Monday, 27 April 2020 00:00

በሃሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)

    ‹‹የሰው ቋንቋ ‹ሰው› መሆን ብቻ ነው››
                               
             አንድ ደግ እናት  ድንገት አመማቸው፡፡ አንድ ልጃቸው ደግሞ ካለፉት ሃያ ዓመታት ጀምሮ የሚኖረው በውጭ አገር ነው፡፡ አገር ቤት በነበረበት ወቅት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያስተምር ነበር፡፡ እንዳጋጣሚ የትምህርት ዕድል አገኘና ወደ ውጭ አገር ሄደ፡፡ ትምህርቱንም በከፍተኛ ውጤት አጠናቀቀ:: የተማረውን ትምህርት የሚያዳብር ስራ በማግኘቱና አገር ቤት ውስጥ የነበረውን የፖለቲካ ሁኔታ ባለመውደዱ ኑሮውን እዛው አደረገ፡፡ አሁን ምርጥ የጠፈር ጥናት ሳይንቲስት ለመሆንም በቃ፡፡
ሰውዬአችን ሙሉ ጊዜውን የሚያሳልፈው በስራውና በምርምር ላይ ተጠምዶ ነው:: የሚወዳቸው እናቱን አልፎ፣ አልፎ በስልክ ከማናገርና ገንዘብ ከመላክ በስተቀር ብቅ ብሎ ሊያያቸው ጊዜ አላገኘም፡፡ አጋጣሚ በሚያገኝበት ጊዜ ግን ከባልደረቦቹና ጓደኞቹ ጋር የናቱን ነገር ማንሳቱና አገር ቤት ደርሶ መመለስ እንደሚፈልግ መጨዋወቱ አልቀረም:: ጓደኞቹ ስራው የሚጠይቀውን ሃላፊነት፣ እንዲሁም ለደህንነቱ በማሰብና እንዳይለያቸው በመፈለግ ‹‹አንድ ቀን አብረን እንሄዳለን›› እያሉ ቁም ነገሩን ወደ ቀልድ ይቀይሩበታል፡፡ ሰሞኑን ግን እናቱ መታመማቸውን ከአነጋገራቸውና ከድምፃቸው በመረዳቱ ሀሳብ ገብቶታል:: ኃላፊውና ጓደኛው ወደ ሆነው ሰው ቢሮ ሂዶ፡-
‹‹እናቴ ታማለች፤ አገር ቤት መሄድ አለብኝ፡፡ ሳላያት አንድ ነገር ብትሆንብኝ ቀሪው ዕድሜዬን ሲፀፅተኝ ነው የምኖረው›› አለው፡፡
‹‹ትንሽ ጊዜ ታገስ፡፡ አንደኛ አሁን እጃችን ላይ ያለው ሥራ አጣዳፊ ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ኮሮና በፈላበት በዚህ ጊዜ ወደዛ መሄድ ‹ሴፍ› አይደለም፡፡ አንለቅህም፡፡ ባይሆን ጥሩ ሃኪም እንዲያያቸው እናደርጋለን››
‹‹የፈለገ ይሁን መሄድ አለብኝ፡፡ አገሬም ናፍቃኛለች››
‹‹ይቺም አገርህ ናት››
‹‹አለም ሁሉ አገሬስ እንደሆነ መች አጣሁት››
‹‹ካ!ካ!ካ! ማ ነበር እንደሱ ያለው? ካርላ ይል?››
‹‹መልካምነት ሃይማኖቴ ነው፣ የሰው ልጆች ሁሉ ወንድሞቼና እህቶቼ ናቸው። በሰላም፣ በፍቅርና በነፃነት የምኖርበት ቦታ ሁሉ አገሬ ነው:: ያለው የመጀመሪያው ፀሐፊ እሱ ይመስለኛል፡፡ … እናቴን የማውቃት ግን ከመወለዴ በፊት ነው፡፡››
ጓደኛውም ከግማሽ ሰዓት በኋላ ተመልሰው እንዲገናኙ ነግሮት ተሰነባበቱ፡። እንደተገናኙም::
‹‹ስንት ቀን ይበቃሃል?›› በማለት ጠየቀው::
‹‹ኳሯንቲን የምደረግበትን ሳይጨምር ሁለት ወይም ሶስት ሳምንት…››
‹‹ለዛ የሚሆን ጊዜ የለንም፡፡ ቴስቶችህንና ሌሎች አስፈላጊ ክትባቶች ካሉ እዚሁ እንጨርሳለን፡፡ ከሁለት ቀን በኋላ ትበራለህ፣ ሶስት ቀን ቆይተህ ትመለሳለህ፡፡ አሁን ፂምህን፣ ፀጉርህን… ምናምን ተስተካከል፡፡… Be in order››
‹‹ለሦስት ቀን ብቻ ቆይተህ ትመለሳለህ ነው ምትለኝ?... እንዴት ይሆናል? ኳራንቲኑስ?››
‹‹እሱን ለኛ ተወው››
‹‹ካ!ካ!ካ!
