Print this page
Saturday, 28 March 2020 13:45

‹‹ግመሌንም አስራለሁ በእግዚአብሔርም አምናለሁ››

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ‹‹አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ በፊቱም የሚበጀውን ብታደርግ ትእዛዙንም ብታዳምጥ ሥርዓቱንም ሁሉ ብትጠብቅ በዓለም ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና፡፡›› /ኦ.ዘፀ.15፡26/  
‹‹እስመ እግዚአብሔር ዐቃቤ ስራይ ውእቱ በመለኮቱ ወፈውሰ ድውያን ውእቱ በትስብእቱ፣ እግዚአብሔር በመለኮቱ መድኃኒት ቀማሚ በሰውነቱ ደግሞ የተቀመመ መድኃኒት ነው››
የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት 2020 ከተስፋ ይልቅ ዓለም አቀፋዊ ስጋትን ይዞ መጥቷል:: ፎሬየንስ የተሰኘው ድረ ገጽ አዲሱን ዓመት ‹‹መርዶ ነጋሪ፣ ጥቁር ዓመት›› ብሎ ገልጾታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱ ነው፡፡ ኖቭል ኮሮና ቫይረስ ኮቪድ 19 ብዙ አለም አቀፋዊ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን አምጥቷል፡፡ ኢራን ደግሞ ለበጎ በሚመስል ሁናቴ ኮሮናን ተከትሎ ከ80 ሺህ በላይ እስረኞችን በጊዜያዊነት ለቃለች፡፡
ኮሮና ቫይረስ መነሻው ቻይና ‹‹ሁቤይ›› ግዛት ይሁን እንጂ አሁን ላይ 198 ሀገራትን በቫይረሱ ተጠቅተዋል፡፡ ከ22ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸውን ተነጥቀዋል:: እስከ አሁን በቫይረሱ ከ500 ሺህ በላይ ሰዎች ተይዘዋል፡፡
በእርግጥ ኮሮና በሕክምናው ደረጃ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ብዙ ትኩረት ያላገኘና ጉንፋን መሰል በሽታ እንደሆነ ከስሙ ጀምሮ ድሮም ይታወቃል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ ተላላፊ በሽታዎች ሁሌም ቢሆን ለዓለም ከባድ ስጋት ናቸው፡፡ ከዚህ በፊትም በታሪክ በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ‹‹ያርሲን›› የሚባል ባክቴሪያ አውሮፓ ላይ ተከስቶ ወደ ሁለት መቶ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተውበታል፡፡ በየዘመኑ፣ ሰዎችን ለሞት የዳረጉ ብዙ ቫይረሶች ተከስተዋል፡፡
ቫይረሱ የመተንፈሻ አካልን የሚያጠቃ ሲሆን ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ነው:: በሽታው ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል የሚያጠቃ ቢሆንም፣ ከአንድ ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት፣ በዕድሜ የገፉ አረጋውያንና ለረዥም ጊዜ ከበሽታ ጋር የኖሩ ሰዎች የበለጠ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡
ብዙ ጊዜ ቫይረስ ወለድ በሽታዎች ፈዋሽ መድኃኒት የላቸውም፤ ለምሳሌ፡- ኤችአይቪ ኤድስንና ሌሎችንም መጥቀስ እንችላለን፡፡

ኮሮና ለምን መጣ?
