Print this page
Tuesday, 21 April 2020 19:55

የንስሃ ዘመን!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ
Rate this item
(10 votes)

  ሳምንት ያህል ከቤት ሳልወጣ ቆየሁ:: ተጋድሜ እውላለሁ፤ ፊልም አያለሁ፣ መፅሃፍ አነባለሁ … እተኛለሁ፡፡ ይሰለቻል:: ነገርየው እየከፋ እንደሄደ ተረድቻለሁ፤ ግን ደግሞ ሳልወጣ ከዚህ የበለጠ መቆየት እንደማልችል ስረዳ ልብሴን ቀያይሬ ተነሳሁ:: ቢያንስ ቢያንስ ለጥቂት ቀናት የሚሆን አስቤዛ እንዲሁም አልኮል ነገር ባገኝ እገዛለሁ፡፡ ቀደም ብዬ ከቤቴ መቀመጥ ጀመርኩ መሰለኝ፣ ገና ዋናው ችግር ሳይመጣ ያጠራቀምኩትን ገንዘብ ልጨርስ ዳርዳር አልኩ፡፡
ከሳምንት ቤት መቀመጥ (በርግጥ 9 ቀን ሆኖኛል!) በኋላ ሰፈሩ ሁሉ አዲስ ሆነብኝ:: የግቢውን በር ከፍቼ እንደወጣሁ የሰፈር ልጆች እርዳታ እንዳበረክት የሚያሳሰብ ፅሁፍ የተጻፈበት ካርቶን ይዘው ቀረቡኝ:: የሰፈሩ ሱሰኛ ልጆች (ቃሚና ጠጪዎች) ተሰብስበው ድሃ ለመርዳት ተፍ ተፍ ሲሉ ደስ ይላሉ፡፡ ለችግረኞች መርጃ እንደሆነ ሲነግሩኝ እርዳታው ለእኔም እንደሚገባ ላሳስባቸው ብዬ አፍሬ ተውኩት፡፡ ጥቂት ሳንቲም ከጣልኩ በኋላ የሰፈሩን ቅያስ አልፌ ወደ ዋና መንገድ ገብቼ ሽቅብ ቁልቁል ቃኘሁ፡፡
አጠገቤ ሁለት የኔ ብጤዎች የውሃ ኮዳ ግማሽ ግማሽ ቀድደው ከረጅም ዘንግ ላይ በማሰር ምፅዋት ሰጪዎች በሩቁ እንዲሰጧቸው የዘየዱትን መላ ሳስተውል ገረመኝ፡፡ አንደኛው ሰውዬ እንዲያውም በየሰዓት ሽርፍራፊው ከጎናቸው ከሸጎጧት ሳኒታይዘር ፈሰስ እያደረጉ መዳፋቸውንና ፊታቸውን አበስ አበስ ያደርጋሉ:: ባለፈው ልገዛ ያልዞርኩበት አልነበረምና ከየት እንዳመጡት ልጠይቃቸው ፈልጌ ጥቂት ተመላለስኩና ተውኩት፡፡ ቀጥሎ ያገኘኋቸው የሰፈር ሱቆች ደግሞ ደንበኞቻቸው በሩቁ እንዲስተናገዱ የገመድ አጥር ሰርተዋል:: ጥቂት የሰፈር ሴቶች አፋቸውን በሻሽ ነገር ጠርዘው ስመለከት (ማስክ) ማድረጋቸው መሆኑ ተገለጠልኝ:: ለጥቆ ከሚገኘው የባንክ የገንዘብ ማሽን ለማውጣት ስደርስ ማሽኑ ላይ የተጻፈውን ማሳሰቢያና አጠገቡ ታስሮ የተንጠለጠለውን በአልኮል የተሞላ የውሃ ኮዳ ስመለከት አይኔን ማመን አቃተኝ:: ከመዳፎቼ ላይ እስኪበቃኝ አፍስሼ ተቀባሁ፡፡ እናም መዳፌን እያሸተትኩ ገንዘቤን አውጥቼ ጉዞ ቀጠልኩ፡፡ ከተማው በጭርታው ፍርሃት ይዘራል፡፡ ጉሮሮዬን ይከረክረኝ ጀመር፡፡ ጉንፋን ነገር ሊይዘኝ መሰለኝ፡፡
