Tuesday, 14 April 2020 00:00

ዘመኑን ለመሻገር ምን ብናደርግ ይበጀናል?

Written by  ከተመስገን ጌታሁን (temesgengt@gmail.com)
Rate this item
(0 votes)

ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው?
በጎንም ዘመን ለማየት የሚወድድ?
አንደበትህን ከክፉ ከልክል፤
ከንፈሮችህም ሽንገላን እንዳይናገሩ፡፡
ይህንን ዘመን እንሻገር ዘንድ አንዱ መንገድ ይህ ነው፡፡ ጓድ ሌኒንስ ቢሆን የአባት አገር ሩሲያ አብዮት እንዳይቀለበስና ወደፊት እንዲጓዝ ወይም እንዲራመድ ምን እናድርግ? ምን ይደረግ? (What to be done?) ወይም ማን ምን ያድርግ አይደል ያለው? እኔም “እናት አገር ኢትዮጵያን ከኮረና ወረራ ለመመከት ምን እናድርግ?” ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ዳር ሆኖ ግራ በመጋባት ስሜት ተመልካች ሆኖ እንዳይቀር፤ ወይም በየዕለቱ የሚሰቀጥጥ ዜና ቁጭ ብለን እየሰማን በፍርሃት እንዳንርድ ምን እናድርግ?
የሁሉንም ሰብዓዊ ፍጡር ሕይወት፤ አኗኗር፤ ባህል፤ እምነትና አስተሳሰብ በቀጥታ የሚነካ ወረርሽኝ ሲነሳ ትክክለኛ የሆነውን መረጃ የምንለይበትና ስለ ወረርሽኙ መረጃ የምንቀባበልበት መንገድ ወራራውን ለመመከት ወሳኝ ነው፡፡ የተዛባ መረጃ ከተላለፈም እንደ ሌላው ዓለም ተስፋ ቆርጠን እጃችንን መስጠት ይመጣል:: ሌላው ቀርቶ ወሳኝ ስለሆነው ነፍስ አድን ማስክ (አፍና አፍንጫ መሸፈኛ) እና ጓንት አጠቃቀም መግባባት አቅቶን የለ?
ቻይናዎች ወረርሽኙን የገቱት መድሃኒት ስላገኙ አይደለም፡፡ ሁሉንም የሚያስማማና በአንድ መንገድ ሁሉም ዜጎች እንዲቆሙ የሚያስችል ብሔራዊ ወይም አገራዊ አስተሳሰብ ለመፍጠር በመቻላቸው ይመስለኛል፡፡ እኛ ወጥ የሆነ የተደራጀ የመረጃ ፍሰት ስርዓት የለንም፡፡ ክልሎች በተበጣጣሰ መልክ ወረርሽኙን  መግታት ቀርቶ መቋቋም አይችሉም፡፡ይሁንና ሁላችንንም በአንድ መንፈስ ሊያቆመን የሚችል አገራዊ አስተሳሰብ ማምጣት እንችላለን፡፡
ትልቅ አቅም ያላቸው አገሮች እንደ ጣሊያን፤ ስፔን፤ አሜሪካ ወዘተ የመሳሰሉት ወረርሽኙን ለመመከት የሚያስችል ሁሉንም አንድ ያደረገ አስተሳሰብ አስቀድሞ መፍጠር ባለመቻላቸው ይመስለኛል ችግሩን የከፋ እንዲሆን ያደረገው፡፡ እነዚህ አገሮች በተሟላ ሁኔታ ፈጣንና ቀልጣፋ፣ ለሁሉም በቀላሉ ተደራሽ የሆነ የመረጃ ፍሰት ስርአትና ቴክኖሎጂ አላቸው፡፡ ይሁንና በሁሉም ዜጋ ዘንድ ቅቡልነት ያለው መረጃ ባለመተላለፉ ምክንያት ፋይዳው ኢምንት ሆኖ የቀረ ነው የሚመስለው፡፡ በዘመናችን ከተፈጠሩት አማላይ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂዎች ጋር የሚመጣጠን “ሰው የመሆን” አስተሳሰብ ከሌለ የዚህ ቴክኖሎጂ ፈጣሪዎችን  ልፋት ውኃ በልቶት  ይቀራል፡፡
