Saturday, 02 May 2020 13:51

ቤት የመዋል በረከቶች--!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ! እኔ የምለው… ሰዋችን ምን ነካው፤በቃ ከተወሰነ ሰዓት በኋላ መጠጥ የለም ተባለ፡፡ በር አዘግቶ ‘ግልበጣ’፣ በር አዘግቶ ሺሻ ማጨስ፣ በር አዘግቶ ጫት መቃም! ምን አለ ለትንሽ ጊዜ ብቻ ብንታገስ! በፊት እኮ አቶ ባል ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ይገባል…በሁለት እግሮቹ እየተራመደ ሳይሆን እየተሳበ፡፡ እሷዬዋ ደግሞ እንቅልፍ ወዲህ ወዲያ እያላጋት ሶፋ ላይ ቁጭ ብላ ትጠብቃለች፡፡ (በነገራችን ላይ ከዓመታት በፊት ባል ሆዬ ከተወሰነ ሰዓት በኋላ ካመሸ የግቢ በር ጥርቅም አድርጋ ትቀረቅራለች ስለምትባል ሴት ሰምተን ነበር፡፡ ደግሞም በምንም አይነት አትከፍትም፡፡ ባልም ወይ ጓደኛ ቤት፣ ወይ ጎረቤት ሄዶ ያድራል ይባል ነበር፡፡ የምር ግን እንዲህ አይነት ግራ ጎኖች የሚያስፈልጋቸው ያሉ አይመስላችሁም!)
“ምነው በጊዜ መጣህ?”
አሪፍ አጠያየቅ አይደል! “እንዴት በዚህ ሰዓት ትመጣለህ!” ብሎ ዘነዘና ነገር ፍለጋ የለ፣ “እዚህ ተጎልቶ የሚጠብቅህ የቀጠርከው ሠራተኛ ያለ መሰለህ!” ምናምን ብሎ ከሀያ ዘጠኝ ወደ ዘጠና ዘጠኝ ዲግሪ ሴንቲግሬድ መተኮስ የለ… “ይንጋና ቤቱን ጥዬልህ እሄዳለሁ፣ ይስፋህ፣” ብሎ እጅ መስጠት የለ፡፡ “ምነው በጊዜ መጣህ?” አለቀ፡፡
“ምን አልሽ?”
እኔ የምለው የድራፍት በርሜሉን አንድ ሦስተኛ ወደ ሆዱ አጋብቶ እኩለ ሌሊት ላይ ሲመጣ የሚያፈጥ ባል የምር ግን ‘አባወራ’ ተብሎ ነው የሚጠራው! የዘመኑ ወጣቶች ስም አውጡለት ቢባሉ “ይሄ ምን አባወራ ነው፣ አባውራ ነው እንጂ!" ይሉ ነበር! ሚስቱ አጋድማ ስትነርተው “ገደለችኝ!” ብሎ መጮህ ፈርቶ “ኸረ ተጋደልን!” ብሎ ጮኸ እንደተባለው አይነት አባውራ ማለት ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
“አይ በጊዜ መጣህ፣ ለምን ትንሽ አታመሽም ብዬ ነው!”
“አቦ አትነጅሽኝ! ይልቅ እራት አልበላሁም፣ የሆነ አፌ የማደርገው ነገር ስጪኝ፡፡”
ምን! የምን አልበላሁም ብሎ ነገር ነው! በጠጣሩ ገባ፣ በፈሳሽ መልክ ገባ ያው ወደ ሆድ አይደል እንዴ የሚገባው! በፈሻስ መልክ የአምስት ሰው ‘እራት’ ገልብጦ “አልበላሁም፣” ብሎ ነገር ምን የሚሉት ስግብግብነት ነው!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው… ‘አፌ የማደርገው ነገር’ የሚለው አባባል ብዙዎቻችን የምንለው ነው፡፡
“አንተ ቆሜ እየጠበቅሁህ አይደል እንዴ!”
“መጣሁ፣ ትንሽ ቁርስ አፌ ላድርግ ብዬ ነው፡፡”
ወይ ደግሞ “ባዶ ሆድሽን ልትወጪ ነው እንዴ! ትንሽ ነገር አፍሽ አድርጊ እንጂ!” እናባባላለን፡፡
እናላችሁ…አለ አይደል…የሚበላውን ነገር አፍ ከማድረግ ሌላ አማራጭ፣ ‘ፕላን ቢ’ ነገር አለ እንዴ!
