Print this page
Sunday, 05 April 2020 00:00

ህዳሴ ግድብ ሃይል ማመንጨት ሲጀምር በዓመት 1 ቢሊዮን ዩሮ ያስገኛል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

          ‹‹ህዳሴ ግድቡን ከማጠናቀቅ የሚገታን አንዳችም ሀይል የለም››

             የህዳሴ ግድብ ስራው ተጠናቆ ሃይል ማመንጨት ሲጀምር በአመት 1 ቢሊዮን ዩሮ ገቢ እንደሚያስገኝ የተገለፀ ሲሆን፤ ግድቡ በመጪው ክረምት ውሃ መሞላት እንደሚጀምርና በ2013 አጋማሽ ላይ በሙከራ ደረጃ ሃይል ያመነጫል ተብሏል፡፡
የህዳሴው ግድብ ግንባታ የተጀመረበት 9ኛ ዓመት ባለፈው ሐሙስ መጋቢት 24 ቀን 2012 ታስቦ ሲውል የግድቡ የሲቪል ኢንጂነሪንግ (ግንብ ስራ) 68፣ በመቶ የኤሌክትሪክ መካኒካል ስራው 44 በመቶ በአጠቃላይም 72.4 በመቶ የግንባታ አፈፃፀም ላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡
ግድቡ በመጪው ክረምት ሐምሌ ወር 4.9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ መያዝ የሚያስችለው ስራ እየተከናወነለት እንደሚገኝም ተነግሯል፡፡
ግድቡን በሐምሌ መሙላት ከመጀመር ወደ ኋላ የሚያስቀር ምንም አይነት ውስጣዊም ሆነ ውጪያዊ ምክንያት እንደሌለ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ የገለፁ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የአለም ስጋት የሆነው የኮሮና ወረርሽኝ ተጽእኖ እንዳያሳርፍ የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ህዳሴ ግድብን ስንገነባ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ውሃ ለመሙላትም የማንንም ፍቃድ አንጠይቅም ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ህብረተሰቡ የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉ የተነገረ ሲሆን፤ ባለፉት 8 ወራት ግማሽ ቢሊዮን ብር ገደማ ከህብረተሰቡ መሰብሰቡንና በአጠቃላይ ባለፉት 9 አመታት በቦንድና በተለያዩ መንገዶች 13.4 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡም ተገልጿል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው፤ ‹‹ህዳሴ ግድቡን ከማጠናቀቅ የሚገታን አንዳችም ሃይል የለም›› ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል - ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፡፡     

Read 9620 times