ሰፈሩ እንደ ድሮው አይደለም፡፡ እግረኛ የሚያጣብበው መንገድ ጭር ወደ ማለቱ ገደማ ነው፡፡ ቀስ በቀስ የመንዱን ጠርዝ ከያዝኩ በኋላ እያሰላሰልኩ መራመድ ቀጠልኩ፡፡ በቆሻሻ ገንዳው አካባቢ ስደርስ በገንዳው ዙሪያ ከከበቡት ጥቂት ውሾች በስተቀር ለወትሮው የሚሰበሰቡት የጎዳና ልጆች አልነበሩም፡፡ በጥቂቱም ቢሆን ደስ ያለኝ መሰለኝ፡፡ እየተከተሉ የሚያጨናንቁኝ ነገር ያስከፋኛል፡፡ (ግን የት ገብተው ይሆን ስል ማሰቤ አልቀረም፡፡)
ሰፊው መንገድ ላይ ስደርስ 150 ሜትር የሚረዝመው መንገድ ጭር ከማለቱ የተነሳ ለሰከንዶች ቆም ብዬ ወደ ፊት ወደ ኋላ በማየት ተገረምኩ፡፡ እውነትም በዚህ ሰዓት ጭር ያለ መንገድ ማየት ከባድ ነው፡፡ በትልቅ ከተማ ውስጥ የመኪና ወይም የሰው ትርምስ ማጣት በራሱ ያስደነግጣል፡፡ አደባባዩ አጠገብ ስደርስ በእግረኛ መሻገሪያ ዜብራው ላይ አንድ ወደል አይጥ እየነጠረ ሲሮጥ በመመልከቴ በድንጋጤ ቆሜ አይኖቼን ማሻሸት ያዝኩ፡፡ በጣም ተገረምኩ፡፡ በአዲስ አበባ ሰፊ ጎዳና በዜብራ ላይ የሚሮጥ አይጥ ተመለከትኩ ብል ማን ያምነኛል::
በጆሮዎቼ ውስጥ ከሸጎጥኳቸው ሁለት ማዳመጫዎች የማዳምጠው የቦብ ማርሌይን ዘፈን ሲሆን በልቤ እያሰብኩ የነበረው ደግሞ ከቀናት በፊት ያየሁትንና ዊል ስሚዝ የሚተውንበትን ፊልም ነበር፡፡ ቦብ ማርሌይ በሚማርክ ድምፅ ‹ሁሉ መልካም ይሆናልና አትጨነቅ!› እያለ ይመክራል፡፡
… ሶስት ትናንሽ ወፎች በማለዳ ከደጃፌ ቆመው ይዘምራሉ፣
አትጨነቅ ሁሉ በጎ ይሆናል እያሉ ….
ባለፈው ያየሁት ፊልም ደግሞ ( I am Legend) ሲሆን በሪቻርድ ማቲሰን መጽሐፍ ላይ ተመስርቶ የተሰራ ነው፡፡ ወቅቱ 2009 እንደሆነና ህክምናን የተላመደና ጀነቲካሊ የተሻሻለ የኩፍኝ ክትባት ለካንሰር ህክምና ይውል ዘንድ የተፈጠረ ቢሆንም ጅምላ ጨራሽ በመሆን የዓለምን ህዝብ ዘጠና በመቶ ያጠፋል:: የተቀሩትንም አብዛኞቹን ወደ ሰው በሊታ ጭራቅነት ይቀይራቸዋል:: አክተሩ በሚኖርበት የኒውዮርክ ከተማ፣ ነዋሪዎች በሙሉ አልቀው የቀረው እርሱና አንድ ውሻው ብቻ ነበሩ፡፡ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች በሙሉ አርጅተውና ሐረግ በቅሎባቸው ኦና ሆነዋል፣ ዘመናዊና ቅንጡ መኪኖች በየመንገዱ ወዳድቀዋል፣ ሞሎችና ሱቆች ያሳዝናሉ፡፡ ከተማም ሆነ ስልጣኔ ወይም ገንዘብ ሰው ከሌለ ምንም ትርጉም እንደሌለው በግልፅ ያየሁበት ፊልም ነበር:: ራሴን በእርሱ ቦታ አድርጌ ሳየው እጅግ ይዘገንናል፡፡ አዲስ አበባን በባዶ ከቦሌ እስከ ጉለሌ ለብቻዬ ቢሰጡኝ ምን ያደርግልኛል፣ ሁሉ የሚያምረው ሰው ሲኖር ብቻ ነው የሚል ሃሳብ ሳይመላለስብኝ አልቀረም፡፡
እኔ ግን ይኸው ወድጄ ሳይሆን ተገድጄ እረፍት ከወጣሁ ሳምንት ሆነ፡፡ ጥቂት ቀናት ወለም ዘለም የምታደርግ ሳንቲም ስለነበረችኝ አንድ ሳምንት ከቤቴ አረፍኩና አሁን እጅ ወደ መስጠት እየደረስኩ ነው፡፡ እናም ብቻዬን በምጓዝበት ጎዳና ላይ ለብቻዬ ፈገግ እያልኩ ባዶውን መንገድ በማቋርጥበት ወቅት እንደ ብራቅ የፈነዳ የሃይገር ባስ ጡሩምባ ከሃሳቤ አናጠበኝና ዘልዬ ከመንገዱ ዳር ለሰከንዶች ደረቴን ደግፌ ቆምኩ፡፡ ቀና ብዬ ግራና ቀኝ ሳጣራ እንደ ጥይት ከተተኮሰው መኪናና ራቅ ብለው በትዝብት ቆም ብለው ከተመለከቱኝ ሽማግሌ በቀር ምንም አይታይም፡፡
አማትቤ መንገዴን ቀጠልኩ፡፡ ጎብጠው ትንንሽ እርምጃዎችን እየቆጠሩ ወደሚራመዱት ሰውዬ ጠጋ አልኩ፡፡ እየፈራሁ ሰላምታ አቅርቤላቸው ወዴት እንደሚሄዱ ጠየኳቸው:: በድካምና በእርጅና የተጨማደደ ፊታቸውን እያፈገጉ ሰላታምዬን መለሱልኝ፡፡ ከስራ ወጥተው ወደ ቤታቸው እየሄዱ እንደሆነ ነገሩኝ::
‹‹የት ነው እሚሰሩት? … ›› ስል ጠየኩ
‹‹…እዚህ ፀጋዬ ጋራዥ ጥበቃ ነው የምሰራው… ድሮ ሜካኒክ ነበርኩ፤ አቅሜና እይታዬ ሲደክም በር ላይ ተቀምጬ መዋል ጀመርኩ፤ የማሳድገው ልጅ አለኝና አልተኛም…››
‹‹ልጅ ሲሉ?…›› አልኩ ግራ ገብቶኝ፡፡ ሰውየው ደክመው ነው የሚታዩት፡፡ እናም ልጅ ሲሉ አልገባኝም፡፡
‹‹የልጅ ልጄን የማሳድገው እኔ ነኝ:: እናቱ (ልጄ) ከሞተች ሁለት አመት ሊሆናት ነው:: አባቱ አይታወቅም፡፡ አሁን ልጄ አምስት አመቱ ነው፡፡ እርሱ ባይኖር እኔ ራሱ እስካሁን በህይወት የምቆይ አይመስለኝም፤ ለእርሱ ስል ነው በብርታት የምኖረው፡፡ ድሮ በደህናው ጊዜ ከባለቤቴ ጋር የምንኖርባት የቀበሌ ቤት ነበረችን፤ እና እስካሁን እዚያችው ውለን እንገባለን፡፡ አሁን የምንኖርባት እኔና እርሱ ብቻ ነን…››
