Sunday, 26 April 2020 00:00

የኢትዮጵያ የሀኪሞች ብቃት ልዩ ነው፡፡

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

    ነፍስ አድንም፣ መማሪያ አርአያም ነው - የሃኪሞች ስኬት፡፡
                 
           ኢትዮጵያ የስልጣኔ ቅርሶችን ብቻ ሳይሆን የዘመናዊ ስልጣኔ አርአያ ፋናዎችንም የያዘች አገር ናት፡፡ ስኬታማ የህክምና ትምህርትና የሀኪሞች የላቀ ብቃት አንዱ የስልጣኔ አርአያ ነው፡፡  
የኢትዮጵያ የህክምና ዘርፍ፣ “ጥሩ መነሻ መሰረት ከተገኘ፣ በዩኒቨርስቲ ትምህርት አማካኝነት፣ እጅግ የላቀ የሙያ ብቃትን መገንባት እንደሚቻል” በተጨባጭ የሚያሳይ ድንቅ ታሪክ አለው፡፡ ‹‹A›› የደረደሩ፣ ‹‹4›› የደፈኑ ተማሪዎች ናቸው - ወደ ህክምና ዩኒቨርስቲ የመግባትና የመማር እድል የነበራቸው፡፡ ይሄ ጥሩ መሰረት (base) ነው፡፡ ለምን በሉ፡፡
ከላይ እስከ ታች፤ ‹‹A›› የሚደረድር ጐበዝ ተማሪ፤ ሁለት ውድ ንብረቶች ይኖሩታል፡፡
አንደኛ ነገር፣ ከሌሎች ተማሪዎች የላቀ፣ የተጣራ፣ በቅጡ የተዋቀረ፣ ጠንካራ የእውቀት መሰረት ያዳብራል -ጐበዝ ተማሪ::
ሁለተኛ ነገር፣ ጥሩ መሳሪያ ይታጠቃል:: ከመሰረታዊ እውቀት ጋር፣ ውጤታማ የማወቅ አቅምን ያጐለብታል - ጐበዝ ተማሪ፡፡ እጅግ የሰላ የአስተዋይነት አቅምን፣ ወይም ደግሞ፣ እጅግ ተግቶ የማጥናት የታታሪነት (የዲሲፒሊን) ፅናትን ይገነባል፡፡
የእውቀት ይዘትና የማወቅ አቅም እርስበርስ እየተመጋገቡ ነው የሚጐብቱት፤ የሚራቀቁት:: በአእምሮ እና በሙያ መበልፀግ እንዲህ ነው:: የእውቀት ግንባታና የማወቅ አቅም ግንባታ  ለየብቻቸው ከተነጣጠሉ ግን፣ እርስ በርስ ተያይዘው ይመክናሉ፡፡ እስከዛሬ ብዙ መክኗል:: የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተብሎ የተዘጋጀው እቅድ ደግሞ፣ የእስከዛሬውን ጥፋት ያባብሳል:: ለምን?
