Monday, 11 May 2020 00:00

ባለ ምስራቾቹ ሚያዝያ እና መስከረም

Written by  አዲሱ ዘገየ (ዲላ ዩኒቨርስቲ፣ የሀገረሰብ ጥናት ተቋም)
Rate this item
(1 Vote)

 “--የብሉይ ኪዳን ታሪኮችን መሠረት በማድረግ የምትጠራው ሀገረ እስራኤል፤ የዘመን መለወጫ በዓልን የምታከብርበት ወር ሚያዝያ ነው፡፡ ይህም ታሪክ አለው:: ከግብጽ ባርነት መውጣት በጀመረችበት ዕለት ያዲሱ ዓመት መባቻ እንዲጀመር መደረጉ አንዱ ነው፡፡ ስለዚህ ሚያዝያን ከግዞት የመላቀቅ፣ ከስደት የመውጣት ትእምርትን የያዘች የነጻነት በዓልና መባቻ አደረጓት፡፡--”
                አዲሱ ዘገየ (ዲላ ዩኒቨርስቲ፣ የሀገረሰብ ጥናት ተቋም)


             የወርኀ ትንታኔን ለማቅረብ የተነሳሁት በዓድዋ እና በአርበኞች በዓል ዕለት ነው:: እኒህ ቀናትን ተከትዬ የካቲትን ዳሰስኩ፣ መጋቢት ቀጠለ፣ ይኸው ሚያዝያ፡፡ “ልማ በሥሉስ ጥፋ በሥሉስ!” እንዲል፡፡ የቀደምት አባቶች፣ እናቶችና የተፈጥሮ ሀብቶች የጋራ ድል ነው፡፡ እነዚህ ድሎች በጊዜና ቦታ የተወሰኑ ናቸውና በየወራቱ የተከናወኑ አንድምታዊ ገጾችን ከውስጥም ከውጭም በኩል አዟዙሮ ማየት የሚያስችል ፍንጭ በወፍ በረር ለማቅረብ ሳያተጋኝ አልቀረም፡፡ ተጨማሪ አጋጣሚ በዛሬዋ ዕለት ተከውኗል፤ ኮሮናን በጸሎት ለመቋቋም ከተለያዩ የእምነት ተቋማት ተሰባስበው ለሀገር ጸሎተ-ምሕላን ለማድረግ የየሃይማኖቱ መሪዎች መስማማታቸው ይታወቃል፡፡ የጸሎተ-ምሕላው መደምደሚያ ዕለት ነበረና ሁሉም የሃይማኖት አባቶች ባንድ መድረክ ላይ የተሰባሰቡበት መዝጊያ መርሃ ግብር ተከናውኖባታል፡፡
በድንበር ወስነን የምናከብራቸው እነዚህ ብሔራዊ በዓላት አንድም መከናወኛ ቦታው ያንድን ሉዓላዊ ሀገር፣ መንግሥትና ሕዝብ መኖሪያ ቀዬ የሚወክሉ ቢሆኑም፣ ማንነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ድንበርና ዘመንን እየተሻገሩ “አህጉር አቀፍ” ብሎም ዓለማቀፍ ዕውቅናና ከበሬታን እያገኙ ናቸው፡፡ እኛ ግን ያለፈ የድል ታሪክን ሰውነታችን ወዶትና መርጦት በጋራ ከማክበር ይልቅ፣ ያለ ስሙ ድሉን ላንድ ብሔር፣ ጎሳ፣ የመደብ ክፍል፣ ቋንቋ ተናጋሪ፣ አካል በመሸለም ከእውነታ የተፋታ አዲስ ታሪክ እንፈጥራለን:: በተቻለን መጠንም ሌሎችን መከፋፈያ የልዩነት ድንበሮችን በማነጽ ማንንም የማያስገባ ጠባብ አእምሯዊ ኬላ እናበጃለን፡፡ የፖለቲካው አስተዳደር አካላት (በተለይ ቅኝ ገዥዎች የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር ብቻ) ያሰመሩትን ድንበር፣ ፈጣሪ በእጁ ቀርጾ ለክቶ ለሚወደው/ዳት አያታችን ማውረሱን ከመተረክ በላይ፣ ከማስፋትና መስፋት፣ ማጥበብና መጥበብን የመረጥን እንመስላለን፡፡ በዚህች ወር ከተከናወኑ የታሪክ አጋጣሚዎች አንዱ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በሀበሻው አቆጣጠር ተመርታ ክብረ በዓላትን ለማክበር የተስማማችበት ወር ነው፡፡  
ወርኀ ሚያዝያ የሀበሻ መልክና ቃና እንዳላት ሁሉ፣ ሀበሻ ካልሆኑ (ሀበሾች እንዳሉ እንኳ የማያውቁ) ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ ሕዝብና አሕዛብ ጋር የሚያስተሳስር የአንድነት መልክ እንዳለን አብነት አደርጋታለሁ፡፡ አንድ ዓይነት፣ ወጥ የሕይወት ፍልስፍናና የኑሮ መልክ/ዘዴ የለንም፡፡ ድንበር ተሻግረን የወረስነው፣ ወይም ድንበራችንን ተሻግረው ከገቡ የሌላ ቡድን አባላት የቀዳነውን (በማወቅም ቢሉ ባለማወቅ) በመደባለቅ ቅይጥና ዝንቅ የኑሮ ዘዬን/ዘዴን ፈጥረናል እንጂ፡፡ አንዲት ቅንጣት የታሪክ አጋጣሚ ዓለምን በስፋት ለማዳረስ አፍታ እንደማይወስድባት ኮሮና አሳይቶናል፤ ዕድሜ ለኮሮና ዘርዓ አዳምን በሙሉ አንድ ላደረገው፡፡
ወርኀ ሚያዝያን በግንቦት ልደታ ቀን የማውጋት ዕድል ካገኘሁ ዘንዳ “ሚያዝያ ማን ናት/ትባላለች? የስሟ ትርጓሜ ምን ድነው? ከሌሎች ጎረቤቶቿ (አስራ ሶስቱ የሀገሬው) ወይም/እና አስራ ሁለቱ የውጭ ሀገራት ወራት የምትመሳሰልበትና የምትለይበት መልኮቿ ምን ምን ናቸው? የሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት አቆጣጠር አንጻር በምን መስፈርት ማዛመድ ይቻላል? እና ተዛማጅ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያግዝ ፍንጭ ይቀርባል፡፡
የሁሉም ወራት የበኩር በእኛ ሀገር አቆጣጠር ወርኀ መስከረም ነው/ናት:: ከመስከረም ቀጥሎ እስከ ጳጉሜ ያሉት የመስከረም ታናናሾች ናቸው፡፡ መጋቢት ላይ ሳለን የካቲትና ኅዳር ታላቆቹ መሆናቸውን አይተናል፡፡ ወርኀ ሚያዝያ መጋቢትን ታላቅ እህቱ/ወንድሙ (ያንድ ቤተሰብ ወላጅ ልጆች ናቸውና 13ቱ ወራት) ታደርጋለች፡፡ ቀድሞ የተወለደው የወደፊቱን/መጪውን በሚወልድበት የመተካካት ሥርዓት ብንመራ ደግሞ መጋቢት ወላጅ፣ ሚያዝያን ልጅ ማድረግ ይቻላል፡፡ ወላጅ በዕድሜ የላቀና ያረጀ ሲሆን፣ ልጁን በመተካቱ በልጁ ይታደሳል፡፡ መጋቢት የሚያዝያ ዋዜማው፣ ሚያዝያ የመጋቢት ማግስቱ/ልጁ ናት:: በሰባቱ ቀናት ውስጥ እነዚህ 13ቱ ወራት መባቻ፣ መባጃና፣ መካተቻ ዕለቶቻቸውን በመለየት እርስ በርስ ያላቸውን የቅርበት ዝምድናና፣ የርቀት ባዕድና ማመላከት ይቻላል፡፡ በዚህ ስሌት መሰረት “የሚያዝያ እና የመስከረም ወራት መባቻቸው አንድ ቀን ላይ ይውላል!” ሲባል ዝምድናቸውን አለመገመት አይቻልም፡፡ በጉርብትና ሁኔታም ታኅሳስ በሚብትበት ዕለት ማግስት የሚያዝያ መባቻ ይውላል ማለትም ታኅሣሥ 1 ሐሙስ ቢውል፣ ሚያዝያ 1 ዐርብ ዋለ ማለት ነውና፡፡ ይህም ታኅሣሥ የሚያዝያ ዋዜማው፣ ሚያዝያ የታኅሣሥ ማግስቱ ነው ያስብለናል፡፡ ይህን በሀገራዊ ምሳሌ ለማስረዳት ሲባል የሚከተለው ይጠቀሳል:: በጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ የሚመራው የክብር ዘበኛ ሠራዊት አባላት በሱሉልታ ልምምድ ሲያደርግ፣ ይህን ልምምድ ብዙዎቹ የታኅሣሥ ግርግር ዝግጅትና ትልቅ ማስጠንቀቂያ አድርገውታል፡፡
“መስከረም ባበባው፣ ሰርግ በጭብጨባው!” ይደምቃሉ፤ ይታወቃሉ፤ ይለያሉ፤ ይብታሉ፤ ብሎ ከመሙላት ባሻገር አስራ ሶስት ወንድማማቾችን የሚያስተሳስሩ ድሮች በአበባና በጭብጨባ የተገለጡ በረከቶች ናቸው፡፡ ዘመን የሚወልደው የባህርይ፣ የግብር፣ ወዘተ አምሳያ ልጅ አለው፡፡ ከነዚህ አንዱ መስከረም አበባን መውለዱ በተለይ ለዓይን፣ አፍንጫ፣ እጅ፣ ሕዋሳትን ደስ ያሰኛል፡፡ ሰርግ (“ለደስታ ጊዜ አለው፤ ለሐዘንም ጊዜ አለው” በሚል ማኅበረሰብ ዘንድ) በጭብጨባ መድመቁ ለስሜት ሕዋሳት በሙሉ የሚያረካ አስደሳች ስሜትን ይፈጥራል፡፡ የዚህ ምሳሌያዊ አነጋገር ፍች “መስከረም ባበባው፣ ሚያዝያ በጭብጨባው! መስከረም ባበባው፣ ሚያዝያም ባበባው! መስከረም በጭብጨባው፣ ሚያዝያ በጭብጨባው! መስከረም በሰርግ ድግስ፣ ሚያዝያም በሰርግ ድግስ! መስከረም ለደስታ፣ ሚያዝያ ለደስታ!” የሚል አንድምታዊ ፍቺዎችን ይዟል፡፡  
የሚያዝያ ወር በሀገሬው ዘንድ አብዛኛውን ጊዜ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት የሚፈጸም ከመሆኑ በላይ ወርኀ ትፍስህት/ደስታና ተሐድሶ የትንሣኤ በዓል የሚከበርበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እነዚህ በዓላት በሀገሬው ዘንድ የደስታና የመዝናናት እንዲሁም ማኅበራዊ ግዴታዎችን ከመወጣት ጋር የተዛመዱ ክዋኔዎች በአንድ ወገን፣ በሌላ ወገን ሃይማኖታዊ ከበራዎችን ከሀገረሰባዊ አምልኮዎች ጋር በመዘነቅ እንዲከወኑባቸው ይመረጣሉ፡፡ በጋብቻ ሥርዓተ ከበራዎች አንጻር የሚያዝያ ወር የሚሰጠው ፍካሬዊ ፍች አንድም፣ የሙሽራውና የሙሽሪት አበባ መልበስ ክብር መቀዳጀትን ሲመለክት፤ አንድም ከሙሽራው አንጻር አባት መሆን፣ ዘር መስጠት፣ ወልዶ የማስወለድ ሚና ይወክላል፡፡