የአሜሪካዊያንን ሕይወት መቅጠፍ እስከሚጀምርበት የመጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ የአሜሪካው ርዕሰ ብሔር “የቻይና ቫይረስ” እያሉ ይሳለቁ እንደነበር የማያውቅ ካለ፣ የአዋጁን በጆሮ ነው የሚሆነው፡፡ ጣሊያን ውስጥ ስለ ኮረና ቫይረስ በነበረው የተዛባ አስተሳሰብ፣ አንድ መቶ ሀያ ሺህ ሕዝብ በሚኖርባት ትንሿ የጣሊያን ከተማ 40 ሺህ ሰዎች በሚይዘው ስታዲየም የሚጫወቱትን የእግር ኳስ ክዋክብትን ለማየት 42 ሺህ ታዳሚዎች ታጭቀውበት እንደነበር በብዙኃን መገናኛ ሰምተናል:: እግር ኳስ የሚደምቀው በደጋፊ ብዛት ነውና ስታዲየሙ ሞልቶ፣ በየቢራ ቤቶቹ ተሰባስቦ እየተቃቀፈና እየተጋፋ ጨዋታውን ሊከታተል ከሌሎች ከተሞች የመጣው የእግር ኳስ አድናቂ የሚወቀስበት አንዳችም ምክንያት የለም፡፡ ይሁንና የተፈጠረውን ንክኪ ካሰብነውና በየዕለቱ ጣሊያን የቀበረቻቸውን ወድ ዜጎቿን በሀዘን ተውጠን ስናስተውል፣ ምን ማድረግ እንዳለብን ማወቅ ይገባናል፡፡ የወረርሽኙ ወደር የለሽ ጥፋት ምን ያህል ከባድ፣ ወረራው ምን ያህል ፈጣን እንደሆነ መገንዘብ አያዳግትም፡፡  
መረጃ በጥንቃቄና በዕውቀት ካልተላለፈ ሊታረም የማይችል እጅግ ከባድ ጉዳት ያስከትላል፡፡ አንድ ወንድ በእምነትና በባህል ምክንያት ብዙ ሴቶች እንዲያገባ በተፈቀደበት ማህበረሰብ ውስጥ ኤችአይቪ/ኤድስን ለመግታት ምሱ አንድ ለአንድ ተወስኖ መኖር ነው ተብሎ ቢሰበክ፣ (አንድ ወንድ ብዙ ሚስቶች (polygamy) አንዲት ሴት ብዙ ባሎች (polyandry) በሚያገቡበት ባህል - በቲቤት ይህ ልማድ አለ/ነበረ) ሀሳቡ በቀላሉ ተቀባይነት አያገኝም፡፡
በትልልቅ ዩኒቨርሲቲዎች ደጃፍ ላይ ተማሪው በዲግሪ እንጂ በኤችአይቪ/ኤድስ እንዳይመረቅ የሚያሳስብ ቢል ቦርድ ሲሰቀል ሊያመጣ የሚችለውን አሉታዊ ጉዳት ማንም ያሰበበት አልነበረም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ስራ ዳጎስ ያለ አበል ስለሚከፈልበትና የውጭ ዕርዳታ ስለሚፈስበት፣ በስግብግብ መሀይማን ሰዎች ፕሮጀክቱ የመጠለፍ ዕድል አለውና ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ተማሪዎችን እንዴት እንደሚያሳቅቅ ልብ ያልነው ቫይረሱ ብዙ ሺዎችን ከቀጠፈ ከብዙ ዓመት በኋላ እጅግ ዘግይተን ነበር፡፡