ፍኖተ ካርታው፣ የእውቀት ይዘትን በማናናቅ ላይ የሚያጠነጥን እቅድ ነው:: ከማሻሻል ይልቅ፣ የህፃናትን የአእምሮ ብልጽግና በእንጭጩ የሚያመክን፣ ከቀድሞው የባሰ አጥፊ እቅድ መምጣቱ ያሳዝናል፡፡ ሳይሮጡ የሩጫ ክህሎት አይዳብርም፡፡ ያለ እውቀት፣ የማወቅ አቅም አይታነፅም፡፡ አንዱ ከሌላው ከተገነጠለ፣ ሁለቱም እየጠወለጉ ይከስማሉ፡፡ ስራ እና መሳሪያ፣ እውቀትና ሃሳብ ሲቀናጁ ነው ሁለቱም ህይወት የሚኖራቸው፡፡ ተደጋግፈው የሚለመልሙት፡፡    
እንዲህ እርስበርስ የሚዳመሩ መሰረታዊ የእውቀት ይዘቶችና የማወቅ አቅሞች በቅጡ ተቀናብረው ሲዋቀሩ፣ አስተማማኝ መሠረትና ብርቱ መንደርደሪያ ይሆናሉ:: ከሌሎች የሙያ መስኮች ይልቅ፣ በሃኪሞች ዘንድ ከፍ ያለ የሙያ ብቃት ጐልቶ የሚታይበት ሚስጥር ይሄው ነው:: በህክምና ትምህርት አማካኝነት እጅግ የላቀ ብቃትን ለመገንባት የተቻለው ከስር በተገነባ ጠንካራ መሠረት መነሻነት ነው፡፡
በጠንካራ መሠረት ላይ፣ የህክምና ትምህርት ጥራት፣ የመምህራኑ ብቃት፣ የተማሪዎቹ ጥረት ተደማምሮ፣ አኩሪ ውጤት ተገኝቷል፡፡ ዓለማቀፍ የሙያ ደረጃዎችን የሚያሟሉ ድንቅ ሀኪሞች ተፈጥረዋል - በኢትዮጵያ፡፡ ከስር፣ ጥሩ መሰረት ይዘው የመጡ ተማሪዎች ወደ ህክምና ትምህርት የሚገቡ መሆናቸው ነው - ዋናው ሚስጥር፡፡
በተቃራኒው፣ ገና ከስር፣ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ፣ የእውቀት ዘር እንዲጠፋ ዘመቻ ከጀመርንስ? “ሞጋች አስተሳሰብ ይቅደም!” በሚል ፈሊጥ ሳቢያ፣ እውቀትን በሚያናንቅ “የትምህርት ፍኖተ ካርታ” አማካኝነት ተማሪዎች እውቀት አልባ እንዲሆኑ ካሰናከልናቸውስ? ወይም ለጐበዝ ተማሪዎች ቅድሚያ የሚሰጠውን  ምልመላ ሸርሽረን የኮታ ምደባ ካነገስንስ? ወይም የህክምና የትምህርት ይዘትን የሚያሳሳ፣ የትምህርት አቀራረብን የሚበጣጥስ የትምህርት ዘዴ ከደረብንበትስ? ወይም “የትምህርት ፈተና አሉታዊ ነው፤ ለጐበዞች ያዳላል” በሚል የተሳከረ ፈሊጥ ሳቢያ፣ የመምህራንን ብቃትና የተማሪዎችን ጥረት የሚያንኳስስ ክፉ ቅኝት ካመጣንስ? አንዱን ወይም ሌላውን ካበላሸን፣ ይህንን ወይም ያኛውን ቀሽም ስህተት ከሰራን፣ ወይም ክፉ ጥፋት ከፈፀምን ነገሩ ሁሉ መና ይቀራል፡፡
ደግነቱ፤ ከማበላሸት ይልቅ፣ ለእውቀትና ለችሎታ፣ ለህይወትና ለጤና፣ ለብቃትና ለጥረት የምንሰጠውን ክብር ከፍ ማድረግ እንችላለን፡፡ ቢያንስ ቢያንስ፣ ክብር ከመንፈግና ከመሸርሸር ከተቆጠብን፣ የህክምና ትምህርትና ብቁ ሃኪሞች፣ ወደፊትም፣ የዘመናዊ ስልጣኔ ጭላንጭልና አርአያ ይሆኑልናል፡፡
በእርግጥ የኢትዮጵያ የህክምና ትምህርት፣ እንከን የማይነካካው፣ የፀዳና የጠራ “ምናባዊ ምድረ ስልጣኔ” ሆኗል ማለት አይደለም:: በየጊዜው የሚጨመሩ ችግሮችን ትተን፣ ነባሮቹን እንኳ ብናይ፣ እጅግ “ብዙ ይቀረዋል” ልንል እንችላለን፡፡