የሚያዝያ ስመ ኮከብ ተውር ሲሆን ፍችው በሬ ማለት ነው፡፡ ከመጋቢት 26 እስከ ሰኔ 25 በሚሸፍነው የጸደይ/በልግ ወቅት የመሬት ባህርይ ይመግባል፡፡ በዚህም ጸደይ በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች የበልግ ዝናብ የሚዘንብበት በመሆኑ ለበልግ አዝመራ መዝሪያ መሬት የምትቆፈርበት፣ የምትታመስበት፣ የምትፈነቀልበት ወር መሆኑን በወሩ መጋቢ ኮከብ በበሬው ተምሳሌታዊ ፋይዳ መገመት ይቻላል፡፡ በልግ/ጸደይ ለክረምት መክረሚያ የሚበጅ የጓሮ አትክልትን ለማግኘት የሚረዳ ቅድመ ዝግጅት ይደረግበታል፡፡ ”በሚያዝያ ጎመን የዘራ ክረምቱን ሁሉ በላ” እንዲል፣ በሀገሬው ልማድ ክፉን ቀን መዝለቅ የሚቻልበትን አንድ አማራጭ ዕድል ይጠቁማል፡፡
የብሉይ ኪዳን ታሪኮችን መሠረት በማድረግ የምትጠራው ሀገረ እስራኤል፤ የዘመን መለወጫ በዓልን የምታከብርበት ወር ሚያዝያ ነው፡፡ ይህም ታሪክ አለው:: ከግብጽ ባርነት መውጣት በጀመረችበት ዕለት ያዲሱ ዓመት መባቻ እንዲጀመር መደረጉ አንዱ ነው:: ስለዚህ ሚያዝያን ከግዞት የመላቀቅ፣ ከስደት የመውጣት ትእምርትን የያዘች የነጻነት በዓልና መባቻ አደረጓት፡፡ አቢብ የሚለው የግእዝ ቃል ፍቺ መፀው፣ ዘመነ መፀው ከክረምት ቀጥሎ የሚብት የጽጌ፣ የፍሬ፣ የልምላሜ፣ ወራት፤ በዓለ ፋሲካ የሚውልበትና ወርኅ ትፍሥህት ወርኅ ተሐድሶ ማለት ነው:: ይህም ሚያዝያ ነው:: የቃሉ ሌላ ፍቺ ማበብ፣ ማፍራት፤ የዕጽዋት:: አበባ መልበስ መቀዳጀት፤ የሙሽራውና ሙሽሪት፡፡ አባት/እናት መሆን ዘር መስጠት/መቀበልና ወልዶ ማሶለድ ይገለጽባታል፡፡ ቀድሞ በዕብራይስጥ አቢብ የሚባለው ከባቢሎን ምርኮ በኋላ ኔሳን ተብሏል፡፡ ምልክታም፣ ባለምልክት፣ ባለታምራት ማለት ነው፡፡ ሁለተኛም ፀአትንና ሽሽትን ፈተናን ያሳያል፤ ንሻን ማለት ደግሞ ከኔሳን ጋር ይስማማል፡፡ ኔሳን ማለት ሚያዝያ ነው፡፡ የኛዎቹ መስከረም እና ሚያዝያ፤ አዝመራዎችና የደን ውጤቶች ወበባነት እንዲሁም ለአቅመ አዳም ወሔዋን ለደረሱ አበቦች የጋብቻ ክዋኔ የሚመረጡ የደስታና ሐሴት ወራቶቻችን ናቸው፡፡  
