Saturday, 11 April 2020 14:45

አለማችን እና የኮሮና ወረርሽኝ በሳምንቱ

Written by 
Rate this item
(8 votes)

    ኮሮና ቫይረስ እስከ ሃሙስ ተሲያት ድረስ በአለም ዙሪያ በሚገኙ 210 አገራትና ግዛቶች ውስጥ ከ1 ሚሊዮን 631 ሺህ 791 በላይ ሰዎችን ሲያጠቃ ከ98 ሺህ 379 በላይ የሚሆኑትንም ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በኮሮና ከተጠቁባቸው የአለማችን አገራት መካከል እስከ ትናንት አመሻሽ ድረስ ከ475 ሺህ 659 በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባት አሜሪካ በአንደኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፣ ስፔን በ157 ሺህ 22፣ ጣሊያን በ143 ሺህ 626፣ ጀርመን በ119 ሺህ 498፣ ፈረንሳይ በ117 ሺህ 749 ተጠቂዎች እንደቅደም ተከተላቸው እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
እስከ ሃሙስ ተሲያት ድረስ 18 ሺህ 279 ሰዎች በኮሮና ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉባት ጣሊያን ብዛት ያላቸው ሰዎች ለሞት የተዳረጉባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር ስትሆን፣ አሜሪካ በ17 ሺህ 838፣ ስፔን በ15 ሺህ 843፣ ፈረንሳይ በ12 ሺህ 210፣ እንግሊዝ በ7 ሺህ 978 ሟቾች እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ኮሮና ወደ ፖለቲካ አጀንዳ?
ለ100 ቀናት ያህል በዋናነት የጤናና የኢኮኖሚ ጉዳይ ሆኖ መላውን አለም ሲያስጨንቅ የቆየው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ በዚህ ሳምንት ደግሞ መንግስታትን ጎራ አስለይቶ ማወዛገብ የጀመረ የፖለቲካ አጀንዳ ወደ መሆን የተሸጋገረ ይመስላል፡፡
አወዛጋቢው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ በዋነኝነት በእኛ የገንዘብ ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው የጤና ድርጅት፣ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ተገቢውን ስራ አልሰራም፤ አሰራሩ ለቻይና የወገነ ነው፤ ለወረርሽኙ ምላሽ የሰጠው ዘግይቶ ነው በሚል በድርጅቱና በዳይሬክተሩ ላይ ትችታቸውን መሰንዘራቸውንና ድጋፉ ሊቋረጥ እንደሚችል ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ፣ ጉዳዩ ፖለቲካዊ መልክ እየያዘ ወደ አዲስ ውዝግብ ማምራቱ እየተዘገበ ነው፡፡
ትራምፕ ይህን ማለታቸውን ተከትሎ፣ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በሰጡት ምላሽ፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ፖለቲካዊ ማድረግ አይበጅምና መቆም አለበት ያሉ ሲሆን፣ ድርጅታቸው ከዘርና ቀለም በጸዳ ሁኔታ ለሁሉም ህዝብ በእኩልነት እየሰራ እንደሚገኝ በመጠቆም፣ ወቅቱ የመነታረኪያ ሳይሆን የጋራ ፈተናን በጋራ ለመከላከል ርብርብ የማድረጊያ ነው ብለዋል፡፡
የቃላት ውርውሩ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ ዶ/ር ቴዎድሮስ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፤ የግድያ ዛቻ እንደደረሰባቸውና ዘረኛና ጸያፍ ስድቦችን ሳይቀር እያስተናገዱ እንደሆነ በይፋ ተናግረዋል፡፡
ትራምፕ በድርጅቱና በዳይሬክተሩ ላይ ዘመቻ መክፈታቸውን ተከትሎ፣  የአፍሪካ ህብረትና ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ከድርጅቱና ከዳይሬክተሩ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጎን በመሰለፍ አሜሪካን መቃወም ጀምረዋል:: የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሞሳ ፋኪ ማሐማት በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኮሮናን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የዓለም ጤና ድርጅትና ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ብቃት ያለው አመራር እጅግ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል ሲሉ የአሜሪካን ትችት ያጣጣሉት ሲሆን የአፍሪካ ህብረትም የዓለም ጤና ድርጅትንና ዳይሬክተሩን ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምን በሙሉ አቅሙ እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።
“የመላው ዓለም ትብብር አስፈላጊ በሆነበት ሰዓት አብሮነትን ያሳዩ እውነተኛ መሪ” ሲሉ ዶ/ር ቴድሮስን ያደነቁት የናሚቢያው ፕሬዘዳንት ሀጌ ጄኒግቦ ሲሆኑ፣ የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በበኩላቸው፤ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ብቁ አመራር መስጠታቸውን መስክረዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ደግሞ የአለም የጤና ድርጅትንና ዳይሬክተሩን “ኮሮናን ለመቆጣጠር የማይተመን ስራ የሰሩ፤ አቻ የለሾች” ሲሉ ያደነቋቸው ሲሆን፣ የናይጄሪያ መንግስትም በፕሬዚዳንቱ ቢሮ በኩል በሰጠው መግለጫ፤ ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተገቢ ዝግጅትና ምላሽ እንዲሰጥ በማድረግ ረገድ የዓለም ጤና ድርጅትና ዳይሬክተሩ ለሰጡት መመሪያና ብቁ አመራር ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