የመኖሪያ ቤት ችግር የሌለባቸው አውሮጳዊያን ዜጎቻቸውን “እባካችሁ እቤታችሁ ተቀመጡ” ብለው ሐኪሞች የተማጸኑትን ጥሪ እንደ ወረደ በቀጥታ ካስተላለፍነው፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቤት የሌላቸው ዜጎች ሳይደናገጡም ሆነ ተስፋ ሳይቆርጡ የዕለት እንጀራቸውን ለማባረር በየመንገዱ ላይ ሲሯሯጡ ልናያቸው እንችላለን፡፡ የገዛውን የአየር ሰዓት ፕሮግራም በቁም ነገር መሸፈን ያቃተው አንድ ባለ ጊዜ የቴሌቪዥን ጣቢያ ነጋዴ፤ “ቢነግሩት የማይሰማ ሕዝብ ነው፤ ባቡሩን ታክሲውንና አውቶብሱን ቀኑ ሙሉ አጣብቦ ለመዋል አደባባይ የወጣ ነው የሚመስለው” ብሎ ባልተረጋገጠ መረጃ ህዝቡን በጅምላ ሲዘልፍ መስማት እጅግ ያማል፡፡ የሚያስከትለውን መጠን የለሽ ጉዳት ሳንገነዘብ በቴሌቪዥን ብቅ ብለን ፈራጅ ብንሆን የሚያስከትለው መዘዝ የት ድረስ እንደሆነ የሚታወቀው፣ይህ አስጨናቂ ወቅት ካለፈ በኋላ ስለ ወረርሽኙ ታሪክ የሚያጠና ሰው ከተገኘ ብቻ ነው፡፡
በሰፊው የሚነገረው “እቤታችሁ ተቀመጡ” የሚለው ምክር፤ ቤት የሌላቸውን ሰዎች እንዴት እንደሚያስቆጣ ለማረጋገጥ የፈለገ ሰው፣ በቴሌቪዥን መስኮት የተናገሩትን  የጎዳና ተዳዳሪዎች ልብ ብሎ ማድመጥ አለበት፡፡ እነዚህ ቤት የሌላቸው ወገኖቻችን በግንዛቤ እጥረት ውጭ መዋልና ማደር ለወረርሽኙ የሚያጋልጥ እንደሆነ ካሰቡና ተጋንኖ በሚነገረው መልእክት በፍርሃት ከራዱ፣ መኖሪያ ቤቶችን በኃይል ሰብረው ለመግባትና እስከ መገዳደል የሚያደርስ ወንጀል ከመስራት የሚገታቸው ነገር ላይኖር ይችላል፡፡
ስለ ቫይረሱ የተምታታ፤ አደናጋሪና አስፈሪ መረጃ በተሰጠ ቁጥር በአገልግሎት ስራ ላይ የተሰማሩ የጥበቃ ሰራተኞች በፍርሃት ሊርዱ ይችላሉ፡፡ በተለይ ሦስትና አራት ቦታ ለሳምንታት ቤታቸው ሳይገቡ በጥበቃ ስራ ላይ ለሚቆዩ ሰራተኞች “ቤት መቆየት ብቻ” ዋናው መዳኛ መንገድ እንደሆነ ካሰቡ፣ በዕጣ ፈንታቸው ተማርረው ለመቆጣት እጅግ ቅርብ ናቸው፡፡ ባለፈው ሳምንት ወደ ባንክ ከመግባቴ በፊት እጄን ለመታጠብ ስጠባበቅ እጁን የሚታጠብ ተገልጋይ፣ በተባለው መሰረት ለሀያ ሰኮንድ ይታጠብ እንደሆነ ለማረጋገጥ ባሰርኩት ዲጂታል ሰዓት ስከታተል አስገራሚ ነገር ታዝቤአለሁ:: ከፊቴ የነበሩት አምስት የባንኩ አገልግሎት ፈላጊዎች እጃቸውን ለመታጠብ በጠቅላላ የፈጀባቸው ጊዜ ስድሳ አንድ ሰኮንድ ወይም በአማካኝ አንድ ሰው 12.2 ሰኮንድ ብቻ ነበር፡፡ ለዚሁ ስራ በቦታው ላይ የተመደበችው ሰራተኛ በስራው አድካሚነት በመሰላቸት፣ ጓንትና ማስክ እንዳጠለቀች ቁጭ ብላ የሚሆነውን መመልከቷ ንክኪውን መቶ ፐርሰንት ስላደረገው በዝምታ ማለፉን ህሊናዬ እምቢ አለኝ፡፡፡
ራሷ ብቻ ቧንቧውን ከፍታ ብትዘጋና የፈሳሽ ሳሙናውን ዕቃ ተገልጋዩ ሳይነካ እንዲጠቀም ብታደርግ ቢያንስ ንክኪውን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት እንደሚቻል ሀሳብ አቅርቤ፣ እኔንም በዚሁ መንገድ እጄን እንድታስታጥበኝ በትህትና ስጠይቃት፣ ፈቃደኛ ሆና ከተቀመጠችበት ተነሳች፡፡ ይሁንና ስራውን ያስተባብር የነበረ የጥበቃ ሰራተኛ ድንገት አራስ ነብር ሆኖ፣ የእጅ መታጠብ ሥርዓቱ ለእኔ የተለየ የሚሆንበት ምክንያት እንደሌለ በቁጣ ነገረኝ፡፡ በዚህ ቢበቃው ጥሩ ነበር፤ ለድብድብ ሁሉ መጋበዙ አስገረመኝ፡፡
የእጅ መታጠብ አስገዳጅ ሕግ መኖር አይደለም ችግሩ፡፡ ይሁንና ሐኪሞች እንደነገሩን፤ ከሀያ ሰኮንድ ያነሰ እጃችንን ከታጠብን ቫይረሱን ማስወገድ አንችልም፡፡ በዚህ ምክንያት ንክኪው ውስጥ ድረስ ዘልቆ አገልግሎት ወደሚሰጡት የባንኩ ሰራተኞች ከተሻገረና በጣም ልዩ ጥንቃቄ ካላደረጉ በስተቀር ተጋላጭ ናቸው፡፡ መቼም ሳንዘናጋ ሙሉ ጊዜያችንን ጥንቃቄ እንደምናደርግ ግን እርግጠኛ መሆን የሚቻል አይመስለኝም፡፡  
የፊት መሸፈኛ ጭምብልና የጓንት እጥረት ያጋጠማቸው ወረርሽኙ የተስፋፋባቸው አገራት፤ ከሕክምና ሙያ ውጭ ያለው ማህበረሰብ ጓንትና ማስክ መጠቀሙ የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ማስታወቂያ ቢለፍፉ እንደ አማራጭ ህብረተሰቡ ቤቱ ሊቀመጥ የሚችልበት ሁኔታ ስላለ ሊያስኬድ ይችላል፡፡ እቤታቸው ሲቀመጡ መንግስታቸው የዕለት ምግባቸውን፤ የንጽህና መገልገያ ቁሳቁሶችንና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን መደጎም ስለሚችል መልእክቱ ሊያዋጣ ይችል ይሆናል፡፡ ፈረንጅ አደረገው ብለን ይህንን ማስታወቂያ እንደ ወረደ ስንለቀው ህብረተሰቡ እቤት ለመቀመጥ ፈቃዱ ቢሆን እንኳን በእለት ጉርሱ ኑሮውን የሚገፋ ማህበረሰብ ፈጽሞ እቤት መቀመጥ ስለማይችል ጭምብል በማድረግ ሊዳን የሚቻልበትን አጋጣሚ አሳጣነው ማለት ነው፡፡ እቤቱ መቀመጥ የሚችል ነገር ግን አንድ ቤት ውስጥ ተፋፍጎና ተጠጋግቶ ለሚኖረው ለእንደኛ ዓይነቱ ማህበረሰብ ጭምብል አትጠቀም ብሎ ማወጅ፣ የእልቂት አዋጅ ከማወጅ የሚተናነስ አይደለም የሚለኝ ይኖር ይሆን?
