Friday, 10 April 2020 00:00

“አዎ! በራሴ የምኮራ በራሴ የምተማመን ጥቁር አፍሪካዊ ነኝ” ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

መሪዎች ለዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም አጋርነታቸውን እየገለፁ ነው

ከቻይና ጋር ተመሳጥረው አዘናግተውናል በሚል በአሜሪካ መንግስት እየተወቀሱ ያሉት የአለም ጤና ድርጅት ሊመንበር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ከዚህም የከፋ የግድያ ዛቻ እንደተሠነዘረባቸው የገለፁ ሲሆን፤ ታላላቅ የአለም እና የአፍሪካ መሪዎች አጋርነታቸውን እየገለፁላቸው ይገኛሉ፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ረቡዕ እለት ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ቀደም ሲል የሪፖፕሊካን ፓርቲ አባሎቻቸው በዶ/ር ቴዎድሮስ ላይ የሚሠነዝሩትን ትችት አጠናክረው “የአለም ጤና ድርጅት እና መሪው ከቻይና ጋር ተመሳጥረው አዘናግተውናል፣ ለዚህም ተቋሙን በገንዘብ ስንደግፍ የነበረበትን አካሄድ ገምግመን ልናቋርጥ እንችላለን” ብለዋል፡፡
የሪፖፕሊካን ፓርቲ አባሎችም ዶ/ር ቴድሮስ የበሽታውን አደገኛነት መጀመሪያ ላይ ደብቀውናል፤ ከቻይና ጋር በመመሳጠርም የበሽታውን ወረርሽኝነት ለማወጅ አመንትተዋል የሚል ክስ ቀደም ብሎ ሲያቀርቡና የተቋሙን ከፍተኛ ወጪ የሚሸፍነው የአሜሪካ መንግስት ድጋፉን እንዲያቋርጥ ሲወተውቱ የነበረ መሆኑም ይታወቃል፡፡
ፕሬዚዳንቱም በእርግጥም ከአለም የጤና ድርጅት ጋር ያለንን ግንኙነት መፈተሽ ያስፈልገናል የሚል መግለጫ መጥተዋል፡፡
ይህን የፕሬዚዳንት ትራምፕን አቋም አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ኢትዮጵያዊው የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በበኩላቸው እስካሁን በትዕግስት ያለፉትንና ለወራት ሲሰነዘርባቸው የነበሩ ጥቃቶችን ጭምር ይፋ በማድረግ እየቀረበባቸው ያለውን ውንጀላ ውድቅ አድርገዋል፡፡
መሪዎች “የኮሮና ወረርሽኝን የፖለቲካ መጫወቻ መሣሪያ ከማድረግ እንዲቆጠቡም መክረዋል፡፡
“እኔ አንድ ግለሰብ ነኝ፤ በኔ ላይ የሚሰነዘሩ ዘለፋዎች ብዙም ግድ አይሰጡኝም አሁን የምመርጠው በየቀኑ እያጣናቸው ያሉ ሰዎችን እንዴት እንታደግ፣ ሰዎችን እንዴት እናድን የሚለው ላይ ማተኮርን ነው፡፡
የሰው ህይወት በየደቂቃ እየጣን ነው፡፡ ለምን ስለዚህ ነገር አናስብም፡፡ እንደ ሰብአዊ ፍጡር ያጋጠመንን ትልቁን ችግር ለምን አናስብም? የኔ ትኩረት የሰው ህይወትን ማዳን ላይ ነው፡፡ በአለም ጤና ድርጅት ውስጥ ፖለቲካ አንሰራም፤ ፖለቲካ የለም፡፡ እኛ የምንጨነቀው በየቀኑ ህይወታቸውን እያጡ ላሉ የአለም ድሃ ሰዎች ነው፡፡ እኛ የምንፀፀተው የሰው ህይወት ባጣን ቁጥር ነው፡፡ ትኩረታችን እሱ ላይ ነው፡፡
እኔ አንድ ተራ ኮሮና የሚያሰጋኝ ግለሰብ ነኝ፡፡ አሁን ባልባለ ነገር ጊዜ የምናጠፋበት ሁኔታ ላይ አይደለንም፡፡ ታዲያ በየቀኑ የሞት መጠን እየጨመረ እንዴት ስለራሴ የስብዕና ግንባታ ልጨነቅ እችላለሁ? የኔ ስብዕና እየሞቱ ካሉ ሰዎች ህይወት በታች ነው፡፡ እኔ ላይ ጥቃት ሲሰነዘር የቆየው ከሁለት እና ሶስት ወራት በፊት ጀምሮ ነው፡፡ ከድሆች፣ የዘረኝነት አስተያየት፣ ፍረጃ ጥቁር ወይም ኔግሮ እጩ መዝለፍ ከተጀመረ ቆይቷል፡፡ ግን የምነግራችሁ ጥቁር ወይም ኔግሮ በመሆኔ እኮራለሁ፡፡
