Wednesday, 13 May 2020 00:00

“የሁለት ከተሞች ወግ” የታሪክ ሰበዝ

Written by  ሻሎም ደሳለኝ
Rate this item
(1 Vote)

  “የበጎ አድራጎት ዘመን ... የክፉ አድራጎት ዘመን ... የብልህነት ዘመን ... የጽኑ እምነት ዘመን ... የጥርጣሬ ዘመን ... የጨለማ ዘመን ... ተስፋ የሚጣልበት ዘመን ... ተስፋ የማይጣልበት ዘመን ... ሁሉም ነገር የተሟላበት ዘመን ... አንዳችም ነገር ያልተሟላበት ዘመን ... የደስታ ዘመን ... የኀዘን ዘመን ... ባጭሩ ዘመኑ ተቃራኒ ሁኔታዎች የነገሱበት ዘመን ነበር። ... ይህ ሁሉ ይፈፀምበት የነበረው ዘመን ከክርስቶስ ልደት ወዲህ በ1775 ዓ.ም ላይ ነበር።” በማለት ይጀምራል፤ በ341 ገጾች የቀነበበው A tale of two cities” የተሰኘው የቻርልስ ዲክንስ ድርሰት። ክቡር ሣህለሥላሴ ብርሃን ማርያም “የሁለት ከተሞች ወግ” በሚል በ181 ገጾች አሳጥረው ወደ አማርኛ  በመለሱት የትርጉም ስራ ላይ ሰፍሮ እንደምናገኘው ማለት ነው።
ይሄ ድርሰት መቼቱን ሎንዶንና ፓሪስ አድርጎ፣ የፈረንሳይን አብዮት እያስታከከ፣ የሚፈስ ታሪክ ቀመስ ልቦለድ ሲሆን ልብ እያንጠለጠለ እስከ ፍፃሜው የሚዘልቅ ድንቅ ድርሰት ነው።
ድርሰቱ በ1859 እ.ኤ.አ ተፅፎ ለህትመት የበቃ ቢሆንም፣ እስከ ዛሬ ድረስ ተወዳጅ ሆኖ መዝለቁን ለተመለከተ የደራሲውን ብቃት አለመመስከር አይቻለውም። ሌዮ ቶልስቶይ፤ ስለ ቻርልስ ዲክንስ  እንዲህ ተናግሮ ነበር፡- “በእያንዳንዱ ምዕተ ዓመት እንደ ቻርልስ ዲክንስ ያለ ታላቅ ደራሲ ከአንድ በላይ አይፈጠርም”
ስለ ደራሲውና ድርሰቱ ይሄን ካልን ዘንዳ በታሪኩ ውስጥ ትኩረት እንድሰጠው ወዳደረገኝ ጉዳይ ላምራ።
ታሪኩ የሚያጠነጥነው ያለ ምንም ጥፋት ለ18 ዓመታት “ባስቲን” በተባለ ወህኒ ቤት ውስጥ “መቶ አምስት ፤ ሰሜን ግንብ” ተብሎ በሚጠራ አደገኛ ስፍራ በግፍ ታስሮ ይሰቃይ ስለነበረ ዶክተር ማኔት የተባለ ሰውና ቤተሰቡ ነው። ይህ ዶ/ር በግፍ ታስሮ በነበረበት ወቅት ጫማ እየሰፋ፣ እነዚያን አሰቃቂ ጊዜያት ይገፋ እንደነበር ይተርክልንና፣ ከነዚያ የሰቆቃ ዘመናት መልስ፣ ከእስር ከተፈታ በኋላ ሉሲ ከተባለች ሴት ልጁ ጋር ያሳለፈውን የእስር መልስ ህይወት ያስነብበናል፡፡
በአንድ ወቅት አባቷን ከፓሪስ ወደ ሎንዶን በመርከብ ይዛ ስትጓዝ፣ መርከብ ውስጥ አይታው ከነበረ ወጣት ጋር በፍቅር ትወድቃለች። ወጣቱ ቻርስ ዳርኔም አባቷን አስፈቅዶ፣ ከዚህች ውብ ሴት ጋር በትዳር ተሳስሮ፣ አንዲት ሴት ልጅ ወልዶ መኖር ይጀምራል። የታሪክ ጡዘት ከዚህ በኋላ ይጀምራል።
ይሄ ቻርልስ ዳርኔ የተባለ ፈረንሳዊ፤ ከልዑላን ዘር የተወለደ ቢሆንም ቤተሰቦቹ በወቅቱ  ጭሰኞች ላይ ያደርሱት የነበረውን ጭቆና ተጠይፎ ስሙን ቀይሮ፣ እንግሊዝ ውስጥ በመምህርነት ሙያ ተሰማርቶ መኖር ጀምሮ ነበር። ሃብትና ንብረቱን ጥሎ ከጭሰኞች የሚሰበሰብን ገንዘብ ተጠይፎ፣ መምህር ሆኖ፣ በስደት ሕይወቱን ከባለቤቱና ከልጁ ጋር ሲገፋ በነበረበት ወቅት ፓሪስ ውስጥ ከሚኖር ጋቤል ከተባለ ከድሮ አሽከሩ ዘንድ ደብዳቤ ይደርሰዋል። ደብዳቤው በቁንፅሉ እንዲህ ይላል. . .