በአጠቃቀም ጉድለት ሊደርስ የሚችለውን የጤና ችግር ለማስቀረት ስለሚቻልበት ዘዴ ነው ለእንደኛ አይነቱ አገር ህዝብ መነገር ያለበት፡፡ ስጋቱ የጭምብል እጥረት እስከሆነ ድረስ ሰው እቤቱ መስራት እንደሚችል አንዲት ዲዛይነር በሰይፉ ሾው ቀርባ አሳይታናለች፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሰይፉንና እንግዳዋን ማመስገን ተገቢ ነው፡፡
ወረርሽኙ ቢስፋፋ ሊደርስ የሚችለውን አስከፊ ጉዳት ተናግሮ፣ ሽብር ውስጥ ብንገባና ተስፋ ብንቆርጥ የሚፈይደው ነገር የለም:: በቅድሚያ ወረርሽኙን የምንከላከልበት መንገድ ሳይዛባ በባለሙያዎች ተገምግሞ፣ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ባከተተ መልኩ ወይም የህብረተሰቡን የአኗኗር ሁኔታ ባጤነ ሁኔታ ማንንም ሳያገልል ነው፣ የመፍትሄ ሀሳቦችና መላዎች ሊነገሩን የሚገባው፡፡
በመሰለኝና በደሳለኝ የሚነገሩ የመከላከያ መንገዶች ጉዳታቸው የከፋ መሆኑን ለመገንዘብ ኤችአይቪ/ኤድስን ለመግታት ሲነገር የነበረውን አጓጉልና አሳፋሪ ማስታወቂያ ማስታወስ ይገባል፡፡ ምንም ከመናገራችን በፊት ሁላችንንም በአንድ ልብ እንድንቆም ሊያደርገን የሚችል ተቀባይነት ያለው ሀሳብ እንዲኖረን ሐኪሞችና የማህበራዊ ሳይንስ ጠበብቶች (ፎክለር፤ ሶስዮሎጂ..ወዘተ) እንዲሁም የሰለጠኑ የማስታወቂያ ባለሙያዎች ተናብበውና ተባብረው መስራት ይገባቸዋል፡፡ ሐኪም የመተላለፊያ ዘዴውን ያውቃል፤ የማህበራዊ ሳይንስ ጠበብቶች ደግሞ ህብረተሰቡን የማያወዛግብና ቅቡልነት ያለው አስተሳሰብን የሚፈጥር መልእክት ማቀናበር ይችላሉ:: በዚህ ዘዴ ህዝቡን በአንድ መስመርና አስተሳሰብ የሚያቆም መልእክት ማስተላለፍ ይገባል፡፡ ችግሩ የጤና ችግር ብቻ እንደሆነ ማሰብ የዋህነት ነው የሚሆነው፡፡   
“ሁላችንም የኮረና ቫይረስ ውጊያ የገጠምን ወታደሮች ነን” ተብሎ በጠቅላይ ሚኒስትራችን የተላለፈው መሪ ቃል (motto) ሁላችንንም በአንድ ልብ የማቆም ትልቅ ጉልበት አለው፡፡ በውትድርና ዓለም የስራ ክፍፍል እንዳለ ሁሉ፣ ማን ምን ማድረግ እንዳለበት በተጠና መንገድ፣ ዝርዝር አሰላለፋችንን ሊገልጹልን የሚችሉ ሀሳቦችን ካንጸባረቅን፣ ይህ መሪ ቃል (motto) ፍሬያማ ይሆናል፡፡
ቤታችሁ ሆናችሁ ስራችሁን መስራት የምትችሉና ቤታችሁ ለመቆየት ሁኔታው የሚፈቅድላችሁ ሁሉ ቤታችሁ ተቀመጡ፡፡ ይህ ሲሆን ወደ ስራ ቦታ ለመሄድ በሚደረግ ጉዞ የሚፈጠረውን የትራንስፖርት መጨናነቅ ማስቀረት ይቻላል፡፡ ስራ ቦታ ተገልጋዩም ሆነ ሰራተኛው አካላዊ ርቀቱን በአስተማማኝ ሁኔታ  ለመጠበቅም ያስችለዋል፡፡     
