Print this page
Saturday, 16 May 2020 11:19

“ኮሮና እስከ መቼ?...”

Written by 
Rate this item
(6 votes)

       “ይህንን ማንም ሰው ሊተነብየው አይችልም!”

            ከትናንት በስቲያ ከወደ ጄኔቫ አንድ ነገር ተሰማ…
“ኮሮና ቫይረስ ፈጽሞ ላይጠፋ ይችላል… አብረውን እንደሚኖሩት ሌሎች በሽታዎች ሁሉ፣ ኮሮናም አብሮን ሊቀጥል ይችላል” በማለት እቅጩን ተናገሩ - ዶ/ር ሪያን፡፡
የአለም የጤና ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶ/ር ማይክ ሪያን ከትናንት በስቲያ በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “ቫይረሱ መቼ ከአለማችን ላይ ሊጠፋ ይችላል?” ተብለው ሲጠየቁ የሰጡት ምላሽ ብዙዎችን ያስደነገጠ፣ ተስፋ ያስቆረጠና ግራ ያጋባ ነበር፡፡
በተለያዩ የአለማችን አገራት ከ100 በላይ የሚሆኑ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ምርምሮች እየተደረጉ እንደሚገኙ የጠቆሙት ዶ/ር ማይክ ሪያን፤ አለም በለስ ቀንቷት ክትባቱን ብታገኝ እንኳን ኮሮናን ላታጠፋው እንደምትችል ተናግረዋል - የመከላከያ ክትባት ከተገኘለት ረጅም ጊዜ ያለፈውንንና አሁንም ድረስ ከአለማችን ያልጠፋውን የኩፍኝ በሽታ እንደ አብነት በመጥቀስ፡፡
ጥቂት ቆይቶ ግን፤ አለቃቸው ሌላ የተሻለና የሚያጽናና ነገር ተናገሩ…
“ኮሮና ቫይረስን ማጥፋት ባይቻል እንኳን፣ እስከ መጨረሻው የአቅማችንን እንጥፍጣፊ ተባብረን ከጣርን፣ የሆነ ጊዜ ላይ ልንቆጣጠረው የምንችለው ነው” አሉ፤ የአለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም፡፡
የዶክተር ቴዎድሮስ ንግግር በተወሰነ መልኩ ቢያጽናናም፣ “መቼ ነው ያ የሆነ ጊዜ?... እስከ መቼ ነው ቫይረሱ በዚህ ሁኔታ የሚቀጥለው?” የሚል ጭንቀትና ስጋት የወለደው ጥያቄን ማጫሩ ግን አልቀረም፡፡
ኮሮና ቫይረስ መላውን አለም በቀውስ ማዕበል እየናጠ፣ ሚሊዮኖችን ወደ አልጋ፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩትን ወደ መቃብር እየሸኘ፣ ኢኮኖሚውን እያንኮታኮተ፣ ማህበራዊ ግንኙነትን እየበጣጠሰ፣ እልፎችን በፍርሃት እያራደና በየቤታቸው አድፍጠው እንዲቀመጡ እያስገደደ የሚቀጥለው እስከ መቼ ነው፣ መቼስ ነው በቁጥጥር ስር የሚውለው ብለው የሚጠይቁ ብዙዎች ናቸው፡፡
“ኮሮና መቼ ነው በቁጥጥር ስር የሚለውለው?” የሚለውን ይህንን የብዙዎች ጥያቄ ለመመለስ፤ ብዙ ርቀት መጓዝ ወይም ብዙ ማብራሪያ መስጠት አላስፈለጋቸውም - ዶ/ር ሪያን፡፡
“ይህንን ማንም ሰው ሊተነብየው አይችልም!” ሲሉ እቅጩን ተናገሩ፡፡
ቀጥሎ የሚመጣው እስካሁን ከሆነው ሁሉ የባሰ እንደሚሆን ብዙዎች እየተናገሩ ቢሆንም፣ ኮሮና ቫይረስ ግን በየደቂቃው በመላው አለም ብዙዎችን ማጥቃቱን፤ ቁጥሮችም በየአንዳንዷ ደቂቃ ማሻቀባቸውን ተያይዘውታል፡፡
እስከ ትናንት በስቲያ አመሻሽ ድረስ…
ኮሮና ቫይረስ በመላው አለም ከ4 ሚሊዮን 477 ሺህ በላይ ሰዎችን እንዳጠቃና 300 ሺህ የሚሆኑትንም ለህልፈተ ህይወት እንደዳረገ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥርም ከ1 ሚሊዮን 680 ሺህ ማለፉ ተነግሯል፡፡ እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ ከ1 ሚሊዮን 435 ሺህ በላይ ሰዎች የተጠቁባትና ከ86 ሺህ በላይ ሰዎች ለሞት የተዳረጉባት አሜሪካ፣ አሁንም በኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎችና ሟቾች ቁጥር ከአለማችን አገራት በቀዳሚነቷ ቀጥላለች፡፡
ስፔን በ272 ሺህ 700፣ ሩስያ በ252 ሺህ 300፣ እንግሊዝ በ233 ሺህ 200፣ ጣሊያን በ220 ሺህ 200 ያህል የቫይረሱ ተጠቂዎች እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ሲይዙ፣ እንግሊዝ በ33 ሺህ 700፣ ጣሊያን በ31 ሺህ 200፣ ስፔን በ27 ሺህ 400፣ ፈረንሳይ በ27 ሺህ 100 ያህል ሟቾች ከአሜሪካ በመቀጠል እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
በኮሮና ሳቢያ የሚጠቁትም የሚሞቱትም ቁጥራቸው ማደጉን ቀጥሏል፤ የአለም ሳይንቲስቶች ደግሞ ደግሞ ለዚህ የጥፋት ማዕበል ማቆሚያ የሚሆን አንዳች መላ ፍለጋ በየቤተ ሙከራው ደፋ ቀና ማለታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከአለም ዙሪያ ከቀረቡ 100 በላይ የሚሆኑ በምርምር ላይ ያሉ የኮሮና ቫይረስ የክትባት አይነቶች ውስጥ የተሻሉና ውጤታማ እንደሚሆኑ የታመነባቸው 8 ያህሉ ተመርጠው እየተሰራባቸው እንደሚገኝና ስራው እየተፋጠነ መሆኑን የአለም የጤና ድርጅት ባለፈው ማክሰኞ ዕለት አስታውቋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት የማፈላለግ ስራውን ለማፋጠን ከተለያዩ አካላት ባለፈው ሳምንት የ8 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ መደረጉን ያስታወሰው ድርጅቱ፤ ያም ሆኖ ግን ይህ ገንዘብ በቂ ባለመሆኑ አገራትና የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት የሚያደርጉትን ድጋፍ በተፋጠነ መልኩ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ሌሴቶ - የመጨረሻዋ አፍሪካዊት አገር
ባለፈው ረቡዕ ማለዳ…
ሁሉንም የአፍሪካ አገራት አዳርሶ አንዲት አገር ብቻ ቀርታው የነበረው ኮሮና ቫይረስ፣ በስተመጨረሻም የመጨረሻዋ መዳረሻው ወደሆነችውና በአገር ተከብባ ወደምትኖረው ደቡባዊ አፍሪካዊት አገር ሌሴቶ ሰተት ብሎ መግባቱ ተሰማ፡፡
