Monday, 20 April 2020 00:00

ከፌስቡክ ገጾች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ኪራይና መስፍን
ሰሞኑን ስሜን ከቤት ኪራይ ጋር አንሥተው ነበር፤ እርግጥ ቤት የለኝም፤ ነገር ግን አግዚአብሔር ይመስገን አልተጎዳሁም፤ ልጆች የሚባሉት አድገው ራሳቸውን ችለዋል፤በርግጥም ጡረታዬ በዛሬው ጊዜ አያኖርም፤ በዚህም በኩል እግዚአብሔር ይመስገንና ጥቂት ሰዎች ሥራቸው አድርገውት በሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ ይረዱኛል፤ የእነዚህ ሰዎች ውለታ በጣም ይከብደኛል፤ እግዚአብሔር ጤንነትና ዕድሜ፣ ሰላምና በረከቱን ይስጣቸው፤ የቤት ኪራዬንም ደርግ ምስጋና ይድረሰውና ጎምዶልኛል፤ ለሁላችንም ማለቴ ነው፤ እነዚህ አሥር የማይሞሉ ሰዎች ባይኖሩ ምን እንደሚደርስብኝና የት እንደምወድቅ አላውቅም፤ ስደትን ግን ጭራሽ አላስበውም!
እኔን የሚያሳዝኑኝ ግን የኔን ዕድል ያላገኙ ስንትና ስንት ኢትዮጵያን ያገለገሉ ሰዎች በችግር ሲቆሉ ሳይ ነው፤ የምንችል ሰዎች በወር አንድ ብር ብናዋጣ ብዙ ሰዎችን መርዳት እንችል ነበር፡፡ በቤት ኪራይ በኩል ያለውን ሙስና ሲያስቡት ያንገሸግሻል! ቤታቸውን በብዙ መቶ ሺዎች ብር እያከራዩ፣ በመንግሥት ዝቅተኛ ኪራይ የሚከፍሉና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቆመናል የሚሉ ሞልተዋል፤ አይከነክናቸውም፤ ስንቱ ዳያስፖራ በብዙ ሺህ ብር እያከራየ፣ እዚያ ደግሞ እንደ ደሀ በምጽዋት ይኖራል፤ የባሰም አለ፤ ሌላ ቀርቶ የኢጣልያን ባንዳዎችም እንደምንረዳ አውቃለሁ፤ የቱ ባለሥልጣን ነው ይህንን የሙስና ምንጭ በሰይፍና በሕግ ሊያጠፋው የሚችል?
መስፍን ወልደ ማርያም ሚያዝያ 2012
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን
ችግር ሁልጊዜ አንዳንድ መልካም ነገሮችን ይዞ ይመጣል፤ የዘመኑ ወረርሺኝም በእኔ አስተያየት ሁለት ጥሩ ነገሮችን አስከትሏል፤ አንዱና ዋናው ከጃንሆይ በኋላ ተሽሮ የነበረው እግዚአብሔርን መልሶ በቦታው ማስቀመጡና በየመገኛዎች የእግዚአብሔርን ስም ማንሣት ተለመደ፤ ይህ ትልቅ ንቃት ነው፤እግዚአብሔር ሁሌም በመንበሩ ላይ ነው፤ አይነቃነቅም፤ ሁለተኛው የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ተረስታ ወደ ጓዳ ተደብቃ ነበር፤ ዛሬ ጉልበትዋ በሙሉ ባይሆንም ታየ፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዝናዋ አልተነገረም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያለበትን ውለታ ገና በትክክልና  በዝርዝር የሚናድረው አላገኘም፤ እንደተዳፈነ ነው፤ ቤተ ክርስቲያኒቱን ተደግፈው የሚወጡ ሁሉ በሥልጣኑ ጣዕምና ሙቀት እዚያው