ኮሮና የመጣበት ምክንያት በውል አይታወቅም፡፡ እንደ መነሻ የሚሰነዘሩ ሀሳቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ፈረንጆች የማይበሉ እንስሳትን ሁሉ ስለሚበሉ ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጮች ናቸው፡፡ ጊንጡን፣ አይጡን፣ ጉርጡን እንዲሁም የተለያዩ የማይበሉ አዕዋፋትና እንስሳትን ስለሚበሉ ለብዙ በሽታዎች ተጋላጮች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ቫይረሱ እንስሳትን ሆስት ሪዘርቬየር /Host Reservior/ አድርጓቸው ይኖራልና፡፡ ሳይንሱ እንደሚለው፤ በሽታው ከሆስቱ የሚመጣ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም እንዲበሉ የተፈቀዱ እንዳይበሉ የተከለከሉም አሉ:: ‹‹ድፍን ሰኮና ያለው እና የማያመሰኳውን አትብሉ›› እንዲል /ኦ.ዘሌ.11፡3/ ነብየ እግዚአብሔር ሙሴ፡፡ በዚህም ምክንያት በውጭው ዓለም የእንስሳት በሽታዎች /Zoonotic Disease/ የተለመዱ ናቸው፡፡
ማይክሮቢያል ዋር /Microbial War/ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ጦርነት በአደጉት ሀገራት የተለመደ ነው፡፡ በመከላከል ስልት አንዱ የሚጠቀሰው ማይክሮቢያል ዋር ነው፡፡ አንድ ሀገር አንድን ሀገር ሲበልጠው የሚጠነስሰው ሳይንሳዊ ውጊያ ነው፡፡ ስለዚህ ኮሮናም ከላብራቶሪ ያመለጠ ነው ለማለት እርግጠኛ ባይኮንም ሊሆን ግን ይችላል፡፡
የእግዚአብሔር ቁጣ /መቅሰፍት/ መዓት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ከሌሎችም ምክንያቶች ባለፈ ሰፊውን ቦታ የሚይይዝ ነው፡፡ በተለይም ይህ ዕምነት ያላቸው ሀገራትና ሕዝቦች የሚያነሱት ምክንያት ነው፡፡
ከእግዚአብሔር ስንወጣ፣ ስመ እግዚአብሔርን መጥራት ስናቆም እግዚአብሔር በመዓት ይገስጸናል፡፡ ነቢዩ ሚክያስ ‹‹ባልሰሙም አሕዛብ ላይ በቁጣ እና በመዓት እበቀላለሁ›› /ት.ሚክ.5፡15/ እንዲል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኢያሱም ‹‹እኛ እስከ ዛሬ ድረስ ከእርሱ ያልነጻንበት የፌጎር ኃጢአት ጥቂት ነውን? በእግዚአብሔር ማኅበር ላይ መቅሰፍት ወረደ፡፡›› /መ. ኢያሱ. 22፡17/ እንዲል፡፡ በተጨማሪም ቅዱስ ዳዊት ‹‹አቤቱ በቁጣህ አትቅሰፈኝ በመዓትህም አትገስጸኝ›› /መዝ.6፡1/ እንዲል፡፡

ኮሮና ቫይረስን እንዴት እንከላከለው?
በመንፈሳዊ በኩል
በዕምነት ውስጥ የሚኖር ሕዝብና ሃይማኖት ያለው ሀገር ምንጊዜም ክፉ ነገር ሲከሰት ወደ ፈጣሪው ይጮሀል፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት አምልኮተ እግዚአብሔር ትልቅ መሳሪያ ነው፡፡ ስለዚህ ምን እናድርግ?
ጸሎት መጸለይ
ሁሉም በገባው እና ባለው ሃይማኖት ፈጣሪውን መለመን አለበት፡፡ ሁሉም ሰው በያዘው ሃይማኖት በግሉም በማህበርም መጸለይ አለበት፡፡ እግዚአብሔርም ይሰማናል፡፡ ቅዱስ ሙሴ ‹‹እርሱም አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ በፊቱም የሚበጀውን ብታደርግ ትእዛዙንም ብታዳምጥ ሥርዓቱንም ሁሉ ብትጠብቅ በግብጻውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም፤ እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና፡፡›› /ኦ.ዘፀ.15፡26/ እንዳለን፡፡ በግብጽ ማለቱ በዓለም ላይ ያመጣሁትን ለማለት ነው፡፡ ስለዚህ አሁንም ተጸጽተን ከተመለስን፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዙን ከተከተልን ችግሩ መከራው ይቀላል፡፡
