Sunday, 19 April 2020 00:00

መሪውን መንግሥት ይጨብጥ!

Written by  በተስፋዬ ድረሴ
Rate this item
(1 Vote)

     “እደግመዋለሁ፤ መሪውን መንግሥት ይጨብጥ፡፡ አገርን ሊያወድም የሚችል፣ ጠላት ብቻ ሊለው የሚገባ፣ ክንድ አዝል አስተሳሰብና ንግግራቸውን ይተው፡፡ ጎበዝ፤ እንጠንቀቅ እንጂ አንርበትበት! ኢትዮጵያ በኮሮና ማግስት እንደ ጽጌረዳ የምትፈካ አገር ናት፡፡ ተጠንቅቀን ዛሬን እንለፍ፡፡”
             
            እናንተ፡- እነዚህ፣ ለኮሮና ቫይረስ “መፍትሔው ፀሎት ወይም ዱዓ ብቻ ነው፤ ሌላው ነገር ሁሉ ከንቱ ነው” የሚሉ ሰዎች የአገራችን ጠላቶች ስውር መልዕክተኞች ይሆኑ እንዴ! ጠረጠርኩ፡፡ ወረርሽኝን መከላከያ ሀይማኖታዊ ወይም መንፈሳዊ መፍትሔዎች፣ ከሰውአዊ መፍትሔዎች ጋር አብረው አይሄዱም ያለው ማነው - ያውም በእኛ አገር? ይሄዳሉ እንጂ! ጎበዝ - ጥብቅ፣ ክርር አናድርግ! እና፣ በየዋህነት ይህን ሰውን የሚያስጨርስ፣ አገርን ባዶ የሚያስቀር አስተሳሰብ የምታራምዱ ሰዎች ንቁ - እባካችሁ፡፡ እወቁልኝ ደሞ፤ አውቄ ነው “ሰውአዊ” ያልኩት፤ “ሳይንሳዊ” በማለት ውዝግብ ውስጥ ላለመግባት ብዬ፡፡
ሰሞኑን እንዲህ ሆነላችሁ፡- አንድ በሙያው ትልቅ ደረጃ ላይ ያለ ምሁር፤ በጨዋታችን መሃል፤ “ይሔ ኮሮና የፈጣሪ ቁጣ ነው፡፡ እንኳን እኛ ስንትና ስንት ባለሙያና ሀብት ያላት አሜሪካም ልትቋቋመው አልቻለችም:: የሚያዋጣው ዝም ብሎ ፈጣሪን መለመን ብቻ ነው” አለኝ፡፡ ምን ልበላችሁ? ብልጭ አለብኝ - ማለቴ፣ አንድ ድንቅ ሀሳብ፡፡ እና አልኩት፡- “ይሔ የሀይማኖተኛ ሳይሆን የጠላት ወሬ ነው፡፡” ቀጠልኩ፡- “ልንገርህ አይደል? ይኼ የለየለት የአገር ክዳት ደባ ነው:: እኔ የኢትዮጵያ ጠላት (አገር/ዜጋ - ለምሳሌ እንትናዊ) ብሆን፣ የማደርገው ልክ አንተ እንዲህ እንደሞከርከው ነው፡፡ ያለ የሌለ አቅሜን ተጠቅሜ ጣፋጭ ቃል፣ ሀረግ፣ ዐረፍተ ነገርና አንቀጾችን እየደረደርኩ፤ ‘...አትድከሙ፤ ያለው ብቸኛ አማራጭ ፀሎት/ዱዓ ነው፤ እንደ ልባችሁ ተቃቀፉ፣ ተሳሳሙ ... ከገበያ፣ ከቤተ ክርስቲያንም ሆነ ከመስጊድ አትቅሩ...’ እያልኩ ልበ መሉ መንፈሳዊ መስዬ በመስበክ ህዝቡን አስፈጀው ነበር፡፡”  ወዲያው፣ ሰውየውን የአገሬ ጠላት ያሰማራው ሰላይ፣ ባንዳ ነገር ይሆናል ብዬ ማሰቤን ረስቼ፣ እንደ ቅን ዜጋ ወቀስኩት፤ እንዲህ ብዬ፡- “ምነው ጃል፣  ሌላ ቢቀር ሌት ተቀን የሚደክሙት ጀግና የመንግሥት ባለስልጣናት (ሀላፊዎች/መሪዎቻችን)፣ እሳት ላይ ተጥደው የሚውሉና የሚያድሩ የህክምና ባለሙያዎቻችን፣ በየመንገዱ ወገባቸው እስኪጎብጥ ድረስ ቆመው እጅ ሲያስታጥቡ የሚውሉ ወጣቶች አያሳዝኑህም?” “መፍትሔው ሀይማኖታዊ ብቻ ከሆነ፣ እነዚህ አካላት ተሳስተዋል ማለት ነው?” ብዬ እየሞገትኩት፡፡ አሁን እየፃፍኩ ያለሁት ራሱ እሱን እያሰብኩ መሰለኝ፡፡
