Saturday, 09 May 2020 13:21

የጥበብ ጓሎች

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(3 votes)

 ጆሮ ግንዱ ጋለ፤ ቀጥታ እንደገባ ጥናታዊ ጽሑፉን ሊያሰናዳ አንደ ፍሬ ቴምር ቀመሰና ወደ መጻሕፍት መደርደሪያው ሄደ:: ለብቻ የሚያስቀምጣቸው መጻሕፍት በቦታቸው የሉም፡፡
መቸም ቢሆን እንደ ስዕለት ልጆች የሚያያቸው መጻሕፍት ከሌሉ የርሱ ሕይወት እንዳለ አይቆጥረውም፡፡  በድንጋጤ ውስጥ ሆኖ ወደ ኋላ አሰበ፡፡ በተለየ ሁኔታ ሰሞኑን ለስራ አንስቷቸው እንደሆን ገመተ:: በፍጹም መጻሕፍቱን ከመጻሕፍት የለያቸው መሸጫ ዋጋቸው አይደለም፡፡ የለያቸው ለርሱ ያላቸው ጠቀሜታ ነው፤ በተለይ በአማርኛና በእብራይስጥ ግጥሞች መካከል ሊሰራ ላሰበው ጥናት ወሳኝ ስለሆኑ አቅፏቸው ቢተኛ ደስ ይለዋል፡፡ ለብቻቸው ያስቀመጣቸው ምናልባት የእሳት ቃጠሎ ቢነሳ እነርሱን ይዞ ለመሸሽ ነው፡፡ ይህ ሃሳብ አንዳንዴ ራሱን ያስቀዋል፡፡ ግን ደግሞ ትክክል ነው፡፡ ቶማስ ጀፈርሰን እርሻ ቦታውን እየጎበኘ ሳለ፣ የቤት ሰራተኛው መጥቶ፣ መኖሪያ ቤቱ መቃጠሉን ሲነግረው፤ ‹‹መጻሕፍቴ ድነዋል?›› ብሎ ነበር የጠየቀው:: እዚያ ታላቅነት ላይ ያደረሱት እነርሱ መሆናቸውን ስለሚያውቅ ነው፡፡  
ስለዚህ  እኔም ትክክል ነኝ ብሎ አሰበ:: እነዚህን መጻሕፍት የለያቸው አንዴ የሚኖርበት ኮንዶሚኒየም ላይ ቤት ከተቃጠለ በኋላ ነው፡፡ የዚያን ቀን እሳቱ እርሱ ቤት የሚደርስ መስሎት የሚይዝ የሚጨብጠውን ሲያጣ መጻሕፍቱን ፈለገ፡፡ በተለይ ለጥናቱ የሚጠቅሙትን:: የሶሻሊስቱ ዐለም ስለ ግጥም ያለውን አመለካከት የያዘውን መጽሐፍ፣ ስለ ግዕዝ ስነጽሑፍና አማርኛ ቅኔ አሜሪካዊው ፕሮፌሰር የጻፉትን ፈልጎ አገኘና በትንሽ ፌስታል ነገር አንጠለልጥሎ ለሽሽት ተዘጋጀ፡፡ ልብሱም ላፕቶፑም ምኑም ትዝ አላለውም፡፡ ቶማስ ጀፈርሰን ለካ እውነቱን ነበር! ብሎ በመደነቅ ወደ ውጭ ብቅ ሲል እሳቱን ተረባርበው አጥፍተውታል:: ቢሆንም እነዚያ መጻሕፍት መቸም ቢሆን ከሌሎች ጋር አይቀላቀሉም:: የባንክ ቡኩ እንኳን ቢሆን፡፡ ዋልያዎቹ እነዚያ መጻሕፍት ናቸው፡፡ በርግጥም አንዳንዶቹ ፈጽሞ በሀገር ገበያ የሌሉ ናቸው:: የአንዳንዶቹ ዋጋ በውጭ ሀገር ስሌት የማይቀመስ ነው፡፡ ለደረሰ ግን ከዋጋው በላይ ጥቅሙና ፍቅሩ ይብስበታል::
