Wednesday, 13 May 2020 00:00

ከፌስቡክ ገጾች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  በትግራይ ክልል ምርጫ ይደረግ?
አንዳንድ የትግራይ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች (እንዲሁም ህወሓት) የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስትና ከዘጠኙ ስምንቱ ክልሎች እየመራ ያለው የብልፅግና ፓርቲ በሀገር ደረጃ ምርጫ የማያካሂድ ከሆነ የትግራይ ክልል (ሀገር?) ለብቻው ክልላዊ (ሀገራዊ) ምርጫ ማካሄድ አለበት እያሉ ነው።
ምክንያት ደግሞ (1) በህወሓት በኩል ፦ በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት መሠረት አንድ አካል ስልጣን መያዝ የሚችለው ወይም በስልጣን የሚቆየው በህዝብ ሲመረጥ ነው። ከመስከረም በኋላ በህዝብ የተመረጠ ሕገ መንግስታዊ ይሁን ቅቡልነት ያለው መንግስት ስለማይኖር የክልሉ መንግስት የቅቡልነት ቀውስ (Legitimacy Crisis) ያጋጥመኛል ከሚል የስልጣን ማጣት ስጋት የመነጨ ነው።
(2) ምርጫ ካልተካሄደ በሌላ የተለየ ሕገ መንግስታዊ ያልሆነ አሰራር ሰበብ፣ የትግራይ ክልል ራስን በራስ የማስተዳደርና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ሊጨፈለቅ ይችላል ከሚል የተነሳ በመሆኑ የትግራይ አክቲቪስቶች መልካም እሳቤ ነው።
ሁለቱም ተገቢ ስጋቶች ናቸው። ግን ምርጫ ማካሄድ ብንችል ጥሩ ነበር። ከዐቅም በላይ በሆነ ምክንያት አልተቻለም። እናም ምርጫ ተራዝሟል! አሁን ህወሓት የቅቡልነት ቀውስ እንዳያጋጥማት ብለን ምርጫ ይደረግ ብለን እንጩህ? ምን አገባን? (ከህወሓት ውጭ ያለን ሰዎች ማለቴ ነው)። የቅቡልነት ቀውስ ሲያጋጥም የክልላችንና ህዝባችን ደህንነትና መብቶች እንዲከበሩ መጠበቅ ግን የሁላችን ሃላፊነት ነው።
ስለዚህ በክልል ደረጃ ምርጫ ይካሄድ ነው የምትሉት? የመንግስት ስልጣን ሕጋዊነትና ቅቡልነት የሚመነጨው ከምርጫ ነው ነው የምትሉት? አዎ ልክ ነው፤ ከምርጫ ነው የሚመነጨው።
ግን’ኮ ምርጫ በሀገር ደረጃ ተራዝሟል!? ምርጫ መራዘሙ ሕገወጥ ነው፣ ነው የምትሉት? የምርጫ መራዘም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀ’ኮ ሕጋዊ ሆነ ማለት ነው!? ሕገ መንግስቱ’ኮ በተለያዩ የሕግና የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ሕጋዊ ውሳኔ እንዲሰጥ ስልጣን ሰጥቶታል። ስለዚህ በሕገ መንግስቱ መሠረት፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀ ውሳኔ ሕጋዊ ተፈፃሚነት አለው። ስለዚህ የትግራይ ክልል የኢትዮጵያ አካል እስከሆነች ድረስ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወጡ ሕጎችን ወይም ውሳኔዎችን የማክበርና የማስከበር ሕገ መንግስታዊ ግዴታ አለባት።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫን ለማራዘም የወሰነውን ውሳኔ ሕገ መንግስታዊ አይደለም ነው የምትሉኝ? ውሳኔው ከሕገ መንግስት አንቀፅ ጋር ይጋጫል የሚል የሕግ ክርክር ተነስቶ በመጨረሻ ሕገ መንግስትን የመተርጎም ስልጣን ያለው የፌደሬሽን ምክር ቤት “ኢ-ሕገ መንግስታዊ” ነው ብሎ ውሳኔ እስካላሰለፈ ድረስ ምርጫን የማራዘሙ ውሳኔ ሕገ መንግስታዊ አይደለም ሊባል አይችልም።
