Print this page
Sunday, 12 April 2020 19:20

የኮሮና ሰሞን ገጠመኝ

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(10 votes)

  የቤቴ መዝጊያ ሲንኳኳ ግር ብሎኝ በዝምታ ጆሮዬን ቀሰርኩ፤በደጉ ቀን የማይንኳኳው ቤቴ በዚህ በምጥ ቀን መንኳኳቱ ግር አለኝ፡፡ አሁንም ተንኳኳ:: ማንም ሰው በሬን አያንኳኳውም፡፡ ወይ ቀበሌ፣ አንዳንዴ ደግሞ ቅባት፣ የቤት ማጽጃ እንዲሸጡ የተፈቀደላቸው ነጋዴዎች ይመጣሉ፤ እርሱም  አልፎ አልፎ ነው:: ጎረቤቶቼ በአውዳመት ቢጠሩኝ፣ ጸበል ቅመስ ቢሉኝ በጀ ባለማለቴ ሁሉም በሚቻል ልክ ትተውኛል፡፡ ታዲያ…በዚህ በፍርሃትና በስጋት ቀን የመጣብኝ ማነው?
‹‹ይቅርታ እኔ ነኝ››
በድምጽዋ አወቅኋት፤ ጎረቤቴ ናት:: ሸንቃጣ ወጣት፤ኮስታራ ሴት፡፡ ግራና ቀኝም አታይም፤ አቤት ኩራቷ ሲያምር!! በፍጥነት ከፈትኩ፡፡ ኮሮና ሁላችንንም ሰፈር አውሎናል፡፡ ምናልባት መጽሐፍ ልትጠይቀኝ ይሆናል፡፡
‹‹ይቅርታ ስለ ድፍረቴ!››
‹‹አረ ግድ የለም››
ጎድጓዳ ሳህን በጓንት ባጠለቀ እጇ ይዛለች፡፡ ምግብ ይዛላኝ መጥታ ነው፡፡
‹‹ከወንደላጤ ሴተ ላጤ ይሻላል ብዬ ነው፡፡››
‹‹አመሰግናለሁ የኔ እመቤት!›› አልኩና ደነገጥኩ፡፡ የሰው ሰው ‹‹የኔ እመቤት ማለቴ አሳፈረኝ፡፡ የምግቡ ነገር ትንሽ ደስ አስኝቶኛል፤የፍሪጅ ምግብ ሰልችቶኛል፤ ፓስታ መቀቀሉም ያስጠላል፡፡ ትንሽ ሰርዲኑ ይሻላል፤እርሱም ሲደጋግሙት ይሰለቻል:: ጣጣ ነው፡፡ ከዚህ ኮረና ከሚባል ልክፍት ይልቅ የቀደሙት ጦርነቶች ይሻላሉ:: ጦርነት ከሆነ ግንባር ሄደህ ትዋጋለህ፤ ከሞትክ መሞት፤ ካሸነፍክ ማሸነፍ!! ይሄ ቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ ማማጥ፡፡ ለላጤው ከባድ ነው፡፡ በተለይ ለሰነፍ ላጤ፡፡ በጓደኛዬ በወንድማገኝ መቅናት የጀመርኩት ሰሞኑን ነው፡፡ በፊትማ አላግጥበት ነበር‹ ‹እትዬ አስካለ››ነበር የምለው፡፡
ቀይ ወጡ ከዶሮ ያስመርጣል፡፡ ጥብሱማ ጣት ያስቆረጥማል፡፡
ድንገት ጎረቤቴ አነቃችኝ፡፡
ታ……ድ…..ለ…..ህ!
ደነገጥኩ፤ምን ተገኘ?
