Saturday, 18 April 2020 15:10

በዓልን በብልህነትና በጥንቃቄ

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

"ደግሞላችሁ…ለጥሬ ሥጋ ወዳጆችም ሲባል የነበረውን ነገሬ ብሎ መመርመሩ ግድ ይላል፡፡ የጥሬ ሥጋ አምሮት የፈለገ እንቅልፍ ይንሳ፣ የፈለገ ሆድን ባር፣ ባር ያሰኝ…አለ አይደል… “እንዲህ ቢሆን እንዲህ ማድረግ ይቻላል፤” እየተባለ “ፕላን ቢ” ምናምን የሚመዘገብበት ጊዜ አይደለም፡፡ “ፕላን ቢ” ብሎ ነገር የለም፡፡"
      

እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤው አደረሳችሁ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…የኮንዶሚኒየም ኑሮ የበዓል ሰሞን ጭቅጭቅን ቀነሰው ወይስ እንዴት ነው ነገሩ!
አሁን አሁን በር አልፈው ጐረቤት ድረስ የሚሰሙ “የበዓል በጀት” ንትርኮች ስለማንሰማ ነው፡፡ የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይሄ የዋዜማ ሰሞን ጭቅጭቅ እኮ…አለ አይደል…ለበዓል የሆነ “ቴስት” ነገር ይሰጠው ነበር፡፡ ልክ ነዋ…
“እኔ እንኳን ልቀርበው እንደሱ የሚያስጠላኝ ሰው የለም!”
“እሷ እኮ ከወጪ ቀሪ በስህተት ከአስራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን ወደዚህ የተሸጋገረች ነች፡፡ እሷን ሳሰለጥን ልኖር ነው!”
-ሲባባሉ ቆይተው ሲጣመሩ እኮ ነገርየው እውነተኛ የሮሚዮና ጁሊየት ግልባጭ ሊመስል ምንም አይቀረው! እናማ ምን ለማለት ነው፣ ድንገት የእኔ ቢጤውን…
“በዚህ ቁመቱ ከእሱ ጋር የምሆነው እቃ ከቁምሳጥን ላይ ሳወርድለት ልኖር ነው!” የምትል ከገጠመቻችሁ በቃ፣ “ፌክ ኒውስ” ነው፡፡
“ስሚ በጠዋት ፊትሽን እንቆቆ የጠጣ በሽተኛ ያስመሰልሽው ምን ልሁን ነው፣ ሰው በሰላም ከቤቱ ላይወጣ ነው!”
“አንተማ ምን አለብህ፣ እኔው ነኝ እንጂ የሰው መጠቋቆሚያ ሆኜ የቀረሁት!”
“አንቺ ሴትዮ፣ ምን ይሁን ነው የምትይው?” (አንቺ ሴትዮ! አንቺ ሴትዮ ነው ያላት! እንደዛ አፈር ምሶ፣ አፈር ልሶ ያገኛትንና “የዘላለሜ ነሽ”ን ሲዘፍንላት የኖረላትን ሚስቱን “አንቺ ሴትዮ” ማለት የጀመረ አባወራ…አለ አይደል…”ኢንቨስቲጌቭ ሪፖርቲንግ” ሊሠራበት ይገባል፡፡ የ “ቋንቋ” ለውጥ ዝም ብሎ አይመጣማ!
“ለገና እሺ መቼም ይሁን ምንም አይደለም ብዬ ዝም አልኩ፡፡ ፋሲካንም እንዲሁ ባዶ ቤት ልናሳልፍ ነው!”
“ምን ጐደለብሽና ነው?”
“ምን! (አሁን ድምጽም እየጨመረ ይሄዳል፣ ሊጨምርም ይገባዋል፡፡ እሱ በዓልን የሚመዝነው በጠጣው ቢራ ብዛት ነውና….ገና ለገና በዴሞክራሲ ስም የፈለገውን መናገር አይችልማ!
ቂ….ቂ…ቂ…) “ጭራሽ ምን ጐደለብሽ ትለኛለህ፤ እ ጌታው በየሰው ቤት ደጃፍ የታሰረው ሙክት ቀን ከሌት እየጮኸ--ጭራሽ ምን ጐደለብሽ! አሁንም በግ ሳይገዛ እንዲሁ የሌሎችን እየቀላወጥን በዓል ልናሳልፍ ነው!”
