Monday, 11 May 2020 00:00

አርበኞችና ባንዳዎች ያመጡት ፈተና

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)

 እናቴ ወይዘሮ ይከኑ ሐሰን ከነገሩኝ ልጀምር፡፡ ወንድማቸው ቀኛዝማች አረጋ ሐሰን፣ ደብረ ሲና፣ የአሁኗ መካነ ሰላም (ወሎ ቦረና) ጣሊያኖች ያስሯቸዋል። ጠባቂዎችን አስክረው ቀኛዝማች አረጋን ከእስር አሰብረው ወደ ጎጃም ይሻገራሉ:: በዚህ የተናደደው ጣሊያን፣ ሁለቱን ወንድሞቻቸውን ሰብስቤ ሐሰንንና መኮንን ሐሰንን ወግዲ ገበያ ላይ ይሰቅላቸዋል፡፡ ኃይሌ ሮባ የተባለውን ባንዳ አዘምቶ ትልቅ ወንድማቸውን ፊታውራሪ ሽበሽ ሐሰንን ያስገድላቸዋል፡፡
ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ወግዲን ባቃጠለ ጊዜ፣ ቀኛዝማች አረጋ ከጎጃም መጥተው ተሳትፈዋል፡፡ ወደ ጎጃም ሲመለሱ ዓባይን የሚያሻግሩ ሁለት ዋናተኞች ይቀጠሩላቸዋል፡፡ ዋናተኞቹ ቃላቸውን አፍርሰው ዓባይ መሀል ላይ ለመሻገሪያ የተቀመጡበትን ጀንዲ ቀደው ውሃ በማስገባት ያሰጥሟቸዋል፡፡ የሴራው ባለቤቶች መገደላቸው ተነግሮኛል፡፡
እንኳን ለሰባ ዘጠነኛው የድል ቀን አደረሳችሁ!  
ብዙዎች አርበኞች ከጎናቸው ቆመው በነበሩና አብረዋቸው ሲታገሉ በቆዩ፣ “ወገኖቻችን ናቸው” ብለው እምነት ባሳደሩባቸው እንዲሁም አገልግሎታቸውን ፈልገው፣ ገንዘብ ከፍለው፣ ካሰብነው ያደርሱናል ብለው እምነት በጣሉባቸው ሰዎች እየተካዱ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡
‹‹እንዴት ሲዳሞ ወንድ የሌለባት አገር ይመስል ጠላት ይግባባት›› ብለው ግርማዊ ጃንሆይ በአስነገሩት አዋጅ መሰረት፤ ተበትኖ የነበረው ጦር መሰብሰብ ጀመረ:: ደጃዝማች ገብረ ማርያም ዝግጅታቸውን ጨርሰው ጠላትን ለማጥቃት ይመቸኛል ብለው ባሰቡት ወደራ በተባለው ጫካ ገቡ:: አብሯቸው የነበረውና እቅዳቸውን በሚገባ የሚያውቀው ባንዳው ፊታውራሪ አደመ ነፍሶ፤ እሳቸውንና አገሩን ከድቶ ለጣሊያኖች ገባ፡፡ የመሸጉበትን አካባቢ በቦምብ አስደበደበው፡፡ ‹‹በቂ ሰው የለኝም አምላኬን ይዤ እሰለፋለሁ›› ያሉት ደጃዝማች ገብረ ማርያም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው፣
