Saturday, 09 May 2020 12:34

ኮሮና፡- ቁጥሩ አሁንም ማሻቀቡን ቀጥሏል...

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 የከፋና የባሰ እንጂ ይህ ነው የሚባል አንዳች የተሻለ ወይም ተስፋ ሰጪ ነገር ሳይሰማ፣ አለም ኮሮና በሚሉት የክፍለ ዘመኑ የሰው ልጆች ፈተና እልፍ አእላፍ ጥፋቶችን ነጋ ጠባ መቁጠር እንደቀጠለች፣ እንደሌሎች ሁሉ ይሄኛውም ሳምንት ተገባደደ፡፡
ቁጥሩ አሁንም ማሻቀቡን ቀጥሏል...
ወሰን ድንበር ሳያግደው፣ የተራቀቀው የዘመኑ ሳይንስ አንዳች መላ ሊያገኝለት አቅቶት፣ በአለም ዙሪያ በስፋት መሰራጨቱን የቀጠለው ኮሮና ቫይረስ፣ እስካለፈው ሐሙስ አመሻሽ ድረስ በመላው አለም በሚገኙ 212 አገራትና ግዛቶች ውስጥ ከ3,851,424 በላይ ሰዎችን ሲያጠቃ፣ ከ266,010 በላይ የሚሆኑትንም ህይወት እንደቀጠፈ  የዎርልዶሜትር ድረገጽ መረጃ ያሳያል፡፡
አሜሪካ አሁንም ከሰንጠረዡ አናት ላይ ናት…
እስከ ትላንት በስቲያ ድረስ 1,265,212 ሰዎች በቫይረሱ በተጠቁባት አሜሪካ፣ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉት ሰዎች ቁጥርም  74,881 መድረሱን ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡
ስፔን በ256,855፣ ጣሊያን በ214,457፣ እንግሊዝ በ201,101፣ ሩስያ በ177,160 የቫይረሱ ተጠቂዎች ከአሜሪካ በመቀጠል በተጠቂዎች ብዛት እንደ ቅደም ተከተላቸው እስከ አምስተኛ ያለውን ስፍራ የያዙ የአለማችን አገራት ሆነዋል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ለሞት የተዳረጉባት ሰዎች ቁጥር በሳምንቱ በእጅጉ በጨመረባትና ጣሊያንንና ስፔንን በመቅደም፣ ከአሜሪካ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ በተቀመጠችው እንግሊዝ፣ የሟቾች ቁጥር 30,076 መድረሱ ሲነገር፤ ጣሊያን በ29,684፣ ስፔን በ26,070፣ ፈረንሳይ በ25,809 ሟቾች ይከተላሉ፡፡
ኢኮኖሚው ክፉኛ እየተጎዳ ነው
በአለማቀፍ ደረጃ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ክፉኛ ከተጎዱት ዘርፎች መካከል አንዱ የሆነው የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ፣ ዘንድሮ እስከ 80 በመቶ የሚደርስ የገቢ መቀነስ እንደሚያስመዘግብ የአለም የቱሪዝም ድርጅት፣ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መረጃ ጠቁሟል፡፡
ባለፉት ሶስት ወራት አገራትን የጎበኙ አለማቀፍ ቱሪስቶች ቁጥር በ22 በመቶ ያህል መቀነሱን በማስታወስ፣ የአለማችን የቱሪዝም ዘርፍ በአመቱ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ እስከ 1.2 ትሪሊዮን ዶላር የሚደርስ ገቢ ሊያጣ እንደሚችል የገለጸው ድርጅቱ፤ቱሪዝሙ መስክ ተሰማርተው የሚገኙ 120 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ከስራ ገበታቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉም አስታውቋል፡፡ ኮሮና ቫይረስ የቱሪዝም ዘርፋቸውን ክፉኛ ከጎዳባቸው አገራት አንዷ በሆነችው ስፔን፤ የአለማቀፍ ጎብኝዎች ቁጥር ባለፈው መጋቢት ወር ብቻ በ64.3 በመቶ መቀነሱን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ላለፉት ሰባት ተከታታይ አመታት ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ቱሪስቶች የተጎበኘች ቀዳሚዋ የአለማችን አገር የነበረችው ስፔን፤ ኮሮና ባሳደረባት ተጽዕኖ ሳቢያ ኢኮኖሚዋ በ5.2 በመቶ መቀነሱ ተነግሯል፡፡ በሌላ ዜና ደግሞ የፊሊፒንስ ጥቅል አገራዊ ምርት ባለፉት ከ20 በላይ ዓመታት ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ መቀነሱን የዘገበው አናዶሉ ኤጀንሲ፤ ባለፉት 3 ወራት ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ያሳየው ቅናሽ 0.2 በመቶ መሆኑንም አስነብቧል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የነዳጅ ገቢዋ በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰባትና በጀቷን ለመቀነስ የተገደደችው ናይጀሪያ፤ ኢኮኖሚዋ በአመቱ በ3.4 በመቶ ያህል እንደሚቀንስ የአገሪቱ የፋይናንስ ሚኒስትር ዛይናብ አህመድ መናገራቸውንም ቢቢሲ ባወጣው ዘገባ አመልክቷል፡፡ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ብዙ የአለማችን ታላላቅ ኩባንያዎች ለኪሳራ መዳረጋቸውንና በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰራተኞቻቸውን ማሰናበት የቀጠሉ ሲሆን ታዋቂው አየር መንገድ ቨርጂን ጋላክቲክ 3 ሺህ ሰራተኞቹን ማሰናበቱን ባለፈው ማክሰኞ ሲያስታውቅ፣ ኳታር ኤርዌይስ ብዛት ያላቸውን ሰራተኞቹን እንደሚያሰናብት ከሰሞኑ ማስጠንቀቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ግዙፉ የፊልምና የመዝናኛው ዘርፍ ኩባንያ ዋልት ዲዝኒ ባለፉት ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ፓርኮቹን በመዝጋቱና አዳዲስ ፊልሞችን ባለማውጣቱ ሳቢያ የ1.4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማጣቱን አስታውቋል፡፡
በመላው እንግሊዝ የሚያዝያ ወር የመኪኖች ሽያጭ ከ1946 ወዲህ ዝቅተኛው ሆኖ መመዝገቡን የዘገበው ቢቢሲ፤ በሰሜን አየርላንድ በሚያዝያ ወር የመኪና ሽያጭ ባለፈው አመት ከነበረበት በ99 በመቶ ያህል መቀነሱንና በወሩ የተሸጡ መኪኖች 24 ብቻ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡ ታዋቂው የመኪና አምራች ጄኔራል ሞተርስ ኩባንያ በበኩሉ፤ በመላው አለም የሚገኙ 13 ሺህ ያህል ሰራተኞቹ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ከስራ ገበታቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ማስታወቁ የተነገረ ሲሆን ታዋቂው የትራንስፖርት ኩባንያ ኡበር፣ ከአጠቃላይ ሰራተኞቹ 14 በመቶ ያህል ወይም 3 ሺህ 700 የሚደርሱትን ላልተወሰነ ጊዜ ከስራ እንደሚቀንስ ሰሞኑን ማስታወቁም ተነግሯል፡፡
በህንድ ከኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ጋር በተያያዘ የእንቅስቃሴ መቋረጥ፣ በሚያዝያ ወር ከ122 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከስራ ገበታቸው መፈናቀላቸውን ቢቢሲ ሲዘግብ፤ ዘ ጋርዲያን በበኩሉ፣ የእንግሊዝ ስራ አጥ ወጣቶች ቁጥር እስከ መጪው አዲስ አመት ድረስ 1 ሚሊዮን እንደሚደርስ መነገሩን አስነብቧል፡፡
የኮሮና የሞት ምጣኔ ጉዳይ
በአለማችን በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ከሩብ ሚሊዮን ማለፉ በመገናኛ ብዙሃን የተዘገበው፣ በሳምንቱ የመጀመሪያ ዕለት ሰኞ ነበር፡፡ የሟቾች ቁጥር ነጋ ጠባ ማሻቀቡ እንዳለ ሆኖ፣ በተለያዩ አገራት በቫይረሱ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ከተጠቁት አንጻር ሲሰላ የሚገኘው ውጤት ግን ጥያቄን የሚያጭርና ለጥናት የሚጋብዝ መሆኑ እየተነገረ ይገኛል፡፡