*    *   *
ወዳጄ፡- ከሚታይ ነገር ውስጥ የማይታየውን ለማየት፣ ከማይታየው የሚታይ ነገር መኖሩን ለማወቅ ጥልቅ አስተዋይነትን ይፈልጋል፡፡ በዚህ ዘመን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ጥበብ፣ በአንድ ሰው አእምሮ ውስጥ የሚንተከተከውን አጓጉል ሀሳብ በመሰረዝ ወይም ዲሊት በማድረግ በምትኩ ዓለማቀፋዊ ሰብዕና ያለው አስተሳሰብ መገንባት እየተቻለ ነው:: በ‹ቴስት ቲዩብ› ወይም በ‹ኪራይ› ማህፀን ፅንስ እንደ ማሳደግ አይነት፡፡ በሌላ አነጋገር፤ የአንድን ሰው አስተሳሰብ በማሻሻል የሰብዕና ተሃድሶ (Personality refrorm) ማድረግ መቻል ማለት ነው፡፡ ሰው ማለት ሀሳብ ነውና፡፡ ‹እገሌ ኮ ጥሩ ሰው ነበር፤ መጥፎ ሆነ› የምንለው የሰውየው አስተሳሰብ ሲቀየር ወይም ድብቅ ፍላጎቱ ሲጋለጥ ነው፡፡ መጥፎውም ‹ጥሩ ሆነ› የሚባለው በዚሁ መንገድ ነው፡፡ ይሄ ድምዳሜ ግን ‹ጠቅላይ› በመሆኑ ‹ሰልፍ ሴንተርድ› የሆኑ አመለካከቶችን አያዳብልም፡፡
ወዳጄ፡- ለብዙዎቻችን ትክክለኛና ምክንያታዊ አይመስለንም እንጂ ‹አለማሰብ› የምንለው ነገር ውስጥ እንኳ በግብር እስከታየ ድረስ ራሱን የቻለ ሃሳብ አለ፡፡
‹‹ዘገምተኞች፣ ቀውሶች›› የምንላቸውን ወገኖቻችን ልብ ይሏል፡፡ መረዳት መቻላችንን አለማወቅ የኛ ችግር ሆኖ ሳለ ‹እንዴት እንደኔ አያስብም› ብለን እንቆጣለን፡፡ እዚች ጋ ድሮ የሰማሁዋት አንድ የእንግሊዝኛ ቀልድ ትዝ አለችኝ፡፡
አጅሬው ውስጥ ለውስጥ በሚያስኬድ ጠባብ መንገድ ላይ መኪናውን ለማዞር ይታገላል:: በዛ በኩል ሲያልፍ የነበረ የመንደር ወፈፌ ድንገት ከመኪናው ጀርባ ተደነቀረበት፡፡ ዞር በል ቢለውም አልተነቃነቀም፡፡ ተናደደ፡፡ ከመኪናው ወርዶ ሊገፈትረው ሲንደረደር የኋላው ጎማ የቆመው ትልቅ ጉድጓድ ጫፍ ላይ ነው፡፡ ትንሽ ወደ ኋላ ፈቀቅ ቢል ኖሮ… አዲዬስ!... ድንጋጤው ሲያልፍ ወፈፌውን፡-
‹‹I thought you were crazy›› አለው:: ምን ብሎ እንደመለሰለት ታውቃለህ?.. መጨረሻ ላይ አስታውሰኝ፡፡
*    *   *
ወዳጄ፡- አንዳንዴ   ጊዜያቸውን ጠብቀው ያልተወለዱ ወይም እንደ ‹ዛራስ ቱራ› ከጊዜያቸው የቀደሙ አስተሳሰቦች ያጋጥማሉ፤ በዘመናቸው ፍሬ ሳያፈሩ ወይም ሳይሳካላቸው የቀሩ፡፡ ለምሳሌ በአስራ ዘጠነኛው ክ/ዘመን ሲነገሩ ከነበሩ ብዙ ቋንቋዎች ተቀይጦ የዓለም ቋንቋ እንዲሆን የታሰበው ‹ኤስፔራንቶ› እንደ ታቀደው አልሆነም፡፡ ዛሬ ላይ ግን የራሳችንን ቋንቋዎች ጨምሮ ብዙ የዓለም ቋንቋዎች ‹ጉራማይሌ› እየሆኑ ነው፡፡ የጊዜ ጉዳይ እንጅ አዲስ የዓለም ቋንቋ እየተፈጠረ ነው፡፡
ወዳጄ፡- ከማይታየው ውስጥ የሚታየውን ፈልግ ያልኩህን አስታውስ!!...
