Saturday, 25 April 2020 13:03

ኮሮና በዓለም ላይ በስፋት መሰራጨቱን ቀጥሏል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  “ገና ለብዙ ጊዜ አብሮን ይቆያል!” በማለት ነበር፣ የአለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ባለፈው ረቡዕ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ፣ የጉዳዩን አስከፊነት የገለጹት፡፡
አብዛኞቹ የአለማችንን አገራት የቫይረሱን የመጀመሪያ ዙር መራር ጽዋ በመጎንጨት ላይ እንደሚገኙ፣ የተወሰኑት ደግሞ ገና የከፋው ነገር እንዳልገጠማቸው የገለጹት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ አለም ከዚህ አስከፊ ቫይረስ ለመገላገል ገና ብዙ ፈተናና ትግል ይጠብቃታል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
እንዳሉትም ቫይረሱ በመላው አለም በስፋት መሰራጨቱን የቀጠለ ሲሆን፣ እስካለፈው ሐሙስ አመሻሽ ድረስ በመላው አለም በሚገኙ 210 አገራትና ግዛቶች ውስጥ ከ2 ሚሊዮን 670 ሺ በላይ ሰዎችን ሲያጠቃ፣ ከ186 ሺህ 400 በላይ የሚሆኑትንም ለህልፈተ ህይወት ዳርጓል::
ከ852 ሺህ በላይ ሰዎች የተጠቁባት አሜሪካ፤በአለማችን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባት ቀዳሚዋ አገር ስትሆን፣ ስፔን ከ213 ሺህ በላይ፣ ጣሊያን ከ187 ሺህ በላይ፣ ፈረንሳይ ከ159 ሺህ በላይ፣ ጀርመን ከ151 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባቸው ቀዳሚዎቹ አምስት አገራት ሆነዋል፡፡
አሜሪካ በ47 ሺህ 808፣ ጣሊያን በ25 ሺህ 85፣ ስፔን በ22 ሺህ 157፣ ፈረንሳይ በ21ሺህ 340፣ እንግሊዝ በ18 ሺህ 738 ሞት እንደ ቅደም ተከተላቸው በርካታ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ለሞት የተዳረጉባቸው ቀዳሚዎቹ አምስት የአለማችን አገራት መሆናቸውንም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ኮሮና፡- የአፍሪካ መሰንበቻ
የአለም የጤና ድርጅት ቀጣዩዋ የጥፋት ማዕከል ትሆናለች ባላትና ከ300 ሺህ በላይ ሰው ለሞት ሊዳረግባት እንደሚችል ባስጠነቀቀባት አህጉረ አፍሪካ፤ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ባሳለፍነው ሳምንት በ43 በመቶ ያህል ማደጉ ተነግሯል፡፡
አፍሪካን ኒውስ እንደዘገበው፤ እስካለፈው ሐሙስ ተሲያት ድረስ በ52 የአፍሪካ አገራት ውስጥ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 26 ሺህ የደረሰ ሲሆን፣ ከ1 ሺህ 240 በላይ የሚሆኑትም ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል፡፡
በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባቸውን አገራት በተመለከተ ዘገባው እንዳለው፣ ከደቡባዊ አፍሪካ አገራት ደቡብ አፍሪካ በ3 ሺህ 635፣ ከምስራቅ አፍሪካ ጅቡቲ በ974፣ ከምዕራብ አፍሪካ ጋና በ1 ሺህ 154፣ ከመካከለኛው አፍሪካ ካሜሩን በ1ሺህ 163፣ ከሰሜን አፍሪካ ግብጽ በ3 ሺህ 659 ተጠቂዎች ቀዳሚነቱን ይዘዋል፡፡ ከ1 ቢሊዮን በላይ ህዝብ ይኖርባታል ተብላ በምትገመተው አፍሪካ፣ ባለፉት 2 ወራት ጊዜ ውስጥ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች ግማሽ ሚሊዮን እንኳን አይደርሱም፡፡
