Saturday, 16 May 2020 11:37

የቫይረሱን ስርጭት መግታት ይቻላል? ቫይረሱን ማጥፋትስ?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የቫይረሱን የስርጭት ፍጥነት መቀነስ፤ በሰፊው እንዳይዛመትም መገደብ እንደሚቻል በየአገሩ በግልጽ ታይቷል፡፡ እጅን አዘውትሮ በሳሙና ከመታጠብና የግል ርቀትን ከማክበር ጀምሮ፣ የእንቅስቃሴ ቁጥብነትና የለይቶ ማቆያ ስፍራ፣ የምርመራና የሕክምና አሰራሮችን ጨምሮ፣ አገር ምድሩን ‹‹ኳራንቲን›› እስከ ማድረግ የደረሱ እርምጃዎች የቫይረሱን የስርጭት ፍጥነት ለማርገብ፤ በሰፊው እንዳይዛመት ለመከልከልም ረድተዋል፡፡
የደቡብ ኮሪያና የታይዋን አይነት እርምጃ አለ፡፡ መፈናፈኛ የሚያሳጣ የቻይና አይነት እርምጃም ሊጠቀስ ይችላል፡፡ አገሩን ሙሉ ባትቆልፍም በውሃን ከተማ ከ10 ሚ. በላይ ነዋሪዎች ለሁለት ወራት ከቤት እንዳይወጡ ተዘግቶባቸዋል፡፡
የእነ ፈረንሳይ ደግሞ ‹‹ሕግና ሥርዓት›› የጎላበት የእንቅስቃሴ ገደብ የመኖሩን ያህል፤ ለነዋሪዎች ስነ ምግባር ሰፊ ቦታ የሚሰጥ የስዊድን መንገድም ሌላ ተጠቃሽ የመከላከያ አቅጣጫ ነው፡፡ የአሜሪካ ከሁሉም ይለያል - የፍሎሪዳና የኒውዮርክ ለየቅል ነው፡፡ መደናበር፣ ግራ መጋባት፣ ግርግርና ግጭት የተከሰተባቸው፣ አገርን የመዝጋት ድንገተኛ ትዕዛዝ የታወጀባቸው እንደ ህንድና ደቡብ አፍሪካ የመሳሰሉ አገራትም አሉ፡፡
የጥንቃቄ እርምጃዎች፣ በየአገሩ የመለያየቱን ያህል፤ በአገር ኢኮኖሚና በዜጎች ኑሮ ላይ የሚያደርሰው ጉዳትና ኪሳራ ቢለያይም፣ በተወሰነ ደረጃ የየቫይረሱን ስርጭት በየአገሩ ለማርገብ አገልግለዋል፡፡ የአንዳንዶቹ አገራት ውጤት ከሌሎች የተሻለ ወይም እጅግ የላቀ ሆኖ መታየቱ፤ ከየአገራቱ ጥረትና ጥበብ ጋር ግንኙነት እንደሚኖረው አያከራክርም፡፡ ነገር ግን፤ ስሌት ውስጥ መግባት ያለባቸው በርካታ ነጥቦች አሉ፡፡
የአውሮፕላን በረራዎች ላይ እገዳ መጣል፤ በሁሉም አገራት ውስጥ ተመሳሳይ ለውጥ አያስገኝም፡፡ ጣሊያን ከማንም በፊት ነበር ወደ ቻይና የአውሮፕላን በረራዎችን ያቋረጠች፡፡ ከኢትዮጵያ በፊት በርካታ የአፍሪካ አገራት፤ የበረራ እገዳ አውጀዋል፡፡ ነገር ግን፣ ከቻይና የሚመጡ በረራዎችን ማገድ ማለት፣ ሰዎች ከቻይና በሌላ አገር በኩል አሳብረው እንዳይመጡ ያግዳቸዋል ማለት አይደለም፡፡ በረራዎቹን ከማገድ ይልቅ፤ የተሳፋሪዎች መነሻ ቦታ በትክክል አውጆ፣ የማጣሪያና የምርመራ ጥንቃቄዎችን ማሻሻል፣ ተመራጭ ዘዴ ሆኗል - ለኢትዮጵያ፡፡ ደግሞም በተግባር ታይቷል፡፡ ያኔ፣ የሌሎች አገራትን ውሳኔ በጭፍን በመኮረጅ የአውሮፕላን በረራዎች ቢቋረጥ ኖሮ፤ አንድ ሁለት ተብለው ከሚቆጠሩ የአገራችን ዘመናዊ ስኬቶች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ የኪሳራና የእዳ ሸክሙ በዝቶ፣ ህልውናውን እስከ ማጣት ሊደርስ ይችል ነበር፡፡ በእርግጥ፣ በረራዎችን በጥድፊያ አለማገድ፣ ለኢትዮጵያ ተገቢ ቢሆንም፣ ለጣሊያን ግን አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ማገናዘብ ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተሳፋሪዎች በአብዛኛው በኢትዮጵያ በኩል ወደ ሌሎች አገራት የሚጓዙ እንጂ እዚሁ የሚቆዩ አይደሉም፡፡ ጎብኚ የሚበረክትባቸው ወራትም ከጥር ወር በፊት መሆናቸው ሌላው አጋጣሚ ነው፡፡ የጣሊያን ሁኔታ ከዚህ ይለያል፡፡  ከአለማችን ቀዳሚ የቱሪዝም መናኸሪያ አገራት መካከል አንዷ ናት፤ጣሊያን፡፡ ፈረንሳይም እንደዚሁ የቱሪዝም ማዕከል ናት፡፡ ወደ ኢትዮጵያ በቀን በአማካይ 3 ጎብኚዎች ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ወደ ፓርክ ብቻ በየዕለቱ በአማካይ ከ40 ሺ በላይ ጎብኚዎች ይጎርፋሉ፡፡
እነ ጣሊያን እና እነ ፈረንሳይ፣ ከሌሎች አገራት… ከእነ ደቡብ ኮሪያና ከእነ ጃፓን በላይ ለኮሮና ቫይረስ በፍጥነትና በሰፊው ቢጋለጡ አይገርምም፡፡ ኒውዮርክም እንደዚሁ፡፡ ዋናዎቹ የቱሪዝም ገበያዎች ናቸውና፡፡  ነገር ግን፣ ከጥንቃቄ እርምጃዎችና ከቱሪዝም ብዛት በተጨማሪ ሌሎች ጉዳዮችም አሉ፡፡ እንደ ጣሊያንና እንደ ፈረንሳይ፣ ግሪክም የቱሪዝም ማዕከል ብትሆንም፤ በኮሮና ቫይረስ አልተጥለቀለቀችም፡፡ ግብፅም ብትሆን በጣም አልተጎዳችም፡፡ እነ ሎሳንጀለስና የፍሎሪዳ መዝናኛ ከተሞችም የኒውዮርክን ያህል አልተጎዱም፡፡ ምናልባት ሞቃታማ፣ ፀሐያማ የአየር ፀባይ፣ የቫይረሱን የስርጭት ፍጥነት ለመቀነስ ረድቷቸው ሊሆን ይችላል፡፡  በአጠቃላይ፤ የቫይረሱ የስርጭት ፍጥነትና ስፋት፣ ከቫይረስ ባህርይ ጀምሮ፣ የበርካታ መንስኤዎችና ሰበቦች፣ ሁኔታዎችና መከላከያዎች ውጤት ነው፡፡   

Read 1520 times