ራስ ደስታ ወደ ኋላ እያፈገፈጉ መዋጋታቸውን ቀጠሉ፡፡ የካቲት 13 ቀን 1929 ጉጉቴ ከተባለው ቦታ፣ በእሳቸው የሚመራው ጦር፣ ከጣሊያን ጋር ገጠመ:: ኃይላቸው ክፉኛ የተመናመነ ቢሆንም መራራ ተጋድሎ አደረጉ፡፡ በጦርነቱ ላይ ደጃዝማች ገብረ ማርያም ሞቱ፡፡ ደጃዝማች በየነ መርድ  ቆስለው ተማርከው፣ በመትረየስ ተደብድበው ተገደሉ፡፡ ከጦርነቱ የተረፉት ራስ ደስታና ጥቂት ሰዎቻቸው ግቤ በረሃ ገብተው መዋጋት እንደሚሻል መከሩ:: ሁለት ሰዎች መንገድ እንዲያሳዩዋቸው ለእያንዳንዳቸው ሰባ ሰባ ብር ከፍለው ቀጠሩ፡፡ ሰዎቹ የገቡላቸውን ቃል አጥፈው ጠላት ካለበት ቦታ አደረሱዋቸው፡፡ ራስ ደስታ በእጃቸው ባለው መሳሪያ ሁሉ ተዋጉ፡፡ የሚተኩሱት ምንም ጥይት ሲያጡ፣ ቀጥ ብለው ቆሙና ተማረኩ፡፡ ለረጅም ጊዜ ገትረው ስቃዩን ያሳዩት የነበረው ግራዚያኒ፤ መማረካቸውን እንደሰማ እንዲገደሉ አዝዞ አስገደላቸው፡፡
ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም ፍቼን ሳይረግጡ መሻገር አይቻልም፡። ፍቼ ላይ ደግሞ ደጃዝማች ወንድ ወሰን ካሳና ደጃዝማች አበራ ካሳ አሉ፡፡ ጣሊያኖች ሁለቱን ማስወገድ አስፈለጋቸው፡፡ በእርቅ እንዲገቡ አቡነ ቄርሎስን፣ ራስ ገብረ ሕይወትን፣ ራስ ሥዩም መንገሻን ፣ ራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖትን ራስ ከበደ መንገሻ አቲከምን ደጃዝማች አመዴ አሊን፣ ደጃዝማች አያሌው ብሩንና ነጋድረስ አፈወርቅ ገብረ እየሱስን እንዲያግባቧቸው ላኩ፡፡ ሁለቱ ተስማምተው እጃቸውን ሰጡ፡፡ ጣሊያኖች ጊዜ አልወሰዱም እጃቸው እንደገቡ ገደሏቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የደጃዝማች ወንድ ወሰን ካሳ ባለቤት የራስ ስዩም ልጅ  ወይዘሮ ከበደች ሥዩም ከአርበኞች ተቀላቀሉ፡፡
ስለ ሌሎች መረጃ የለኝም፤ ራስ መንገሻ ወደ አርበኝነት ተመልሰው አምባላጌ ላይ የመሸገውን የጠላት ጦር በመውጋት እጁን እንዲሰጥ አድርገዋል፡፡  ራስ ኃይሉ ተከለ ሃይማኖት፣ ደግሞ ራሳቸው ፈልገው ወይም አርበኞች ፈልገዋቸው እንደሆን በትክክል ደፍሮ መናገር ባይቻልም፣  አንዳንድ አርበኞችን በአስታራቂነት ከጣሊያን ጋር በመደራደር ፋታ እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡
እንደ ራስ አበበ አረጋይ ያሉት አርበኞች ደግሞ አደራዳሪነታቸውን ጊዜ ማግኛና ማገገሚያ አድርገው ተጠቅመውበታል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ከስደት በተመለሱ ጊዜ ራስ ተቃውመው ጦር ባይመዙም፣ በንጉሡ ላይ የነበራቸውን ቅሬታ ከመግለጥ ወደ ኋላ አለማለታቸው ድብቅ አይደለም፡፡ ወደ ሌሎች ባንዳዎች እንለፍ፡፡