ኡ! ወግ ይዞኝ ጠፋሁ፤ ይቅርታ:: ከወዲሁ ልንገራችሁና፣ የጽሁፌ አንኳር መልዕክት “ኮሮናን በሚመለከት የምንስማማባቸው ምላሾች ላይ አትኩረን፣ ልዩነቶችን አጥብበን፣ ትግሉን በድል ለማጠናቀቅ እንጣር” የሚል ነው፡፡ ምላሾችን ሁለት ቦታ ብቻ ከከፈልን፤ አንደኛው፣ መንግሥታዊ፤ ማለትም ሀይማኖት ላይ ያልተመሰረተ (secular) ምላሽ ሲሆን፤ ሁለተኛው፣ ሀይማኖታዊ/መንፈሳዊ ምላሽ ወይም የሀይማኖት ተቋማት ምላሽ ነው፡፡ መንግሥታዊ ምላሽ በመሰረቱ ሰውዓዊ የሆኑ የምክንያትና ውጤት አረዳዶች ላይ የተመረኮዙ ተጨባጭ የመፍትሄ እርምጃዎችን ነው የሚከተለው፡፡ ያም ቢሆን፣ ምላሹ በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ማናቸውንም ተቋማት፣ የሀይማኖት ተቋማትንም ጨምሮ፤ ማስተባበርንና ቫይረሱን ለመዋጋት ማሰለፍን ይጨምራል፡፡ የሀይማኖት ተቋማት ምላሽም የመንግሥትን ድጋፍ ከማስተባበር የሚያግደው ነገር የለም:: እስከ ዛሬ እየታየ ያለውም ይኸው ነው፡፡
የሁለቱ አካላት ጥምረት፣ በጥሩ መናበብ እስከተካሄደ ድረስ፣ የጠላትን ጦር ከታች በእግረኛ ሰራዊት፣ ከላይ በአየር ሀይል እንደ መደብደብ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ሂደቱ የሚጠይቀው የሁለቱን ወገኖች ብልህ (smart) መሆን ብቻ ነው፡፡ ይሁንና፤ በዚህ ሂደት መሀል በሰዎች ዘንድ የግንዛቤ ብዥታዎችና የሚና ግጭቶች ሊታዩ ይችላሉ፤ ታይተዋልም:: የብዥታው ሚስጢር እነሆ፡- በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ፣ መንግሥት ሀይማኖት ላይ ላልተመሰረተ ምላሹ መልምሎ ያሰማራቸው ተቋማት ሰራተኞች፤ እንደ ግለሰብ ሀይማኖታዊውን ምላሽ (ብቻ) የሚያምኑበት ቢሆን እንኳ ቢያንስ፣ ቢያንስ በመንግሥት የስራ ሰዓት (የመንግሥት ወንበር ላይ እስከተቀመጡ ድረስ) መታዘዝ ያለባቸው መንግሥታዊውን የመከላከል ስትራቴጂ ነው፡፡ ደሞዝ በሚበሉበት ሰዓት ስለ እጅ መታጠብ እንጂ ስለ  ሌሎች ሀይማኖታዊ ምላሾች  በማስተማር መጠመድ የለባቸውም - እንደ ማለት ነው፡፡ ይህን ካደረጉ መንግስታዊ ምላሾች ሊዳከሙ ይችላሉ። ዜጎች በግል ሰዓታቸው የሚያምኑበትን ማድረግ ይችላሉ:: ሀይማኖተኛነታቸው መንግሥታዊውን ምላሽ ከማሳለጥ አያግዳቸውም፡፡ “አገር የጋራ፣ ሀይማኖት የግል ...” የሚለው አባባል ሁሌም የተከበረ ነው፡፡
እንዲህ እንዲያ እያልኩ በሰውኣዊና በሀይማኖታዊ ወይም መንፈሳዊ አካሄዶች መካከል ያሉ ልዩነቶችና አንድነቶችን ሀይለ ቃል ሳይወጣኝ፣ “ፈራጅ” ሳልሆን እነካካላችኋለሁ፡፡  ጽሁፌ ብዙ ብዥታዎችን ያጠራል ብዬ አምናለሁ፡፡  አያምልጣችሁ!