“ነግሬሻለሁ፣ አሁን ለበግ የማወጣው አምስት መቶና ስድስት መቶ ብር የለኝም፡፡ “(አዎ፣ በታሪክ ከሰሞናት አንድ ሰሞን፣ አምስትና ስድስት መቶ ብር የስፔይን ተዋጊ ኮርማዎችን የሚያካክል ሙክት መግዛት ይቻል ነበር፡፡ ለታሪካዊ መረጃ ያህል ነው፡፡ ልክ ነዋ…ደግሞ ነገ “ኢትዮጵያ በታሪኳ መቼ ነው በግ በአምስትና ስድስት መቶ ብር ተሽጦባት የሚያውቀው! ፊክሺን ነው፣ ይሄ ታሪክ እንደገና መጻፍ አለበት!” የሚል ቦተሊከኛ የተነሳ እንደሁ ለ “ሪፈረንስ” እንዲረዳ ያህል ነው፡፡)
“እኮ…ልጆቹ የጐረቤት በጐች ሲጮሁ እየሰሙ እንደጓጉ በዓልን ይዋሉ ማለት ነው!”
እናላችሁ…እንዲህ፣ እንዲህ እየተባለ ይቀጥላል፡፡ ለነገሩ ምን መሰላችሁ…እንዲህ አይነት ነገሮች እኮ አንዳንዴ ለበዓሉ ድምቀትም ያግዛሉ፡፡ ልክ ነዋ… “ሂሱን ውጦ” ሙክቱን እየነዳ የሚመጣ አባወራ ከፕሮግራም ውጪ የሚያቀርበው “የሽልማት” ጥያቄ ጥሩ ምላሽ ያገኛላ! ቅዳሜ ሌት ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ፍስኩ ዘርፈ ብዙ ሊሆን ይችላል ለማለት ያህል ነው፡፡
እናላችሁ…ስልጣኔ በዝቶብን ይሁን፣ ኪስ ሳስታ ሬድ ዞን ውስጥ ስለገባች ይሁን፣ የመለፋለፍ አቅም እያጣን ይሁን…ብቻ እንዲህ አይነት ንትርኮች ወይ ቀንሰዋል፤ ወይ ደግሞ የመነታረኪያ ዘዴ ተለውጦ ሊሆን ይችላል፡፡
“በግ ይዘህ የማትመጣ ከሆነ ለሚቀጥሉት ሰባት ወራት አጠገቤ ድርሽ አትልም፡፡” አራት ነጥብ፡፡ የ “እድሜ ይፍታህ፣” ብይን እንኳን የዚህን ያህል አያስደነግጥም፡፡
ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ…ይቺ የፋሲካ ቅዳሜ የስንቱን “ዓይን እንዳበራች” በአንደኛ መደብ ታሪክ የማጽፍልን ያስፈልጋል፡፡ አሀ…በአንድ ወቅት “የኑሮ ዘዴ” እንዲህ ነበራ! እድሜ ባይደርስም “ለአቅመ አዳም” የሚደረስበት፡፡ እንደ ዘንድሮ አስራዎቹን የጀመረ ልጅ አባቱ ላይ የሚያፈጥበት ጊዜ አልነበረማ! (ስሙኝማ…የምር ግን ማጋነን ይሁን፣ አይሁን እንጃ እንጂ በአስራዎቹ ያሉ ልጆች እንኳን ካሰኛቸው ወላጆቻቸውን የሚቆጡበት ዘመን ነው የሚባል ነገር አለ፡፡ ለነገሩ እንዲሁ በአለፍ አገደም የሆኑ ቦታዎች እግር ጣል አድርጐን ስናይ እንደ ልጅ የሚያደርጋቸው ወላጆችም አይተናል፡፡
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይቺ ፈረንካ በአካፋ የምትነሳበት ጊዜ አልፎ በቡልዶዘር የምትዛቅ ስትሆን አእምሮ ውስጥ ከጥቅም ውጪ የምታደርጋቸው ቡሉኖች አሉ እንዴ! ግራ ይገባላ! አስራዎቹን ለጀመሩ ልጆቻቸው ጥቅል አስር ሺህ ብር “የኪስ ገንዘብ” የሚሰጡ ወላጆች የበዙበት ዘመን ነው ይባላል፡፡ ጉርምስና እድሜ ላይ እንኳን ላልደረሱ ታዳጊዎች አስር ሺህ ብር የኪስ ገንዘብ! ጉድ እኮ ነው!
