Saturday, 02 May 2020 13:50

የትርፍ ጊዜ ሥራ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ቅዳሜ ስምንት ሰዓት ተኩል፡፡
አዲሱን ቤቴን ለማደራጀት፤ ቀስ እያልኩ የቤት እቃዎች ገዝቶ ማሟላት ከጀመርኩ አንድ ዓመት ሞላኝ፡፡ የቀረኝን የመጽሐፍ መደርደሪያ ለመግዛት በባልደረቦቼ ጥቆማ መሰረት፣ “ፍሎውለስ ፈርኒቸርስ” የሚባል ቤት መጥቻለሁ፡፡ የሱቁ ስፋት የትየለሌ፤ ምርጫውም ብዙ ዓይነት ነው፡፡
“የእንጨት ይሻልሻል የብረት?” አለኝ፣ ቀለብላባው የሽያጭ ሠራተኛ፡፡ በራሴ ዐይቼ ልወስን ብለውም ከገባሁ ጀምሮ እየተከታተለ ይነዘንዘኛል፡፡
“ያለውን አይቼ ልወሰን…በራሴ ዐያለሁ…” አልኩት በመታከት፡፡
“አዳዲስ ሞዴሎች አስገብተናል፡፡ እዚያ ጋ የምታያቸው ከዕንጨት የተሠሩት በቅርብ ከብራዚል የመጡ ናቸው፡፡ ንጹህ እናቸው:: ዋጋቸው ትንሽ ቢወደድም የዘለዓለም እቃዎች ናቸው፡፡ የብረቶቹ…እነዚያ እዛ ጋ ያሉት የቻይና ናቸው፡፡ ዋጋቸው ዝቅ ያለ ነው፤ ግን ጥራታቸውም ምንም አይልም…እኔ የምመክርሽ ግን…”
“በናትህ በራሴ ልይ!” ሳላስበው ጮህኩበት፡፡
በርግጐ ሄደ፡፡
ኡፍፍፍ!
ረጋ ብዬ ከብራዚል መጡ ወዳላቸው የዕንጨት መደርደሪያዎች ሄድኩ፡፡ ቀልቤን ወደሳበው ሄጄ መነካካት ስጀምር፣ ከኋላዬ በጣም የማውቀው የወንድ ድምጽ ስሜን ሲጠራ ሰማሁ፡፡ ደቤ?
ዞርኩ፡፡
ደቤ ነው፡፡
“እንዴት ነሽ?” አለኝ በቆመበት ከላይ እስከ ታች እያየኝ፡፡ እንዴት ነሽ አባባሉ ቅርበታችንን የማይመጥን የሩቅ ሰው ድምፀት ነበረው፡፡
ምናባቱ ቆርጦት ነው መጥቶ አቅፎ የማይስመኝ?
“ደህና ጋሽ ደቤ…” በሹፈት መልክ እየሣቅኩ ተጠጋሁት፡፡
ስጠጋው እንደ መጠጋት… ወደ ኋላ ሸሸት አለና፤ ሊገባኝ ባልቻለ ምክንያት ለተሰበሰበ ሕዝብ የሚያወራ ያህል ጮኸ ብሎ፤
“ምን ልትገዢ መጣሽ እዚህ…? እኛ ለልጆቹ አልጋ መቀየር ፈልገን ልናይ ብለን ነው…ነይ ገኒንና ልጆቼን ላስተዋውቅሽ..” አለ፡፡
አመዴ ጨሰ፡፡
ደቤና በግምት አርባ አመት የሚሆናት ደርባባ፤ ቀጭንና ጸጉረ ረጅም ሴት፣ ከትንሽ ልጅ ጋር ወደኔ እየመጡ ነው፡፡ ከልጁ ከፍ የምትለው ሴት ልጅ፣ አንዱ የሚሸጥ ሶፋ ላይ ቁጭ ብላ ከእጆቿ በእጥፍ የሚበልጥ ስልክ እየጐረጐረች ነው፡፡