“ምሳ ልብላና ቡና አብረን እንጠጣለን፡፡”
“ምሳ አፍህ ነው የምታደርገው ወይስ ፕላን ቢ ነው!”
አይነት ነገር ይባላል እንዴ! ‘አዋቂ በበዛበት’ አላዋቂ ሆነን እንዳንቀር ብለን ነው!
እናላችሁ…ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ቤቱ ገብቶ…አለ አይደል… የፈረደባት ባለቤቱን… “አቦ አትነጅሽኝ!” የሚል አባወራ ቀዝቀዝ የሚልበት ጊዜ አሁን ነበር፡፡ እኩለ ሌሊት ድረስ ጋቢ ተከናንባ መጠበቅ የሰለቻት የቤት እመቤትም ‘እንደ ሰዉ’ በጊዜ መተኛት ትችላለች፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ምናልባት እኮ እሷና እሱ ቁጭ ብለው የማውራት የበለጠ ጊዜ ሲያገኙ “ሰማንያው ዜሮ ይሁንልኝ አይነት ነገራቸውን ይተዉ ይሆናል! ስሙኝማ…ይህ ሰማንያ የመቅደድን ነገር ካነሳን… ምን አለ መለያየታቸው ካልቀረ “በቃ የዚህ ታሪክ መጨረሻ ይኸው ነው፣” ብለው ‘መጽሀፉን የማይዘጉት!’
እናላችሁ… “የእኔ ድርሻ፣” “የአንቺ ድርሻ፣” በኋላ እኮ አርፎ የማይቀመጥ መአት አለ፡፡ አለ አይደል…ታሪኩ ወደ ‘ቻፕተር’ ምናምን ይሸጋገራል፡፡ አንደኛው ወገን የሌላኛውን በጎ ነገር ማየት አይፈልግም፡፡ እሱዬው…
“ከእሱ ከተለያየች በኋላ ይኸው ቀለብ እርቋት፣ ወዟ ሁሉ ተሟጦ እህል ወፍጮ ስር ውላ የምታድር መስላለች፣” እንዲባልለት ይፈልጋል፡፡ እሷዬዋ…
“ሳይቸግረው ከእሷ ተለያይቶ ጠዋት ማታ በብስጭት አረቄውን እያንቃረረ ይኸው ወላልቃ ሱማሌ ተራ የተጣለች የድሮ ቮልስ መስሏል፣” እንዲባልላት ትፈልጋለች፡፡ ታዲያላችሁ “መልካሙ ሁሉ እንዲገጥምህ እመኝልሀለሁ፣”  “የደስታና የጤና ኑሮ እንዲገጥመሽ ከልቤ እመኛለሁ፣” መባባል እኮ ማንንም ኪሎ አይቀንስም፡፡ ከተለያዩ፣ በቃ ተለያዩ ነው… ‘ታሪካዊ ጠላትነት’ አይነት ነገር ምን አመጣው!
“ስታበሳጨኝ ኖራ እሷ ከሌላ ሰው ጋር በሰላም ልትኖር! ሞቻታለኋ! ጨርቋን አስጥዬ ነው የማስኬዳት!”
“ስንት ዘመን ሙሉ እንዳስለቀሰኝ፣ የተወለደበትን ቀን ባላስረግመው ከምላሴ ጸጉር! ዘመዶቼ እነማን እንደሆኑ አያውቅም!” ኸረ እባካችሁ ተረጋጉ! ለዛ የቀበሌ አዳራሽ ለሚያክለው የሰርጉ ሊሞ ብላችሁ ማርሹን ቀነስ አደርጉት፡፡
ታዲያላችሁ… እሷንም፣ እሱንም ሥራ ‘ቢዚ እያደረጋቸው’ ብዙ ሰዓት አብረው ለማሳለፍ ይቸግራቸው የነበሩ አባወራና እማወራ፣ አሁን ቁጭ ብለው የሆድ የሆዳቸውን ለማውራት አሪፍ ጊዜ አግኝተዋል፡፡ አንጠልጥለው የተዋቸውን ነገሮች ሁሉ ሰከን ብለው የሚመክሩበት ጊዜ አሁን ነው… ላወቀበት ነው ታዲያ፡፡
“ሆዴ እሱን ነገር መላ ሳናበጅለት እንደሁ ተንጠልጥሎ ቆየ እኮ፡፡ ምን ይመስልሻል፣ እንዴት ብናደርገው ይሻላል?”