ቀልጠው ይቀራሉ፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ለአሥር እውነተኛ ተማሪዎች የሊቅነት ማዕርግ የሚያሰጣቸው ነው፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የትምህርት ሚኒስቴር ነበረች፤ የበጎ አድራጎት ሚኒስቴር ነበረች፤ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ነበረች፤ የባህልና የቅርስ ጥበቃ ሚኒስቴር ነበረች ... በዛሬው ጊዜ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተማሩ ሰዎች አላጣችም፤ በጥቁርና በነጭ ልብስ የተሽሞነሞኑ ዓለማውያን ናቸው፤ እንደ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ያለው እንኳን ደፍሮ ጉልበተኞችን መጋፈጥ አልቻሉም፡፡
መስፍን ወልደ ማርያም
ሚያዝያ 2012
ስለ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም
የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ ር ቴዎድሮስ አድሃኖምን በተመለከተ አንዳንድ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ደርሰውኛል። በኔ በኩል ታይፔ (ታይዋን ) ላይ ተቀስቅሶ አሜሪካ የተሻገረውን ተቃውሞ ከሕወሃት ወንጀል ለይተን እንመልከተው የሚል አቋም አለኝ። ባለኝ መረጃና ከባለሙያዎችም አስተያየት በመነሳት፣ ከኮረና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ሥልጣን እንዲለቁ የሚያስደርግ የዶ/ር ቴዎድሮስን ስህተት ማየት አልቻልኩም። ይህንንም ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ አፕሪል 7/2020 በኢሳት ዕለታዊ ፕሮግራም ላይ አንጸባርቂያለሁ። በነገራችን ላይ በውይይቱ ላይ የነበርነው አራታችንም ወንድማገኝ፣ ፋሲልና መሳይ ሁላችንም በዶ/ር ቴዎድሮስ ላይ የተነሳውን የአሜሪካውያኑንና የታይዋንን ተቃውሞ በተመለከተ ተመሳሳይ አቋም አንጸባርቀናል።
Sisay Agena Gole·
የአቶ ስዩም መስፍን “ምስጢር” እና አዲሶቹ የሕወሓት ኮርቻ ተሸካሚዎች!
ዓለማችን በአስጨናቂው የኮሮና ቫይረስ መፍትሄ አጥታ ግራ ተጋብታለች፣ በየዕለቱም የሺህዎችን ሞት እየሰማን እንገኛለን። አዳዲስ መቶ ሺዎችም በቀናት ልዩነት በቫይረሱ ሰለባ እየሆኑ ነው። ቁጥሩ ባይሰፋም ሞት ባይመዘገብም፣ ሃገራችንም በአሳሳቢው ወረርሺኝ መጨነቋ ዕውነት ነው። በደካማ ኢኮኖሚ ፡ በዝቅተኛ የጤና ሽፋንና የባለሙያ ዕጥረት ችግሩን እንዴት እንቋቋመው ይሆን በሚል በሃገርም በውጭም ያለው ኢትዮጵያዊ ግራ በተጋባበት ወቅት፣ በኮሮና ቫይረስ “ኮሮና” አጥልቀው ማለትም አክሊል ደፍተው እንደገና ሊሞሸሩብንና ግፍና ጉድፋቸውን ሊያድሱብን የሚዶልቱ የፖለቲካ ነጋዴች በመልዕክተኞቻቸው ያደረጉትን አይተናል።
