Thursday, 09 April 2020 20:26

በኢትዮጵያ አንድ ተጨማሪ ሰው የኮሮና ቫይረስ ተገኘበት

Written by 
Rate this item
(5 votes)

በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 56 ደርሷል  
 
 በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 294 ሰዎች መካከል1 ግለሰብ የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘበት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ፡፡ ይህም በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር ወደ 56 ከፍ አድርጎታል፡፡
ቫይረሱ እንዳለበት የተረጋገጠው ግለሰብ ትውልደ ኢትዮጵያዊና የካናዳ ዜግነት ያለው የ43 ዓመት ጎልማሳ መሆኑን በፌስቡክ ገፃቸው የገለፁት ሚኒስትሯ፤ የጉዞ ታሪክ ያለውና ከካናዳ ወደ ዱባይ፣ ከዚያም ከዱባይ ወደ ኢትዮጵያ የመጣና በለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል፤ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ  የነበሩ 554 ግለሰቦች በተደረገላቸው ምርመራ ከኮሮናቫይረስ ነጻ በመሆናቸው ከህብረተሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ  መደረጉን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ገልጸዋል፡፡ የለይቶ ማቆያ የኮሮናቫይረስ ሥርጭት እንዳይስፋፋ ከሚያደርጉ የዓለም የጤና ድርጅት ምክረ ሃሳቦች አንዱ  መሆኑን ሚኒስትሯ አስታውሰዋል፡፡
 ከተለያዩ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የመጡ መንገደኞች፣ በራሳቸው ወጪ፣ በሆቴሎች ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑንና በአስገዳጅ ሁኔታ ከተለያዩ ሀገራት የተመለሱ ኢትዮጵያዊያንም  በመንግስት ወጪ፣ በዩኒቨርሲቲዎችና በትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲቆዩ መደረጋቸውን የጤና ሚኒስትሯ  ጠቁመዋል።  በአሁኑ ወቅት 2 ሺህ 36 ሰዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ አስፈላጊው የጤና ክትትል  እየተደረገላቸው መሆኑንም አክለው ገልጸዋል፡፡

Read 4059 times