አሰላሰለ፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ የምታውቀውና የሰማቸው ሊሊ ናት:: እርሷም ቢሆን ለዚህ አይነቱ መጽሐፍ ደንታ የላትም፡፡ ልቦለድ፣የሚባል ነገር፣ ግጥም የሚባል ቅዠትና ፍልስፍና አትወድድም:: እርሷ ፍቅሯ የታላላቅ ሰዎች የሕይወት ታሪክ ላይ ነው፡፡ እነርሱን ስታይ ለሃጯ ይዝረከረካል፡፡ ታስሮ ስጋ እንዳየ ውሻ መሬት ትቆፍራለች፡፡ እርሱ የርሷ ነገር ይገርመዋል:: ስንት ጥበብ እያለ የሕይወት ታሪክ ላይ ማበድ፡፡ ምስጢሩን ከነገረችው በኋላ ስቆ ትቷል፤ አባቷ ናቸው የከተቧት፡፡
አባቷ የደርግ ኮሎኔል ነበሩ፤የጦር ጄኔራሎችን፣ የፖለቲከኞችን ታሪክ ሲወዱ አይጣል ነው፡፡ እርሷም በትርፍ ጊዜዋ እሳቸው አንብበው ያስቀመጧቸውን መጻሕፍት ስታነብብ ተለክፋ ቀረች:: የእነ ሮበርት ሊን፣ የእነ ሸርማንን፣ የእነ ሃሚልተንን፣ የእነ ከማል አታቱርክን ሳይቀር አንብባለች፡፡ እንደኛ ሀገሩ እንደ ብርጋዲየር ጀነራል ተስፋዬ ሀብተማርያም የምታደንቀው ግን የለም፡፡ በዐለም አየር ወለድ ታሪክ ያልተፈጸመ ጀግነት ለመስራት ከጓዶቻቸው ጋር ተሰልፈው፣ በዐለም አየር ወለዶች ታሪክ ያልተሞከረውንና ያልታየውን ረጂም ከፍታ ለመጀመሪያ ጊዜ በመዝለል ተዐምር የሰሩ ጀግና ናቸው›› ትላለች፡፡ ስትናገር እንባዋ ይመጣል፡፡
በሀገሯም በራስዋም ጉዳይ እልኸኛ ነች፡፡ እልኸኛ ትወዳለች፡፡ አባትዋን የምትዋዳቸው አባቷ ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን እልኸኛ ስለሆኑ ነው፡፡ ተሟግተው መሸነፍ፣ ተዋግተው ድል ማጣት አይወድዱም:: ጦር ሜዳ ላይ ከአዛዣቸው ትዕዛዝ ሳይቀበሉ ውጊያ በመግጠም ብዙ ጊዜ ተቀጥተዋል:: ማዕረጋቸው እንዳያድግም ሆነዋል፡፡ በዚህ ግን አይናደዱም፡፡ እንኳን እኔ አሉላ አባነጋም በዶጋሊው ድል ተቀጥቷል፤ ገበየሁ በአምባላጌው ድል በራስ መኮንን ተወቅሶ ታስሯል፡፡ ጀግና ክብሩ ነጻነቱ ነው፡፡›› ይላሉ::
እርሱ ግን ሊሊን ሲመክራት ትስቃለች:: እነ ማርቲን ሉተር ኪንግን፣ እነ ጋንዲን አንብቢ ሲላት ከት ብላ ትስቃለች፡፡ አነርሱ ክርስቶሳዊ መንገድ የያዙ ይመስላሉ፡፡ ፓሲቭ መሆን አይመቸኝም፡፡ አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ፊሊፕ ያንሲ ‹‹ላወቅሁት ኢየሱስ›› በሚል መጽሐፋቸው የጎዘጎዙትን የክርስቶስ መንገድ አልመርጠውም:: ማድረግ እየቻልክ የሚወጉህን ይቅር ማለት! ነጻነት ለመስጠት ባሪያ መሆን! ቂቂቂቂ…አይዋጥልኝም፡፡ ለሁሉም የዘራውን ማሳጨድ ደስ ይለኛል:: እንደ ዶክተር ዐቢይ ይቅርታ ብቻ! ኖ ኖ እንደ ዐጼ ምኒልክ የጠላቴን ሬሳ በወታደራዊ ክብር ማስቀበር! ትለዋለች፡፡ ቢሆንም ጣፋጭ ናት፡፡ ለደሃ የምታዝን፣ በሞያዋ ጎበዝ ሃኪም ናት፡፡