“ከአቤ ወህኒ ቤት
ፓሪስ
ለመስፍን ቻርልስ ኤቭሬሞንድ
ክቡር ጌታዬ:-”
ብሎ ይጀምራል፤ አሽከሩ ጋቤል ለጌታው ቻርልስ ዳርኔ በፃፈለት ደብዳቤው።
“...እርስዎን በታማኝነት ከማገልገል በስተቀር በህዝብ ላይ የፈፀሙት በደል በፍፁም የለም። በመሆኑም ለእግዚአብሔር ብለው፤ ለፍትህና ለገዛ ስምዎም ብለው ካለሁበት ሥቃይ ይገላግሉኝ።
እርስዎ መጥተው ካልረዱኝ በስተቀር የሞት ቅጣት እንደሚፈፅሙብኝ የተረጋገጠ ስለሆነ በእርስዎ ምክንያት ሕይወቴን እንዳላጣ የተቻለዎትን እንደሚያደርጉልኝ ተስፋ አለኝ።
ያልታደለው ታማኝ አሽከርዎ
ጋቤል
እዚህ ጋ ነው እንግዲህ ሰው ለእግዚአብሔር፣ ለስምና ለፍትህ ሲል ምን ያክል መስዋዕትነት ይከፍላል ብዬ እንድጠይቅ ያስገደደኝ። የአሽከሩ የጋቤል ሕይወት ነፃ ለመውጣት የቻርልስ ዳርኔ ወደ ፓሪስ መመለስ ላይ ትንጠለጠላለች። ቻርልስ ወደ ፓሪስ ከተጓዘ ደሞ እራሳቸውን የአብዮት መሪ ነን በሚሉ ሰዎች ሕይወቱ ልትቀጠፍ ትችላለች። ምክንያቱም “ኮብላይ ልዑላን” ወደ ፈረንሳይ ከተመለሱ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ አንገታቸውን ተቀልተው እንዲገደሉ ህግ አውጥተው ነበርና።
ቻርልስ ዳርሌ “ስም ከመቃብር በላይ ይውላል” ይሉትን ብሂል አምኖ የተቀበለ ይመስላል። ነፍሱን ስለ አንድ አሽከሩ ነፃ መውጣት ሲል አደጋ ላይ ይጥላል። ቢያሻው መልክህ አስጠላኝ ብሎ አርባ ጊዜ ጀርባውን ሊገርፈው ለሚችል አሽከሩ ብሎ  ልዑልነቱ ሳይጫነው፣ ለእውነት ሲል፣ ወደ ገዳዮቹ ቀዬ ሊያቀና ይወስናል። እንዲህ ሲል . . .
“ለእግዚአብሔር፤ ለፍትህ ፤ ለሰብዓዊ ርኅራኄና ለገዛ ስሜም ስል ወደ ፓሪስ መሔድ አለብኝ”።
ተደብቆም ወደ ፓሪስ ያመራል። እዛ እንደደረሰም አስቀድመው ሲጠብቁት የነበሩ ጊዜ ያነገሳቸው አብዮተኞች፣ እያዳፉ ወህኒ ቤት ይወረውሩታል። ከአንድ ዓመት በላይ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ እንደ ታጎረ ይቆያል። እድል ከሱ ጋር ተሟጣ አልቀረችም ነበርና የሚስቱን አባት የዶ/ር ማኔት ስም በአብዮተኞቹ ዘንድ ያለውን ቅቡልነት ተጠቅሞ፣ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ይደረጋል።
ዘመኑ የበቀልና የአውሬነት ዘመን ስለነበር ሰው የሚገደለው፣ ያለ ምንም የህግ ውሳኔ ነበር። ይሄንን አጉልቶ የሚያስረዳው ታሪክ እንዲህ ሰፍሮ ይገኛል ...