‹‹ወይኔ….ቤትሆቨን….ሊንከን….ሉተር ኪንግ….ዳንቴ…..አደፍርስ…..ማክስዌል….ፍሮይድ…
የአይን አዋጅ ሆነባት፡፡
‹‹ገነት ውስጥ ነህ…ለካ፤ ለዚህ ነው በርህን ዘግተህ፣ድምጽህን የምታጠፋው?››
ፈገግ ብዬ ዝም አልኩ፡፡ አልተጠጋቺኝም::
‹‹ርቀትህን መጠበቅ አትርሳ!! እኔ ሐኪም ነኝ፡፡ እኛ ለናንተ ለመሞት የተዘጋጀን ወገኖች ነን፡፡ ጥንቃቄን ማስተማር ዋነኛ ዐላማችን ነው፡፡››
ንግግርዋ አሳዘነኝ፡፡ እኛ ግን ሃኪሞችን ለምን አንረዳቸውም፡፡ ከብዙ ሺህ ደጎች መካከል  ሁለትና ሶስት ጠማሞችን እያየን እንገፋቸዋለን፤እንተቻቸዋለን፡፡
‹ቤትሆቨን የሚሳዝነኝና የሚገርመኝ ሰው ነው፡፡ በልጅነቱ የተሳካለትና ልጅነቱን ያላጣጣመ ዕድለቢስ ነው፡፡ ውጤት ብቻ ሳይሆን ሕይወትም ጣዕም ያስፈልገዋል፡፡ ብዙ ነገሩ ከቶማስ ኤዲሰን ጋር ይመሳሰላል:: ጆሮዋቸውን ያማቸዋል፡፡ በድህነትም አልፈዋል፡፡ በርግጥ የቤትሆቨን አባት ሰካራም በመሆኑ ቤተሰቡን አሰቃይቷቸዋል:: ያኛው ልጁን እንደ በሽተኛ ማየቱ ዞሮ ዞሮ ያመሳስላቸዋል፡፡
ቁጭ አላለችም፤ ”የምትፈልገው ምግብ ምን እንደሆነ ባላውቅም የጾም ምግብ ነው ያመጣሁልህ፡፡” ትንሽ ቆየችና ‹‹ወደፊት ከዚህ ክፉ ቀን ካለፍን መጻሕፍት ታውሰኛለህ፡፡››
‹‹የፈለግሺውን መውሰድ ትችያለሽ›.
‹‹ታንክዩ››
‹‹ሳህኑን ልስጥሻ?››
‹‹ሌላ ጊዜ ይደርሳል››
አሳዘነችኝ፡፡
‹‹ሐኪሞች የሃገር ወታደሮች እንደሆኑ ታምናለህ ብዬ አስባለሁ፡፡ መቸም የሚያነብ ሰው፣ ከማያነብ የተሸለ ዐይን አለው ብዬ አምናለሁ፡፡”
ሆዴን አባባችው፤ጦር ሜዳ ያለች መሰለኝ፡፡
‹‹ከቤት ስትወጣ ጭምብል ማጥለቅህን አትርሳ!.. ታክሲ ውስጥ ስትገባ ሰልፍ ላይ አትጋፋ!! በተቻለ መጠን ተጠንቀቅ!! ኮሮና የሚይዝህ ወንበር ላይ ብቻ አይደለም፤ ሰልፍ ላይ ስትጋፋም ነው፡፡››
ሀኪም ቤት ያለሁ መሰለኝ፡፡
ቁጭ አላለችም፡፡
‹‹ኦ!...ሮዛ ፓርከር…አንበሳ ሴት!!....የጥቁሮች ነጻነት ቀንዲል!!››አለች መጻሕፍት መደርደሪያዬን እያየች፡፡
‹‹ሃሪየት ቱብማንን የበለጠ አደንቃታለሁ::›› ብዬ የአለም ታላላቅ ጥቁሮችን ሕይወት መጽሐፍ ገለጥኩላት:: አንገቷን ቀልበስ አድርጋ ‹‹ሁለቱም በየዘመናቸው የሰሩት ስራ ድንቅ ነው፤አንዷን ከአንዷ መለየት ይቸግራል፡፡››
ከሄደች በኋላም ድምጽዋ አልረሳ አለኝ:: የሰው ልጅ እንዲህ ውብ ሲሆን እንዴት ደስ ይላል!? ስሟን ሳትነግረኝ ሄደች!? ይሄ ቆሻሻ ኮሮና የሚባል መርዝ እንዳይነካት:: ይቺን መሰለች ድንቅ ልጅ፡፡ ምርጥ ዜጋ!! ራራሁላት፡፡
አልጋዬ ላይ ጋደም ብዬ ማሰብ ጀመርኩ:: የሰው ልጅ ከፍጥረቱ ጀምሮ በፈተና የሚያልፍ፣ በእሳት የሚፈተን፣ ምስኪን ነው›› ብዬ አምን ነበር፡፡ አሁን አሁን ሳየው ደግሞ ከደግ ሰዎች ይልቅ ክፉዎች ይበዛሉ:: ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ሌሎችን ህይወት ገደል ይከታሉ፤ ይዋሻሉ፤ ያስመስላሉ፡፡ አሁን እንኳ ወረርሽኝ ሲገባ ሌላው ሲሞት በመዝረፍ መበልጸግ ይፈልጋሉ፡፡
ደግሞ የሌላውን ችግር ችግራቸው አድርገው እንቅልፍ የሚያጡ አሉ፡፡ አሁን ይህቺ ሀኪም ብቸኝነቴን አውቃ፣ ቤቴን አንኳኩታ መምጣቷ የዚህ ማሳያ ነው፡፡
በዚሁ መንፈስ የጋንዲን መጽሐፍ ማንበብ ጀመርኩ፡፡ መልካም መሆን እንዴት ያለ መታደል ነው! ነጻነቱን የማያስነካ መልካም ሰው መሆን ደስ ይላል!!