ልጄ መቶ ብር እንደሁ ቀልቧን አጥታለች! የምር እኮ የሆነ ኮሚክ ነገር ነው፡፡ በፊት እኮ መቶ ብር ይዞ የወጣ ሰው የሸመተውን በታክሲ አስጭኖ ይመጣ ነበር፡፡ (“ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ መቶ ብር መቼ ለአንድ ሰው ምሳ የሚበቃ ምግብ ተገዝቶበት የሚያውቀውን ነው!”.የሚል ቦተሊከኛ የተነሳ እንደሆነ ለታሪክ ማመሳከሪያ እንዲሆን ብለን ነው፡፡)
ስሙኝማ…እንዲህ እንደ ፋሲካ አይነት ትላልቅ በዓላት ሲመጡ…አለ አይደል…የበዓል ስሜት የሚሰጠውና ሞቅ፣ ሞቅ የሚያደርገው የገበያው ሁኔታ ነው፡፡ የገቢያው ግርግሩ፣ የ “ቀንስ፣” “አልቀንስም፤” ክርክሩና የመሳሰሉት የሚፈጥሩት ነገር አላቸው፡፡
እዚህ ማዶ…
“ስማ፣ እሱ በግ ስንት ነው?”
“ይህኛውን ነው?”
“እሱን አይደለም፡፡ ያኛውን …አ፣ እሱን…”
“አራት ሺህ…”
“አራት ሺህ! በአራት ሺህ ብር መኪና አልገዛም እንዴ!”
“ታዲያ እዚህ ምን አመጣህ! ሰውዬ አትነጅሰን፡፡ ሥራችንን እንሥራበት፡፡ ምን፣ ከየትም ይመጡና…”
እናላችሁ…የፈለገው አይነት የጠነከረ ልውውጥ ቢኖርም አይደብርም፡፡ በዓል ነዋ!
እዚህ ማዶ…
“ይቺኛዋን እርግጧን በልና ልውሰዳት፡፡”
“እሺ በቃ፣ አራት መቶ ውሰጃት፡፡”
“አራት መቶ! ሁለት ዶሮ አይደለም እኮ ያልኩህ!”
“ይቺ ምን ትላለች! ወይ ውሰጅ፣ አለበለዛ ገበያተኛ አትከልይብኝ!”
ልውውጡ የፈለገ ያህል የጠነከረ ቢሆንም አይደብርም፣ በዓል ነዋ!
ዘንድሮ ግን ይህ ሁሉ አይሠራም፡፡ “ዛሬ ትናንት አይደለም፣” ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ መቼም አይደለም፡፡ የተለወጡ ሁኔታዎችን መገንዘብ ግድ ይላል፡፡ አፍ፣ ለአፍ ገጥሞ ዋጋ የሚከራከሩበት ጊዜ አይደለም፡፡ ከገበያተኛ ጋር እየተገፋፉ የሚገለማመጡበት ጊዜ አይደለም፣ አስር ዶሮ እያነሱ እየጣሉ፣ አስራ አንደኛውን የሚገዙበት ጊዜ አይደለም፡፡
ደግሞላችሁ…ለጥሬ ሥጋ ወዳጆችም ሲባል የነበረውን ነገሬ ብሎ መመርመሩ ግድ ይላል፡፡ የጥሬ ሥጋ አምሮት የፈለገ እንቅልፍ ይንሳ፣ የፈለገ ሆድን ባር፣ ባር ያሰኝ…አለ አይደል… “እንዲህ ቢሆን እንዲህ ማድረግ ይቻላል፤” እየተባለ “ፕላን ቢ” ምናምን የሚመዘገብበት ጊዜ አይደለም፡፡ “ፕላን ቢ” ብሎ ነገር የለም፡፡ ወይ ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር ሰምቶ ራስን፣ ቤተሰብንና ህብረተሰብን መጠበቅ፣ ወይ ጆሮ ዳባ ብሎ አደጋ ላይ መውደቅ ነው፡፡ እና በዚህ በዓል ብዙ ልምዶቻችንን መተውና በተለይ ማህበራዊ እርቀትን መጠበቅን የመሳሰሉትን መከላከያ እርምጃዎች መውሰድ ብልህነት ይሆናል፡፡ በዓልን በብልህነትና በጥንቃቄ እንድናሳልፍ ይርዳንማ!
መልካም የትንሳኤ በዓል ሰሞን ይሁንልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!  


Read 1955 times