መከራ ሊመክራቸው አቅም ያጣላቸው እጅግ በርካታ የአፍሪካ አገራት ዜጎች ከኮሮና ቫይረስ ራሳቸውን እንዲጠብቁ የተላለፈላቸውን መመሪያ ላለማክበር አሻፈረኝ ማለታቸውን የቀጠሉ ሲሆን፣ ከማግለያ ቦታ የሚያመልጡ ሰዎችም ከቀን ወደ ቀን በእጅጉ መበራከታቸው ተነግሯል፡፡ በኬንያ መዲና ናይሮቢ ባለፈው ማክሰኞ ከማግለያ ቦታ አምልጠው የወጡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን አድኖ ለመያዝ የአገሪቱ መንግስት ፖሊስ ማሰማራቱ ተዘግቧል::  
ከ3 ሺህ 465 በላይ ሰዎች በቫይረሱ በተጠቁባት ደቡብ አፍሪካ፤ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የእንቅስቃሴ ገደብ መመሪያን ጥሰው እንዳሻቸው መሆናቸውን ተከትሎ የአገሪቱ መንግስት ዜጎችን በግዳጅ ወደ መስመራቸው ለመመለስ ከ70 በላይ ተጨማሪ ፖሊሶችንና ወታደሮችን ማሰማራቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ በኒጀር ከቤት አትውጡ የሚለውን የመንግስት መመሪያ በመቃወም አደባባይ የወጡ አስር ሰዎች ለእስር የተዳረጉ ሲሆን፣ በጋናም ባለፈው ቅዳሜ ህግ ተላልፈው የልደት በዓል በድምቀት ሲያከብሩ ከተገኙ ከ50 በላይ ሰዎች ውስጥ ስድስት ናይጀሪያውያን እያንዳንዳቸው የ2 ሺህ 500 ዶላር ቅጣት ተጥሎባቸዋል፡፡
በሞሮኮ በአንድ ቀን ብቻ መንግስት የኮሮና ቫይረስን ወረርሽኝ ለመግታት ያወጣቸውን ህጎችና መመሪያዎች ጥሰዋል የተባሉ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው የተነገረ ሲሆን፣ ከ3 ሺህ 377 በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ የተጠቁባት ሞሮኮ፤የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጣችበትና የእንቅስቃሴ ገደብ ከጣለችበት መጋቢት ወር አጋማሽ አንስቶ ህግ ተላልፈው በመገኘታቸው ለእስር የተዳረጉት ዜጎች ቁጥር ከ50 ሺህ በላይ እንደሚደርስም ቢቢሲ ባወጣው ዘገባ አመልክቷል፡፡
የመንግስትን የእንቅስቃሴ ገደብ ጥሰዋል የተባሉት የደቡብ አፍሪካ የኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ስቴላ ናቤኒ የ53 ዶላር የገንዘብ ቅጣትና የሁለት ወር የስራ እገዳ የተጣለባቸው ሲሆን፣ ከቤት የመውጣት ክልከላን ችላ ብለው ተሰባሰብው የተገኙ 30 ናይጀሪያውያን የእግር ኳስ ተጫዋቾችም በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ድንበራቸውን ላለመዝጋት ከወሰኑና ምንም አይነት የእንቅስቃሴ ገደብ ካላደረጉ ጥቂት የአፍሪካ አገራት አንዷ የሆነችውና ከ100 በላይ ዜጎቿ በቫይረሱ የተጠቁባት የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ፤ “ከአርብ እስከ እሁድ ባሉት ቀናት አምላክ ኮሮና ቫይረስን ከአገራችን እንዲያጠፋልን ተግታችሁ በመጸለይ አሳልፉ” ሲሉ ለህዝባቸው ጥሪ ማቅረባቸው ተዘግቧል፡፡

አለም በኮሮና ጦስ የከፋ ረሃብ አንዣቦባታል
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመላው አለም እስከ 250 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን ለአስከፊ የረሃብ አደጋ ሊዳርግ እንደሚችልና መንግስታት የሚደርሰውን ቀውስ ለማስቀረት ከወዲሁ መዘጋጀት እንዳለባቸው የአለም የምግብ ፕሮግራም አስጠንቅቋል፡፡ በአስከፊው ረሃብ በከፍተኛ ሁኔታ ይጠቃሉ ተብለው የሚጠበቁት ቀዳሚዎቹ 10 የአለማችን አገራት የመን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ አፍጋኒስታን፣ ቬንዝዌላ፣ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ሶሪያ፣ ናይጄሪያና ሄይቲ መሆናቸውንም ድርጅቱ ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡ አለም በዚህ አስከፊ ረሃብ የሚደርሰውን ቀውስ ለመግታት፣ ጥበብ በተሞላበት አካሄድ በአፋጣኝ ርብርብ ማድረግ እንዳለበትም የድርጅቱ ዳይሬክተር ዴቪድ ቤስሊ ማስታወቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ አሜሪካ ለአለም የጤና ድርጅት የምትሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ማቋረጧን በይፋ ባስታወቁ በቀናት ዕድሜ ውስጥ፣ ለክልከላው ሰበብ ተደርጋ የተቀመጠችው ቻይና የኮሮና ቫይረስን ወረርሽኝ ባለማቀፍ ደረጃ ለመግታት ለሚደረገው ጥረት ማገዣ የሚውል ተጨማሪ የ30 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለአለም የጤና ድርጅት እንደምትለግስ አስታውቃለች፡፡

ፕሬዚዳንቱ የጨለጡት “አገር በቀል መድሐኒት”
የማዳጋስካር መንግስት ኮሮናን ለመከላከልም ሆነ በቫይረሱ የተያዘን ሰው ለመፈወስ ፍቱን እንደሆነ ተረጋግጧል ያለውን ከተለያዩ ዕጽዋት የተቀመመ አገር በቀል “የኮሮና መድሐኒት” ከሰሞኑ በይፋ ያስመረቀ ሲሆን፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አንድሬ ራጆሊናም፣ መድሐኒቱ ፍቱን መሆኑንና የጤና ጉዳት እንደማያደርስ ለማሳየት በህዝብ ፊት ተጎንጭተውታል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ይህን ተከትሎ ለቢቢሲ በሰጠው መግለጫ፤ “እስካሁን ድረስ አለማችን ኮሮናን የሚፈውስ ምንም አይነት መድሃኒት አላገኘችም፤ “መድሐኒት” ተብለው በየጓዳ ጎድጓዳው የሚመረቱ መሰል አደገኛና ባዕድ ነገሮችን ከመውሰድ ተቆጠቡ” ሲል አስጠንቅቋል፡፡
121 ሰዎች በተጠቁባት ማዳጋስካር፣ ማላጋሲ ኢንስቲቲዩት ኦፍ አፕላይድ ሪሰርች በተሰኘው የአገሪቱ ተቋም ተሰርቶ “ኮቪድ ኦርጋኒክስ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ መድሐኒት፣ የኮሮና ቫይረስን በ7 ቀናት ውስጥ  የመፈወስ አቅም እንዳለው በሙከራ መረጋገጡን ባለፈው ሰኞ በተከናወነው የምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተው የነበሩ ሁለት ሰዎች በመድሐኒቱ መፈወሳቸውንም ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ይሄን ይበሉ እንጂ፣ የመድሐኒቱ ውጤታማነትና አደገኛ አለመሆን የአለም የጤና ድርጅትን ጨምሮ በማንኛውም አለማቀፍ ተቋም ተመርምሮና ተጠንቶ እውቅና እንዳልተሰጠው የዘገበው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ፤ የህክምና ባለሙያዎችና ሳይንቲስቶች መሰል እውቅና ያልተሰጣቸው “መድሐኒቶች” እጅግ አደገኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ ማስጠንቀቃቸውን ገልጧል፡፡
የኮሮና ቫይረስ በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ አለምን ማጥለቅለቁን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከአሜሪካ እስከ አውሮፓና እስያ የህክምናው ዘርፍ ልሂቃንና ተመራማሪዎች ሌት ተቀን ክትባት ወይም መድሃኒት ለማግኘት ደፋ ቀና ከማለት አልቦዘኑም፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት፣ የተለያዩ አገራት የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ማዕከላትን ጨምሮ በርካታ የአለማችን አገራት ተቋማትን በኮሮና ክትባትና መድሃኒት ዙሪያ ከ150 በላይ ምርምሮችን በማድረግ ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተው ያገገሙና የዳኑ ሰዎችን ደም በመውሰድ ታማሚዎችን ለማከም የሚያስችል ምርምር በማድረግ ላይ የሚገኙ ተቋማትም አሉ፡፡
