Sunday, 05 April 2020 00:00

‹‹ምልክቱ ሳይታይባቸው በሽታውን የሚያስተላልፉ ሰዎች ተበራክተዋል››

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(9 votes)

   ምንም የበሽታው ምልክት ሳይታይባቸው በሽታውን የሚያስተላልፉ ሰዎች እየተበራከቱ በመምጣታቸው ሕብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ተገለፀ፡፡ የበሽታው ስርጭት መጠን አነስተኛ ነው የሚለው የተሳሳተ አመለካከት ሊታረም እንደሚገባንና የበሽታው ተጠቂዎች ቁጥር አነስተኛ የሆነው አገሪቱ ያላት የመመርመር አቅም አነስተኛ በመሆኑ እንደሆነም ተናግሯል፡፡
በትላንትናው ዕለት በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጠው ስድስት ሰዎች አምስቱ በአዲስ አበባ የተገኙ  መሆኑንና እነዚህ ሰዎችም በሽታው ተገኝቶባቸው ከነበሩ ሰዎች ጋር ንኪኪ ስለነበራቸው በጥርጣሬ በማቆያ ውስጥ ገብተው የተመረመሩና ምንም የበሽታው ምልክት ያልታየባቸው እንደነበሩም ተገልጿል፡፡
የድንገተኛና ጽኑ ህሙማን ሀኪሙ ዶ/ር ዳግማዊ ቴዎድሮስ እንደሚናገሩት፤ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች እንደሚታየውና አሁን በአገራችን እየሆነ ያለው ሁኔታ እንደሚጠቁመው፤ ምልክቱ ሳይታይባቸውና በጤናማ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ቫይረሱን ወደ ሌሎች የሚያስተላልፉ ሰዎች ቁጥር እየተበራከተ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ የአለም አገራት ወደ አገራችን የሚገቡ መንገደኞች በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቆዩ የተሰጠውን መመሪያ በመተላለፍ በተለያዩ መንገዶች ከማቆያ ውስጥ እየወጡ ከሕብረተሰቡ ጋር እየተቀላቀሉ ያሉበትን ሁኔታ እየሰማን በመሆኑ በእነዚህ ሰዎች ላይ መንግሥት የሚወስደውን እርምጃ ጠበቅ ማድረግ እንዳለበትም ዶ/ር ዳግማዊ አሳስበዋል፡፡
የበሽታው ስርጭትን በተመለከተ በአሁኑ ሰዓት እየወጡ ያሉ መረጃዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን የጠቆሙት ዶ/ር ዳግማዊ፤ ይህ ሁኔታ ግን በአገሪቱ ያለውን አጠቃላይ የበሽታ ስርጭት የሚያመላክት መረጃ ነው ከሚለው የየዋህ አስተሳሰብ ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
መረጃዎቹ አገሪቱ ያላትን የመመርመር አቅም እንጂ የበሽታ ስርጭቱን መጠን የሚያመላክቱ እንዳልሆኑም ተናግረዋል:: አያይዘውም፣ ሕብረተሰቡ ከመንግሥት የሚወጡ መረጃዎችን ማመን፣ ራሱን ከበሽታው ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ፣ የበሽታው ምልክቶች ከሚታይባቸው ሰዎች መጠበቅና ለሚመለከተው አካል ጥቆማ ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያውና የኮቪድ 19 በሽታ መከላከል ኮሚቴ ውስጥ በመስራት ላይ የሚገኙት ዶ/ር ሰለሞን ወርቁ እንደሚገልጹት፤ አሁን በበሽታው መያዛቸው መረጋገጡ የሚጠቁሙ ቁጥሮች የእኛን የመመርመር አቅማችንን እንጂ የበሽታውን ስርጭት መጠን የሚያመለክት አለመሆኑን ሕብረተሰቡ ሊገነዘብ ይገባል፡፡