አሁን ወደ መጻሕፍቱ ተመለሰ፡፡ ሊሊ ጋ ለመደወል ፈለገና የሰሞኑ ለከፋዋን ሲያስብ መልሶ ተወው፡፡ አንዳንዴ በሩ ላይ ቁልፍ ረስቶ ስለሚሄድ ምናልባት ከጎረቤቱ ያለው ጎረምሳ ጫት መቃሚያ አድርጎት ይሆን! ቁልፍ በር ላይ አንጠልጥሎ መሄድ ልማዱ ነው፡፡ ቢሆንስ ላፕቶፕ እያለ መጽሐፍ ምን ያደርግለታል!..እንዳያስታውቅበት ላፕቶፑን መውሰድ ባይፈልግ እንኳ መጻሕፍቱን እንዴት ለያቸው? ምናልባት ፌስታል ውስጥ በመሆናቸው ጠርጥሮ ይሆናል፡፡
መርሳት አልቻለም፤ አነዚህ መጻሕፍት ከጠፉ ደርሶ ክንፍ የሌለው ወፍ ነው፤ የማይጠቅም ሰው!! አለቀ!1 እንባ ተናነቀው::
ሊሊ ባታበሳጨው ሄዶ ከርሷ አንዳች መላ ያመጣ ነበር፡፡ አሁን የቀረው  በድሩ ጋ ሄዶ ማኪያቶ መጠጣት ብቻ ነው፡፡ እዚያ ተንፈስ ብሎ የሚያደርገውን ማሰብ፡፡
ታክሲ ተሳፍሮ ጦር ኃይሎች ቴዲ ካፌ ገባ፡፡ ብዙ ሰው የለም፡፡
‹‹ምን ላምጣልህ!›› አለ በድሩ፡፡
መልስ አልሰጠውም፡፡
‹‹የሰሞኑን ነው››
ገብቶታል፡፡ ቀሽር ማለቱ ነው፡፡ ይሄ ኮሮና የሚባል ጣጣ ከመጣ በኋላ ብዙ ሰው ፌጦና ዝንጅብል አብዝቷል፡፡ ደረሰም ሰሞኑን ሰውን መስሏል፡፡
ሳቀና፣ ‹‹አይደለም፤ ማኪያቶ አድርግልኝ›› አለው፡፡
ማኪያቶውን ይዞ ሲመጣ፣ በዚያው ቁራጭ ወረቀት ሰጠው፡፡
ቸኩሎ ሲከፍተው፣ የሊሊ እጅ ጽሑፍ ነው፡፡
ልታገስህ አልችልም፤ የቀድሞ ገርል ፍሬንድህን ገድል እኔ ጋ የምታወራው ምን ለማለት ፈልገህ ነው? ቀሽም ነህ:: ሊሊ ከማንም የማታንስ ለውጤት የምትኖር ሴት እንጂ የማንንም ጅል ፍቅር የምትለማመጥ ለማኝ እደለችም:: የምትኮራባቸው ታንቡሮችህን በቅጣት ወስጄያቸዋለሁ፡፡
ዛሬ ማታ አሜሪካ በራሪ ነኝ፡፡ ደህና ሁን፡፡ ወደ ቀድሞዋ ፍቅረኛህ መመለስህን ሰምቻለሁና ጎጆህን ያሙቀው፡፡
በድሩን ሲጠራው እጁና መላ ሰውነቱ ይንቀጠቀጣል፡፡ የቀድሞ እጮኛው ሰሞኑን አብራው ተቀምጣ ያያቸው እርሱ ነበር፡፡
‹‹በቀደም ሊሊ መጥታ ነበር እንዴ!››
‹‹አዎ፤ አንተና ሳሮን ተቀምጣችሁ እያለ አንገቷን ብቅ አድርጋ አይታ ሄዳለች፡፡››
ክው እንዳለ ማኪያቶውን ሳያስብ ጨለጠው፡፡ ምን ብሎ ይነግራታል! የቀድሞ ፍቅረኛው ባል አላት፤ የዛን ዕለት ድንገት ነው የተገጣጠሙት፡፡
በአጋጣሚ የተሞላች ሕይወት--- ኡፍፍፍ?
ተነስቶ ሄደ፡፡

Read 1409 times