የጀርመን የፌዴራል የክትባቶች ተቋም በሰዎች ላይ የኮሮና ክትባት ሙከራ እንዲደረግ ባለፈው ረቡዕ ፈቃድ የሰጠ ሲሆን የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ሳይንቲስቶችም በሰዎች ላይ የክትባት ሙከራ ለማድረግ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸው ተነግሯል፡፡
ያም ሆኖ ግን፣ ለኮሮና ክትባት ወይም መድሐኒት ለማግኘት በአለም ዙሪያ በርካታ ምርምሮች እየተደረጉ ቢሆንም፣ ከ18 ወራት በፊት ክትባት ወይም መድሐኒት ይደርሳል ብሎ መገመት ከንቱ ምኞት ነው ይላሉ - የታዋቂው መድሃኒት አምራች ኩባንያ ሮቼ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰቭሪን ሽዋን፡፡

እምቢተኝነት - የኮሮና ትግል ፈተና
ሮማኒያ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት የጣለችውን የእንቅስቃሴ ገደብ ጥሰው የተገኙ ዜጎቿን ከሚያገኙት የወር ገቢ በስድስት እጥፍ በሚበልጥ ገንዘብ እንደምትቀጣ ብታስታውቅም፣ የአገሪቱ ዜጎች ግን ቫይረሱንም የገንዘብ ቅጣቱንም ከቁብ ሳይቆጥሩ፣ ገደቡን እየጣሱ እንደፈለጉ መሆናቸውን ቀጥለዋል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ባለስልጣናት አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መመሪያና ህጉን ተላልፈው በተገኙ ዜጎች ላይ ከ200 ሺህ በላይ ጊዜ ቅጣት መጣሉንና በዚህም ከ78 ሚሊዮን ዩሮ በላይ የቅጣት ገንዘብ መሰብሰቡን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ እምቢተኝነቱ በብዙ አገራት የተለመደ ሆኗል:: የኮሮና የእንቅስቃሴ ገደቦችንና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመሪያዎችን የሚተላለፉ ዜጎቿን እየተከታተለች መቅጣቷን የተያያዘችው እንግሊዝ፤ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ3 ሺህ 500 በላይ ቅጣቶችን መጣሏ ተነግሯል፡፡
በአሜሪካ የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ በመቃወም ዋሽንግተንና ኮሎራዶን ጨምሮ በርካቶች ከሰሞኑ አደባባይ ወጥተው ተቃውሞ ያሰሙ ቢሆንም፣ በአገሪቱ በተሰራ አንድ ጥናት 61 በመቶ ያህሉ አሜሪካውያን “ቤት መቀመጥ ኮሮናን ለመከላከልና በቁጥጥር ስር ለማዋል በእጅጉ ጠቃሚ ስለሆነ ሊቀጥል ይገባል” ማለታቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

የአየር ብክለት ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ቀንሷል
በመላው አለም ቁጥር ስፍር የሌላቸው ቀውሶችና ጉዳቶችን እያደረሰ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ፣ በአንጻሩ  ለአለማችን ያበረከተው “በጎ” ነገር እንዳለም እየተነገረ ነው - የአየር ብክለት በእጅጉ መቀነሱ፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት ሲባል አገራት ድንበሮቻቸውን መዝጋታቸው፣ የጉዞና የእንቅስቃሴ ገደቦች መጣላቸው፣ የሚዘጉ ኢንዱስትሪዎች መበራከታቸው በአለማችን የአየር ብክለት ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ፣ በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ማድረጉን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