ምርጫ ካልተደረገ የሚባለው ሕገ መንግስቱ እንዳይጣስ አይደል? የትኛው ሕገ መንግስት? የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አይደል? የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት እንዳይጣስ በትግራይ ምርጫ ይደረግ ከተባለ፣ ስለ ሕገ መንግስቱ መከበርም መጠንቀቅ አለብን። በሕገ መንግስቱ መሠረት ምርጫ የሚካሄደው በሀገር ደረጃ በተቋቋመው ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ አዘጋጅነት ነው። ሕጋዊው ምርጫ ቦርድ ደግሞ አሁን በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫ ማስተናገድ አልችልም ብሏል።
ስለዚህ የትግራይ ክልል መንግስት ምርጫ እንዲካሄድ ከፈለገ፣ ሀገራዊውንና ሕጋዊውን የምርጫ ቦርድን ማሳመን ይጠበቅበታል። ምክንያቱም ምርጫው ሕጋዊ እንዲሆን በሕጋዊ አካል መዳኘት ይኖርበታል። በሌላ ሕጋዊ ያልሆነ ቦርድ ተዘጋጅቶና ተዳኝቶ፣ ሕጋዊና ተቀባይነት ያለው ምርጫ ማካሄድ አይቻልም! የሲዳማ ሪፈረንደም፣ የአዲስ አበባና የሱማሌ ክልል ወዘተ ምርጫዎች የተከናወኑት በዚሁ ሀገራዊ ቦርድ አማካኝነት ነው።
ሕጋዊው የምርጫ ቦርድ የትግራይ ክልልን ምርጫ ለማከናወን ፍቃደኛ ባይሆንስ? (ማድረግ አልችልም ብሏል)። የትግራይ ክልል የራሱን ክልላዊ (ወይ ሀገራዊ) ምርጫ ቦርድን አቋቁማለሁ እያለ ነው። ለብቻ ይቻላል እንዴ? የክልል ምርጫ ቦርድ? በየትኛው የሕገ መንግስት አንቀፅ? ሕገ መንግስቱ እንዳይጣስ ብለህ፣ ሕገ መንግስቱን ጥሰህ፣ የራስህን ህገ ወጥ ምርጫ ቦርድ አቋቁመህ ምርጫ ልታካሂድ? ሕገ ወጥ ድርጊት ነው። ሕገ መንግስቱ፤ ክልሎች የራሳቸውን ክልላዊ ምርጫ ቦርድ በማቋቋም ምርጫ ማካሄድ ይችላሉ አይልም። ሕገ መንግስት በመጣስ ሕገ መንግስት አይከበርም!
የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አይመለከተኝም በማለት ራሱ እንደቻለ ወይ እንደተገነጠለ ሀገር (በነሱ ቋንቋ ዲ ፋክቶ ስቴት) በማሰብ የራስን ምርጫ ቦርድ አቋቁሞ፣ የክልል ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ታስቦ ከሆነ... የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት የማይመለከትህ ከሆነ ታዲያ፣ የትኛው ሕገ መንግስት እንዳይጣስ ነው ምርጫ ካላደረግን የሚባለው? እንደተለየ ሀገር ማሰቡ በራሱ’ኮ ፀረ የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት ነው። በራስህ ፍቃድ ፀረ ሕገ መንግስት ስትሆን’ኮ ቅጣት እየጋበዝክ ነው። ቅጣቱ ደግሞ የትግራይ ህዝብ መስዋእትነት የከፈለለት የራስን በራስ የማስተዳደርና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቶችን አደጋ ላይ ትጥላለህ።
በሆነ መንገድ ራስህን ቻልክና፣ ምርጫው በተያዘለት ቀነ ገደብ (ነሐሴ 23, 2012 ዓ.ም) ለማካሄድ ቆርጠህ ተነስተሃል እንበል።
በክልል (ሀገር) ደረጃ የመንግስትን ስልጣን የሚገድብ፣ የዜጎችን መብት የሚጠብቅ፣ የስልጣን ምንጭ የሚጠቁም ወዘተ-- ሕገ መንግስት አዘጋጅተህ ማስፀደቅ ይኖርብሃል። በፀደቀው ሕገ መንግስት መሠረት የምርጫ ቦርድን ማቋቋም ይኖርብሃል። የምርጫ ሕግ አዋጅ አዘጋጅተህ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን መመዝገብ አለብህ። የምርጫ ቁሳቁስ ከውጭ ሀገር አስገባ (14 ቀናት Quarantine ሆነው ይገባሉ)። መራጭ ህዝብ መዝግብ። የምርጫ ፈፃሚዎች ስልጠና ስጥ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ህዝብ እየሰበሰቡ የምረጡኝ ቅስቀሳ ያካሂዱ ....... ሁሉም በጥቂት ወራት ውስጥ!