በጣም ጥሩው ዜና፣ በአሁኑ ሰዓት፣ መረጃው የደረሰው አእምሮው ጤነኛ የሆነ ዜጋ፣ ኮሮና ቫይረስ በመጨባበጥ፣ በማስነጠስ፣ በሳል ወዘተ-- አይተላለፍም ብሎ አያምንም፡፡ ለዚህም ነው፤ እንደ  መንግሥታዊ ተቋማት ሁሉ የሀይማኖት ተቋማትም፣ ከቤት መዋልንና መቀራረብን መቀነስን በመፍትሔነት ተስማምተውባቸው እየተገበሯቸው የሚገኙት፡፡ ይህ መልካም ጅምር ነው - በአይነቱ ልዩ፡፡
አሁን ደግሞ የሀይማኖት ተቋማት በፊናቸው የሚያራምዷቸውን እምነቶች ወደ ዜጎች ምላሾች  ወረድ አድርገን እንቃኝ::
እንዲህ ነው ነገሩ፡- ሀይማኖተኛ ሰዎች በሽታው የሚመጣው በቫይረስ መሆኑን ያምናሉ:: እጅን በሳሙና እንደመታጠብ ያሉ የመከላከያ እርምጃዎች የሚሰሩ መሆናቸውን ይቀበላሉ:: ነገር ግን፣ ኮሮና ቫይረስ ተራ በሽታ አምጪ ህዋስ ነው ብለው አይቀበሉም፡፡ በምትኩ፣  በሽታው ፈጣሪ (እግዚአብሔር ወይም አላህ) ሰዎችን ለማስተማር ሲል ከላይ ያወረደው የቅጣት “በትር” ለመሆኑ ነው እውቅና የሚሰጡት::  ሰዎችን ለቅጣት ያበቃቸውም ገደብ አጥቶ የነበረ፣ ግድብ ጥሶ የፈሰሰ የሀጢዓታቸው ብዛት ነው፡፡ ስለሆነም፣ ከዚህ ቅጣት ለመዳን የሚቻለው የፈጣሪን ይቅርታና ምህረት በመጠየቅ (በመጸለይ/ዱዓ በማድረግ)፣ በተግባርም ፈጣሪ የሚወዳቸውን ተግባሮች በመፈፀምና መልካም ባህሪዎችን በማሳየት (ም) ነው፡፡ ማለት፣ የታወቁት የጥንቃቄ እርምጃዎች ብቻቸውን መፍትሔ አይሆኑም፡፡
ታዲያ ይሄ ምን ያጣላል? ምንም! ዋናው ከኮረና ወረርሽኝ መትረፍ እስከሆነ ድረስ ሰዋዓዊ መከላከያዎች ላይ ፀሎት/ዱአ ቢጨመርበት ጉዳት የለውም::  “ቢጨመር” ያልኩት ሀይማኖታዊ ምላሽ በሌሎች አገሮች ከታየው በላይ (በልዩ መልኩ) ኢትዮጵያችን ውስጥ እየተተገበረ ስላለ ነው:: እዚህ ላይ “ወፍ እንዳገሯ ትጮኻለችን’’ በድጋሚ እናስታውሳለን!
እርግጥ ነው፤ አተገባበር ላይ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ አሁኑም የታዩ አሉ:: መንግሥታዊም ሆነ ሀይማኖታዊ ተቋማት፤ እንዲሁም ሌሎች አካላት፤ የተስማሙባቸውን የእውቀት ትጥቆች የሚያስጥሉ ሀሳቦችና ባህሪዎች የሚከሰቱባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች የሚከተሏቸው ሀይማኖቶች፤ ከሚያራምዷቸው አስተሳሰቦችና አስተምህሮቶች ጋር በሚጋጭ መልኩ “አልታዘዝም” ባይ፣ አፈንጋጭ ሆነው ይፋ ይወጣሉ:: በራሳቸው ሰዓት ልዩ የመረጃ ምንጭ ይሆናሉ::   ከአዛዡ እውቅና ውጪ ጀብድ ለመፈፀም እንደሚተጋ የሰራዊት አባል፣ ብቻቸውን አዋጭ ነው ያሉትን እርምጃዎች በድፍረት ይወስዳሉ፡፡  በዚህም ሰበብ፣ ከፖሊስና መሰል አካላት ጋር ግብ ግብ ይገጥማሉ፡፡  