ግማሽ ቢሊዮን ሰዎች ወደ ድህነት
ሊገቡ ይችላሉ
አለማችንን ከዳር እስከ ዳር ያዳረሰው አስከፊው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በመላው አለም የሚገኙ ግማሽ ቢሊዮን ሰዎችን ወደ ድህነት ሊያስገባ እንደሚችል አለማቀፉ ተቋም ኦክስፋም ባለፈው ሃሙስ ባወጣው ሪፖርት አስጠንቅቋል፡፡
በመላው አለም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ከ400 ሚሊዮን እስከ 600 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ወደ ከፋ ድህነት ሊገቡ እንደሚችሉ የጠቆመው ተቋሙ፣ ያደጉ አገራት መንግስታት ያላደጉ አገራት ከኢኮኖሚ ድቀት እንዲያገግሙ ለማስቻል የ1 ትሪሊዮን ዶላር የእዳ ስረዛ ማድረግ እንደሚኖርባቸው አመልክቷል፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ አንዳንድ የሰሃራ በታች፣ የመካከለኛው ምስራቅ እና የሰሜን አፍሪካ አገራትን ከ30 አመታት በፊት ወደነበሩበት የእድገት ደረጃ ሊመልሳቸው እንደሚችል ግምቱን የሰጠው የተቋሙ ሪፖርት፣ ወረርሽኙ ካለፈ በኋላ ከአለማችን 7.8 ቢሊዮን ህዝብ መካከል ግማሽ ያህሉ ድህነት ውስጥ ሊገኝ እንደሚችልም አስታውቋል፡፡

ውሃን ተከፍታለች
አለምን መከራ ላይ የጣለው የኮሮና ወረርሽኝ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተባትና የቫይረሱ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተከትሎ ላለፉት 11 ሳምንታት ያህል እንቅስቃሴዋን አቋርጣ ሙሉ ለሙሉ ተዘግታ የቆየችው የቻይናዋ ውሃን ከተማ፤ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ዳግም ተከፍታ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዋ መግባቷ ተዘግቧል፡፡
በመንግስት የተላለፈውን ትዕዛዝ ሙሉ ለሙሉ በማክበር ለ76 ቀናት ያህል ቤታቸው ውስጥ ተከትተው የከረሙት የውሃን ሰዎች፤ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር መቻሉን ተከትሎ፣ ሰሞኑን ዳግም የውጭውን አየር ለመተንፈስ የተፈቀደላቸው ሲሆን ትራንስፖርትን ጨምሮ መደበኛ እንቅስቃሴዎችም ተጀምረዋል፡፡