ምሕላ መያዝ
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በእግዚአብሔር ለሚያምኑ ሀገራት ምሕላ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ መ.ዜና መዋዕል ካልዕ 20፡9 ‹‹ክፉ ነገር ፣ የፍርድ ሰይፍ ወይም ቸነፈር ወይም ራብ ቢመጣብን ስምህ ባለበት በዚህ ቤትና በፊትህ ቆመን በመከራችን ወደ አንተ እንጮሀለን አንተም ሰምተህ ታድነናለህ አሉ::›› እንዳለን ለሁሉም ነገር በሕብረት ሆኖ ወደ ፈጣሪ መጮሕ ይገባናል፡፡
ማዕጠንት ማጠን
በሀገራችን አንድ አባባል አለ ‹‹ሕዳር ከታጠነ በሽታ የለም›› ይባላል፡፡ ስለዚህ ጸሎተ ዕጣን ተደግሞ ማዕጠንት በየቀኑ መታጠን አለበት፡፡ “የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልዐኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ›› /ዮሐ›ራዕይ.8፡4/ እንዲል፡፡ የጠፋው መስቀል የተገኘው በዕጣን ነው አሁንም የጠፋው መድኃኒት የሚገኘው በእግዚአብሔር ነው ምክንያቱም ‹‹ማዳን የእግዚአብሔር ነው›› /መዝ.3፡8/ እንዲል ቅዱስ ዳዊት፡፡
 የቅዱሳንን ዕምነት እና ጸበል መጠቀም
 በልዩነት በበሽታ፣ በተለይም በወረረሽኝ እና በተላላፊ በሽታዎች ቃል ኪዳን ለተገባላቸው ቅዱሳን የእነሱን ዕምነት መቀባት፣ ጸበላቸውን መጠጣት፣ በጸበላቸው መጠመቅ ፍቱን መድኃኒት ነው፡፡
ለአብነትም የቅዱስ ቂርቆስን፣ የአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስን፣ የአቡነ ሐብተ ማርያምን፣ የአቡነ ሐራን እና የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ገድል ማንበብ፣ በቤታችን ማስነበብ ወረርሽኙን ለመከላከል ትልቅ መሳሪያ ነው፡፡
ቅዱስ ዳዊት ‹‹ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም መቅሰፍትም ወደ ቤትህ አይገባም በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና::›› እንዲል በመንገድህ ማለቱ በሕይወትህ ሲል ነው፣ መላእክቱን ማለቱ ቅዱሳንን ነው አንድም ቅዱሳን መላእክትን ነው፡፡ ስለዚህ የቅዱሳኑን ዕምነት መቀባት፣ ጸበል መጠጣት፣ መልክዕ መድገም፣ ገድል ማንበብ በሽታውን ለመከላከል ፍቱን መድኃኒት ነው፡፡
በሀገራችን ኢትዮጵያ ታሪክ ንጉሶች የሚፈልጉትን ጉዳይ ለማስፈጸም የሚፈልጉትን ጽላት አስገብተው መቅደሳቸውን ይሰሩ ነበር፡፡ ለአብነትም አባቶቻችን በአድዋ የቅዱስ ጊዮርጊስን ጽላት ይዘው ጣሊያንን ድል ነስተዋል:: እቴጌ ምንትዋብ ቁስቋም ማርያምን አሰርተው ብዙ ችግሮችን አልፈዋል፡፡ አጼ ቴዎድሮስ መድኃኒዓለምን ይወዱ ነበር፡፡ ሌሎች ነገስታትም እንዲሁ፡፡ ስለዚህ ሁሌም ቅዱሳኑን መማጸን ተገቢም ትክክልም አዋጭም ነው፡፡
እግዚአብሔር ሁሉን ማድረግ የሚችል የሁሉ መድኃኒት ነውና፡፡ ቅዱስ ያሬድ ‹‹እስመ እግዚአብሔር ዐቃቤ ስራይ ውእቱ በመለኮቱ ወፈውሰ ድውያን ውእቱ በትስብእቱ፣ እግዚአብሔር በመለኮቱ መድኃኒት ቀማሚ በሰውነቱ ደግሞ የተቀመመ መድኃኒት ነው›› እንዲል፡፡
.በስጋዊ በኩል