ከተቀረው የአፍሪካ አገር በተለየ መልኩ በኮሮና ሳትደፈር ይህን ያህል ጊዜ መቆየቷ በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ አድርጓት የሰነበተችውና  በአህጉሩ በኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ቀዳሚነቱን በያዘችው ደቡብ አፍሪካ ዙሪያዋን ተከባ የምትገኘው ሌሶቶ፤ ከውጭ አገራት በመጡ መንገደኞች ላይ ባደረገችው ምርመራ አንደኛው በቫይረሱ መጠቃቱን ማረጋገጧን ይፋ አድርጋለች፡፡
በመላው አፍሪካ በዚህ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ከኤች አይ ቪ ኤድስ ጋር ተዛማጅ በሆኑ ምክንያቶች ሳቢያ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ የአለም የጤና ድርጅት ባለፈው ማክሰኞ በሰጠው መግለጫ ማስጠንቀቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት፤ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በአፍሪካ ለ6 ወራት የፀረ-ኤች አይ ቪ መድሐኒት አቅርቦት ቢቋረጥ፣ ከኤድስ ጋር በተዛመዱ በሽታዎች የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እንደሚጨምር መነገሩን የጠቆመው ዘገባው፣ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት መንግስታት ለጉዳዩ ትኩረት ካልሰጡት እስከ መጪው የፈረንጆች አመት ድረስ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኤድስና ተዛማች በሽታዎች ሳቢያ ሊሞቱ እንደሚችሉ ድርጅቱ ማስጠንቀቁንም አክሎ ገልጧል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ሳይንሳዊ መንገድን ተከትሎ ያልተሞከረና ደህንነቱ ያልተፈተሸ መድሐኒት ለጤና አይበጅምና ከመውሰድ ተቆጠቡ ብሎ በአደባባይ የተቃወመውን ባህላዊ የኮሮና ቫይረስ መድሃኒቷን በግዛቷ ውስጥ በገፍ መሸጧን የተያያዘችው ማዳጋስካር፣ ይህንኑ መድሓኒቷን ታንዛኒያ፣ ጊኒ ቢሳዎ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ጨምሮ ወደተለያዩ የአፍሪካ አገራት “ኤክስፖርት” በማድረግ ተጠምዳ ነው ሳምንቱን ያገባደደችው፡፡
ማዳጋስካር “ፍቱን መድሐኒት አግኝቻለሁ፤ ከአሁን በኋላ ቫይረሱ ወደ ዜጎቼ ድርሽ አይልም” ብላ ብትምልም፣ የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ግን ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ 18 ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ፣ አጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 230 ከፍ ብሏል፡፡
በአፍሪካ የወረርሽኙ መስፋፋት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚደርስበት አደገኛው የጥፋት ጊዜ ገና እንደሆነ ባለሙያዎች እያስጠነቀቁ ቢሆንም፣ በርካታ የአፍሪካ አገራት ግን ለሳምንታት ተግባራዊ ሲያደርጉት የነበረውን የእንቅስቃሴ ዕገዳ ከሰሞኑ ማላላት መጀመራቸው እየተነገረ ነው፡፡ የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠር ሲሉ ጥለዋቸው የነበሩ የእንቅስቃሴ ገደቦችና እገዳዎች ኢኮኖሚያቸው ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠር መጀመሩን በማየት ተግባራዊ ሲያደርጓቸው የነበሩ ገደቦችንና እገዳዎችን ለማላላት እየወሰኑ ያሉ የአፍሪካ አገራት እየተበራከቱ መሆናቸውን የዘገበው ቢቢሲ፤ ጂቡቲ፣ ማሊ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጋቦን፣ ኒጀር እና ኡጋንዳ ለማላላት ያወጡትን ዕቅድ ይፋ አድርገዋል ብሏል።
በጊኒ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት መንግስት የጣላቸው የእንቅስቃሴ ገደቦች ለሙስናና ተገቢ ያልሆነ ጥቃት ዳርጎናል ያሉ ዜጎች ባለፈው ማክሰኞ አደባባይ ወጥተው ባደረጉት ተቃውሞ፣ ከፖሊስ ጋር በተፈጠረ ግጭት  ስድስት ሰዎች መገደላቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በኮሮና ተጽዕኖ በቀን 6 ሺህ ህጻናት ሊሞቱ ይችላሉ
በማደግ ላይ ባሉ አገራት ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ መከላከል በሚቻሉ በሽታዎች ሳቢያ የሚከሰተው የህጻናት ሞት በመጪዎቹ ስድስት ወራት በ45 በመቶ ያህል ሊጨምር እንደሚችልና በየዕለቱ በመላው አለም 6 ሺህ ያህል ከአምስት አመት ዕድሜ በታች ያሉ ህጻናት ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ አስጠንቅቋል፡፡
በአገራቱ የሚገኘው ውስን የጤና ሃብትና ቁሳቁስ ከነባር በሽታዎች ወደ ኮሮና ቫይረስ መከላከል ከመዞሩ ጋር በተያያዘ በተለይ በአፍሪካ፣ እስያና ላቲን አሜሪካ ድሃ አገራት በ6 ወራት ውስጥ ተጨማሪ 1.2 ሚሊዮን ህጻናት እንዲሁም 57 ሺህ ያህል እናቶች ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉም ድርጅቱ አስታውቋል፡፡ ድርጅቱ በተጠቀሰው የ6 ወር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው የህጻናት ሞት ሊከሰትባቸው ይችላል ብሎ የጠቀሳቸው ቀዳሚዎቹ አስር አገራት ባንግላዴሽ፣ ብራዚል፣ ኮንጎ፣ ኢትዮጵያ፣ ህንድ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ናይጀሪያ፣ ፓኪስታን፣ ኡጋንዳ እና ታንዛኒያ ናቸው፡፡

ኢኮኖሚው እንዴት ሰነበተ?
ባለፉት ሶስት ወራት የአለማችን ንግድ በ3 በመቶ ያህል እንደሚቀንስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የንግድና የልማት ተቋም ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መረጃ አስታውቋል:: የንግድ መቀነሱ በቀጣዮቹ ሶስት ወራትም ተጠናክሮ ሊቀጥልና ከሚያዝያ እስከ ሃምሌ ወራት 27 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል የጠቆመው ተቋሙ፣ ባለፈው መጋቢት ወር የሸቀጦች ዋጋ በአለማቀፍ ደረጃ በ20 በመቶ መቀነሱንም አስታውሷል፡፡
ዘ ጋርዲያን በበኩሉ፣ አለማቀፍ የመኪኖች ሽያጭ በ2020 የፈረንጆች አመት በ20 በመቶ ያህል እንደሚቀንስ መነገሩን ከሰሞኑ ለንባብ ባበቃው ዘገባው አመልክቷል፡፡ የአለማችን ኢኮኖሚ በፈረንጆች አመት 20202 በ3.2 በመቶ ያህል ቅናሽ እንደሚያሳይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ ያስታወቀ ሲሆን፣ ከ300 በላይ የአለማችን ህግ አውጪዎች አለማቀፉ የገንዘብ ተቋምና የአለም ባንክ የድሃ አገራትን ዕዳ እንዲሰርዙ ጥሪ ማቅረባቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የህንድ መንግስት የኮሮና ቫይረስ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቋቋምና በወረርሽኙ ሳቢያ የንግድ እንቅስቃሴያቸው የተጎዳባቸውንና ስራቸውን ያጡ ዜጎችን ለመደጎም በማሰብ የ264 ቢሊየን ዶላር የኢኮኖሚ መታደጊያ በጀት መመደቡን ባለፈው ረቡዕ ሲያስታውቅ፣ ጣሊያንም የ59.6 ቢሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ማነቃቂያ በጀት ማጽደቋን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ኮሮና ቫይረስ ያን ያህል ተጽዕኖ እንዳልፈጠረባት በሚነገርላት አውስትራሊያ የሥራ አጥ ዜጎች ቁጥር ወደ 6.2 በመቶ ማደጉና ከ6 መቶ ሺህ በላይ የአገሪቱ ዜጎች ለስራ አጥነት መዳረጋቸው መነገሩን ቢቢሲ ዘግቧል:: በአገሪቱ ከመንግሥት ድጋፍ እየተደረገላቸው የሚገኙ ዜጎች ቁጥር ከ6 ሚሊዮን በላይ መድረሱን የጠቆመው ዘገባው፣ 1 ሚሊዮን አውስትራሊያውያን ደግሞ ሥራ አጥ ስለሆንን ድጋፍ ይደረግልን የሚል ማመልከቻ ለመንግስት ማቅረባቸውን አመልክቷል፡፡