የግርማ ኃይለ ጊዮርጊስ የተባለ አርበኛ፣ በጦርነት ላይ ቆስሎ፣ ከተደበቀበት ቦታ ሆኖ ለዘመዱ ‹‹ቆስዬ ተኝቻለሁ፤ መንቀሳቀስ አልችልምና ድረስልኝ›› ብሎ ይልክበታል:: መልዕክተኛውም መልክቱን ያደርሳል፡፡ ዘመዱ ግን ለጠላት ጠቁሞ አስገደለው፡፡
ኤከማ ጉዲና እና በዳሳ ኦዳ የተባሉ ሰዎች፣ ልጅ ኃይለ ማርያም ማሞን ለመርዳት እንፈልጋለን ብለው ይቀርባሉ፡፡ የሰዎቹ አላማ እሳቸውን ለመግደል ነበርና ተኩስ ይከፍታሉ፡፡ በተኩስ ልውውጡ ልጅ ኃይለ ማርያም ግራ አይናቸውን ቢያጡም፣ ሕይወታቸው መትረፍ ችሏል፡፡ የካቲት 3 ቀን 1929 ባደረጉት ጦርነትም፣ ልጅ ሀይለ ማርያም 360 ባንዳ መግደላቸው ይታወቃል፡፡  
ቀምቢ ከምሳ የሚባለው የአባ ውቃው አሽከር፣ አርበኞችን ‹‹ከእናንተ ጋር ነኝ›› እያሉ እየቀረቡ አሳልፈው ለጠላት ከሚሰጡት ሰዎች አንዱ ነበር፡፡ አሊ ኡመር የተባለ ባንዳ፣ መኢሶን በተባለ ወንዝ 383 አርበኞችን አስገድሎ ወንዝ ከቷል፡፡ ፊታውራሪ ተሰማ ከተማ ደግሞ 13 ሰዎች ቤት ተዘግቶባቸው እንዲቃጠሉ አድርጓል:: አባ አብርሃም (አቡን ናቸው) ራስ እምሩ ወደ ተምቤን ሲዘምቱ፣ በአደራ የሰጧቸውን ሰላሳ ሺህ ብር ለራስ እምሩ በመመለስ ፋንታ ለጣሊያን አስረክበዋል፡፡
ቃል በቃል ባንዳ ማለት የማይቻል ግን ሥራቸው የባንዳ የሆነ ማለትም፣ ለጠላት የሚያገለግል ሥራ የሰሩ ብዙ ግለሰቦች እና አካባቢዎች አሉ፡፡
ልጅ ወሰን ኃይሉ የዋግን፣ ደጃዝማች ነጋሽ ወርቅነህ ደግሞ የሰሜንን አርበኛ እየመሩ ናቸው፡፡ ልጅ ኃይሉ በደጃዝማች ነጋሽ ላይ የበላይ መሆን ፈለጉ፡፡ ተደጋጋሚ የደብዳቤ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ፣ ልጅ ኃይሉ በደጃዝማች ነጋሽ ላይ ጦርነት ከፈቱ፡፡ ከቀኑ ስድስት ሰዓት እስከ ለሊቱ ሶስት ሰዓት በቀጠለው ጦርነት፣ ከሁለቱም ወገን ብዙ ሰው አለቀ፡፡ ኃይሉ ተሸንፈው ተመለሱ፡፡ በልጅ ኃይሉ ትምክህት ጠላትን ለመዋጋት የሚችለው ኃይል አለቀ፡፡
ወንጀሉ ባለቤት እያንዳንዱ ላይ ያረፈ ነው ማለት አለመሆኑን እንደ ተጠበቀ ሆኖ፣ በዚያ ዘመን አንዳንድ አካባቢዎች ንጉሡን ስለጠሉ ብቻ ለጣሊያን የሚበጅ የባንዳ ስራ መስራታቸውም እውነት ነው፡፡  
በንጉሡም ሆነ በራስ ሙሉጌታ የሚመራው ጦር ወደ ጦር ግንባር ሲጓዝ፣ ድል አልቀናው ብሎ ወደ አካባቢው ሲመለስ፣ በራያ አዘቦ፣ በዋጅራት፣ በወረ ሂመኖ ወዘተ-- የጠበቀው ሞት የአከባቢው ባንዳነት ማሳያ ነው፡፡
በነገራችን ላይ አስራ ሰባት ከመቶ የሚሆኑት ባንዳዎች እስከ መጨረሻው ድረስ ከጣሊያኖች ጎን ተሰልፈው መዋጋታቸውን ያውቃሉ?
ከዘመናዊ ባንዳዎች ይሰውረን!!

Read 2899 times