ወሬውን ለመቀየር ያህል ስለ አዲሱ በሽታ የሚያውቁትንና ምን ያህል እየተጠነቀቁ እንደሆነ ጠየኳቸውና እንዲህ ሲሉ መለሱልኝ፤ ‹‹ከቤት ዋሉ ሲባል እሰማለሁ፤ ቢኖረንና ብንውልማ መች ጠልተን ነው በመጦሪያ ጊዜያችን ላይ ታች የምንለው:: እኔምልህ …. ልጄ እኔ ሰርቼ ካልገባሁ ዳቦ መብላት አይችልም፡፡ እኔም በህይወት ከሌለሁ ይቸገራል፡፡ የማደርገው ጠፍቶኝ እንጂ ብቆይ እወዳለሁ…››
‹‹አይዞዎት በርቱ፤ ያው እንደሚባለው እጅዎትን ቶሎ ቶሎ ይታጠቡ፤ ከሰው ጋር አይጨባበጡ፡፡›› ስል ደሰኮርኩ፤ ዝም ከምል ብዬ፡፡
‹‹ታዲያ እርሱንማ እያደረግሁ ነው፡፡›› አሉኝ ቆም ብለው እያዩኝ፡፡
‹‹አልኮል ወይም ሳኒታይዘርም ካገኙ እጅዎትን ቶሎ ቶሎ ያባብሱ፤ መቼም አይገኝም ከተገኘ ብዬ ነው…››
‹‹…እሱንም ፈልገን ፈልገን አጣን… ግና መቼም ካልተገኘ ምን ይደረጋል፡፡ አሁን በዚያን ሰሞን አንዱ አልኮል ነው ብሎ በውድ ዋጋ የሸጠልን ቀለም (ጂቪ) የተበጠበጠ ካቲካላ ሆኖ ተገኘ… ›› ፈገግ እያሉ …
‹‹ሰውየውን አታስይዙትም ነበር ..›› አልኩ ምን እንደተደረገ ለመገመት እየሞከርኩ፡፡
‹‹አይ ልጄ እዚህ አገር ስንት ጭልፊት አለኮ:: ከሸጠልን በኋላማ ከየት እናገኘዋለን … የፈሰሰ ውሃ አይታፈስም ብለን ለወደፊቱ ትምርት ወስደን ቀጠልን’ጂ አላገኘነውም፡፡ አንድ ታሪክ አውቃለሁ፡፡ እንዲህ የሚል  …
ሰውየው የመኪናው ጎማ ይተነፍስበትና ለመቀየር ብሎኖቹን እየፈታ ከመንገዱ ዳር ካለው የቆሻሻ መውሰጃ ቱቦ ጠርዝ ላይ ይደረድራል … ፈትቶ እንደጨረሰ ጎማውን ነቅሎ በተቀያሪው ከተካ በኋላ ዞር ሲል ብሎኖቹ በዚያ አልነበሩም፡፡ በአጠገቡ የሮጠ አንድ መንደርተኛ ውሻ ረግጧቸው በፈሳሽ ቆሻሻ ከተሞላው ቱቦ ውስጥ ወድቀው ጠፍተዋል፡፡ ሰውየው ግራ ገብቶት ወገቡን ይዞ ሲተክዝ ፊት ለፊቱ ካለው የእብዶች ሃኪም ቤት የግምብ አጥር በላይ የሚያጮልቅ አንድ ሰው (ያው እብድ ይሆናል መቼም …) እንዲህ ይለዋል …
‹…ሰውዬ አስብ እንጂ …የጠፋው ጠፍቷል.. ከቀሩት ሶስት ጎማዎች ላይ አንድ አንድ ብሎን ፍታና አራተኛውን አስረህ ሂድ…›
በተሰጠው ሀሳብ በጣም ተገርሞ እንደዚያው አደረገና ቀና ብሎ እያስተዋለው ‹…ግን’ኮ እብድ መሆን አለብህ እዚያ ውስጥ የታሰርከው…› ይለዋል …
ሰውየውም እንዲህ ይመልሳል ‹እብድ ልሆን እችላለሁ፤ ደደብ ግን አይደለሁም!…›
እናም ነገርዬው እንደዛ ነው፡፡ የፈሰሰ ውሃ ስለሆነ እኛ እርሱን ትተን ወደፊት ቀጥለናል:: የጣልነውን በማሰብ ከመሰቃየት ወጥተን ወደ እለት እንጀራችን አልፈናል፡፡ አሁን በጎዶሎም ቢሆን ወደፊት መቀጠል ብቻ ነው አማራጩ፡፡”
