Wednesday, 15 April 2020 00:00

ኮሮናን ከጉዳይዋ ያልጣፈችው መርካቶ!

Written by  ብርሃኑ ሰሙ ethmolla2013@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

  “ከጎጃም በረንዳ እስከ አውቶቢስ ተራ፣ ከሰባተኛ እስከ ምዕራብ ሆቴል፣ ከዘይት ተራ እስከ ምናለሽ ተራ፣ ከዱቄት ተራ እስከ ዶሮ ተራ … አሁንም በመርካቶ የሚታየው ትርምስ ያው ነው፡፡ በዚህ ትርምስ መሐልደግሞ ኮሮና ቫይረስን በከፊል የሚያረክሰውን ውሃና ሳሙና ማየት ብርቅ ሆኗል፡፡”
                  
              ቅዳሜ መጋቢት 26 ቀን 2012 ዓ.ም በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ በሰው ልጆች የኑሮ ታሪክ ውስጥ፣ ኮሮናን ጨምሮ አራት ዓለም አቀፍ ወረርሽኞች መከሰታቸውን በማውሳት፤ ሀገራችን ኢትዮጵያም የችግሮቹ ተጋሪ እንደነበረች ጠቁመው፣ ወቅታዊውን ችግር ለመቅረፍ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካነሷቸው አራት ወረርሽኞች አንዱ የነበረውና ‹‹በ1918 የተከሰተው ኢንፍሉዌንዛ›› በሀገራችንም መጠነ ሰፊ ጉዳት አድርሶ፣ ወረርሽኙን መቆጣጠር በተቻለ ማግስት፣ በፋሽስት ጣሊያን የመወረር አደጋ ያጋጠማት ኢትዮጵያ፤ ወረርሽኙ ዳግመኛ ቢከሰት ሀገሪቱንና ሕዝቧን የከፋ ጉዳት እንዲገጥማቸው እኩይ ሃሳብ ታቅዶ ነበር፡፡
በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን የወረረችው ፋሽስት ጣሊያን፤ አዲስ አበባን የነጮችና የጥቁር መኖሪያ በማለት ለሁለት በመክፈል ማስተር ፕላን አዘጋጅታ፤ ኢትዮጵያዊያን እንዲኖሩበትና እንዲገበያዩበት የመረጠችላቸው ስፍራ፤ የከተማው ምዕራብ አቅጣጫ እንዲሆን ያደረገችበት አንዱ ምክንያት፣ የአዲስ አበባ ንፋስ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ስለሚነፍስ፣ “በድንገት ተላላፊ በሽታ ቢከሰት ኢትዮጵያዊንን ይፍጃቸው” በሚል ዓላማ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የዛሬዋ መርካቶ የዘር መድልዎ ማሳያ ብቻ ሳትሆን የዚህ ክፉ ሀሳብም ውጤት ናት፡፡
በወቅቱ ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን የተሻለ ዘመናዊ ስልጣኔ ላይ ደርሳ የነበረችው ጣሊያን፤ በግፍ የወረረቻትን ሀገር ለማዘመን ይጠቅማል ብላ አቅዳ ተግባራዊ ለማድረግ ከሞከረቻቸው ሥራዎች መሐል፣ ለአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ማዘጋጀቷ አንዱ ነበር:: የቅየሳ ባለሙያዎቿ ያነሱት ‹‹የምሥራቅ ንፋስ›› ጉዳይ፣ የሚገነቡ ሕንጻዎችን በርና መስኮት አቅጣጫ ከመምረጥ ባለፈ፣ የፋሽስቱ ባለስልጣናት፤ ሳይንሳዊ ዕውቀትን ለፖለቲካዊ ተንኮል ሊጠቀሙበት እቅድ ነደፉበት፡፡ በከተማዋ ኢንፍሉዌንዛ መሰል ወረርሽኝ ቢከሰት፣ ንፋሱ ደዌውን እያራወጠ ኢትዮጵያዊያንን እንዲያጠቃላቸው ተመኙ::