የመማሪያ መፃሕፍት፣ የአዳዲስ ጥናቶች መረጃና ጆርናሎች፣ የቴክኖሎጂና የህክምና መሳሪያዎች፣ የመምህራን ቁጥርና የሙያ ዘርፍ ውስንነት፣ ገና ከጅምሩም የኤሌመንተሪና የሃይስኩል ትምህርት መዳከም ጥቂቶቹ ነባር ችግሮች ናቸው፡፡
እንዲያም ሆኖ፣ በድህነትና በኋላቀርነት ውስጥም ሆኖ፣ ወደ ስልጣኔ የመራመድ እድል እንዳለ፣ በፍጥነት መገስገስም እንደሚቻል በአርአያነት ያሳየናል  - የአገራችን የህክምና ትምህርት ስኬታማ ገጽታ፡፡
የህክምናው ዘርፍ፣ ለበርካታ ዓመታት፣ ብቁ ሀኪሞችን አስመርቋል፡፡ በአገር ውስጥም፣ በውጭ አገራትም፣ ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ ድረስ፣ በላቀ ብቃት የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎችን አፍርቷል፡፡ የጠንካራ መሰረት ጥቅምን አጉልቶ አሳይቷል፡፡
ብቁ ሃኪሞች ደግሞ፣ ለዘወትር የጤና ችግር ብቻ ሳይሆን፣ ለፈታኝ የወረርሽኝ ጊዜም፣ ነፍስ አድን ናቸው፡፡ አሁን፣ ፈታኝ ጊዜ ከፊት ለፊት ተደቅኗል፡፡ ሃኪሞች፣ የብቃታቸውን ያህል እንዲበረቱ እንመኝላቸው፡፡
በእርግጥ፣ ብቁ ሃኪም መሆን ማለት፤ ሁሉንም ነገር የማወቅና የመስራት ችሎታ ማለት አይደለም፡፡
ሃኪሞች፣ በተለይ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቋቋም፣ ስራቸውን በብዛትና በጥራት፣ በትጋትና በጥንቃቄ እንዲሰሩ ከፈለግን፣ አመቺ ሜዳ መፍጠር የግድ ነው፡፡ ወረርሽኝን ለማሸነፍ፤ ለዘለቄታውም ጤንነትን ለማስፋት የሚረዱ፣ ጊዜያዊና ቋሚ የአሰራር ስርዓቶችን ማሰናዳት ያስፈልጋል፡፡ ይሄን ኃላፊነት፣ በደፈናው በሃኪሞች ላይ መጫን ግን ስህተት ነው፡፡
አዎ፤ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቋቋም የሚታለሙ አቅጣጫዎች፣ የሚዘጋጁ እቅዶች፣ የሚዋቀሩ ተቋማትና የሚከናወኑ ተግባራት ሁሉ፤ በህክምናና በጤና ባለሙያዎች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው:: ነገር ግን፣ ሃኪሞች ሁሉ ሆስፒታል እንዲገነቡ፣ አምቡላንስ እንዲፈበርኩ፣ የፋይናንስና የበጀት ቀመር እንዲሰሩ መጠበቅ፣ ስህተት ነው፡፡
ወረርሽኝን ለማሸነፍ የሚያስችሉ ጊዜያዊና ቋሚ የአሠራር ስርዓቶችን አመቻችቶ የማሰናዳት ኃላፊነት፣  የሃኪሞች ዋና ሸክም መሆን የለበትም፡፡
አዎ፤ በሀኪሞች እውቀትና ምክር ላይ የተመሰረተ መሆን ይገባዋል - የአሰራር ስርዓቱ:: በተለይ ደግሞ፤ ወረርሽኝ ላይ ባተኮረ የጤና ዘርፍ የሰለጠኑ፣ ያጠኑ፣ ምርምር ያካሄዱና የሰሩ የጤና ባለሙያዎች፣ ከፍ ያለ ድርሻ አላቸው፡፡ ይሄ አንድ እውነት ነው፡፡
ነገር ግን፤ ልብ ልንለው የሚገባ ሌላ እውነት አለ፡፡ ለሰፊ እና ለውስብስብ የወረርሽኝ ፈተና የሚመጥን፤ በቂ አቅምና ልምድ፣ እንኳን በኢትዮጵያ፣ በአውሮፓ አገራትም በብዛት አልታየም፡፡ ሁለቱንም እውነታዎች አጣምሮ መያዝ ያስፈልጋል፡፡