“ቻርልስ ዳርኔ በታሰረበት በላፎርስ ወህኒ ቤት በበነጋታው ለፍርድ እንዲቀርቡ የተወሰነላቸው እስረኞች ሃያ ሦስት ነበሩ። ይሁን እንጂ ስም በተጠራ ጊዜ ቻርልስ ዳርኔና አስራ ዘጠኝ ሌሎች እስረኞች ብቻ ‘አቤት’ ብለው በዚያ መኖራቸውን ሲያረጋግጡ የተቀሩት ሦስቱ ‘አቤት’ ሳይሉ ቀሩ።” ይለንና እነዛ ሦስቱ ሰዎች አስቀድመው ከፍርድ ቤት ውሳኔ በፊት በባለ ጊዜዎች ተገድለው እንደነበር ይተርካል። የይስሙላ ፍትህ ይስተዋል ነበርና።
ይሄ ኩነት አሁን ካለንበት ሀገራዊ ኩነት ጋር ፍፁም አንድ አይነት ሆኖ እናገኘዋለን:: አጠፋም አላጠፋም የሰው ነብስ በደቦ ፍርድ እንደ ቀልድ ይረግፋል። በውሸት ዜና የዱላና የድንጋይ እራት ይሆናል። በቅርቡ በአገራችን ዘቅዝቆ መስቀልና ሰውን ከእነ ነፍሱ ማቃጠል፣ የ”ባለ ነፃ አውጪ ነኝ” ባዮች ፍርድ ሆኖ ታዝበናል፡፡ ይሄን በ1859 ማለትም ከ160 ዓመት በፊት የነበረን ኋላ ቀር የደቦ ፍትህ፣ ዛሬም ስንተገብረው ለተመለከተ ኢናሊላሂ የሚያስብል ይመስለኛል።
ታሪኩ እንዲህ ሲል ይቀጥላል። ለፍርድ ከቀረቡት 20 እስረኞች መሃል የመጀመሪያዎቹ 15 ሰዎች፣ ሙሉ በሙሉ የሞት ፍርድ ተፈረደባቸው። አንገታቸውን ለመቅላትም የ1:30 ጊዜ ብቻ ፈጀባቸው። ካስተውሎት የራቀ ፣ ከበቀለ ያልፀዳ አብዮተኛ፤ ከፍርድ በፊትም ሆነ ከፍርድ በኋላ አንገት ከመቅላት ወደ ኋላ አይልም። በፍርድ ሸንጎ የተቀመጡና ለህግ ቆመናል የሚሉ ሰዎች ክሱን ሳያደምጡ በፊት ውሳኔ እንደሚሰጡ አይተናል። ሰምተናል። ጊዜ አገኘን ያሉ ጊዜ በጣለው ላይ አንድ ሺህ ገፅ ክስ ሲያሰናዳ ተመልክተናል። ሰምተንማል።
“...ቻርልስ ዳርኔም ተራው ሲደርስ ከሸንጎ ፊት ቀረበ። መደበኛ ዳኞቹ አምስት ነበሩ። ... ፍርዱን የሚመሩት ህጋዊ ዳኞች ቢሆኑም ውሳኔ የሚሰጡት ግን “ጁሪስ” የተሰኙ ህዝባዊ ዳኞች ነበሩ። እነዚህም የህግ እውቀት የሌላቸው ነገር ግን ከሕዝቡ መሐል ተውጣጥተው የተመረጡ ሰዎች ነበሩ።”
የፀረ ሽብር አዋጁን የሚያወጡት ሽብር ምን እንደሆነ የማያውቁ፣ ፍትሁን የሚዘውሩት ፍትህን የማያውቁ፣ ሽምግልና የሚሾሙት ከራሳቸው ጋር ሲስማሙ የማይታዩ መሆናቸውን ዛሬም እያየን ይመስለኛል። ዛሬም ጁሪሶች አሸን ናቸው። ህግ ሳይሆን ስሜት የሚመራቸው ጁሪስአዊያን ዛሬም ሞልተውናል። የማንክደው ሃቅ ነው፡፡

Read 2138 times