ከሰም በረሀን አቋርጦ፣ ከኤረር ተራታ ጋር በመጋጨት ጉልበት ፈጥሮ፣ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ የሚምዘገዘገው ‹‹የምስራቅ ንፋስ›› መናገሻ አካባቢን፣ በአሁኑ ዘመንም የሪል ስቴት አልሚዎች ቦታውን የሚመርጡበት አንዱ ምክንያት በዚህ ንፅህናው ምክንያት ነው፡፡ የምሥራቅ ንፋስ ተመራጭ ብቻ ሳይሆን ኃይለኛነቱንም ኢትዮጵያዊያን በተለይ ገበሬዎች የቆየ ዕውቀት እንዳላቸው ይታያል፡፡ አብዛኛው ባላገር መኖሪያ ጎጆውን ሲቀልስ በሩን በምስራቅ አቅጣጫ የማያደርገው የንፋሱ ኃይል ሊያስከትልበት የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል በማሰብ ነው፡፡ ፋሽስቶቹ ካሳንችስ፣ አራት ኪሎንና ፒያሳን አቋርጦ የሚያልፈው ንፋስ መርካቶ ላይ ‹‹ጣጣውን›› እንዲጨርስ ያቀዱት ከዚህ  በመነሳት ነበር፡፡       
ፋሽስቶች እንዳቀዱት ሳይሆን ቀርቶ፣ ወረርሽኙም ሳይከሰት ወራሪው ተሸንፎ ተባረረ፡፡ በወረርሽኝ እልቂት የጦር አውድማ ልትመስል ትችላለች ተብላ የታሰበችው መርካቶ፤ የኢትዮጵያዊያን አንድነት ጎልቶ የሚታይባት ብቻ ሳትሆን እስከ ዛሬ መቀጠል የቻለ የሀገሪቱ ሥራና ሀብት ማመንጫ ሥፍራ ለመሆን በቃች፡፡ መርካቶና መርካቶውያን እዚህ ዘመን ላይ ለመድረስ በርካታ ውስብስብና አስቸጋሪ ጉዳዮችን አሳልፈዋል፡፡ ያልተቀረፉላቸው ብዙ ችግሮችን ይዘው፤ ከዛሬ ነገ ይቀረፋል በሚል ተስፋ አድርገው ባሉበት ወቅት ነው፤ ዓለምንና ሕዝቦቿን ያስደነገጠው የኮሮና ቫይረስ የተከሰተው፡፡  
ኢንፍሉዌንዛን መሰል ወረርሽኝ በአዲስ አበባ ከተማ ቢከሰት ወረርሽኙን ‹‹የምስራቅ ንፋስ›› እየወሰደ ያራግፍባታል የተባለችው መርካቶ፤ የዚያ ክፉ ሀሳብ ሰለባ ሳትሆን ለዛሬ ደርሳለች፡፡ አሁን የንፋስን አቅጣጫ እየተከተለ የሚያጠቃ ሳይሆን፣ ሰዋዊ ንክኪን (መቀራረብን) ዋነኛ ምክንያት አድርጎ በመስፋፋት ዓለምን አዳርሶ እያስጨነቀ ያለው ኮሮና ቫይረስ፤ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ፣ ለወረርሽኙ መስፋፋት ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው በስጋት ከሚታዩ አካባቢዎች አንዷ መርካቶ ሆናለች፡፡ ባለፉት ሳምንታትም የበርካታ መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ስባለች፡፡   
የኮሮና ቫይረስ በሀገራችን መከሰቱ ከታወቀ በኋላ፣ ወረርሽኙን መከላከል ያስችላል በሚል፤ መንግሥትን ጨምሮ በተለያዩ አካላት የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው፡፡ የትምህርት ተቋማት መዘጋታቸው፣ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ ገደብ መጣሉ፣ የተወሰኑ የመንግሥት ሠራተኞች ሥራቸውን ከቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ መደረጉ፣ በመገበያያ ስፍራዎች የሚታየውን መጨናነቅ የማስተንፈስ ስራ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ችግሩን መከላከል የሚያስችሉ  … በርካታ ጥረቶች በመደረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