“አንተ እንዳልክ፣ እኔ አንተ በምትለው እስማማለሁ፡፡”
አሪፍ አይደል! አለበለዛ ሀያ አራት ነጻ ሰዓት ተገኘ ተብሎ በየምናምን ሰዓቱ፣ ሀያ አምስት ሴንቲ ሜትር ውፍረት ባለው እንትን ላይ ዘሎ ጉብ…የፖፑሌሽን ኤክስፕሎዥን ጥያቄ ያስነሳል፡፡ እንኳን ይሄ ተጨምሮ እንዲሁም በዝታችኋል እያሉን ነው! ቂ…ቂ…ቂ…
የምር ግን፣ ምን አለ መሰላችሁ…አሜሪካኖች ቤት መቆየትን በተመለከተ ካነሱት ነገር አንዱ ይሄ ‘ዶሜስቲክ ቫዮለንስ’ የሚሉት ማለትም የቤት ውስጥ ጥቃት የመጨመር ነገር ነው፡፡ በተለይም አባወራዎቹ ብዙ ሰዓት እቤት በመቀመጥና ምናልባትም ከሥራ የመቀነስና የመንሳፈፍ አይነት ችግር ብስጭታቸውንና እልሀቸውን፣ የትዳር ጓደኞቻቸው ላይ እንዲወጡ ሳያደርጋቸው አልቀረም የሚል ነው፡፡  
ሁለተኛው ግን…አለ አይደል… መአት ልጆች የሚጸነሱበትና ከበርካታ ወራት በኋላ ሌላ ዙር ‘ቤቢ ቡም’ የሚሉት አዳዲስ በተወለዱ ልጆች የመጥለቀልቂያ ዘመን ጅማሮ ነው ይላሉ፡፡ (እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ይሄ ‘ኔቸር’ የሚሉት ጉዳይ፣ ነገረ ሥራው እንዴት ነው! አሀ…ልክ ነዋ…በደስታ ጊዜ ‘ዘሎ እዛው!’ በብስጭት ጊዜ ‘ዘሎ እዛው!’ ሳይንሱ ይከለስልንማ!)
ስሙኝማ፣ የምር እኮ በፊት ‘ሼር መደራረግ’ … አለ አይደል… ‘ፌክም’ ይሁን እውነተኛ የፌስቡክ አካውንት አያስፈልገውም ነበር፡፡
“ማነሽ እከሊት፣ እስቲ አንድ ጣሳ ሹሮ ላኪልኝ…”
በቃ ሌላ ጣጣ፣ ‘ፕሮጀክት ፕሮፖዛል፣’ ልብ የሚያራራ ‘በእጅ የሚሰጥ’ ደብዳቤ፣ ጥሩ አንደበት ያለው አማላጅ ምናምን ብሎ ነገር አልነበረም…አሁን እንዲህ አይነት ዘመን ሊመጣ! የምር አኮ ዘንድሮ የሹሮ እቃው የተራገፈ ከመሆኑ ሌላ ትልቁ ችግር ‘የትርጉም’ ጉዳይ ነው፡፡ “ሌላ ትርጉም እስካልተሰጠው ድረስ ‘ሹሮ ላኪልኝ’ ማለት ‘ሹሮ ላኪልኛ ማለት ነው፣’ የሚል ‘አሜንድመንት’ ምናምን አናስገባ ነገር! የዘንድሮ አተረጓጎም…ምን አለፋችሁ…በቃ ሌላ ገመድ መቋጠር በሉት፡፡
“ማነሽ እከሊት፣ እስቲ አንድ ጣሳ ሹሮ ላኪልኝ…”
“አጅሪት በእሷ ቤት ሥጋ ሲያምርሽ ይቅር ማለቷ ነው!”
“አሁን ሥጋ የሚል ነገር ያነሳ አለ! በተዘዋዋሪ እኮ ሥጋ አማረኝ ብላ ልብ መብላቷ ነው፡፡” ቂ…ቂ…ቂ…
ቤት መዋልን ለደግ እናድርገውማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1821 times