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ለሦስት ወራት አስቸኳይ ጊዜ አውጀሃል። ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። መሰብሰብ አይፈቀድም። እንዴት ተደርጎ ነው ምርጫ የሚካሄደው?
በማይሆነው ነገር አንድከም!
የተፈጠረ ይፈጠር ግን የህዝቦችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት (Right to Self Rule) እና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት (Right to Self Determination) እደግፋለሁ፤ ለተፈፃሚነቱም እታገላለሁ!
(ከአብርሃም ደስታ ፌስቡክ)

«በደቦ ሀገርን” የማስተዳደር ምኞት?
የተቃውሞው ጎራ በጥቅሉ ከተወሸቀበት አቅም የማጣት ቅርቃር፣ የፖለቲካዊም ሆነ የኢኮኖሚያዊ ርዕዮተ ዓለም መልፈስፈስ፣ የሞራል፣ የስነ-ምግባር ስብራትና የእርስ በርስ ጥላቻና ሽኩቻ አኳያ፣ ሕገ መንግስቱ ቢፈቅድ እንኳን በሽግግር መንግስት ስም “በደቦ ሀገርን” ማስተዳደር ይቅርና አንድ ተቋም እንኳን እንዲመሩ ሕዝብ ሊፈቅድላቸው አይገባም ባይ ነኝ። በተለይ ደግሞ “ቀን አልፎብሃል” በሚል ሰበብ ሕጋዊ መንግስት ፈርሶ በሽግግር ስም የስብስብ መንግስት መመስረት፣ ዴሞክራሲን ለማስፈንም ሆነ ሃገርን በሰላም ለማስቀጠል ዋስትና ሊሆን ይችላል የሚል እምነት የለኝም።
ደርግ በሽግግር ስም መንግስት ከሆነ በኋላ፣ ስልጣኑ እስኪደላደል ድረስ፣ ተቃውሞን ለመግታት በመጀመርያ የወሰደው እርምጃ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን ማገድ ነበር። ቀጥሎ ተቃዋሚውን ለመምታት የዴሞክራሲያዊ፣ የፍትሕና የደህንነት ተቋማትን አፍርሶ፣ ነፍሰ በላ በሆኑ ኮሚሽኖች፣ ጊዜያዊ ቢሮዎች፣ አስተባባሪ ኮሚቴዎች፣ የቤተ መንግስት ቡድኖችና መሰረታዊ መዋቅሮች መተካት ነበር። ከዛ በኋላ በስልጣን ጨምዳጆች፣ ስልጣን ይገባናልና ተገፋተናን በሚሉ ሃይሎች መካከል በተቀሰቀሰው “ርዕዮተ ዓለም ለበስ” እና በጦር መሳሪያ የታገዘ ግብግብ የፈሰሰውን ደም፣ የተመዘገበውን ሀገራዊ ውርደት፣ የኢኮኖሚ ድቀት፣ ረሃብ፣ ቸነፈርና ስደት ታሪክም እንኳን እስከ ዛሬ መዝግቦ የጨረሰው ጉዳይ አይደለም።
ሕጋዊ መሰረት ያለውን መንግስት አፍርሶ አንድም ሕጋዊ መሰረት የሌለው ወይም በምክር ቤት አንድም ውክልና ያላገኘ ፓርቲና ግለሰብ (መሰባሰብ ከቻሉ) ተረባርበን መንግስት እንመስርት ሲሉን የሚገባኝ ነገር፣ “መንግስት ሆይ፤ ማጥፋትህ ካልቀረ እኛም እንጨምርበትና በደንብ በሕዝብ ላይ እንጫወት” ሆኖ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ከማይተማመኑበት መንግስት ጋር አሰላለፍን ማሳመር ለመተንተን እንኳን የሚያዳግት ነው።