ወረርሽኙ በፍጥነት ከመስፋፋቱ ጋር በተያያዘ፣ ማሕበራዊ ግንኙነትን ማቋረጥና መቀነስ ዋነኛውና ብቸኛው መፍትሔ በመሆኑ፣ አቅሙ ያላቸው ሀገራት ተግባራዊ እያደረጉት ነው፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የኢኮኖሚ አቅማቸው ከማይፈቅድላቸው ሀገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ‹‹ሕዝቡንና ሀገሪቱን ወደባሰ ቀውስ የሚመራ ውሳኔ አንወስንም›› በማለት፤ ኮሮና ቫይረስ እንዳይስፋፋ ማድረግ ብቻ ሳይሆን መቆጣጠር በሚያስችል ሂደት፣ ምርትና አገልግሎቶች የማይቋረጥባቸውን መንገድ እንከተላለን ብለዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ሀሳብ ያንጸባረቁት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ፤ በከተማዋ ንግድ ቢሮ በኩል በዚህ ሳምንት ተግባራዊ ካደረጓቸው ሥራዎች መሐል፣ የፒያሳ አትክልት ተራን ወደ ጃን ሜዳ እንዲዛወር መደረጋቸው አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ነጋዴዎቹን የማንሳቱ ሂደትና አተገባበሩ ብዙ አነጋጋሪ ጉዳዮች ቢኖሩበትም፣ የትግራይ አዛውንቶች ‹‹ለምጣዱ ሲባል አይጧ በክብር ትለፍ›› እንዲሉ፣ ከታየው ችግር ይልቅ ነጋዴዎቹ ቦታ እንዲቀይሩ የተገደዱበት ዓላማ ትልቅ ስለሚሆን በአድናቆት የሚታይ እርምጃ ነው፡፡
እንደ ፒያሳ አትክልት ተራ መጨናነቅ የሚታይባቸው የከተማዋ (በየክልሉ ያሉትን የከተማና የገጠር መገበያያ ስፍራዎችንም ማሰብ ይቻላል) የንግድ ስፍራዎችን ለማስተንፈስ ተመሳሳይ እርምጃ በመውሰድ ችግሩን መቅረፍ የሚቻል ቢመስልም፣ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ አቅሙ እንዴት ይፈጠር፣ ፍላጎቱ ከየት ይምጣ፣ ትብብሩ እንዴት ይቀናጅ … ? የሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሹ ጉዳዮች ናቸው፡፡
በገበያ ስፍራዎቻችን የሚታየው ትርምስ፣ ማስተንፈሻ ዘዴ ካልተበጀለት፣ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት መቀነስ ቀርቶ መከላከሉን ማሰብ ይከብዳል፡፡ ለዚህ እውነታ ባለፉት ሳምንታት የሕዝብ ቁጥሯ ብዙም ሳይቀንስ፣ በየዕለቱ በርካታ ሰዎች ሲርመሰመስባት በነበረችው የአዲስ አበባዋ መርካቶ ጥሩ ማሳያ ናት፡፡ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን በ1965 ዓ.ም ‹‹አይ መርካቶ!›› በሚል ርዕስ በጻፈላት ግጥም ‹‹የዋይታ›› እና ‹‹የግርግር ቋት›› በሚል የገለጻት መርካቶ፤ ከምስረታ ዘመኗ እስከ ዛሬ አልላቀቅ ያላት ትርምስ ይታይባታል፡፡ ከ80 ዓመት በፊት ፋሽስት ጣሊያን የወረርሽኝ ማረፊያ፣ የሕዝቦች ሞት ማምረቻና የሀገር መጥፊያ እንድትሆን የተመኘላት መርካቶ፤አሁን የኮሮና ቫይረስ ማስፋፊያና ማከፋፈያ እንዳትሆን ፈጥኖ መንቃት አስፈልጓል፡
መርካቶ ‹‹የኮሮና ቫይረስ ዋነኛ ማዕከልና ማከፋፈያ እንዳትሆን›› ባለፈው ሳምንት በተለያዩ አካላት የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ሰንብተዋል፡፡ አርቲስቶችና ኮሜዲያን ከጤና ሚኒስቴርና ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሴክረቴሪያት ጋር በመተባበር ቅስቀሳ አድርገዋል፡፡ የሁለቱ አዳራሽ (መሀል ገበያ) ነጋዴዎች ለአንድ ሳምንት ሱቅና መደብሮቻቸውን በመዝጋት ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ላይ የተሳተፉ ሲሆን ከትላንት በስቲያ መልሰው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡ ‹‹የበጎ አድራጎት›› ሱቅ ባለቤቶችም ተመሳሳይ እርምጃ ወስደዋል፡፡