በመጨረሻም አመስግኜና መልካም እየተመኘሁ ሰውየውን ተሰናብቼ ወደ ሰፈሬ ስመለስ፣ በእጄ የያዝኳትን ባዶ የውሃ ኮዳ እያየሁ ጥቂት አሰብኩ፡፡ ወደ ቅድሙ የባንክ ማሽን አቀናሁ፡፡ እዚያ አልኮል ሞልቶ የተንጠለጠለውን ዕቃ አስታውሼ ጥቂት ቀንሼ ወደ ቤቴ ብወስድ ብዬ አስቤ  ነበር:: ከዚያ ስደርስ ግን ባየሁት ነገር ተገረምኩ:: የቅድሙ አልኮል የተሞላ ኮዳ ገመዱ ተቆርጦ ተወስዷል::  
ጥበቃውም ፈገግ ብሎ እያየኝ፤ ‹‹በቀን ውስጥ ብዙ ጊዜ አልኮሉ ይሰረቃል፡፡ አሁን አንተ ስትመጣ (በእጅህ ባዶ የፕላስቲክ ኮዳ ስላየሁ) ልትሰርቅ መስሎኝ ተደብቄ እያየሁህ ነበር፡፡ ግና ስትመጣ ከእነ ዕቃው የለም ለካ…›› አለና ሳቀ፡፡ ደነገጥኩ፤ ደግሞም ተናደድኩ፡፡
‹‹ስታየኝ ሌባ እመስላለሁ’ንዴ!›› ስል አፈጠጥኩበት፡፡
‹‹ጌታዬ ሌባማ ታይቶ አይታወቅም:: እንዲያው ግን ስለጠረጠርኩዎ ይቅር ይበሉኝ…››
የማይታወቅ ነገር በልቤ እያጉተመተምኩ መንገዴን ወደ ሰፈሬ ቀጠልኩ፡፡ ጌታ ከውርደት አድኖኛል ስል አሰብኩ፡፡ የሆነ ያልሆነውን እያሰብኩ ዳላስ ጠጅ ቤት ራሴን አገኘሁት:: ሰዎች እዚያና እዚህ ፈንጠር ፈንጠር ብለው ይጯጯሃሉ፡፡ ጥግ ላይ ጨለምለም ካለው ቦታ ደግሞ ቅድም ለችግረኛ ብለው ከቤት ስወጣ ሳንቲም የተቀበሉኝ የሰፈር ዱርዬዎች ከበው ይጨፍራሉ፡፡ ንዴቴ የፊቴን ግለት ሲጨምረው ታወቀኝ፡፡ እንዴት ከዚህ ድሃ ህዝብ እየሰረቁ …. ስል አሰብኩና ተውኩት:: አንድ ብርሌ አዝዤ መተከዝ ጀመርኩ:: ቢመቸን ለካ ሁላችንም ጥቂት ጥቂት ሌብነት አለብን ብዬ ተረጋጋሁና ጠጄን ማንደቅደቅ ጀመርኩ፡፡ ጌታ ሆይ፤ ይህንን ዘመን ካሳለፍከን መቼም የታሪክ ምልክት የመሆን እድል አለን፡፡ የዚያን ግዜ እንዲህ ነበርኩ እያልን መተረካችን አይቀርም:: ፈጣሪ ለምልክት የሚያስቀረን ከሆነ፡፡ ቅድም ሲከረክረኝ የነበረው ጉሮሮዬ ሲለቀኝ ታወቀኝ፡፡
ወደ ፈተና  እንዳትገቡ ጸልዩ ነበር የተባለው:: እኛ ይኸው ዘው ብለን ጠለቅንበትና ጸሎት ጀመርን፡፡ ይሰማን ይሆን፡፡ እጠራጠራለሁ:: ከሁለተኛው ብርሌ ጠጅ በኋላ ግን እንደሚሰማን እርግጠኛ ነኝ ስል ጮህኩ፡፡ ፀጥ ብለው ለሰከንዶች ያስተውሉኝ ጀመር፡፡ ምን ገዶኝ … በፀጥታው መሃል ሶስተኛውን አዘዝኩ:: በሞቅታዬ መሃል ቢሆንም’ንኳ ተስፋ ይታየኛል::


Read 1866 times