በአለማችን በአየር ብክለት በከፍተኛ ደረጃ ተጎጂ እንደሆኑ በሚነገርላቸው ዋና ዋናዎቹ ከተሞች ባለፉት ሶስት ሳምንታት የአደገኛ በካዮች ልቀት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን የጠቆመው ዘገባው፤ ከአለማችን ከተሞች መካከል የከፋ የአየር ብክለት የሚታይባት የህንዷ ኒው ዴልሂ የበካዮች ልቀትን በ60 በመቶ በመቀነስ ቀዳሚነትን መያዟን አመልክቷል፡፡
የደቡብ ኮርያዋ ሴኡል፤ የቻይናዋ ውሃን እና የህንዷ ሙምባይ፤ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ እጅግ አደገኛና ለጤና ጎጂ በካይ ንጥረነገሮች ልቀት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰባቸው ሌሎች የአለማችን ከተሞች መሆናቸውም ተነግሯል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋቱንና አገራት ከፍተኛ የጉዞና የእንቅስቃሴ ገደብ መጣላቸውን ተከትሎ፣ የቱሪዝሙ መስክ በአለማቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት የዘገበው ፎርብስ መጽሄት፣ በ2020 የፈረንጆች አመት የአለማችን አየር መንገዶች ገቢ በ314 ቢሊዮን ዶላር እንደሚቀንስ መነገሩን አመልክቷል፡፡
በአሜሪካ 44 በመቶ ያህሉ አውሮፕላኖች በረራ አቋርጠው መቀመጣቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ በአገሪቱ በቱሪዝሙ ዘርፍ ከስራ ገበታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር እስከ መጪው ሳምንት 8 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጧል፡፡
ህጻናት እና ኮሮና
እስከ ፈረንጆች አመት 2020 መጨረሻ በመላው አለም ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ለሞት ሊዳረጉ፣ እስከ 66 ሚሊዮን የሚደርሱ ሌሎች ህጻናትም ወደ ከፋ ድህነት ሊገቡ እንደሚችሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል፡፡
በመላው አለም በሚገኙ 150 አገራት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ሳቢያ፣ የነጻ የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ የነበሩ 369 ሚሊዮን ያህል ህጻናት፣ የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት የሚያቆሙ ሲሆን ይህም   ለሞት ሊዳርጋቸው እንደሚችል ድርጅቱ ጠቁሟል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ያደረጉ የአለማችን አገራት 188 መድረሳቸውን የዘገበው ሮይተርስ፤ በዚህም ከ1.5 ቢሊዮን በላይ ህጻናት ከትምህርት ቤት ቀርተው ቤት ለመዋል መገደዳቸውን አመልክቷል፡፡

አሜሪካ ከዚህ የከፋው ሊመጣባት ይችላል
ኮሮና እስከ ትናንት በስቲያ ተሲያት ድረስ ከ800 ሺህ በላይ ሰዎችን ባጠቃባትና ከ45 ሺህ በላይ የሚሆኑትንም ለሞት በዳረገባት አሜሪካ፤ በቀጣይ ሁለተኛ ዙር የከፋ የኮሮና ቫይረስ ማዕበል ሊከሰት እንደሚችል በአገሪቱ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ሮበርት ሬድፊልድ ማስጠንቀቃቸው ተዘግቧል፡፡
