Saturday, 25 April 2020 12:27

የአዲስ አበባ ሆቴሎች በየወሩ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ እያጡ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 88% ያህሉ በከፊል ወይም ሙሉ ለሙሉ ሊዘጉ ይችላሉ

             የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ታስቦ በአገር ውስጥና በአለማቀፍ ደረጃ በተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦች ሳቢያ በአዲስ አበባ የሚገኙ ሆቴሎች በየወሩ ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ እያጡ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበር ሰሞኑን ይፋ ባደረገው የጥናት ውጤት መሰረት፤ በአዲስ አበባ ከሚገኙና የማህበሩ አባል ከሆኑ 130 ሆቴሎች ውስጥ 66 በመቶ ያህሉ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ሊዘጉ ይችላሉ ተብሏል::
የሆቴሎቹ መኝታ ክፍሎች ፆማቸውን ማደር ከጀመሩ ሰንበት ማለታቸውን የዳሰሳ ጥናቱ ያመላክታል፡፡ 130 የሚደርሱት ሆቴሎቹ በአጠቃላይ 8,997 መኝታ ክፍሎች እንዳላቸው የጠቀሰው የዳሰሳ ጥናቱ፤ በአሁኑ ወቅት ከእነዚህ አልጋዎች 2 በመቶ ያህሉ ብቻ ተይዘው እንደሚያድሩ ይጠቁማል፡፡
በማህበሩ ስር ከተሰባሰቡት ሆቴሎች ውስጥ 38 በመቶ ያህሉ ባለሦስት ኮከብ፤ 19 በመቶዎቹ  ባለ 4 ኮከብ መሆናቸውን የጠቆመው ጥናቱ፤ ከእነዚህ ውስጥ 88 በመቶዎቹ በኮሮና ሳቢያ ሙሉ ለሙሉ አሊያም በከፊል ሊዘጉ ይችላሉ፤ በዚህም የሰራተኞቻቸው እጣ ፈንታ ለአደጋ ይጋለጣል ብሏል፡፡  ሆቴሎቹ በጠቅላላ በሥራቸው ለሚያስተዳድሯቸው ከ15 ሺህ በላይ ሰራተኞች ደሞዝ መክፈል እየተቸገሩ መሆኑም በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

Read 10260 times