አዎን! የሕወሃቶች መሪዎች ከታሪክ የማይማሩ፣ በሰረቁት የማያፍሩ፣ በመግደላቸውና በማሰቃየታቸው የማይጸጸቱ፣ ከነቆሻሻቸው ዛሬም ዙፋን የሚመኙ ነውረኞችና በቅዠት ዓለም የሚንከላወሱ ጉዶች ናቸው። በሁለት እግር መቆም ቸግሯቸው በክራንች ተደግፈውና ትንፋሽም አጥሯቸው፣ ቬንትሌተር ተገጥሞላቸው እያየናቸው፣ ዛሬም እንደያኔው መንገድ መሪዎችን ከየብሄሩ እየመለመሉ የሚያሸክሙትን ነውረኛ ተልዕኮ እያየን እንገኛለን። ለመንገድ መሪነት ወይንም ኮርቻ ተሸካሚነት ከመረጧቸው አገልጋዮች አንዱ በፈጸመው ድርጊት መታሰሩን ተከትሎ፣ ከሕወሃት ሰፈር የተሰማው ጫጫታ መልዕክቱን ይበልጥ ግልጽ አድርጎታል።
ለብዙዎች ያልገባቸው ነገር ግን በደንብ ሲጤን፣ ብዙም የማይገርመው የአማራ ሕዝብ መብት ተሟጋች ነን የሚሉ አንዳንድ ግለሰቦች፣ ለሕወሃቱ መልዕክተኛ ያሰሙት ጩኸት ነው። አማሮች ሲገደሉና ሲፈናቀሉ የሕወሃት አገልጋይ የንበረ፥ ዛሬም ከጸጸት ይልቅ ለዚያው ጨቋኝና ዘረኛ ቡድን ጉዳይ ፈጻሚ ሆኖ ለቀጠለ ግለሰብ፣ የአማራ ብሄር መብት ተሟጋች ነን የሚሉ ጠበቃ ሆነውለት ስናያቸው፣ እነ አቶ በረከት ስምኦን ወደ ወህኒ ከመጋዛቸው በፊት ለሕወሃት አዳዲስ ብዙ መንገድ መሪዎችን ማዘጋጀታቸውን እንድንጠራጠር ያደርገናል። በመሆኑም በጫጫታው ከመገረም ይልቅ ከምር የመብት ጥያቄ ያነሱ ወገኖች፣ ዙሪያቸው ያሉትን እንዲያውቁና እየሆነ ያለውን ቆም ብለው እንዲመረምሩም ዕድል የሚሰጥ ይመስለኛል።
በቅንነትና በአካባቢ ስሜት ግለሰቡን የሚደግፉ ካሉም፣ ከአካባቢያቸው እንዲህ ያሉ ነውረኞችን መጠየፍ እንጂ ማቀፍ መከራን እንደሚጠራና የመከራ ጊዜን እንደሚያረዝምም ማስተዋል ያስፈልጋል።
በተለይ ወጣቶቹ አሁን ከሚነገረው ተረት ይልቅ በተጨባጭ ያለፋችሁበትን ትናንትንና የዛሬን ዕውነት መርምሩ። አሁንም በአክቲቪዝም፥በሚዲያና በፖለቲካ ፓርቲ ተደራጅተው፣ በየራሳቸው ግላዊና ቡድናዊ ፍላጎት አብዝተው ከሚጮሁት ውስጥ የትኞቹ የሕወሃት ፈረሶችና ኮርቻ ተሸካሚዎች እንደሆኑም  ለመለየት መሞከሩ ይጠቅማል። በሕወሃት የአገዛዝ ዘመን የሸሸው የሃገር ሃብት (በብሩኪንግ ኢንስቲቲዩት ጥናት፤ ከ80 ቢሊዮን ዶላር በላይ)፤ ዛሬ ሃገር ለማመሱ ተግባር በከፊልም ቢሆን ሥራ ላይ መዋሉን እያየን ነው።
እዚህ ላይ በደማቁ ላሰምርበት የምፈልገው የትናንት ቆሻሻ ድርጊት፣ በሕውሃት መልዕክተኞችም ላይ ቢሆን ዛሬ ሲደገም ማየት አልፈልግም ብቻ ሳይሆን ለሕግ የበላይነት ትግሌን እቀጥላለሁ። ግለሰቡ ሕዝብ ላይ ሽብር ለመንዛት የተነሳበት ዓላማና ቅንጅቱ እንዲሁም ውጤቱ ላይ መሰረት ያደረገ ምርመራ እንጂ ከሕወሃት ጋር ያለው ግንኙነት በራሱ ወንጀል ሆኖ ሊቀርብ አይገባም።