ለነገሩ የሰው ቋንቋ ‹ሰው› መሆን ብቻ ነው፡፡ በተለይ በችግር ጊዜ!
እንስሳትና አራዊት፣ አማልክትና ዩፎዎች፣ ከዋክብትና እፅዋት የሚግባቡበት እውነተኛው የነፍስ ቋንቋማ ‹ኢነርጂ› ነው፤ በሙዚቃ፣ ፍቅርና ሥነ ጥበብ የሚተርጉም! አይመስልህም?
*    *   *
ወደ መጀመሪያው ጨዋታችን ስንመለስ:: ሳይንቲስቱ በተባለው ጊዜ ወደ አገሩ መጣ:: ከአውፕላን እንደ ወረደ በራሱ ወጭ ወደ ሚቆይበት (quarantin) ሆቴል አቀና:: በዚያችው ቅጽበት የእናቱ በር ተንኳኳና እናትና ልጅ ከዓመታት በኋላ ተገናኙ:: ናፍቆታቸውን ከተወጡ በኋላም ምርቃታቸውን ተቀብሎ፣ በሦስተኛው ቀን ወደ ሥራ ተመለሰ፡፡ የሆነው እንደዚህ ነው፡- ኤርፖርት ሲደርስ ተመሳሳይ ልብስ የለበሰ ተመሳሳይ ሰው፣ ተመሳሳይ ዶክመንት፣ ተመሳሳይ መኪናና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ ተሟልተው ይጠብቁት ነበር:: በዕቅዱ መሰረት ስትራቴጂክ በተባለው ቦታ ላይ ዝውውር ተደረገ፡፡ ሁሉም ነገር እንደታቀደው ተከናወነ፡፡ እሱን ተክቶ ወደ ሆቴል የሄደው ሌላ ‹እሱ› ነበር፡፡
‹‹እህሳ?›› አለው አለቃው፤ እንኳን ደህና መጣህ ለማለት፡፡
‹‹ምትሃት’ኮ ነው፡፡ ክሎኒንግ ይመስላል››
‹‹ለእኛ ምንም አይደለም፡፡ ካ!ካ!ካ!››
‹‹እነማን ናችሁ እናንተ?››
‹‹አንተን ጨምሮ ኢንዲ ጂኒየሶች››
‹‹What?››
‹‹‹ኢንዲ›… sit is mute!››
ካ! ካ! ካ!!
*    *   *
ወዳጄ፡- ቅድም አስታውሰኝ ያልኩህ ምን መሰለህ? አጅሬው ወፈፌውን
‹‹ቀውስ ነገር ትመስለኝ ነበር›› እንዳለው ተጨዋውተናል፡፡ ወፈፌውም፤
‹‹ልሆን እችላለሁ፤ ግን እንደ እናንተ ደደብ አይደለሁም››  (Yes, I can be crazy, but not stupid like you) በማለት ነበር የመለሰለት አሉ::
ወዳጆቼ፤ አትዘናጉ ራሳችሁን ከኮሮና ጠብቁ!!
ሰላም!!


Read 1556 times