አንዳንድ አገራት ጥቂት ሰው በቫይረሱ ተይዞባቸው ብዙ ሰው ሲሞትባቸው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ብዙ ሰው ተይዞባቸው ጥቂት ሞቶባቸዋል፡፡ አገራት ምን ያህል በታማኝነት የተጠቂዎችንና የሟቾችን ትክክለኛ ቁጥር ይገልጻሉ የሚለው ጉዳይ ከአገራት የሞት ምጣኔ ጋር ተያይዞ የሚነሳ መሆኑም ይነገራል፡፡
የአለማችን አገራት የኮሮና ቫይረስ የሞት ምጣኔ የተለያየ እንደሆነ የዘገበው አልጀዚራ፤ ከ0 ነጥብ 1 በመቶ በታች የሆነው እጅግ ዝቅተኛ የአለማችን የኮሮና ቫይረስ የሞት ምጣኔ ከተመዘገበባቸው አገራት መካከል ኳታርና ሲንጋፖር እንደሚገኙበት አመልክቷል:: ኒውዚላንድና አውስትራሊያና በተመሳሳይ ከአለማችን አገራት አነስተኛ ነው የተባለው የ1 በመቶ የሞት ምጣኔ እንደታየባቸውም ገልጧል::
ቤልጂየም በ16 በመቶ ከአለማችን አገራት ከፍተኛውን የኮሮና ቫይረስ የሞት ምጣኔ መያዟንና፣ በአንጻሩ ደግሞ የኮሮና ቫይረስ የሞት ምጣኔ በእንግሊዝ 15 በመቶ፣ በጣሊያን 14 በመቶ፣ በአሜሪካ በ6 በመቶ ላይ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ በአልጀሪያ ከአፍሪካ ከፍተኛው የ10 በመቶ የሞት ምጣኔ መመዝገቡንም አመልክቷል፡፡
ወደ መደበኛ ህይወት መመለስ
የኮሮና ቫይረስ መነሻ በሆነችው የቻይናዋ ውሃን ከተማ ለወራት ተዘግተው የነበሩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሳምንቱ መጀመሪያ ዳግም የተከፈቱ ሲሆን፣ ከ120 በላይ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ተነግሯል፡፡ በጀርመን አንዳንድ ከተሞች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መከፈት መጀመራቸውንም ዘ ዴይሊ ሚረር ዘግቧል፡፡
ስፔን፣ ፖርቹጋል፣ ቤልጂየም፣ ፊንላንድ፣ ናይጀሪያ፣ ህንድ፣ ማሌዢያ፣ ታይላንድ፣ እስራኤል፣ ሊባኖስና ሌሎች በርካታ የአለማችን አገራት በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ተዘግተው የቆዩ ፋብሪካዎችን፣ የግንባታ ፕሮጀክቶችን፣ ፓርኮችንና ቤተ መጻህፍትን ስራ እንዲጀምሩ መፍቀዳቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ስሎቫኪያ በኮሮና መዘጋት ሳቢያ የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት በሚል ከሰሞኑ ሬስቶራንቶች፣ ሆቴሎችና ሱቆችን ጨምሮ የተለያዩ የንግድ ተቋማት እንዲከፈቱ የወሰነች ሲሆን፣ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎችና የሰርግ ስነስርዓቶችም ሰው ሳይበዛ እንዲከናወኑ እንደምትፈቅድ ፍንጭ ሰጥታለች፡፡
የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎችና ሟቾች ቁጥር እየጨመረ ባለባት ፓኪስታን፤ መንግስት የእንቅስቃሴ ገደቦችን ማላላት እንደሚጀምር ከትናንት በስቲያ ያስታወቀ ሲሆን ሁለተኛ ዙር የወረርሽኝ ማዕበል ያሰጋታል የተባለችው ጀርመን በበኩሏ፤ የተዘጉ ሱቆችንና ትምህርት ቤቶችን በሙሉ ከሳምንታት በኋላ ለመክፈት ማሰቧም ተነግሯል፡፡
ኮሮና እና ምርጫ
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመላው አለም መስፋፋቱን ተከትሎ፣ በተለያዩ የአለማችን አገራት ሊካሄዱ ቀን ተቆርጦላቸው የነበሩ አገራዊና ክልላዊ ምርጫዎች መስተጓጎላቸውና መራዘማቸው ተነግሯል፡፡
የኢንዶኔዢያ መንግስት ባለፈው ሰኞ ባደረገው ስብሰባ፣ በመጪው መስከረም ሊያከናውነው የነበረውን ክልላዊ ምርጫ፣ በኮሮና ሳቢያ ወደ ታህሳስ ወር እንዲሸጋገር መወሰኑን ታይም መጽሄት ዘግቧል፡፡ ሶርያ በሚያዝያ መጀመሪያ ልታደርገው የነበረውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ፣ ወደ ግንቦት መጨረሻ ስታራዝም፣ በኢራንም በሚያዝያ አጋማሽ ሊከናወን ቀን ተቆርጦለት የነበረው ሁለተኛ ዙር ምርጫ፣ ወደ መጪው መስከረም እንዲሸጋገር ተደርጓል፡፡
