብዙውን ጊዜ ሁላችንም በራሳችን አጥር ውስጥ ብቻ ነው የምንንቀሳቀሰው፡፡ እኛ ይሄ መቀጠል የለበትም በሚል፣ ከኛ ጋር የሚያመሳስል አላማ ያላቸውን ፓርቲዎች ቢሮ ሄደን እንጎበኛለን፡፡ እንወያያለን:: የመንግሥት ቢሮዎችንም ሄደን በይፋ እንጎበኛለን፡፡ ይሄን የምናደርገው እነሱ እየሰሩ ያለውን ስራ በተግባር ለመረዳት የማሻሻያ ሀሳብ ካለንም ለማጋራት ነው፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የነበረን የጉብኝት መርሃ ግብር በአብዛኛው አብረን እንዴት እንሰራለን በሚለው ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ከእነዚህ ውይይቶችም ብዙ ጥቅም አግኝተናል፡፡ እያንዳንዳችን ያለንን የአመለካከት ልዩነትም ተገንዝበንበታል፡፡ አንዳንዱ በብሄር ጉዳይ ላይ ጽንፍ የረገጡ አቋሞችን ያራምዳል:: ሌላው የአንድነት ሀይል ነን በሚል ጽንፍ የረገጡ ሀሳቦችን ያራምዳል፡፡ ግን ከእነዚህ ጋር ሁሉ እንዴት በጋራ ጉዳይ ላይ አብረን መሥራት እንችላለን የሚለውን ነገር ነው በውይይታችን እየተገነዘብን የመጣነው፡፡ ሌሎች ፓርቲዎችም በዚህ መሰል ግንኙነት፣ የሌሎችን ሀሳብና አቋም እንዲገነዘቡ እንመክራለን፡፡
የፓርቲያችሁ ራዕይና ግብ ምንድን ነው?
ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ለወደፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ግዙፍና የመጀመሪያው የመሆን ራዕይ ነው ያለው፡፡ ይህን ለመሆን የሚያስፈልጉትን ነገሮች በሀሳብ ደረጃ ወረቀት ላይ አስቀምጠናል፡፡ የራሳችንን የጽ/ቤት ሕንፃ እስከ መገንባት የሚደርስ እቅድ ነው ያለን:: አንድ ፓርቲ ማለት የወደፊት እጩ መንግሥት ነው፡፡ ይሄን መረዳት ያስፈልጋል:: ስለዚህ የራሱ ጽ/ቤት የሌለው ፓርቲ አገር ለመምራት ማሰብ የለበትም:: አገርን ተረክቤ አስተዳድራለሁ የሚል ፓርቲ፣ የራሱን መቀመጫ ጽ/ቤት በራሱ አቅም መገንባት አለበት የሚለው አቋማችን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የራስ ሕንፃ ላይ ጽ/ቤት ያለው ፓርቲ እንዲሆን ነው ትልቁ አላማችን፡፡ ይሄ ራዕያችንንና መዳረሻ ግባችንን አስፍተን እንድናይና ለአላማችን ቁርጠኛ እንድንሆን ያደርገናል፡፡

Read 5093 times