የዚህ አይነት ሰዎች በራሳቸው መንገድ የሚያደርጉትን ጥረት እንዲቀጥሉ ለምን አይተውም? ተብሎ ሊጠየቅ ይችል ይሆናል:: እእ! ችግሩ፣ ሰዎቹ ምናልባት፣ በመጥፎ አጋጣሚ፣ ለቫይረሱ ቢጋለጡ፣ እነሱም ሆኑ በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ይጎዳሉ፡፡ ሲጀመር፣ ኮረናን በሚመለከት በግል ሪስክ (ውጤቱ በውል ያልታወቀ እርምጃ) ለመውሰድ መሞከር ትክክል አይደለም - የአንድ ሰው ስህተት የሌሎችን ድካም በዜሮ ያጣፋልና፡፡ በሽታው፤ አለ አይደል?  እንደ የደም ግፊት፣  እንደ የልብ ህመም፣ እንደ ሪህ፣ እንደ የሆድ ድርቀት የአንድ ሰው ብቻ ጣጣ ቢሆን ኖሮ፣ አልመከር ያለ ሰው “የራስህ ጉዳይ” ተብሎ ሊተው ይችል ነበር - ማንም የራሱ ብቻ ያለመሆኑ ሳይረሳ! ኮሮና ተላላፊ  - በዚያ ላይ “አስታማሚ-ከቤት” የማይገኝለት መዘዘ ብዙ፡፡
ወደ ምክረ ሀሳቡ ስንደረደር፡- ኮሮናን በሚመለከት የሚካሄደውን ጦርነት፣ ሀይማኖተኞችም ሆኑ ሀይማኖት የሌላቸው ሰዎች፣ እንዲሁም ሁለቱንም በአንድነትና በእኩልነት የሚያስተዳድረው መንግሥት ይምራው፡፡ ሁለቱ አካላት በጋራ የሚስማሙባቸው የመፍትሔ እርምጃዎች ላይ ያትኩሩ፡፡ የሀይማኖት ተቋማት እንቅስቃሴ የመንግሥት ምላሽ የሚያሳልጥ ይሁን፡፡ ሁሉም የእምነት ተቋማት ተከታዮቻቸውን ስለ ቫይረሱ መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች ያስተምሩ፤ ከየቅዱስ መጽሀፎቻቸውና ሌሎች ምንጮች በመጥቀስ የመጠንቀቅን አስፈላጊነት ይስበኩ፡፡ ምክሮቻቸውንም ሆነ የመንግሥትን ትዕዛዝ አንከተለም የሚሉ እምቢ ባዮችን ይገስፁ፣ ያውግዙ::  ሰውዓዊ መከላከያን ሳያዛንፉ፣ በልዩ ጥንቃቄ፣ መተግበር ኢ-ሀይማኖታዊ መሆን የሚመስላቸው ወገኖች ካሉም፣ አስተሳሰባቸውን በትምህርት ያቃኑላቸው፡፡ በተረፈ፣ የየራሳቸውን እምነት ያስኪዱ::
ምን ቀረ? በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ምሁራን (መምህራን፣ ጋዜጠኞች፣ ሙዚቃኞች ወዘተ) ሕዝቡ “እችላለሁ” የሚል ስሜት እንዲያድርበት ያበረታቱት፡፡ ከመንግሥት ጋር ሲተባበሩ ድርሰቶቻቸው ሰውአዊ ምላሾችን የሚያግዙ ይሁኑ:: ግለሰቦች በሶሻል ሚዲያዎች ላይ በቁጥር (በዜና/መርዶ) ናዳ የህዝቡን ስነልቡና አያዳክሙት! ራሳቸው ተብረክርከው ህዝቡን ሊያብረከርኩ የሚችሉ መረጃዎችን (ትንተናዎችን) ከማሰራጨት ይቆጠቡ:: ደሞ፣ ደሞ - “መድሀኒት የሌለው በሽታ” ማለታቸውን ይተው፡፡ መድሃኒት ያልተገኘለት ቢሉ ነው የሚሻለው:: ተስቦም’ኮ በአንድ ወቅት መድኃኒት የሌለው በሽታ ተብሎ ነበር፡፡ የህክምናን ባለሙያዎች ወደ ፊት ረድፍ እንዲመጡ መንገድ ይልቀቁላቸው፡፡  ሀይማኖታዊ ትንተናን ለሀይማኖት አባቶች፣ ... ወዘተ በመተውና በመተባበር  በተቻላቸው መጠን ራሳቸውንና ወገናቸውን ከወረርሽኙ ለማትረፍ ይጣሩ፡፡ እደግመዋለሁ፤ መሪውን መንግሥት ይጨብጥ፡፡ በጀመርኩት ልጨርስና፣ አገርን ሊያወድም የሚችል፣ ጠላት ብቻ ሊለው የሚገባ፣ ክንድ አዝል አስተሳሰብና ንግግራቸውን ይተው፡፡  ጎበዝ፤  እንጠንቀቅ እንጂ አንርበትበት! ኢትዮጵያ በኮሮና ማግስት እንደ ጽጌረዳ የምትፈካ አገር ናት፡፡ ተጠንቅቀን ዛሬን እንለፍ፡፡

Read 2035 times