በአንድ በኩል፤ በተላላፊ በሽታና በወረርሽኝ ዙሪያ የተማሩና የተመራመሩ ባለሙያዎች፣ ትክክለኛ፣ የሚያዋጣና የሚያዛልቅ የአሰራር ስርዓትን በማሰናዳት በኩል ወሳኝ ድርሻ አላቸው፡፡ ይህ ስንል ግን፤ “የወረርሽኙን ነገር በናንተ ላይ ጥለነዋል” የምንልበት፣ በቂ የሙያ ብቃቶችን ያሟላ ተቋም አለ ማለት አይደለም፡፡
የህክምና ብቃት፣ ወይም የወረርሽኝ ተመራማሪ ብቃት ማለት፣ ተቋማትን የማዋቀርና የሥራ አስኪያጅነት ብቃት እንደማለት ቆጥረን፣ ሁሉንም ኃላፊነት በሃኪሞች ላይ አልያም በወረርሽኝ ተመራማሪዎች ላይ ከጫንን፣ ትልቅ አላዋቂነት ነው፡፡ ጊዜያዊና ቋሚ የአሰራር ስርዓቶችን የመፍጠርና የመዘርጋት ብቃትም፤ ልዩ ብቃት ነው፡፡ ሁሉንም ነገር ያጣጣመና ያዋሃደ ትክክለኛ አላማን በጽናት ይዞ ለስኬት የማራመድ የአመራር ብቃት ከጤና ሙያ ውጭ፣ ብዙ የሙያ አይነቶችን እንደሚፈልግም መዘንጋት የለብንም፡፡
 የወረርሽኙን ፈተና የሚመጥንና የአገርን አቅም ያገናዘበ፣ ውጤታማ እና የተሳለጠ የአሰራር ሰርዓትን በፍጥነት እያስፋፉ መዘርጋትና ማጠናከር፤ እጅግ ከባድ ስራ ነው፡፡ ዋና ዋናዎቹን የስራ ዘርፎች አቀናጅቶ  ማስፈፀም፣ እያንዳንዱን ዝርዝር ስራ ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚችል መዋቅርን መምራትም፣ ፈታኝ ስራ ነው፡፡ ምን ለማለት ፈልጌ ነው?
“በማህበረሰብ ጤና ኢንስቲቱይት” እና በጤና ሚኒስቴር መካከል ያለውን ልዩነት በማነፃፀር፣ እውነታዎቹን በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡
የተላላፊ በሽታዎች ስርጭትን በሚመለከት፣… የወረርሽኝ አጥኚ ባለሙያዎች፣ ሰፊና ጥልቅ እውቀት፣ እንዲሁም የሰላ ክህሎት ይኖራቸዋል:: የተላላፊ በሽታ ህመምተኞችን ወደ ጤንነት በመመለስ በኩል ደግሞ፤ የጠቅላላና የስፔሻላይዜሽን መስክ ሃኪሞች፣ በእውቀትና በክህሎት እንደየዘርፋቸው የላቀ ደረጃ ይኖራቸዋል፡፡ ይሄ አንድ የማነፃፀሪያ ምሳሌ ነው፡፡
የማህበረሰብ ጤና ኢንስቲቱዩት፤ በወረርሽኝ ላይ ያተኮረ ጥልቀት አለው፡፡
ይህን ጨምሮ ሌሎች ተቋማትንና የሙያ መስኮችን አዋህዶ የመምራት ሰፊ አቅም ያለው ደግሞ፣ በጤና ሚኒስትር ይሆናል፡፡
እነዚህን ሁለት እውነታዎች ያገናዘበ የአሰራር ማስተካከያና ሽግሽግ በጊዜ ፈጥኖ መከናወን ተገቢ ነው፡፡ መቀጠልም አለበት::
ከዚህ ጐን ለጐን፣ ከውጭ አገራት ጊዜያዊ ድጋፍ የማግኘት ጥበብም፣ ቀላል ብቃት አይደለም፡፡ በዚያ ላይ፣ ከአንዳንድ የአገር ውስጥ ተቋማት፣ የልምድና የሙያ እገዛ ማግኘት ይቻላል፡፡
በዚህ በኩል፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ በርካታዎቹን የስኬት መሰረቶችና የስልጣኔ ገጽታዎችን በብቃት የሚያሟላ ቀዳሚው ድንቅ አርአያ፣ መማሪያና አጋዥ ተቋም ነው፡፡

Read 4699 times