መክፈትና መዝጋት፣ ማላላትና ማጥበቅ
ነገሩ አላምር ሲላቸው የእንቅስቃሴ ገደቦችንና ዕግዶችን ከጣሉ ከሳምንታት በኋላ፣ ተዘግቶ መቀመጥ ከቀጣዩ የኢኮኖሚ ቀውስ እንደማያስጥል የታያቸውና ገደቦችን ያነሱ አገራት፣ ከቀናት በኋላ ደግሞ ቫይረሱ በፍጥነት መሰራጨቱ ክፉኛ ሲያስደነግጣቸው መልሰው ገደቦችን መጣላቸው እየተዘገበ ይገኛል፡፡
ቫይረሱን በቁጥጥር ስር አውያለሁ ብላ ህጎቿን ባላላች በሳምንት እድሜ ውስጥ የተጠቂዎች ቁጥር እንደገና ያሻቀበባት ሊባኖስ፣ በፍጥነት ያላላችውን ህጎች መልሳ አጥብቃለች:: የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት በማሰብ የጣለችውን የእንቅስቃሴ ገደብ ከሰሞኑ ማላላት የጀመረችው ፓኪስታን፣ በአንዳንድ ግዛቶች ከፍታው የነበረውን የንግድ እንቅስቃሴ የማህበራዊ እርቀት ደንቦች አልተከበሩም በሚል ከጥቂት ቀናት በኋላ መልሳ መዝጋቷ ተነግሯል፡፡
ያላሏቸውን ህጎች መልሰው ካጠበቁና የእንቅስቃሴ ገደቦችን እንደ አዲስ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመሩ ሌሎች የአለማችን አገራት መካከል ህንድና ኢራን እንደሚገኙበት ተነግሯል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የእንቅስቃሴ ገደቦችን ማላላትና ዜጎቻቸውን ወደ መደበኛው እንቅስቃሴ ለመመለስ የመረጡ ህንድ፣ ሩስያ፣ አሜሪካና ሲንጋፖርን የመሳሰሉ በርካታ አገራት መኖራቸውን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
እንግሊዝ በቤታቸው ሆነው ስራቸውን መስራት የማይችሉ የተወሰኑ ሰራተኞች ወደ ቢሮ እንዲገቡ ለመፍቀድ ማሰቧን ስትገልጽ፣ ሜክሲኮ የተወሰኑ የመኪና አምራች ኩባንያዎችን ከሰሞኑ እንደምትከፍት አስታውቃለች:: የጣሊያን ትምህርት ሚኒስቴር በመጪው መስከረም ሁሉም የተዘጉ ትምህርት ቤቶች እንደሚከፈቱ ማስታወቁን የዘገበው ሮይተርስ፣ አውስትራሊያና ጀርመን ለ2 ወራት የዘጉትን ድንበራቸውን በመጪው ሰኔ ለመክፈት መስማማታቸውን ገልጧል፡፡