አፍሪካ በመሰንበቻው
ኮሮና ቫይረስ እስከ ትናንት አርብ አመሻሽ ድረስ በ52 የአፍሪካ አገራት ከ12 ሺህ 300 በላይ ሰዎችን ማጥቃቱ የተነገረ ሲሆን፣ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉት ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ632 ማለፉ ተዘግቧል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአህጉሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ቀውስ እንደሚያስከትልና ከወወርሽኙ ጋር በተያያዘ በዚህ አመት ብቻ 20 ሚሊዮን ያህል አፍሪካውያን ከስራ ገበታቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡
የአፍሪካ አገራት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በአመቱ በ15 በመቶ ያህል ሊቀንስ እንደሚችል ያስታወቀው ህብረቱ፣ የአፍሪካ መንግስታት ገቢም ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር እስከ 30 በመቶ ቅናሽ ሊያሳይ እንደሚችል አመልክቷል፡፡
የአፍሪካ አገራት የገቢና የወጪ ንግድ ከ35 በመቶ በላይ ሊቀንስ እንደሚችልና አገራቱ በድምሩ 270 ሚሊዮን ዶላር ያህል ሊያጡ እንደሚችሉም ህብረቱ ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል፡፡
የጋና መንግስት ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች በመጪዎቹ ሶስት ወራት ውሃ በነጻ እንዲጠቀሙ መፍቀዱን በሳምንቱ መጀመሪያ ያታወቀ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ናና አኩፎ አዶ በቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር መንግስት ዜጎች ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የሚከሰትባቸውን የኑሮ ጫና እንዲቋቋሙ ለመደገፍ የሶስት ወር የውሃ ወጫቸውን ሊሸፍንላቸው መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡
በቦትሱዋና ፓርላማ ውስጥ የምትሰራ አንዲት ነርስ በኮሮና ቫይረስ መያዟ መረጋገጡን ተከትሎ የአገሪቱ መንግስት ሁሉም የፓርላማ አባላት ለ14 ቀናት ወደ ማግለያ ቦታ እንዲገቡ መወሰኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንቷ ለ14 ቀናት በማቆያ ሰንብተው ከሰሞኑ የወጡባትና እስካሁን ድረስ 13 ዜጎቿ በኮሮና የተያዙባት ቦትሱዋና የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ያስተላለፈችውን የ28 ቀናት የእንቅስቃሴ ገደብ ወደ ስድስት ወራት ለማራዘም ማሰቧም ተነግሯል፡፡
የሱማሊያ ዘመናዊ ሙዚቃ አባት እንደሆኑ የሚነገርላቸው ታዋቂው የሱማሊያ ንጉስ አህመድ ኢስማኤል ሁሴን ሁደይዲ፣ በተወለዱ በ92 አመታቸው በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሰሞኑን ለንደን ውስጥ ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን የዘገበው ደግሞ ቢቢሲ ነው፡፡  
የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ዜጎችን ከጭንቀትና ድብርት የሚያላቅቁ ሙዚቃዎችንና መዝናኛ ፕሮግራሞችን በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ለሚያሰራጩ የአገሪቱ አርቲስቶችና ዝነኞች የ1 ሚሊዮን ዶላር ያህል የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ማስታወቃቸውን የዘገበው ደግሞ ሲቲዝን ቲቪ ነው፡፡

አለማቀፍ ንግድ በ32 በመቶ
ሊቀንስ ይችላል
የአለም የንግድ ድርጅት ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ፣ በዚህ አመት የአለማችን ንግድ፣ ከአስር አመታት በፊት ከተከሰተው አለማቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ በከፋ ሁኔታ እስከ 32 በመቶ የሚደርስ ቅናሽ ሊያጋጥመው እንደሚችል ማስታወቁን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡ በሁሉም የአለማችን አካባቢዎች ባለ ሁለት ዲጂት የንግድ ቅናሽ እንደሚከሰት የጠቆመው ተቋሙ፤ በተለይ ደግሞ የእስያ አገራትና የሰሜን አሜሪካ የወጪ ንግድ በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀንስ እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡

የሃሰተኛ መድሃኒቶች መብዛት
እና የኮንዶም እጥረት  
በማደግ ላይ በሚገኙ አገራት ከኮሮና ወረርሽኝ መስፋፋት ጋር በተያያዘ ሃሰተኛ መድሃኒቶች በከፍተኛ መጠን በገበያ ላይ በገፍ እየተሸጡ እንደሚገኙ የአለም የጤና ድርጅት ማስጠንቀቁን ቢቢሲ ዘግቧል:: ደረጃቸውን ያልጠበቁ ወይም ሃሰተኛ መድሃኒቶች የአፍሪካ አገራትን ጨምሮ በስፋት እየተሸጡ እንደሚገኙ የጠቆመው ድርጅቱ፣ መሰል  መድሃኒቶችን መውሰድ ለከፋ የጤና ችግር ሊዳርግ እንደሚችልም አስጠንቅቋል፡፡
ሁለቱ የአለማችን ዋነኛ የመድሃኒት አምራቾች ቻይና እና ህንድ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በመዘጋታቸው በአለማቀፍ ደረጃ የመድሃኒት አቅርቦት ከፍላጎቱ በእጅጉ ያነሰ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ ይህን ተከትሎም በየጓዳው እየተመረቱ ለገበያ የሚቀርቡ ሃሰተኛ መድሃኒቶች በእጅጉ መጨመራቸውን ገልጧል፡፡ ባለፈው ወር በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ በአለማችን 90 አገራት በተደረገ ፍተሸና ምርመራ 14 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የተለያዩ አይነት አደገኛ መድሃኒቶች ሊሸጡ ሲሉ መያዛቸውንና 121 ያህል ሰዎች መታሰራቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የኮሮና ወረርሽኝ መስፋፋትን ተከትሎ በርካታ የኮንዶም አምራች ኩባንያዎች ስራቸውን በማቋረጣቸው ሳቢያ አቅርቦትና ፍላጎቱ አለመጣጠኑንና በአለማቀፍ ደረጃም የኮንዶም እጥረት መከሰቱን ያስታወቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ ይህም የከፋ ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችል ማስጠንቀቁን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ማሌዢያን ጨምሮ በአለማችን ከፍተኛ መጠን ያለው ኮንዶም በማምረት በሚታወቁ አገራት የምርቱ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ የአቅርቦት መጠኑ በቀጣይ እየቀነሰ ሲመጣ ጥንቃቄ በጎደለው ወሲብ ለኤችአይቪ ኤድስና ለሌሎች በሽታዎች የሚጋለጡ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር እንደሚችል መሰጋቱንም አመልክቷል፡፡

በዱባይ መጋባትም መፋታትም ተከልክሏል፣ ኮሮና ድመቶችን ሊያጠቃ ይችላል
በዱባይ የኮሮና ቫይረስ መስፋፋቱን ተከትሎ መንግስት ላልተወሰነ ጊዜ ዜጎችን ከመጋባትም ሆነ ትዳራቸውን አፍርሰው ከመፋታት ማገዱን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ በሌላ ዜና ደግሞ ኮሮና ቫይረስ ድመቶችን ሊያጠቃ እንደሚችል በአንድ ጥናት መረጋገጡን የዘገበው አልጀዚራ፤ በአንጻሩ ቫይረሱ ውሾችንና ሌሎች የቤት እንስሳትን እንደማያጠቃ መረጋገጡን አመልክቷል፡፡
በሳይንስ ጆርናል ላይ ከሰሞኑ ለንባብ የበቃውን የጥናት ውጤት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ ቫይረሱ ምንም እንኳን ድመቶችን ቢያጠቃም ድመቶች ቫይረሱን ወደ ሰዎች እንደማያስተላልፉ በጥናቱ መረጋገጡንም አክሎ ገልጧል፡፡



Read 13627 times