Saturday, 28 March 2020 15:21

ጥበብ በሃሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)

    ሞት እንዲህ ሲል ለጌታው አመለከተ፡-
‹‹ቡድሃ የመጨረሻው ነቢይ እኔ ነኝ ብሎ ነበር፡፡ … አልሆነም፡፡ ኢየሱስም ከሀሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ ብሎ እንደ ሄደ አልተመለሰም፡፡ ዲያብሎስም ‹Cornered› እሆናለሁ በሚል ስጋት አንዴ ማህበራዊ ሚዲያ ውስጥ፣ አንዴ ቴክኖሎጂ ውስጥ፣ አንዴ ሃይማኖት ውስጥ እየተደበቀ ጭራው ሊጨበጥ አልቻለም፡፡ እኔ ግን ከዘመነ ቃየል ጀምሮ እያገለገልኩህ እገኛለሁ፡፡ ትጋቴ ታይቶ ድጋፍና ማበረታቻ ይደረግልኝ››…
ጌታውም፤ ‹‹ምንድነው የምትፈልገው?›› ሲል ጠየቀው፡፡
‹‹አንደኛ የተጣለብኝ ማዕቀብ ይነሳልኝ››
‹‹የምን ማዕቀብ?››
‹‹ለምሳሌ ‹Silencing the gun› ምናምን የሚሉት››
‹‹ገና መቼ ተፈተሸና?››
‹‹እሽ ረዳት ይሾምልኝ››
‹‹ህመም፣ ድህነት፣ ስደት ወዘተ፣  ያንተ ረዳቶች አይደሉም እንዴ? አነሰኝ ነው የምትለው?››
‹‹ማለቴ… ቦነስ እንኳ ይሰጠኝ እንጂ ጌታዬ››
እግዜር ትንሽ አሰበና፡- ‹‹የተፈጥሮ ተለዋጭ ጭነትና ዳኝነት፣ የሳይንስን ጥቅም፣ በችግር ጊዜ የሚገለጠውን የክፉ ሰው ገመና ለማሳየት ሲባል አንዳንዴ ማበረታቻ ቢሰጥህ ተገቢ ነው፡፡› አለውና ማመልከቻው ላይ ‹‹የጠየቁት እንዲሰጣቸው ፈቅደናል›› ብሎ አዘዘለት፡፡… አጅሬም ወደ ግምጃ ቤቱ ሮጠ:: … ከዛስ?
*   *   *
ወዳጄ፡- መቅደም ያለበትን ጉዳይ ማስቀደም ተገቢ ነው፡፡ ‹‹First things first›› እንደሚሉት፡፡ መቅደም ያለበት ጉዳይ ደግሞ ‹ራስን ማዳን› ነው፡፡ ሁሉም ራሱን ከተከላከለ ኮሮና ይሸነፋል፡፡ ራስን ማዳን ሌሎችን ማግለል፣ ለሌሎች አለማሰብ አይደለም፡፡ ሌሎችን መጠበቅ እንጂ፡፡ ፅንሰ ሃሳባዊ ትርጉሙ ‹‹ Loving but detached›› ማለት ነው፡፡ በዘልማድ “ሶሻል ዲስታንሲንግ” (Social distancing) እንደምንለው፡፡… ሌሎች ከሌሉ ማን አለ?
ወዳጄ፡- የማናየው ጠላት አጠገባችን አለ፡፡ ካልተጠነቀቅን፣ ካልነቃን አይለቀንም:: ስንጨባበጥ፣ ስንተዋወቅና፣ ስንሳሳም ድንገት ዘው ሊልብን ይችላል፡፡ CVD 19 የሚያጠቃው “እንደ ወዳጅ መሳይ ጠላት” አድብቶ ነው፡፡ ካልተነካካን ግን ማረፊያ አያገኝም፣ አይራባም፡፡ መንገድ ከለቀቅንለት አልፎ ይሄዳል፡፡… ሶሺያል ዲስ ታንስ!!
ወዳጄ፡- መቼም ከሜክሲኮ አደባባይ ወደ ሳር ቤት ወይም በተቃራኒው ባለው መንገድ ሳታበር አትቀርም፡፡ በትራንስፖርትም ሆነ በሌሎች መኪኖች የሚሳፈሩ ተጓዦች ድልድዩ አጠገብ ሲደርሱ ግራና ቀኝ ያሉ መስኮቶች መከፈታቸውን ለማየት ይገላምጣሉ፡፡ ከወንዙ እየተንደረደረ የሚመጣው ክርፋት ‹ክፍተት›› አግኝቶ ካላለፈ፣ የመንገደኛውን ጤና ያውካል፡፡
የመጀመሪያው አሜሪካዊ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ የነበረው ሲንክሌር ሊውስ ፑልታይዘር በተሸለመበት “ኦሮው ስሚዝ” በተሰኘ መጽሐፉ እንደጠቀሰው፤ በተለይ ከአንደኛው የአለም ጦርነት በኋላ የእያንዳንዱ አሜሪካዊ መኖሪያ ቤቶች መስኮቶች መከፈት እንዳለባቸውና ግለሰቦችም ንጽህናቸውን እንዲጠብቁ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ደንብ አስከባሪዎች እንደሚያስገድዱ ይገልጻል፡፡ መጽሐፉ ወጣቱ ዶክተር አሮው ስሚዝ፣ የህብረተሰቡን ጤና ለማገዝ ከትምህርት ቤት ጀምሮ የሚያልፋባቸውን ውጣ ውረዶች የሚተርክ ልብ ወለድ ነው:: አንድ ጊዜ ከመምህራኖቹ አንዱ የሆነው ዶ/ር ጎት ሊብ፤ ተማሪዎቹን ሲያስመርቅ የተናገረው ዛሬ እኛ አገር ከምናየው ፈጣጣ እውነት ጋር እየተዛመደ ይገርመኛል፡-