ሲሪላንካ ቀጣዩን ምርጫ ከሚያዝያ መጨረሻ ወደ ሰኔ አጋማሽ ገፋ ስታደርገው፣ በህንድም የተወሰኑ ክልላዊ ምርጫዎች በወራት እንዲራዘሙ መደረጉን ዘገባዎች ያስረዳሉ፡፡
በአህጉረ አፍሪካ ከወራት በኋላ ምርጫ ሊያካሂዱ ቀጠሮ በያዙ ጊኒ፣ ብሩንዲ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ጋና፣ ኒጀር፣ ታንዛኒያናና ቶጎ በመሳሰሉት አገራት፣ ኮሮናቫይረስ፣ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳን ሊያስቀይር ይችላል ተብሏል፡፡  
በዓለም ላይ 90 ሺ የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ተይዘዋል
ከ260 በላይ ነርሶች ለሞት ተዳርገዋል
በመላው አለም ቁጥራቸው ከ90 ሺህ በላይ የሚደርስ የጤና ባለሙያዎች በስራ ገበታቸው ላይ እያሉ በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸውን ኢንተርናሽናል ካውንስል ኦፍ ነርስስ የተባለው አለማቀፍ ተቋም ባለፈው ረቡዕ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
ኮሮናቫይረስ በመላው አለም ከ260 በላይ ነርሶችን ለሞት መዳረጉን የጠቆመው ተቋሙ፤ ራሳቸውን ከቫይረሱ መከላከል በማይችሉበት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ የሚሰሩና ተገቢው ጥበቃ የማይደረግላቸው የጤና ባለሙያዎች እየተበራከቱ ከመምጣታቸውና በብዙ አገራት ጥናት ካለመደረጉ ጋር በተያያዘ፣ በቫይረሱ የተጠቁ ባለሙያዎች ቁጥር ከተባለው በእጥፍ ያህል ሊጨምር እንደሚችልም አመልክቷል፡፡
በመላው አለም በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከ3.5 ሚሊዮን በላይ መድረሱን የጠቆመው ተቋሙ፤ የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ የመያዝ ዕድል በአማካይ 6 በመቶ ነው ቢባል እንኳን፣ በዚህ ስሌት ከ200 ሺህ በላይ ባለሙያዎች በቫይረሱ ተይዘው ሊሆን እንደሚችል ግምቱን አስቀምጧል፡፡
ኮሮናና አፍሪካ
ኮሮና ቫይረስ በአፍሪካ አገራት እስከ ትናንት በስቲያ አመሻሽ ድረስ ያጠቃቸው ሰዎች ቁጥር 51 ሺ 700 የደረሰ ሲሆን ለሞት የተዳረጉት ሰዎች ቁጥር ደግሞ ወደ 2 ሺህ 12 ከፍ ማለቱን የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠር ማዕከል ይፋ ባደረገው መረጃ አስታውቋል፡፡
በአህጉሪቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የተጠቁት በደቡብ አፍሪካ መሆኑንና በአህጉሪቱ 7 ሺህ 800 ያህል ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸውን የጠቆመው መረጃው፤ ግብጽ በ7 ሺህ 600፣ ሞሮኮ በ5 ሺህ 408፣ አልጀሪያ በ4 ሺህ 997 ተጠቂዎች እንደሚከተሉም አብራርቷል፡፡ በአፍሪካ በኮሮና ሟቾች ቁጥር ቀዳሚነቱን የያዘችው 476 ሰዎች የሞቱባት አልጀሪያ ስትሆን፣ በግብጽ 469፣ በሞሮኮ 183 ሰዎች እንደሞቱም መረጃው አክሎ ገልጧል፡፡
የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል በ20 የአፍሪካ አገራት የሰራውን ጥናት ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ አብዛኞቹ አፍሪካውያን ለ14 ቀናት ከቤት እንዳይወጡ ቢከለከሉ ለረሃብና ለውሃ ጥም እንደሚጋለጡ ተናግረዋል፡፡