በሶሰተኛው ቀን መጥታ ‹‹ራስህን እየጠበቅህ ነው?›› አለችኝ፡፡
‹‹አዎ››
‹‹ራስህንም ሌሎችንም ለማዳን መስራት አለብህ››
ከርሷ ጋር ስሆን ሓኪም ቤት ያለሁ እንደሚመስለኝ ስነግራት ከት ብላ ሳቀች፡፡
‹‹እንደዚህ ያለ ሰው አትመስልም፤ በርግጥ እንደምታነብ እጠረጥር ነበር፤ሳይህ ብዙ ጊዜ መጽሐፍ እጅህ ላይ አይቻለሁ፡፡ ስላወኩህ ደስተኛ ነኝ፡፡›.
‹‹እኔም በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ….እንዳንቺ ዐይነት ሰው በቀላሉ አይገኝም፤ከብርቆቹ ተርታ ነሽ፡፡
አድናቆቴን በፈገግታ አለፈችው፡፡
ከጎረቤት የሚሰማኝ የሂሩት በቀለ ዘፈን ጆሮዬ ገባ፤
ጣራና ግርግዳው በወርቅ ቢሰራ፣
ገንዘብ ተቆልሎ ቢመስል ተራራ፣በከፋው ጎዳና በዚያ የሞት መንገድ፣
ተከትሎ አይሄድም ሀብት የስጋ ዘመድ፡፡
ያለው ከሌለው ጋር ተካፈሎ እንደመብላት፣
ለምን ይሰስታል ዕድሜ አይለውጥባት፤
የሌለው ዘመዱን ሸኝቶት በጥርሱ፣
ችጋር ይዞት ሲሞት ምንድነው ማልቀሱ?
ጋዜጠኛውንም አደነቅሁት፡፡
በዚህ በዞረበት ዘመን፣ ስለ ኮረና፣ የሒሳብ መምህር ትንታኔ እንዲሰጠው በሚጠይቅ ሚዲያ ውስጥ አልፎ አልፎ ሙዚቃ እንኳ ለይተው የሚመርጡ መኖራቸው ደስ አሰኘኝ፡፡
ሐኪሟ ጎረቤቴ ቀልቤን እያጠፋቸው ነው፡፡ ስሟ ሳምራዊት መሆኑን ስትነግረኝ፤ ሳምራውያን የእስራኤል ወገኖች ሆነው፣ ግን የአይሁድ ሰዎች እንደሚንቋቸው ስነግራት ሳቀች፡፡ ስትናደድ አላየኋትም፤ለብዙ ነገር ትስቃለች፡፡ ኮሮና ብቻ አያስቃትም፡፡ ‹‹ተጠንቀቅ!››
ስትለኝ፣ሁለት እጆቼን ቁልቁል አውርጄ፣ ቀጥ ብዬ ስቆም በሳቅ ተንፈራፈረች::
ሌላ ቀን ስናወራ ‹‹ዕድሜ ለኮሮና…›› ብዬ ሳልጨርስ፣ ‹‹ተው የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፈ ወረርሺኝ በምንም ዐይነት አይዘመርለትም›› ብላ ኮስተር አለች፡፡
‹‹ማለቴ መዝሙር መች ዘመርኩኝ፣ ስላስተዋወቀን ክሬዲቱን እንዳልወስድ ብዬ ነው››
‹‹የኔና አንተም ነገር ገና ነው፤ መኖርም መሞትም አለ፡፡››
‹‹አያርግብሽ!›› አልኩና ጴጥሮስን የሆንኩ መሰለኝ፡፡ ኢየሱስን እንዳይሰቀል ፈልጎ “አያድርግብህ›› ሲለው ‹‹ዞር በል አንተ ሰይጣን!›› ብሎት ነበር፡፡ ሳምሪም አንዳንዴ እንደ ክርስቶስ፤ ፍጹም ሀቀኛ ናት፡፡
አንድ ቀን ምግብ ውጭ ልጋብዛት ፈልጌ ነበር፡፡ አልቻለችም ቢዚ ናት፡፡ በዚያ ላይ ብትሞት የፍስክ ምግብ አትበላም፡፡ ብዙ ነገሯ ለዘብተኛ ቢሆንም፣ ጾም ላይ ፍንክች የለም፡፡ ምናልባት ተሳክቶልን ብንጋባ ታስቸግረኛለች፤ ግን ሁሉም ሰው በሁሉም ነገር አይግባባም፡፡
አንዴ ግን ‹‹ጾም ታበዣለሽ›› ስላት ከት ብላ ሳቀች፡፡ ለምን እንደሳቀች ስላልገባኝ አተኩሬ ስመለከታት፣ ‹‹ግር አለህ መሰለኝ፤ እኔ የምጾመው ልጄ  ስለሚጾም ነው፡፡››
ላቤ ከጀርባዬ ጠብ…ጠብ ሲል በህልሜ መሰለኝ፡፡
ከትት ብላ ሳቀችና ‹‹አሁንስ አልገባህም?››
ዝምምም….