‹‹አንዳንዶቻችሁ ልታድኑ፣ አንዳንዶቻችሁ ልትገድሉ  (Some of you are going to heal and some of you are going to kill) እየሄዳችሁ ነው›› ብሎ ነበር፡፡
ወዳጄ፡- የሰው ልጅ ያለ ምግብና ውሃ ለቀናት ቢሰነብትም፣ ለደቂቃዎች ሳይተነፍስ መቆየት ግን አይችልም፡፡ እንደ ኢትሃንደር ስንጥብ ካልተበጀለት በስተቀር፡፡ የሲኒሲዝም ንቅናቄ አባት የሚባለው ዴዎጋን$ ራሱን ያጠፋው ‹እንቢ አልተነፍስም› በማለት እንደነበረ ተጽፏል፡፡ ትንፋሽ የሕይወት ምህዋር ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከሞዛምቢክ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲጓዙ የነበሩ ስልሳ አራት ስደተኛ ወንድሞቻችንም ሕይወታቸውን ያጡት በአየር እጥረትና በውሃ ጥም እንደሆነ ስንሰማ፤ ክፉኛ ማዘናችንን መግለጽ ተገቢ ነው፡፡
ወዳጄ፡- የውሃ ነገር ከተነሳ ዓባይን በሚመለከት ባለፈው ሰሞን ሶስቱ የጀርመን WSP ጻሐፊዎች በግብፅና ኢትዮጵያ መካከል ለተፈጠረው ‹ውዝግብ› መፍትሄ ብለው (WSP solution) ያቀረቡትን መንደርደርያ ተመልክቼው ነበር፡፡ WSP እንደሚለው፤ የግድቡ ውሃ ሙላት ኢትዮጵያ ካቀደችው ጊዜ (Time table) በላይ ለምሳሌ በአምስትና ስድስት ዓመታት ቢራዘም፣ አገራችን በነዚህ ዓመታት ውስጥ ከግብርናና መስኖ፣ ከአሳ ሀብት፣ ከኤሌክትሪክ ሃይል ሽያጭና ከኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ በሰው ሀብት ልማት፣ ስራ አጥነት መቀነስና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙርያ ልታገኘው የምትችለው ጥቅም ተሰልቶ ሊሰጣት ይገባል ይላል፡፡ ግድቡን በአጭር ጊዜ መሙላት የግብፃውያን ወንድሞቻችንን ህልውና በእርግጥ አደጋ ላይ የሚጥል ከሆነ በግሌ የቀረበውን ሀሳብ መመርመር ችግር ያለው አይመስለኝም፡፡ መቀበል ያለመቀበል የጋራ ጉዳይ ነው፡፡
“It is the mark of an educated man to be able to entertain a thought with out accepting it” የሚለን ታላቁ አርስቶትል ነው፡፡
*   *   *
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- አጅሬ ሞት እየተቻኮለ ወደ ግምጃ ቤቱ በመሄድ ማዘዣውን ለኃላፊው አቀረበ፡፡ ኃላፊውም ለሞት የሚሰጥ ቦነስ ምን እንደሆነ ስላልገባው ከፊቱ የተደረደሩትን ፓኬቶች ሲመለከት ባንደኛው ላይ ‹ቫይረስ› የሚል ተጽፎበት ያይና…
‹‹ይሄን ነው የምትፈልገው?›› ብሎ ይጠይቀዋል፡፡
አጅሬም፡-
‹‹አዎ›› ብሎ ተቀብሎት ‹‹ቦነስ ቫይረስ፣ ቦነስ ቫይረስ›› እያለ እየፈነደቀ ዓለምን ሲዞር፣ አርጀንቲና ላይ ተደናቅፎ፣ ሁዋን ላይ ተከሰከሰ፡፡ ፓኬቱ ተበተነ፡፡
ሰላም!!    


Read 1739 times