የአብዶ በረንዳ ጫት መሸጫ ሱቆች ታሽገዋል፡፡ አልፎ አልፎ በግል ውሳኔ የተዘጉ ሱቆች አሉ፡፡ ፖሊሶችና ደንብ አስከባሪዎች ሕዝቡ እንዲራራቅ ይጥራሉ፡፡ አልፎ አልፎ በጋራና በግል እየሆኑ ህብረተሰቡ እጁን እንዲያጸዳ ቆመው አልኮል የሚያድሉ በጎ ፈቃደኞች መኖራቸው ተመስገን ያሰኛል፡፡ በመኪና በመንቀሳቀስ ስለ ቫይረሱ ግንዛቤ ለመስጠት ጥረት የሚያደርጉ አካላትም ይታያሉ፡፡   
እንዲህም ሆኖ መርካቶ ‹‹የዋይታ›› እና ‹‹የግርግር ቋት›› መለያዋን፣ ዛሬም በአስጊው የኮሮና ቫይረስ አስፈሪ ዘመን ለመተው የፈለገች አትመስልም፡፡ ከጎጃም በረንዳ እስከ አውቶቢስ ተራ፣ ከሰባተኛ እስከ ምዕራብ ሆቴል፣ ከዘይት ተራ እስከ ምናለሽ ተራ፣ ከዱቄት ተራ እስከ ዶሮ ተራ … አሁንም በመርካቶ የሚታየው ትርምስ ያው ነው፡፡ በዚህ ትርምስ መሐል ኮሮና ቫይረስን በከፊል የሚያረክሰውን ውሃና ሳሙና ማየት ብርቅ ሆኗል፡፡ መርካቶ በርካታ ምሁራን፣ ባለሀብቶች፣ አርቲስቶች፣ ፖለቲከኞች፣ ስፖርተኞች ... በማፍራት ብትታወቅም፤ ወገኖቻቸውን ለማዳን፣ ታች ወርደው ግንዛቤ ለመስጠት የሚታትሩ የታዋቂ ‹‹ልጆቿን›› ዕርዳታ ማግኘት የቻለች አትመስልም፡፡
ለዚህ እውነታ ብዙ ማሳያዎችን ማቅረብ ቢቻልም፤ የመርካቶ አክስዮን ማህበራት በገነቧቸው ሕንጻዎች ውስጥ የሚገኙ የመጸዳጃ ቤቶች፣ የንግዱ ሕብረተሰብ ብቻ ሳይሆን ወደ መርካቶ የሄዱ ተገልጋዮች እጃቸውን በውሃና በሳሙና የሚታጠቡበት ዕድል የሌለ መሆኑ (በዚህ ክፉ ዘመን) መርካቶ የከፋ አደጋ ላይ መውደቋን በግልጽ የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡  
ሀገሪቱ ሕዝቧ የኢኮኖሚ አቅማቸው የጎለበተ ባለመሆኑ ‹‹የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን በመዝጋት ሕዝብና ሀገርን ሊጎዳ የሚችል ውሳኔ አናስተላልፍም›› ከሚለው የመንግስት ውሳኔ ጀርባ ያለውን አርቆ አሳቢነት ዘላቂ ለማድረግ፣ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር ያስፈልጋል፡፡ ሥራዎችን በማስቀጠል ውስጥ ሊገኝ የሚችለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ደግሞ ያለ ሕዝብና ሀገር ምንም ነው፡፡
ሕዝብም ሀገርም የሆነችው መርካቶ፤ ‹‹የግርግር›› እና ‹‹የዋይ ቋት›› መሆኗን ለማስቀረት ባለፉት 40 ዓመታት በርካታ ጥረት ቢደረግም አንዱም አልተሳካም፡፡ ዛሬ ‹‹መርካቶ የኮሮና ቫይረስ ማዕከልና ማከፋፈያ እንዳትሆን›› ለመከላከል የሚያስችል ተጨባጭ ሥራ በአስቸኳይ የሚያስፈልጋት ጊዜ ላይ ደርሳለች፡፡ ለዚህ እውን መሆን ደግሞ ቀዳሚውን እርምጃ መውሰድ ያለባቸው የንግዱ ማሕበረሰብ አባላት፤ በተለይም ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ አክስዮን ማህበራት ይመስሉኛል፡፡

Read 2224 times