“ፋሲካ የሌለው ጦም፣ ደስታ የሌለው ዓለም!” ይባላል፤ ከፋሲካ አስቀድሞ ያለውን ፈተና የሚበዛበት ዐውድ ይጠቁማል፡፡ ፋሲካ ማለት ማለፍና መሸጋገር፣ ደስታና ሐሴት የሚገልጽ በመሆኑ፡፡ ፋሲካ፤ ከትንሣኤ ሌሊት ቅዳሴ ውጭ ጀምሮ እስከ ዳግም ትንሣኤ ያለው ስምንት ቀን:: የፋሲካ ምስጢር ከግብጽ ወደ ፍልስጥኤም መሻገርን መደብ አድርጎ የተሰጠ ስያሜ ነው:: በማለፍና በመሻገር ለተገኘው ድል መስዋዕት የማቅረቢያ ሥርዓትን ያሳያል:: ምክንያቱም መሻገር፣ ማለፍ፣ መዝለል፣ መራመድ፣  ዐልፎ ዘሎ ተራምዶ መሄድ:: መብዛት፣ መትረፍ፣ ከልክ ማለፍ፣ መተላለፍን ይጠቁማል፡፡ ለዚህ ሲባል ቂጣ፣ ብርኩታ፣ ርሚጦ፣ ጥረሾ፣ ተጋግሮ ይበላል፤ (ሊጡ ሳይቦካና ርሾ ሳይገባበት) ወዲያው ተለውሶ የሚጋገር ነው፡፡
ሚያዝያና መስከረም የአበባ ማበቢያ ወቅትን ይወክላሉ፡፡ ሁለቱ ወራቶች (በሀበሻ ቢሉ በፈረንጅ፣ በሀገሬው ቢሉ በውጭ ሀገራት) በማክሰኞ ፍጥረቶች ማለትም አታክልት፣ ዕፅዋት፣ አዝርዕት ወዘተ ወደ አበባነት የዕድሜ ክልል መሻገርን የሚገልጹ ወቅቶችን ይወክላሉ፡፡ የሀገሬው መስከረም ከዘመነ-ክረምት ወደ ዘመነ-ጽጌ መሻገሪያ ወራችን ናት፡፡ በጎርጎርሳውያኑ ቀመር የእኛ ሚያዝያ ወር “ኤፕሪል/April” እና “ሜይ/May” የተሰኙ ወራትን ስለሚይዝ፣ በዚህ አንጻር ያለው ፍቺ “ኤፕሪል” የአታክልትና ዕፅዋት ወደ ቡቃያነት፣ አበባነት፣ ዕድገት ደረጃ መሸጋገር ማለት ነው:: ለዚህ ሲባል አውሮፓውያኑ ቅርጫት ሙሉ ዕንቁላል በማቅረብ የወሩን ተምሳሌታዊ ፍቺ ሲገልጹ፣ የአዲስ ሕይወት ጅማሮ፤ የዓለም መክፈቻና ተስፋ ያለው የአዲስ ሕይወት ጅማሮን አመላካች ነው፡፡
ዛፎችና አበቦች የሚያድጉበት የመፀው መግቢያ ማለት ነው፡፡ ወደ ዘመነ-ጽጌ/መፀው  (Spring/ስፕሪንግ) መተላለፍን መሻገርን ገላጭ ወር ነው፡፡ አትክልትና አዝርዕት ወደ ቡቃያነት የሚያድጉበት ነው:: በእንግሊዝኛ ወርኀ ሜይ/May ማያ/Maia የተሰኘች ሴት ጣዖት የምትሠለጥንበት ወር  መሆኑ ሲገለጽ፣ ማያ እናት የሚል ፍቺ ሲኖረው፣ ይህቺ እናት የአበቦች ንግሥት ሆና ተስላለች፡፡ በሰሜኑ ንፍቅ ክበብ የሚገኙ በረዷማ ሀገራት ተሞክሮ የሚጠቅሰው ጥቅስ፤ ሁለቱ ወራቶች በሂደት የሚወጡትን ግብር እንደሚከተለው ይገልጻል፡- “April Showers; May Bring Flowers” በዚህ የተነሳ ወርኀ ሜይ የፍቅርና ስኬት ወር ስትባል፤ ዳግም መወለድ፣ መታደስ፣ አዲስ የሕይወት መልክ የሚጀመርባት ናት፡፡ “ሁል ጊዜ ፋሲካ የለም!” የሚለውን ሀገራዊ ብሒል፤ ከጎረቤት ሀገራት በወረስነው ቃል (ፋሲካ) ስንገልጽ ሁልጊዜማ ደስታ፣ ሐሴት፣ ፈንጠዝያ የለም ማለታችን ነበር:: ይህ አባባል በእኛ ላይ እንዲሰራ ዘመኑ ፈቀደ፡፡