ነባራዊውም ሆነ ተጨባጭ ሁኔታው የሚነግረን ይህንኑ ነው። ከተቃዋሚዎች የምንጠብቀው እንጠረጥረዋለን ከሚሉት መንግስት ተርታ በመሰለፍ ስልጣን የመጋራት ጥያቄ መደርደርን አይደለም። ይልቁኑ ነጻ፣ ገለልተኛና ተዓማኒት ያለው ምርጫ እንዲካሄድና በሕዝብ ይሁንታ ተመርጦ ለማገልገል እንዲቻል፣ የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብት ተቋማቱ እንዳይፈርሱ፣ ገለልተኛና አሳታፊ እንዲሆኑ፣ ይበልጥ እንዲጠናከሩ፣ በገዢው ፓርቲ ካድሬዎች እንዳይበረዙና እንዳይከለሱ መታገልን ነው።
የሀገሪቱ የስልጣን ባለቤት ክልሎች እንጂ የከተማ ውስጥ ፓርቲዎች ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩና ፓርቲያቸው አይደሉም። የሽግግር መንግስት መቋቋም ካለበትም በፌ/ም/ ቤትና በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ውክልናና መቀመጫ ባላቸው የክልል መንግስታት ይሁንታ ብቻ ነው። ይህንን ማድረግ የሚችለው ደግሞ ሁሉንም ወንበር የያዘው በስልጣን ላይ ያለው ሃይል ብቻ ነው። በፈቃደኝነት በመንግስቱ ውስጥ ለማሳተፍ ቢፈልግ እንኳን ሕጋዊ መብትም ሆነ ስልጣኑ የለውም።
ፈረንሳዮች “ቪቭ ላ ዲፌራንስ” (ልዩነት ለዘላለም ይኑር እንዲሉ) የቱንም ያህል የጠነከረ ሃሳብ ቢፈልቅ፣ የቱንም ያህል የተወናበደ የሚመስል ጥምረት ቢፈጠር መብት ነውና ሕግ እስካልተጣሰ ድረስ መከበር አለበት። ነገር ግን፣ ተጨባጭ ሁኔታውን (Objective reality) ተጠቅሞ አለመረጋጋት ለመፍጠር ያቆበቆበ ሃይል እንዳለና ሁኔታዎችም ለአስከፊ ግጭት የተመቻቹ እንደሆነ እየታወቀ ለመንግስት (Ultimatum) የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ማስቀመጥ ግን አደገኛ መልዕክት ሊያስተላልፍ ይችላል።
(ከሙሼ ሰሙ ፌስቡክ)

ህዝብ እኮ ስልጣን የራበው ሁሉ እየነቀለ የሚጥደው  የቦና ጎመን አይደለም
የጃዋርንና የልደቱን ውይይት አየሁት፤ ሰማሁት፡፡ ላየው የቀሰቀሰኝ ዋና ነጥብ አንድ ላይ ያመጣቸውን ጉዳይ የማወቅ ጉጉት ነበር፡፡ አገኘሁት፡፡ ያቀረቡበት መንገድ ነው ልዩነቱ፤ የጀዋር በፖለቲከኛ (ብስለትና መሰሪነት)፣ የልደቱ በወታደር (ጉልበትና ማስፈራራት) ከመቅረቡ በስተቀር፤ ‹መስከረም 30 የመንግስት ህጋዊ ተቀባይነት ስለሚያበቃ፣ መንግስት እኛ የምንለውን የማይቀበል ከሆነ፣ ህዝቡ ከእኛ ጋ ቆሞ መንግስትን እንዲቃወም- እንዲታገል› ነው፡፡
በጎው ነገራቸው፣... ‹‹መንግስት ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሁኔታው ላይ መወያየትና መስማማት አለበት›› የሚለው ነው፡፡ በርግጥ መንግስት ይህን ማድረግ አለበት፤ ይህ ሕዝብ በኮሮና ድቀቱ ላይ፣ በፖለቲካ ምክንያት የሚፈጠር ነውጥን የሚሸከም ትከሻ አይደለም፤ የሚሰማ ጆሮ የለውም፡፡