የምንመረምራቸው ሰዎች ቁጥር እየበዛ በሄደ መጠን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችም ቁጥር እየጨመረ እንደሚሄድ መታወቅ አለበት፡፡ ስለዚህም ሕብረተሰቡ በቁጥሩ ማነስ ከመዘናጋት ይልቅ የሚወስዳቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች የበለጠ ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል፡፡ በሽታው ወደ አገራችን ቢገባ ሊያዝ የሚችለውና የሚሞተው ሰው ቁጥር ቅድሚያ ትንበያ ተደርጎበት እንደነበረ ያመለከቱት ዶ/ር ሰለሞን፤ አሁን እየታየ ያለው ሁኔታ ግን ከግምቱ እጅግ በጣም ያነሰና ተስፋ ሰጪ ነገሮች የሚታዩበት ነው ብለዋል፡፡
በአለማችን በሽታው በተሰራጨባቸው አገራት የታዩ ልምዶች እንደሚያመለክቱት፤ በሽታው መግባቱን ባረጋገጡባቸው ጥቂት ቀናት ውስጥ የስርጭቱ መጠን ከቀን ወደ ቀን በከፍተኛ መጠን እየጨመረ የሄደ ሲሆን ይህ ሁኔታ በአገራችን አለመከሰቱ የፈራነውን ያህል ቀውስ እንደማያመጣ ተስፋ ሰጪ ጉዳይ ነው፤ በእርግጥ ይህን ለማለት ጊዜው ገና ቢሆንም ብለዋል፡፡
በሽታው ከተቀሰቀሰባት የቻይና ግዛት ወደ አውሮፓና አሜሪካ ለመዛመት ብዙ ጊዜያት አለመፍጀቱን ያስታወሱት ዶ/ር ሰለሞን፤ በቀጣይነት አፍሪካ በሽታው በስፋት ሊሰራጭባት ይችላል የሚል ቅድመ ግምት የተሰጣት አህጉር በመሆኗ አደጋው ገና ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
በሽታው አዲስ ከመሆኑ አንፃር በዓለም አቀፍ ደረጃም በቂ መረጃዎች አለመኖራቸውን ያወሱት ዶ/ር ሰለሞን፤ አሁን ባለው ሁኔታ መበርታት ያለብን በሽታውን በመከላከሉ ላይ ብቻ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የድንገተኛ ጽኑ ሕሙማን ስፔሻሊስት ዶ/ር ወልደሰንበት ዋጋ ነው በበኩላቸው፤ በሽታው አለምን አንድ ያደረገ፣ ሃያላን የተባሉ አገራት ለእርዳታ እጆቻቸውን ሲዘረጉ ያየንበትና ከሁላችንም ግምትና ሃሳብ ውጪ የሆነ ክስተት መሆኑን ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት በአገራችን እየታየ ያለው ነገር ከግምት በታች መሆኑ የሚያጽናና ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ ይህ አሁን በመንግሥት እየተገለፀ ያለውና የበሽታውን ስርጭት መጠን የሚያመለክተው ቁጥር በአገሪቱ በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ቁጥር የሚያመላክት ነው ለማለት እንደማያስደፍር የተናገሩት ዶ/ር ወልደሰንበት አገሪቱ ያላት የጤና ሲስተምና የመመርመር አቅም አነስተኛነት ሊሆን ይችላል የሚል ግምት እንዳላቸው ገልጸው፤ ብዙ ሰዎችን ብንመረምር ብዙ ኬዞችን ልናገኝ የምንችልበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሞት መጠን እየጨመረ መሄዱን የሚያመላክቱ መረጃዎች አለመኖራቸው በሽታው የከፋ ጉዳት እያስከተለ አለመሆኑን የሚያመለክት እንደሆነም ዶ/ር ወልደ ሰንበት ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ግን በሕብረተሰቡ ውስጥ መዘናጋትን በመፍጠር በበሽታው ላለመያዝ ከሚያደርገው ጥንቃቄ ሊያቅበው እንደማይገባ አሳስበዋል:: በዚህ ወቅት በአገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ሰው በበሽታው ቢያዝ ለማስተናገድ የሚያስችል ዝግጅትና አቋም የሌለ ከመሆኑ አንፃር፣ ሕብረተሰቡ በበሽታው ላለመያዝ በሚያደርገው ጥንቃቄ ላይ ማተኮር እንዳለበት የሚያስገነዝብ ነው ብለዋል - ዶ/ር ወልደሰንበት ዋጋ ነው፡፡     

Read 11493 times