በቀን 18 ሚሊዮን ኮሮና ተኮር ሃሰተኛ ኢሜሎች ይላካሉ
የኢንተርኔት አጭበርባሪዎች ለጂሜይል ተጠቃሚዎች በየዕለቱ 18 ሚሊዮን ያህል ሃሰተኛ የኢሜል መልዕክቶችን እንደሚልኩ ታዋቂው የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጎግል ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት መስፋፋት ጋር በተያያዘ መሰል ሃሰተኛ ኢሜይሎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸውን የጠቆመው ጎግል፣ ባለፈው ሳምንት ብቻ መሰል ከ100 ሚሊዮን በላይ መልዕክቶችን ማገዱንና 20 በመቶ ያህሉ ከኮሮና ቫይረስ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን በመግለጽ፣ አጭበርባሪዎች በእነዚህ ሃሰተኛ መልዕክቶች አማካይነት የተጠቃሚዎችን የግል መረጃዎች እንደሚመነትፉ አመልክቷል፡፡

በኤርትራ 1 ታማሚ ሲቀር፤ በፔሩ ግማሽ ያህሉ ሃኪሞች ኮሮና ይዟቸዋል
በኤርትራ በኮሮና ቫይረስ ከተጠቁት 39 ሰዎች መካከል 38ቱ ከሆስፒታል አገግመው መውጣታቸውንና በህክምና ላይ የሚገኘው አንድ ሰው ብቻ መሆኑን የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ባለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ የፔሩ መንግስት በኮሮና ቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ በተጠቃችው ኢኩቶስ የተባለችው የአገሪቱ ከተማ ውስጥ የህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ ከነበሩ 350 ዶክተሮች መካከል 189 የሚሆኑት በቫይረሱ መጠቃታቸውን እንዳስታወቀ ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡

ሲጋራ ከኮሮና አያስጥልም፤ ይልቁንም የበለጠ ያጋልጣል
ከሳምንታት በፊት ከወደ ፈረንሳይ የወጣ አንድ ጥናት፣ ሲጋራ አጫሾች ከማያጨሱት ጋር ሲነጻጸር በኮሮና ቫይረስ የመጠቃት ዕድላቸው ዝቅ ያለ እንደሆነ ጠቁሞ ነበር፡፡ የአለም የጤና ድርጅት ግን ይህን እና ሌሎች መሰል ጥናቶችን ይፋ የሚያደርጉ አሳሳች ሳይንቲስቶችን “የማይመስል ነገር እየመከራችሁ ሰውን አታሳስቱ” ሲል ከሰሞኑ ማስጠንቀቁንና በአንጻሩ ሲጋራ ማጨስ ለኮሮና የማጋለጥ ዕድሉ ከፍ ያለ እንደሆነ መግለጹን አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡
አጫሾች በኮሮና ቫይረስና በሌሎች የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች የመጠቃት እድላቸው ከማያጨሱት የበለጠ ከፍ ያለ መሆኑን ድርጀቱ በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ ባደረገው መረጃ ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፣ ማጨስ ሳንባን በመጉዳት ሰውነታችን ኮሮናንና ሌሎች በሽታዎችን የመከላከል አቅሙ አነስተኛ እንዲሆን እንደሚያደርግ መጠቆሙንም አክሎ ገልጧል፡፡


Read 13107 times
Administrator

Latest from Administrator