Print this page
Saturday, 16 May 2020 12:00

ዘንድሮ በክልሉ ምርጫ ከማካሄድ ወደ ኋላ እንደማይል ህወኃት ገለፀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

  የፌደራሊስት ሃይሎች ጥምረት፤ ምርጫው መራዘሙ ተገቢ ነው ብሏል


           በዘንድሮ አመት ምርጫ ማካሄድ የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑን ህወኃት በድጋሚ የገለፀ ሲሆን፤ በህወኃት አስተባባሪነት የተመሠረተው የፌደራሊስት ሃይሎች ጥምረት በበኩሉ፤ ምርጫው መራዘሙን እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡
ከሰሞኑ የህወኃት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረ ፂዮን ገ/ሚካኤል ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ “ህወኃት ምርጫን በሚመለከት የወሰደው አቋም ፖለቲካዊና ህገ መንግስታዊ ነው” ብለዋል፡፡
“በክልል ደረጃ ኮሮናን እየተከላከልን ምርጫውን በጥንቃቄ ማካሄድ እንችላለን፤ ምርጫውን በዘንድሮ አመት ማካሄድ ወሳኝ ጉዳይ ነው” ብለዋል ዶ/ር ደብረፂዮን፡፡
የፌደራል መንግስት ጉዳዩን በህገመንግስት ትርጉም ለማስተናገድ መሞከሩም ህገ መንግስታዊ ድጋፍ የለውም ሲሉ የተቃወሙት ሊቀ መንበሩ፤ ህገመንግስቱ የምርጫ ጊዜን አስመልክቶ የሚተረጐም ነገር የለውም፤ መፍትሔ የሚሆነው ፖለቲካዊ ውይይት ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
የትግራይ ክልል በየትኛውም መንገድ ምርጫውን ከማካሄድ ወደ ኋላ እንደማይል ያስገነዘቡት ዶ/ር ደብረጽዮን፤ ምርጫውም በህግ ማዕቀፍ በክልሉ ከሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከማህበራትና ከህዝብ ጋር በመመካከር የምርጫ ቦርድንም ባሳተፈ ሁኔታ ህጋዊ አፈፃፀም እንዲኖረው ይደረጋል ብለዋል፡፡
በትግራይ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር እና (ትዴት) አረና፤ የህወኃትን አቋም የተቃወሙ ሲሆን ሳልሳይ ወያኔ እና ባይቶና ምርጫ ዘንድሮ መካሄዱን እንደሚደግፉ አስታውቀዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ መቀሌ በተካሄዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብሰባና ፎረሞች በህወኃት አነሳሽነት የተመሠረተው የኢትዮጵያ ፌደራሊስት ሃይሎች ጥምረት፤ ህወኃት በምርጫ ጉዳይ ላይ የያዘውን አቋም እንደማይደግፍ አስታውቋል፡፡
ቀደም ሲል በመቀሌ ጉባኤና በሌሎች ስብሰባዎች፣ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መካሄድ አለበት ሲል የቆየው ጥምረቱ፤ “ይህ ውሳኔዬ ስህተት ነው፤ አሁን በመንግስት የቀረበውን የመፍትሔ ሃሳብ እደግፋለሁ” ብሏል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎችም ዋነኛ ትኩረታቸውን ከኮሮና ወረርሽኝና ከህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ በተጋረጡ የሉአላዊነት አደጋዎች ላይ በማድረግ፣ ለብሔራዊ ጥቅም እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል - ጥምረቱ፡፡
ጥምረቱ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ የመጀመሪያ ጉባኤውን በአዲስ አበባ ያደረገ ሲሆን መደበኛ ጽ/ቤቱንም በአዲስ አበባ መክፈቱን ለአዲስ አድማስ የደረሰው መረጃ ያመለክታል፡፡


Read 12917 times