አልጨነቅም፡፡ የግድያ ዛቻም ተሰንዝሮብኛል ግን ብዙም ግድ አይሰጠኝም፡፡ ምክንያቱም በቀጥታ እኔ ላይ ነው የሚያነጣጥረው፡፡ እኔን የሚያናድደኝ በኔ ምክንያት ሁሉም አፍሪካዊ ወይም ጥቁር ህዝብ ሲሰደብ ነው፡፡ ይሄ ሲሆን መታገስ አልቻሉም፡፡ ይሄ ሲሆን መስመሩን አልፋችኋል ልል እፈልጋለሁ፡፡ ይበቃል ይሄን መታገስ አንችልም፡፡ በኔ ላይ የሚፈፀም ነገር ምንም አይመስለኝም የዘረኝነት ጥቃትም ቢሆን ምክንያቱም እኔ በራሴ የምተማመን በራሴ የምኮራ ጥቁር አፍሪካዋ ነኝ፡፡ አዎ በራሴ የሞኮራ ጥቁር አፍሪካዊ ነኝ ሲሉ በግል የሚሰነዘርባቸው እንደማያስጨንቃቸው ነገር ግን በሳቸው ምክንያት አፍሪካውያን ወይም ጥቁሮች መሰደብ እንደሌለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
ከ3 ወር በፊት ጀምሮ ይህ መሰሉ ዘለፋ እየተፈፀመባቸው መሆኑን አሁን ግን ሊበቃ ይገባል ብለዋል ዶ/ር ቴድሮስ፡፡
“እኛ እዚህ ተቋም ውስጥ እስካለን ድረስ የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን፤ የማይፀጽተንን ስራ ሁሉ እንሠራለን፡፡ ነገር ግን እኛ መልአክ አይደለንም ሰዎች ነን ልንሳሳት እንችላለን ያንን ግን እየተመካከርን እናስተካክላለን ብለዋል ዶ/ር ቴድሮስ በዚህ ንግግራቸው፡፡
አሁን ጠንካራ አለማቀፋዊ ህብረት እንደሚያስፈልግ የገለፁት ዶ/ር ቴድሮስ የኮቪድ ፖለቲካን ኳራንቲን አድርጉት አሁን አያስፈልግም” ብለዋል፡፡
በዶ/ር ቴድሮስ ላይ የተጀመረውን የማጥላላት ዘመቻ ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት ዋና ፀሐፊ ሙሣ ፋቂን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ተቃውመውታል፡፡
አሁን ትኩረት ሊደረግ የሚገባው በጋራ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መዋጋት ለይ መሆን እንደሚገባው የገለፁት ሙሣ ፋቂ የዶ/ር ቴድሮስ የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት እንደሚደግፉና አካሄዳቸው ተገቢነት ያለው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ መላው አፍሪካም እንደሚደግፋቸው አረጋግጠዋል፡፡
የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፓል ካጋሚ በበኩላቸው ዶ/ር ቴድሮስ የአፍሪካውያን ሙሉ ድጋፍ አላቸው፤ አሁን ላይ ትኩረት ሊደረግ የሚገባው በሽታውን መከላከል ላይ መሆን አለበት የተጠያቂነት ጉዳይ በኋላ ጊዜውን ጠብቆ የሚመጣ ነው ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበርና የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ስሪዬል ራማሮሣ በበኩላቸው “የኮሮና ወረርሽኝን በመከላከል ጥረት ውስጥ የአለም ጤና ድርጅት እና የዶ/ር ቴድሮስ አመራር የተለየ ነው፤ በምንም የማይታመን ዋጋ ያለው አመራር ነው” ሲሉ ድጋፋቸውን ገልፀዋል፡፡
በተመሳሳይ የናይጀሪያ መንግስትም በይፋ በጉዳዩ ላይ በሰጠው መግለጫ የአለም ጤና ድርጅትም ሆነ ዶ/ር ቴድሮስ ለኮሮና ወረርሽኝ ተገቢ ዝግጅትና ምላሽ እንዲሰጥ በወቅቱ አሳስበዋል ለዚህ ማሳሰቢያውም ምስጋና ይገባዋል ብሏል፡፡
የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴም በትዊተር ገፃቸው “አሁን ላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ወረርሽኙን መከላከል ነው፤ ወረርሽኙን ለመከላከል በማደረገው ጥረትም የዶ/ር ቴድሮስ እና ተቋማቸው ሚና መተኪያ የሌለው ነው ብለዋል፡፡
የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በቅርቡ ሁለት የሀገራቸው ሳይንቲስቶች በአፍሪካውያን ላይ የኮሮና ክትባት መሞከር አለበት ያሉትን ባወገዙበትና የሀገራቸው አቋም አለመሆኑን ባስገነዘቡበትና መግለጫቸው የአለምጤና ድርጅትም ሆነ ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴድሮስ እያደረጉ ያለው ጥረት የሚደገፍ ነው ሙሉ ድጋፋችንን እንሰጣቸዋለን ብለዋል፡፡    


Read 1943 times