ቤት የሌላቸው ወገኖቻችን በሚውሉበትና በሚያድሩበት ቦታ ተገቢውን የአካል ርቀት እንዲጠብቁ፣ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ የሚያደርግ አሰራር ቢዘረጋ፣ ከመገለል ስሜት ስለሚያወጣቸው፣ ወረርሽኙን በመመከት ረገድ አስተማማኝ ወታደሮች እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል፡፡ ለእነዚህ ወገኖች ለጊዜው አገልግሎት የማይሰጡ ተቋማትን በጊዜያዊ መጠለያነት መስጠት ጥሩ ቢሆንም፣ ወረርሽኙ ካለፈ በኋላ ሌላ ማህበራዊ ቀውስ እንዳይፈጥር በቅጡ ማሰብ ይጠይቃል፡፡  
የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በስራ መቀዛቀዝ ምክንያት የሚፈጠረውን ሸክም እንዲጋሩ ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን (ምንድን ናቸው ብትሉኝ አላውቃቸውም፤ ነገር ግን ጥርሳቸውን የነቀሉ ባለሙያዎች እንዳሉ ይታወቃል) መንግሥት ቢወስድ ኢኮኖሚው ባይነቃቃ እንኳን ቀውሱን መቀነስ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ መንግሥትና የፋይናንስ ተቋማት ቢያበረታቷቸውና (እያበረታቱ መሆኑን በደምሳሳው አውቃለሁ) በዚህ መንገድ ችግሩ እስኪቀረፍ ድረስ ድጋፉ ቢቀጥል፣ ባለሀብቶች ወረርሽኙን ለመዋጋት በግንባር ቀደምትነት የተሰለፉ ወታደሮች የማይሆኑበት ምክንያት የለም፡፡
በኮረና ወረርሽኝ አስገዳጅ ሁኔታ አገራዊ ምርጫው ላልተወሰነ ጊዜ በመራዘሙ ምክንያት ድምጻቸውን አጥፍተው ከባድ ቁዘማ ውስጥ የገቡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ቢያንስም ቢበዛም ደጋፊ ስላላቸው ወረርሽኙን ለመመከት የማህበረሰብ ንቅናቄ ውስጥ ቢሳተፉ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያደርጉ እገምታለሁ፡፡
በኮረና ቫይረስ ዙሪያ በየቀኑ ለሀያ አራት ሰዓት፣ ሳምንቱን ሙሉ (24/7) የሚደረግ ቅስቀሳና የሚተላለፍ ዜና በመላና በጥበብ ካልተከወነ የስነልቡና ጫና መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ይሄ ደግሞ በማህበረሰቡ ውስጥ ፍርሃትና ጭንቀት ይነዛል፡፡ ይሄ የእኔ ግምት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ባላዋቂነታቸው ምክንያት ባልተገራ አንደበታቸው ከንቱ የሆነ አስተሳሰባቸውን የሚደፉብንን ደካሞች ከሚዲያው በተቻለ መጠን ገለል ማድረግ ይገባል፡፡ የስነልቡና አዋቂዎች በተለያዩ ሚዲያዎች ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ከተደረገ፣ ልክ የውጊያ ስልት እንደሚነድፍ ብቃት ያለው የጦር ጀኔራል በመሰለፍ፣ ከፊት መስመር ውጊያ ላይ ግብግብ የገጠሙ ውድ ሐኪሞቻችን በመርዳት ደጀን ይሆኑናል የሚል እምነት አለኝ፡፡
በሁሉም ጦር ግንባር ሁሉም ዜጋ እንዲሰለፍ ከተደረገ ወረራውን መመከት አያዳግተንም፡፡ ወረርሽኙ የሚያስከትለውን ሰብዓዊ ጉዳት ትርጉም ባለው ሁኔታ መቀነስም እንችላለን፡፡ ያኔ ይህንን ክፉ ዘመን በአነስተኛ መስዋዕትነት በእርግጥ መሻገር እንችላለን፡፡ ሰላም!!


Read 1908 times