በዚሁ አጋጣሚ የግለሰቡን መታሰር ከአቶ ስዩም መስፍን ቃለ ምልልስ ጋር ለማያያዝ፣ የሕወሃት ሰዎች ያደረጉት ጥረት፥ የአቶ ስዩምን ቃለ ምልልስ ያላዩ እንዲመለከቱት ዕድል ቢሰጥም፣ ማሰብ ለሚችልና ለሚጠይቅ ሰው ግለሰቡን ለመታሰር የሚያበቃው፣ መንግስትንም የሚያበሳጨው ጉዳይ በአቶ ስዩም ቃለ ምልልስ ውስጥ ላገኝ አልቻልኩም።
አንዳንዶች በአቅም ማነስ ሌሎች ደግሞ ሆን ብለው ከአቶ ስዩም መስፍን ቃለ ምልልስ እንደ ትልቅ ምስጢር የሚጠቅሷቸውን ሁለት ነጥቦች እንመልከት። አንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ለግብጾች አባይ የጋራችን ነው በማለት ቃል ገብተዋል የሚል ሲሆን፥ ሁለተኛው የኢንጂነር ስመኘው ግድያ፣ በግብጾች ፍላጎት የተፈጸም እንዲመስል አቶ ሥዩም ዙሪያ ጥምጥም ያደረጉት ጉዞ ነው።
የሕወሃት ምክትል ሊቀ መንበርና 21 ዓመት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዩም መስፍን፤ ከግብጽ ዲፕሎማቶች ሰማሁ ብለው ዶ/ር ዐቢይን ለመወንጀል፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናገሩ ያሉትን ቃል በቃል ልጥቀስ።
“ኢትዮጵያ አባይን ከእግዚአብሄር የተረከበችው በሁላችንም ስም ለማስተዳደር ነው። በናንተ ላይ ጫና የሚፈጥር ሥራ አንሰራም።”
አቶ ስዩም መስፍን እንደ ትልቅ ወንጀል፣ እንደ ሃገር ክህደት ያስቀመጡት ዶ/ር ዐቢይ አህመድ “አባይ” የሁላችንም የጋራ ሃብት ነው ብለው ለግብጾች ተናግረዋል የሚል ነው። ግብጾች እንዲሁም ሱዳኖች ስለ አባይ የማያገባቸው ከሆነ እና ሁሉ ነገር በኢትዮጵያ መልካም ፈቃድ ላይ ከተመሰረተ በሕወሃት የአገዛዝ ዘመን፣ እነ አቶ ስዩም መስፍን ከግብጾች ጋር ይደራደሩ የነበረው ታዲያ ለምን ነበር? የአረብ ሊግ አባል ስለመሆን ወይንስ ስለ ሌላ ?
የአቶ ስዩም “ምስጢር” ከንቱና  ርሳቸውን ከታዘብናቸው በላይ ይበልጥ እንድንታዘባቸው የሚያደርግ ቢሆንም፥ በአቅም ማነስና የራሳቸው ሰዎች ካልነገሯቸው ለማይገባቸው ደግሞ አቶ መለስ ዜናዊ ስለ አባይ ግድብ ከመሞታቸው አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃለ ምልልስ የተናገሩትን ልጥቀስ። (በነገራችን ላይ የአቶ መለስን ቪዲዮ ሃሙስ March 26/2020 ኢሳት ዕለታዊ ፕሮግራም ላይ ተጠቅመንበታል)
አቶ መለስ ስለ አባይ ቃል በቃል እንዲህ ነበር ያሉት፡-
“አባይ የኢትዮጵያ ብቻ ፥የኡጋንዳ ብቻ ወይንም የግብጽ እና የሱዳን ብቻ አይደለም። በአባይ ተፋሰስ ሃገራት ያለነው የሁላችንም ሃብት ነው”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩት በተባለውና በአቶ መለስ ንግግር መካከል ያለው ልዩነት ካይሮና አዲስ አበባ ከመነገሩ ውጭ ህሊናው ለአቅመ አዳምና ሄዋን ለደረሰ አንድነቱ ግልጽ ነው።