ብድግ ባላ ወጣችና ፎቶግራፎች አሳየችኝ፡፡
ርቀትህን ጠብቅ!!
ሐኪም ቤት ያለሁ መስሎኝ ደነገጥኩ፡፡
ከት ብላ ሳቀች፡፡
ፎቶግራፎችዋን አሳየችኝ፡፡
‹‹ያ እጮኛዬ ልጅ ነበረው፤ ልጅ እንዳለው ደብቆ፣ሳንጋባ ሞተ፡፡ ልጅትዋ ተማሪ ስለነበረች እኔ ጋ እንዲማር አመጣሁት፡፡  
 ተነስቼ አንቄ ልስማት ስል ‹‹ርቀትህን ጠብቅ!›‹አለችኝ፡፡
‹‹ኮሮና ዕድሜህ ይጠር››
‹‹አ….ሜ….ን!!››
ስራው እያጣደፋት ብዙ መገናኘት አቃተን፤ ነገሩ እየባሰ መጣ፡፡ የሰው ቸልተኝነት እያበሳጫት መማረር ጀመረች፡፡
ፖለቲካ ላይ ሲራቀቅ ያየነው ምሁር ነኝ ባይ ሁሉ፣ ትከሻ ለትከሻ ሲገፋፋ ታየዋለህ፡፡ ይህቺ ሀገር!!››
ሬዲዮው ፣ ቴሌቪዥኑ ፌስ ቡኩ ሁሉ የልብ አያደርስም፡፡ የሚያወራው የሚመለከተው ብቻ አይደለም፡፡ የጂኦግራፊ፣ የእርሻ፣ የጨርቃጨርቅ መምህር ሁሉ ትንታኔ ይሰጣል፡፡ ተዋናዩ ስለ ኮሮና ያስተምራል:: ሳምራዊት ትስቃለች፣ትበሽቃለች፡፡ ቀኑ ይገፋል፤ ችግሩ ይጨምራል፡፡
እኔም ከመጽሐፎቼ ስር ፍሬ እለቅማለሁ::
ከእንቅልፌ ነቅቼ ፊቴን ስታጠብ በር ተንኳኳ፡፡ ሳምራዊት ናት ብዬ ፉጨቴን እያስነካሁት ነበር፡፡ በሩን ስከፍት የኮንዶሚኒየሙ የኮሚቴ ሰብሳቢ ነበር:: ትንሽ ሃፈረት ቢጤ ቢሰማኝም ምንም እንዳልመሰለው ሆኜ ‹‹ምን ልታዘዝ!››አልኩ:: እርዳታ እየጠየቁ እንደሆነ ነገረኝ፡፡ ሰፈር ውስጥ ላሉ ጎዳና ተዳዳሪዎች ገንዘብ እየጠየቁ ነው፡፡ መቶ ብር ሰጠሁና “ሌላም ጊዜ ያቅሜን አዋጣለሁ፡፡›› አልኩ፡፡
‹‹መጠንቀቅ ነው!››
‹‹ሌላው ሳምራዊት…›› ብዬ ሳልጨርስ ‹‹ሳምራዊት መተቃቷን ሳትሰማ አትቀርም:: አዞረኝ፡፡
አሁን ዜና ላይ ተነገረ፡፡ እንግዲህ ፈጣሪ ይርዳት!!
በሩን እንዴት እንደዘጋሁት አላውቅም፤መሬት ላይ ተደፍቼ ማልቀስ ጀመርኩ፡፡ ምን ትል ይሆን?››
ምንም አትልም፤እንደ በጎ ወታደር ራሷን ስለ ሌሎች ለመስጠት ተዘጋጅታ ነበር፡፡ እንባዬ ቁልቁል እየፈሰሰ ከቤት ወጣሁ፡፡
‹‹ተጠንቀቅ!›› አለኝ ድምጽዋ፡፡


Read 3198 times