የጃዋርና የልደቱ ትልቁ ችግር፣ ህዝብን በኪሳቸው እንደያዙት ሳንቲም ሲፈልጉ ሊያስቀምጡት፣ ሲፈልጉ ደግሞ አውጥተው ሊጠቀሙበት፣ ደፍነው ለጅምላ ግዢ፣ ዘርዝረው ለችርቻሮ ሊያውሉት የሚችሉት አድርገው መቁጠራቸው ነው፡፡ ህዝቡን እውን ቢያውቁት የትላንቱን ውይይታቸውን ይዘውለት ለመቅረብ ባልደፈሩ ነበር፡፡ በተለይ እዚህ ላይ የልደቱ ድፍረት ለከት አልነበረውም፤ ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት ስብሰባ እንኳን ለመምራት፣ መብት እንደሌለው ሲናገር፣ ስለ ራሱ ሀገር የሚያወራ ፈጽሞ አይመስልም፤ በወረርሽኝ ምክንያት ምርጫ ስለተራዘመበት መንግስት ሳይሆን፣ ሀገር ለቅቄ እወጣለሁ ያለበትን ቀን ስላላከበረ ቅኝ ገዢ የሚያወራ ነው የሚመስለው፡፡ የሚገርመው ከወራት በፊት ልደቱ ‹‹ተቃዋሚ ፓርቲዎችን 10 ሺህ ፊርማ እንዲያሰባስቡ መጠየቅ፣ ፓርቲዎችን ማዳከምና እንዳይመሰረቱ ማድረግ ነው.. ባለበት አፉ ዛሬ 100 ሚሊየን ህዝብ ከጎኑ እንደሆነ በሙሉ ልብ ሲናገር መስማት ጤንነቱን ያጠራጥራል፤ ... ህዝብ እኮ ስልጣን የራበው ሁሉ እየነቀለ የሚጥደው የቦና ጎመን አይደለም፡፡
.ውይይታቸውን ልብ ላለ የልደቱና የጀዋር ልዩነት (ምንም እንኳን ጃዋር የፓርቲያቸውን የመፍትሄ ሀሳብ ግልጽ ባያወጣውም) ለችግሩ የሚያቀርቡት የመፍትሄ ሀሳብ ላይ ነው፡፡ በግሌ የጃዋር ፓርቲ የሽግግር መንግስትን እንደ መፍትሄ የሚያቀርብ አይመስለኝም:: ፕሮፌሰር  መረራ እና ጃዋር እራሱ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪዎች በመሆናቸው እውቀታቸውን ተጠቅመው፣ የተሻለ ሀሳብ ሊያቀርቡ ይችላሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡
.የልደቱ ‹‹የሽግግር መንግስት›› ሀሳብ ግን እንዳለው ቀድሞም በቀዳማዊ ኢህአዴግ መውደቅ ፍትጊያ (2009/10) የነበረ፣ ዛሬም ከኮሮና ጋር ያለ ነው፡፡ ልደቱ ከፍተኛ የስልጣን ፍላጎት ያለው ይመስለኛል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የ97ቱ ምርጫ ህዝባዊ ቅቡልነቱን እንዳወረደውና የሚፈልገውን የስልጣን እርካብ እንደማያስረግጠው ያውቃል፡፡ በመሆኑም ፓርቲዎች በመዋጮ የሚያቋቁሙት የሽግግር መንግስት ነው ብቸኛ የማርያም መንገዱ፡፡ ይኸው ነው፡፡
በርካታ ሀገሮች በኮሮና የተነሳ ምርጫ አራዝመዋል፤ የትኛው ሀገር ነው የሽግግር መንግስት የመሰረተው? የሽግግር መንግስት የተወሰነ ጊዜ ተሰፍሮለት የሚመሰረት ነው:: አሁን ያጋጠመው ችግር ወረርሽኝ ነው፤ 6 ወር ወይም አመት ሊወስድ ይችላል፤ አናውቅም፡፡
ለሁለቱም...
ፖለቲከኛ መሆን ካሻችሁ ህዝቡን እወቁት፤ አክብሩት፡፡ አክብሮታችሁ ቀርባችሁ ከማወቃችሁ ይሁን፡፡ ህዝብን የማያከብር ፖለቲከኛ ህዝብን ሊመራ አይችልም፡፡ ህዝብን አክብሩ፡፡ ህዝብ ጉልበት ስትፈልጉ የምትገዙበት የምስጢር ኪሳችሁ ሳንቲም፤ ስልጣን ሲርባችሁ እየነቀላችሁ የምትጥዱት የጓሮአችሁ ጎመን አድርጋችሁ አትቁጠሩት፡፡
(ከበድሉ ዋቅጅራ ፌስቡክ)

Read 6029 times