Saturday, 25 April 2020 12:53

ኮሮና፡- በዱባይ ከ20ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ከሥራ ይፈናቀላሉ ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

 በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሚኖሩ ከ4ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከሥራቸው ተፈናቅለው ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን የገለፀው በዱባይ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ጽ/ቤት፤ በቀጣይም ከ20ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ተመሳሳይ ችግር እንደሚገጥማቸው አስታውቋል፡፡ ኮሙኒቲው ባሰራጨው መረጃ በሁለት ሣምንት ጊዜ ውስጥ ከስራቸው የተፈናቀሉ 4ሺህ ያህል ኢትዮጵያውያንን መመዝገቡንና ቁጥሩም በየጊዜው እየጨመረ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በወረርሽኙ ሳቢያ በሀገሪቱ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ለ15 ቀናት የሚቀጥል ከሆነ እስከ 20ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ስራ አጥ ሊሆኑ እንደሚችሉም የኮሚኒቲው ቅድመ - ትንበያ  ያመለክታል፡፡
በአሁኑ ወቅት ስራ አጥ መሆናቸው የተረጋገጠ ከ4ሺህ በላይ ዜጐች በየቀኑ እርዳታ እንዲሰጣቸው ጥያቄ እያቀረቡ ቢሆንም ኮሚኒቲውና ቆንጽላ ጽ/ቤቱ በጋራ በሚያደርጉት ጥረት ግን ድጋፍ ማድረግ የቻሉት በየቀኑ ለ250 ሰዎች ብቻ እንደሆነ አስታውቋል፡፡  
ለችግር ከተዳረጉት ኢትዮጵያውያን መካከል የሚበዙት ሴቶችና ህፃናት መሆናቸውንም ከተሰበሰቡ መረጃዎች ለማወቅ መቻሉን ኮሚኒቲው ጠቁሞ፤ እነዚህ ዜጐች በአመዛኙ በሰው ቤት ሠራተኝነትና በእለት ተእለት ገቢ የሚያስገኙ አነስተኛ ስራዎች ላይ ተሠማርተው የሚገኙ እንደነበሩ አመልክቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከ7ሺህ ሰባት መቶ በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሲያዙ 46 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል፡፡

Read 12344 times