እኔስ? እኔ ደግሞ ድንገተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶ መቀመቅ እንዲያወርደኝ እየተመኘሁ ነው፡፡
“ፍሬሕይወት! እንዴት ነሽ…? ገነት እባላለሁ” አለችኝ ሴትዮዋ፤ እጆችዋን በትህትና ለሰላምታ እየሰጠችኝ፡፡ ከድንጋጤዬ ሳላገግም፤
“ሃ…ገነት! ፍሬሕይወት እባላለሁ” አልኩና ጨበጥኳት፡፡
“ዐውቃለሁ…ደብሽ ብዙ ጊዜ ስላንቺ ያወራል እኮ…” አለች፡፡
ፈገግታዋ የደግ ሰው ነው፡፡
ሁለት የወለደች የማትመስል፤ ቅርጿ የተስተካከለና ተረከዝ አልባ ጫማ ብታደርግም፤ ከገመትኩት በላይ ረጅም ሴት ናት፡፡ ጠይም ፊቷ ላይ ትንሽ ድካም ቢታይም፤ መረጋጋትና ደግነት የሰፈነበት ቆንጆ ሴት ናት፡፡ ረጅም ግን ሣሣ ያለው ጸጉሯ በየመሀሉ ጥቂት ሽበቶች አሉት፡፡ ቢሆንም ግርማ እንጂ ዕድሜ አልጨመረባትም፡፡
“ይሄ ደግሞ ማርኮን ይባላል…ማርኮን ፍሬሕይወትን ሰላም በላት…” አለች፣ ፈገግታዋ ሳይጠፋ፡፡
ማርኮን ሚጢጢ እጆቹን ለሰላምታ ዘረጋልኝ፡፡ ልቤ ከልክ በላይ እየመታ ጐንበስ ብዬ እንደ ትልቅ ሰው ጨበጥኩት፡፡
“ያቺ ደግሞ አርሴማ ትባላለች…” አለ ደቤ፣ ስልክ ወደ’ምትጐረጉረው ትንሽ ልጅ እያመለከተ፡፡ ድምፁ ይንቀጠቀጣል፡፡
አርሴማ ለዐመል ቀና አለችና፣ ቀኝ እጇን በቻው ቻው አውለበለበችልኝ፡፡ ቁርጥ እናቷን ናት፡፡
“አርሴማ…ሰው እንደዚህ ነው ሰላም የሚባለው? ነይና ሳሚያት!” አለች ገነት ባልገመትኩት የቁጣ ድምጽ፡፡
አርሴማ ፍንጥር ብላ ተነስታ መጣችና ቀኝ እጇን ዘረጋችልኝ፡፡
“ሳሚያት…” አለች ገነት፡፡ አርሴማ ልትስመኝ ስትንጠራራ ጐንበስ ብዬ ሁለት ጊዜ አገላብጬ ሳምኳት፡፡
“ጐበዝ የኔ ልጅ!” አለች ገነት፡፡
እሺ..ቀጥሎ ምን ሊሆን ነው በሚል እጆቼን ወደ ኋላ አጣምሬ በግራ መጋባት ቆምኩ፡፡ ገነትን ላለማየት ሰፊውን ቤት፣ ልጆችዋንና አልፎ አልፎ ደቤን ዐያለሁ፡፡ የገነትን ዐይኖች ሽሽት አንዴ አረንጓዴውን ሶፋ፣ አንዴ ወድጄው የነበረውን መደርደሪያ፣ አንዴ ቀይ በነጩን ምንጣፍ፣ አንዴ ቅድም እየተቅለበለበ ሲረብሸኝ የነበረውን ልጅ ዐያለሁ፡፡
ምናለ አሁን መጥቶ ከዚህ ሁኔታ ቢገላግለኝ? ምን ሰበብ ፈጥሬ እግሬ አውጪኝ ልበል?
(ከሕይወት እምሻው “ማታ ማታ እና ሌሎች ትረካዎች” የተቀነጨበ)


Read 3084 times