ጥናቱ ከተደረገባቸው ሰዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ለ14 ቀናት ከቤት ሳይወጡ ቢቆዩ ያላቸውን ገንዘብ ጨርሰው ባዶ እጃቸውን እንደሚቀሩ መናገራቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ መንግስታት ዜጎችን ከቤት እንዳይወጡ ከመከልከላቸው በፊት መሰረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸው ጥናቱ ምክረ ሃሳብ ማቅረቡንም አመልክቷል፡፡
የኬንያ መንግስት “ተመርምረን ቫይረሱ ቢገኝብንና ወደ ኳራንቲን ብንገባ ክፍያውን አንችለውም” የሚል ፍራቻ ያለባቸውን ዜጎች ወደ ኮሮና ምርመራ እንዲመጡ ለማበረታታት በማሰብ፣ ከውጭ አገራት ገብተው እንዲሁም ቫይረሱ እንዳለባቸው ተጠርጠረው ለ14 ቀናት በልዩ ማቆያ ውስጥ ለሚቆዩ ዜጎች፣ አጠቃላይ ወጪያቸውን ለመሸፈን መስማማቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
“ምንጩን ከማጣራት፤ ማዕበሉን መግራት”
ቻይና እና አሜሪካ - በቃላት ጦርነት
ወትሮም በንግድ ጦርነት እሰጥ አገባ ውስጥ የከረሙት አሜሪካና ቻይና፤ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ሌላ መነታረኪያ ሆኖ በመጣላቸው ኮሮና ቫይረስ ሳቢያ የጀመሩትን የቃላት ጦርነት በሳምንቱም አጠናክረው ገፍተውበታል፡፡
ኮሮና ቫይረስ በአሜሪካም ሆነ በመላው አለም እያደረሰ ላለው ጥፋት የቻይናን መንግሥት ተጠያቂ ማድረጉን የቀጠለው የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር፤ ቫይረሱ ውሃን ውስጥ ከሚገኝ ቤተ ሙከራ የወጣ ነው በሚል ላቀረበው ውንጀላ፣ ቻይና “በሬ ወለደ አትበሉ!” የሚል ምላሽ ሰጥታለች፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ “ቻይናውያን የሰሩትን ትልቅ ስህተት ለማመን አልፈቀዱም፤ ወደዚያው ሄደን ጉዳዩን ለማጣራት ብንሞክርም አልፈቀዱም” በማለት ከሰሞኑ ላቀረቡት ወቀሳ፣ ምላሽ የሰጡት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቻይና ልዑክ በበኩሉ፤ “ኮሮና ቫይረስ ከየትና እንዴት ተነሳ የሚለውን ጉዳይ እንመርምር የሚለውን ወቅቱን ያልጠበቀ ጉዳይ ትቶ፣ ከፍተኛ ጥፋት እያደረሰ ያለውን ወረርሽኝ ለማስቆም ትኩረት ሊሰጥ ይገባል” ብለዋል፡፡
የወቅቱ ዋነኛ ትኩረቴ ወረርሽኙን ማቆም ነው ያለችው ቻይና፤ ኮሮና ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ስር ሳይውል ጉዳዩን ላጣራ ብለው የሚመጡና በሽታውን የፖለቲካ አጀንዳ ለማድረግ የሚፈልጉ አለማቀፍ ባለሙያዎችን እንደማትቀበልም ልዑኩ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ ስታውቋል፡፡
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ሁዋ ቹዊንግ በበኩላቸው፤ የትራምፕ አስተዳደር “ቻይና ግልጽነት በጎደለው አካሄድ ቫይረሱ አለምን እንዲያጥለቀልቅ አድርጋለች” በሚል ለሚያቀርበው ወቀሳ በሰጡት ምላሽ፣” ጉዳዩን ለሳይንቲስቶችና የህክምና ባለሙያዎች ቢተውላቸው ይሻላል ባይ ነኝ… አገራዊ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚፍጨረጨሩ ውሸታም ፖለቲከኞች፣ ሳይንስ ውስጥ ምን ጥልቅ አደረጋቸው” ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
 የፊት ጭምብል ከ50 በላይ አገራት
ግዴታ ሆኗል
የፊት ጭንብል ከኮሮና ቫይረስ የማስጣሉ ነገር አወዛጋቢ ሆኖ ቢቀጥልም፣ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መስፋፋቱን ተከትሎ፣ ዜጎቻቸው የፊት ጭምብል እንዲያደርጉ የሚያስገድዱ አገራት ቁጥር ከ50 በላይ መድረሱን አልጀዚራ ዘግቧል::