ቀጣዩ ወረርሽኝ ምናልባትም በአሜሪካ የጉንፋን በሽታ በሚበራከትበት ወቅት ላይ የሚከሰት ከሆነ የሚያደርሰው ጥፋት ከአሁኑ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ያስጠነቀቁት ዶ/ር ሮበርት ሬድፊልድ፤ ሊያጋጥም የሚችለውን ይህን ፈታኝ ሁኔታ ለመጋፈጥ ከአሁኑ መዘጋጀት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
በተያያዘ ዜና፤ በአሜሪካ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ባለፈው ሳምንት ብቻ 4.4 ሚሊዮን ሰዎች ለስራ አጥነት መዳረጋቸውን የዘገበው ዘ ኢንዲፔንደንት፤ ባለፉት 5 ሳምንታት ለስራ አጥነት የተዳረጉት ሰዎች ቁጥር ከ26 ሚሊዮን በላይ መድረሱንም አመልክቷል፡፡

ዲያስፖራው የሚልከው ገንዘብ በ142 ቢ. ዶላር ይቀንሳል
በመላው አለም በውጭ አገራት የሚገኙ ዲያስፖራዎች ወደ አገር ቤት የሚልኩት ገንዘብ፣ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በ142 ቢሊዮን ዶላር እንደሚቀንስ የአለም ባንክ ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል፡፡
በውጭ አገራት የሚኖሩ ዲያስፖራዎች ከሰሃራ በታች ወደ ሚገኙ የአፍሪካ አገራት በዚህ አመት የሚልኩት ገንዘብ በ23.1 በመቶ ያህል ወይም በ37 ቢሊዮን ዶላር ይቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ድርጅቱ አስታውቋል፡፡ በሽታው በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን ከስራ እያፈናቀለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ ከአገራቸው ውጭ የሚኖሩ ዲያስፖራዎች ከራሳቸው ተርፎ ለቤተሰብ የሚልኩት ገንዘብ የማግኘት ዕድላቸው ጠባብ እንደሆነ የጠቆመው ድርጅቱ፤በተለይም ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው አገራት ከዲያስፖራው የሚላከው ገንዘብ በአማካይ በ20 በመቶ ያህል ሊቀንስ እንደሚችል አስታውቋል፡፡
ዲያስፖራው የሚልከው ገንዘብ መቀነሱ በሁሉም የአለም አካባቢዎች የሚከሰት ቢሆንም በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል የተባለው ግን በአውሮፓና በማዕከላዊ እስያ አገራት እንደሆነ የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ በእነዚህ አገራት እስከ 27.5 በመቶ ያህል ሊቀንስ እንደሚችል መነገሩን አመልክቷል፡፡
በምስራቅ እስያና በፓሲፊክ አገራት ደግሞ ዲያስፖራው የሚልከው ገንዘብ እስከ 13 በመቶ መቀነስ ያሳያል  ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፤ባለፈው የፈረንጆች አመት 2019 በመላው አለም ዲያስፖራው ወደ አገር ቤት የላከው 554 ቢሊዮን ዶላር በታሪክ ከፍተኛው ሆኖ የተመዘገበ መሆኑንም አስታውሷል፡፡

የፊት ጭምብል ነገር
ከኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ጋር ተያይዞ እነማን መቼና በምን ሁኔታ ላይ ሊጠቀሙት ይገባል በሚል ያደጉ አገራት የህክምና ባለሙያዎችን ሳይቀር ሲያወዛግብና ሲያነጋግር የቆየው የፊት ጭምብል ጉዳይ አሁን አሁን እየለየለት የመጣ ይመስላል፡፡
በበርካታ አገራት የፊት ጭምብል ማድረግ ከኮሮና እንደሚከላከል በመታመኑ ዜጎች አዘውትረው እንዲጠቀሙ የተደረገ ሲሆን በመላው የጀርመን ግዛቶች  ሁሉም ሰው ግብይት በሚፈጽምበትና የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶችን በሚጠቀምበት ወቅት የፊት ጭንብል እንዲያደርግ የሚያስገድድ መመሪያ ከሰሞኑ ተግባራዊ ሊደረግ እንደሆነ ቢቢሲ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡


Read 13357 times