በሚያዝያ ወራት ከሚከበሩ የዓለም አቀፍ በዓላት መካከል ለአብነት ያህል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ከመጨረሻው ወደ መጀመሪያ ቀናት ብናልፍ፣ ሚያዝያ 30 ቀን የዓለም የቀይ መስቀል ቀን ይከበራል:: ቀጥሎ የዓለም የአትሌቲክስ ቀን አንዱ ነው፤ ይህም የአርበኞች ቀን ሲከበር መሣ ለመሣ ይከበራል፡፡ በዚህ የሚያዝያ ወር ላይ ተወልዶ በዓለማቀፍ ውድድሮች ላይ በርካታ ሪከርዶችን የሰባበረው አትሌት (ሻለቃ) ኃይሌ ገብረሥላሴ፤ የወርኀ አትሌቲክስ ልጅ ነው፡፡ በዚህ ወር ተወልዶ ሳለ፣ በአትሌቲክስ ባያሸንፍ ነበር የሚቆጨው/ን፤ የዚህ አትሌት ሙያዊ ብሎም ወታደራዊ ማዕረጉ ከወሩ ጋር መጣጣማቸው አላገዙት ይሆን? አንድ!
በሀበሻና ፈረንጅኛ ስያሜያቸው መስከረምና ሚያዝያ ለአበባነት ታጭተዋል:: በኢትዮጵያ መስከረም፣ የአደይ አበባ፣ በፈረንጆቹ ሜይ፣ የሊሊ አበባ እንዲያፈሩ ወቅቱ አይመግባቸውም? ለዚህ ማስረጃ አንድ ታሪክ ላውሳ፡- አንጋፋው የፊልም ተዋናይ፣ ሲድኒ ፓቲዬር፣ “ሊሊስ ኦፍ ዘ ፊልድ” በሚለው ፊልሙ የኦስካር ሽልማት ሲቀበል የመጀመሪያው ጥቁር አሜሪካዊ ሆኖ የተዘገበው በሚያዝያ ወር ላይ ነው፡፡ እና በአበባ ወር ላይ አበባን ማውሳት አሸናፊ አያደርግም?
በዚህ ጽሑፍ ስለ ወራት እኩልነት በምናወሳበት ወቅት ስለ ሰው ልጆች እኩልነት የሚያወሳው የቀይ መስቀል ማኅበር ምሥረታ የተከናወነው በዚሁ ወር ነበር፡፡ በፈጠራ ሥራዎችና ውጤቶች አማካይነት የሚገለጸውን የነጻነት ቀን በተመለከተ የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን እና የመጻሕፍትና የቅጅ መብት ቀን ከነጻነት እንቅስቃሴዎች አይለዩም፡፡ ወርኀ ሚያዝያ ቀ.ኃ.ሥ. ጃማይካን ሲጎበኙ፣ በጃማይካ ዋና ከተማ ዝናብ በመዝነቡ እስከዛሬ ድረስ በራስ ተፈሪያን ዘንድ ዓመታዊ በዓል ሆኖ ይከበራል:: በትምህርት ረገድ የአዲስ አበባው ሊሴ ገብረ ማርያም ት/ቤት፣ የተፈሪ መኮንን ት/ቤት፣ የጄኔራል ዊንጌት ፪ኛ ደረጃ ት/ቤት፣ የሆለታ ጦር ት/ቤት የተመሰሩቱበት ወር ነው:: ከዚህ ባሻገር እንደ ት/ቤት የሚቆጠረው ብርሃን በቆቃ የመብራት ኃይል ማመንጫ  ተመርቆ ሥራ የጀመረው በዚያ ዘመንና ወር ነበር፡፡
ዕድሜ ለግንቦት ልደታ ለሚያዝያ ልጅ! ዕድሜ ለሰኔና ሰኞ ለሚያዝያ የልጅ ልጅ!...

Read 3335 times