እንግሊዝና ሲንጋፖርን የመሳሰሉ አገራት ለታማሚዎችና የህክምና ባለሙያዎች የፊት ጭንብል እጥረት እንዳይፈጠር ከመስጋት ጤነኛ ሰዎች የፊት ጭንብል እንዳይጠቀሙ ዜጎቻቸውን ቢመክሩም፣ በአንጻሩ ዜጎቻቸው ያለ ጭንብል እንዳይንቀሳቀሱ የሚያስገድዱ አገራትም እየጨመሩ ነው፡፡
የፊት ጭንብል ማድረግን ግዴታ ካደረጉና ቅጣት በመጣል ላይ ከሚገኙ የአለማችን አገራት መካከል ናቸው ብሎ ዘገባው ከጠቀሳቸው መካከልም ቬንዙዌላ፣ ቬትናም፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ስሎቫኪያ፣ ኩባ፣ ሞሮኮ፣ ቱርክ፣ ካሜሩን፣ እስራኤል፣ አርጀንቲና፣ ሉክዘምበርግ፣ ጃማይካ፣ ኡጋንዳና ኳታር ይገኙበታል፡፡ የፊት ጭምብል ማድረግን ግዴታ ያደረጉ አገራት መመሪያውን ተላልፈው በሚገኙ ዜጎች ላይ የየራሳቸውን ቅጣት መጣል የጀመሩ ሲሆን፣ ለአብነትም የፊት ጭምብል ሳያደርግ ሲንቀሳቀስ የተገኘን ሰው በ3 ወራት እስራትና በ1 ሺህ 300 ዶላር የምትቀጣዋ ሞሮኮ ትጠቀሳለች፡፡
የአለም ጤና ድርጅት፣ ጤነኛ ሰዎች የፊት ጭምብል ማድረግ እንደማይጠበቅባቸውና በአንጻሩ ደግሞ የሚያስሉና የሚያስነጥሱ፣ የጤነኝነት ስሜት የማይሰማቸው እንዲሁም የታመመ ሰው የሚንከባከቡ ሰዎች ግን የግድ የፊት ጭምብል ማድረግ አለባቸው የሚል ምክር ሲለግስ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
8 ቢሊዮን ዶላር ለክትባት
የአለማችን መሪዎች፣ የተለያዩ ድርጅቶችና ለጋሾች፣ ለኮሮና ቫይረስ ክትባት ምርምር፣ ምርትና ስርጭት የሚውል 8 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ ደፋ ቀና እያሉ ቢሆንም፣ አሜሪካ ግን የለሁበትም ብላለች፡፡
ገንዘቡን ለማሰባሰብ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ከሚገኙት መካከል አውሮፓ ህብረትና እንግሊዝ እንዲሁም ኖርዌይ፣ ጃፓን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ካናዳና ሳኡዲ አረቢያ የሚገኙበት ሲሆን ቃል ከገቡት ለጋሾችና ዝነኞች መካከልም 1 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል የገባችው ታዋቂዋ ድምጻዊት ማዶና ትገኝበታለች፡፡
ዜጎችን ወደ አገር ቤት መመለስ
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በተጣሉ የበረራ ገደቦችና የድንበር መዘጋቶች ሳቢያ ከአገራቸው እንደወጡ የቀሩ ዜጎቻቸውን እያፈላለጉ ወደ አገር ቤት የሚመልሱ መንግስታት ተበራክተዋል፡፡ ህንድ በተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት፣ ሲንጋፖር፣ እንግሊዝና አሜሪካ የሚገኙ 400 ሺህ ያህል ዜጎቿን፣ በኤር ኢንዲያ አየር መንገድ አማካይነት ወደ አገር ቤት የመመለስ እንቅስቃሴዋን ከትናንት በስቲያ ጀምራለች፡፡
የፓኪስታን መንግስት በመላው አለም በሚገኙ 88 ያህል አገራት ውስጥ ተበትነው የሚገኙ ከ100 ሺህ በላይ ዜጎቹን፣ በ33 ልዩ የአውሮፕላን በረራዎች ወደ አገራቸው መመለስ እንደሚጀምር ከሰሞኑ ይፋ ማድረጉን የዘገበው አናዶሉ ኤጀንሲ፤ ከዚህ ቀደም ከ38 አገራት 15 ሺህ ፓኪስታናውያንን መመለሱንም አስታውሷል፡፡
ናይጀሪያ በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስና በለንደን የነበሩ ከ565 በላይ ዜጎቿን ወደ አገር ቤት ለመመለስ ዝግጅቷን ያጠናቀቀች ሲሆን ግብጽ በበኩሏ፤ በኩዌት የኮሮና ቫይረስ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ጥሰዋል በሚል የተባረሩ 500 ያህል ዜጎቿን መመለስ ጀምራለች፡፡



Read 13049 times