አቶ ስዩም መስፍን የኢንጂነር ስመኘውን ግድያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የካይሮ ጉዞ ጋር ለማገናኘት ያደሩጉትን ጥረት መልሰው ሲያዳምጡት ካላፈሩበት፣ ተጨማሪ ተረት ተረት እንጠብቃለን።
ኢንጂነር ስመኘው እንዲገደሉ ግብጽ የምትፈልግበት ምክንያት ቢኖር እንኳን፣ ከግድቡ ሥራ ገለል እንዲሉ መሆኑ ግልጽ ነው። ለዚህ ተባባሪ ሆነው የሚጠቀሱት ዶ/ር አብይ አህመድ ደግሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው። ስለዚህ ሞት በሌለበት ኢንጂነር ስመኘውን በደብዳቤ የማሰናበት ሙሉ ስልጣን እያላቸው ግድያን ምን አመጣው? የኢትዮጵያን የደህንነት ተቋምና የመከላከያ መዋቅር በዘረኛ አገዛዝ ጠፍረው በፍጹም ፈላጭ ቆራጭነት ሲመሩ የነበሩትን የሥርዓቱና የሥልጣኑ ባለቤቶችን ጄኔራል ሳሞራ የኑስ እና አቶ ጌታቸው አሰፋን በሁለት መስመር ደብዳቤ ለሸኘ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ኢንጂነር ስመኘውን ማንሳት እጅግ ቀላሉ ርምጃ መሆኑ ግልጽ ነው።
ይልቁንም ከአቶ ስዩም መስፍን ቃለ ምልልስ እንደተረዳነውና ከሌሎች ምንጮችም እንደሰማነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዳሴው ግድብ የገንዘብ ብክነት ጋር በተያያዘ ኢንጂነር ስመኘውን አነጋግረዋል። አቶ ስዩም ባይነግሩንም ከሌሎች እንደተገነዘብነው ደግሞ የዘረፋው መሪዎችና ዘራፊዎች ሜቴክ ውስጥ ያሉ የሕወሃት ጄኔራሎችና ተባባሪዎቻቸው ናቸው።
ይህ ከሆነ ዘንዳ ምስጢሩ እንዲከደንና መረጃ እንዲጠፋ ኢንጂነር ስመኘው ላይ ማን ሊያነጣጥር እንደሚችልም መጠርጠር ይቻላል። ... አሳ ጎርጓሪ ... አይደል የሚለው ተረቱ! በመጨረሻም ለአቶ ስዩም መልዕክቴ፤ ብሄርተኛ የሰፈሩ ተሟጋች እንጂ የሃገራዊ ሉዓላዊነት ጠበቃ እንደማይሆን ከሕወሃት የ27 ዓመት  አገዛዝ በላይ አስረጂ የለምና፣ የከሰረውን የፖለቲካ ሸቀጣችሁን መልሳችሁ ደደቢት ላይ አራግፉት። አትጨቅጭቁን!
Sisay Agena Gole
ሰውም እንደ ሣር!
ሳር እንዲያድግ ንጥረ ነገር ይፈልጋል። ሰው እንዲያድግ ምግብ ይፈልጋል። ሳር እንዲያድግ ዉሃ ይፈልጋል። ሰው እንዲያድግ እውቀት ይፈልጋል። ሳር እንዲያብብ የፀሐይ ብርሃን ይፈልጋል። ሰው እንዲያብብ ነፃነት ይፈልጋል። ሳር እንዲያድግ መረገጥ የለበትም። ሰው እንዲያድግ መረገጥ (መጨቆን) የለበትም። ሳር እንዲያድግ፣ እንዲያብብና ፍሬ እንዲሰጥ ንጥረ ነገር፣ ዉሃ፣ የፀሐይ ብርሃንና እንክብካቤ ይፈልጋል። ሰው አድጎ፣ ኣብቦ ፍሬ እንዲያፈራ ምግብ፣ እውቀት፣ ነፃነትና ክብር ይፈልጋል። ሳር ያለ ፀሐይ ብርሃን ፍሬ አይሰጥም። ሰውም ያለ ነፃነት ራሱን መግለፅ አይችልም። ሳሩ ሰው ነው።ማዕድኑ ምግብ ነው። ዉሃው እውቀት ነው። የፀሓይ ብርሃኑ ነፃነት ነው። ያለ መረገጡ ያለ መጨቆን ነው። ሰውን ነፃ ለማውጣት የእውቀት ዉሃን እንረጫለን። It is so!!!
