Saturday, 02 May 2020 11:52

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የተላለፉ እየተቀጡ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በተለያየ መንገድ የተላለፉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እያዋሉ ለህግ እየቀረቡ መሆኑንና አዋጁን የማስፈፀም እርምጃዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ በ10ሩም ክፍለ ከተማዎች በሚገኙ የአቃቤ ህግ ጽ/ቤቶች በኩል አዋጁን በሚተላለፉ ግለሰቦች ላይ ክትትልና እርምጃ እየተወሰደ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ከሰሞኑም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 78 ሰዎች አዋጁን በተለያየ መንገድ በመተላለፍ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክፍለ ከተማው አቃቤ ህግ ጽ/ቤት የገለፀ ሲሆን ዘጠኝ ያህሉ ደግሞ በአንድ ቤት ውስጥ በመሰብሰብ ጫት ሲቅሙ ተይዘው ፍ/ቤት መቅረባቸውንና እያንዳንዳቸው በ3ሺህ ብር መቀጣታቸውን አስታውቋል፡፡
በቁጥጥር ስር የዋሉት ቀሪዎቹ ግለሰቦች ጉዳይም ተጣርቶ ጉዳያቸው ወደ ፍ/ቤት እየቀረበ መሆኑ ከአቃቤ ህግ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በተመሳሳይ፤ በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ልዩ ቦታው “ቁልፍ ተራ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንድ ቤት ውስጥ ቁጥራቸው 6 የሆኑ ሰዎችን ሰብስቦ ጫት ሲያስቅምና ሹሻ ሲያስጨስ የተገኘ ግለሰብ ክስ ተመስርቶበት፣ በ5ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ መቀጣቱን የአቃቤ ህግ  መረጃ ያመለክታል::
በዚህ አዋጅ መሠረት ለአሽከርካሪዎች የወጣውን መመሪያ የተላለፉ አሽከርካሪዎች እየተቀጡ መሆኑም ታውቋል፡፡
ከጠቅላይ አቃቤ ህግ በተገኘው መረጃ መሠረት፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከተፈቀደው ሰው በላይ ትርፍ በመጫንና ከታሪፈ በላይ በማስከፈል ወንጀል ከ270 በላይ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተጠቁሟል፡፡
የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ደንብ በማይተገብሩ ግለሰቦችና አካላት ላይ በቀጣይም ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ ጠ/አቃቤ ህግ አስገንዝቧል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍ የባልደራስ ሊቀ መንበር ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ታስረው መፈታታቸውም ይታወሳል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በመተላለፍ በእምነት ስም እስከ 1 መቶ የሚደርሱ ሰዎችን ሰብስባ የተገኘችው ራሷን ንግስተ ነገስት ዘኢትዮጵያ ብላ የምትጠራው ግለሰብም በቁጥጥር ስር ውላለች፡፡
አዲስ አድማስ በግለሰብ እስር ጉዳይ ለማጣራት ባደረገው ጥረት ግለሰቧ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጣስ ከመከሰስ ባለፈ ሌሎች እየቀረቡባቸው ያሉ ቅሬታዎችን መሠረት በማድረግ ፖሊስ ምርመራ እያከናወነ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
መንግስት ይህን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስመልክቶ የሚወሰዱ የህግ እርምጃዎች የሰብአዊ መብትን በማይጥሱ መልኩ እንዲሆን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አሳስቧል፡፡  

Read 11003 times