Abraha Desta April 12 ·
እንደ ሀገር ቆም ብለን ማሰብ--
አንዱ ቢሳሳትና ሌላው ትክክል ቢሆን የተሳሳተውን በመተቸት ትክክለኛውን ታበረታታለህ። ሁለቱም ትክክል ከሆኑ ሁለቱንም ታወድስና ትክክለኝነትን ታሰፍናለህ። ሁለቱም ስህተት ከሆኑና አንዱን መርጠህ ከተቸህ ሌላኛውን የበለጠ እንዲሳሳት ታደርጋለህ።
ጎርፍ (እንደ ስህተት ቢመሰል) በአንድ ወይ ሁለት ወይ የተወሰነ አቅጣጫ ቢፈስ ትገድበዋለህ (በመምከር ወይ በመተቸት)። በሁሉም አቅጣጫ የሚፈስ ጎርፍ ይገደባል እንዴ? ባንዱ ወገን ብትገድበው በሌላ በኩል ይፈሳል፤ አቅጣጫ መቀየር ነው የሚሆነው። እንዲያውም በአንድ በኩል ስትገድበው በሌላ በኩል ለሚፈሰው ጎርፍ ጉልበት ትሰጠዋለህ።
ሁሉም በተሳሳተበት ወቅት አንድን ከሌላ አብልጦ መተቸት፣ ሌላውን የበለጠ እንዲሳሳት ዕድል ከመስጠት ያለፈ ትርጉም የለውም። እንደ ሀገር ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል!
Abraha Desta March 10 ·
በበረሐ ላይ የተገኘ ምንጭ
በዚህ ፈታኝ ሰዓት በቤታችን ሆነን ሕማማትን እያሳለፍን ነው። ባላገሩ ቴሌቭዥን ቅድሚያውን ወስዶ ሥርዓተ ሰሙነ ሕማማትን በቀጥታ ለማስተላለፍ መነሣቱ የሚያስመሰግነው ነው። ሰሙነ ሕማማት ለክርስቲያኖች የፍሬ ወቅት ነው። አብርሃም ወልዴና የባላገሩ ቲቪ አመራሮች፣ ይሄንን ሰሞን በቀጥታ ቴሌቪዥን ለማስተላለፍ በመወሰናችሁ፣ ‘’የሰማ ያሰማ’’ የሚለው ቃል ኪዳን ይድረሳችሁ።
Daniel KibretApril 13
ዕውቀት ሲሽኮረመም አላዋቂነት--
የአንዳንድ ሰው ጅልነት፣ የጅልነትን ልክ ያለፈ ነው። ኦርቶዶክስ ሳይሆን ርትዕት ነው ትክክል የሚል የጨዋ ሙግት ምንድን ነው? አንዱ ግእዝ፣ አንዱ ግሪክ ነው። ምሥጢር የአካድ፣ ቁርባን የሱርስት፣ ቄስ የግሪክ፣ ሆሳዕና የዕብራይስጥ፣ አቡሻሕር የዐረብ ቃላት ናቸው። ምን አዲስ ነገር ተገኝቶ ነው?
ቤተ ክርስቲያን ከዓለም ስትነጋገር የኖረች ናት። የግእዝን ቃላት በዐረብኛና በአርሜንያ ውስጥ ታገኛቸዋለህ። ልጆቿና መጻሕፍቷ ሲሄዱና ሲመጡ የኖሩ መሆናቸውን የማያውቅ እንግዳ ልጅ፣ ኦርቶዶክስነት ጥያቄው ቢሆን አይገርምም። መለስ ብለህ መጻሕፎችህን አንብብ። ከ12ኛው መክዘ ጀምሮ በግእዝ ድርሰቶች ውስጥ ኦርቶዶክስ የሚለውን ቃል ታገኘዋለህ። ዕውቀት ሲሽኮረመም አላዋቂነት ዕውቀት ይሆናል ።
Daniel Kibret

Read 2733 times