የጤና ባለሙያን ምክር መቀበል /ማክበር/ መተግበር
የኢትዮጵያ መንግስት ኮሮና ከመከሰቱ በፊት የማንቂያ ደብዳቤ /አለርት ሌተር/ እና ለባለሙያዎች ስልጠና መስጠቱ፣ ሌሎች ስራዎችንም መስራቱ ይታወሳል፡፡ ከተከሰተም በኋላ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩትና ሌሎችም አካላት ብዙ ስራዎችን እየሰሩ ነው::
የቫይረሱ ምልክቶች፡- ከፍተኛ ትኩሳት፣ ሳል፣ እንደ ንፍጥ ያለ ፈሳሽ ነገር፣ የጉንፋን ምልክት፣ ጉሮሮ መከርከር፣ የሆድ ሕመም፣ የመገጣጠሚያ ሕመሞችና የመተንፈስ ችግር ምልክቶች ሲሆኑ ምልክቶቹ ለመታየት ከ2-14 ቀናትን ሊወስዱ ይችላል፡፡
በባለሙያ ቫይረሱን ለመከላከል የተሰጡ ምክሮች፡-
1. እጅን በሳሙና መታጠብ
2. የግል ንጽሕናን መጠበቅ
3. ምግብን አብስሎ መመገብ
4. ከእንስሳት ጋር ንክኪ አለማድረግ
5. ጭምብል መጠቀም
6. ከሰዎች ጋር አለመጨባበጥ
7. ትልልቅ ስብሰባዎችን መሰረዝ
8. መስኮት መክፈት ወዘ.ተ ለአብነት የሚጠቀሱ መከላከያ ዘዴዎች ናቸው፡፡
ንጽሕናን መጠበቅ በቤተ ክርስቲያንም የሚገኝ አስተምሕሮ ነው፡፡ ነብየ እግዚአብሔር ሙሴ ‹‹ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው ከፈሳሹ ነገር ሲነጻ ስለመንጻቱ ሰባት ቀን ይቆጥራል፣ ልብሱንም ያጥባል፣ ገላውንም በምንጭ ውኃ ይታጠባል፣ ንጹሕም ይሆናል /ኦ.ዘሌ.15፡13/ እንዲል፡፡ ካህንም ወደ መቅደስ ሲገባ ታጥቦ ንጹሕ ሆኖ ነው የሚገባው፡፡ አይበለውና ነገ ሰሞነኛ ቀዳሽ ሆኖ ቢነስረው ገብቶ መቀደስ አይችልም:: ቤተ ክርስቲያን የነፍስ ንጽሕናን ብቻ ሳይሆን የስጋ ንጽሕናንም ታስተምራለች:: ስለዚህ ንጽሕናን መጠበቅ ሳይንሳዊ ብቻ ሳይሆን በሃይማኖትም የተደገፈ ነው፡፡
በሽታ የመከላከል አቅማችንን የሚጨምሩ ምግቦችን መመገብ፡፡ በሽታው በባሕሪው ኢሚዩኒታቸው /Immunity/ የወረዱ ሰዎችን የሚያጠቃ በመሆኑ አመጋገባችንን በተወሰነ መልኩ ማስተካከል::
ለምሳሌ፡- በቅርቡ ሲወራ የነበረው ማር፣ ጤና አዳም፣ ዝንጅብል፣ ፌጦ፣ ሽንኩርት፣ ሎሚ ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉት በሀገራችን ዘመናዊው ሕክምና ሳይመጣ ለመድኃኒትነት የምንጠቀማቸው ናቸው፡፡ ሁልጊዜም እነዚህን ነገሮች ብንጠቀም ጉዳት የለውም፡፡ ነገር ግን ከአባቶች ነው የተላለፈ የሚለው ምንም እንኳን መልካም ነገርን ወደ አባቶች ማስጠጋት የተለመደ ቢሆንም፣ ጉዳዩን በማስተዋልና በጥበብ መመርመር ይገባል፡፡ የፌስ ቡክ አባቶች ሊሉ ይችላሉ፤ የሆነው ሆኖ ግን በመጠኑ መጠቀም ለኮሮና መድኃኒትነት ባይሆኑም ለጤናም ጠቃሚ ናቸው፡፡ በርግጥ አባቶች የፈውስ ስጋዊም የፈውስ መንፈሳዊም ጥበቡ አላቸው፡፡
ቫይረሱ ከ26-27 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ ሙቀት መቋቋም የማይችል በመሆኑ ይሞታል፡፡ ስለዚህ እንደ ሻይ፣ ሾርባና የመሳሰሉትን ትኩስ ነገሮች መጠቀም የቫይረሱን የመተላለፍ አቅም ይገድበዋል፡፡ ሳይቃጠል በቅጠል ነውና የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ ጉዳት የለውም፡፡ ምክንያቱም ስጋዊ ጥበብም ከፈጣሪ ስጦታዎች አንዱ ነውና፡፡
አለመጨነቅ
ገና ሊይዘን ይችላል በሚል መጨነቅ የለብንም፡፡ ምክንያቱም ጭንቀት በራሱ በሽታ ነውና፡፡ ተጨንቀንም የምንጨምረው ነገር ብዙ አይኖርምና፡፡ አትንካኝ አትንኪኝ እስከ ማለት መድረስ የለብንም፤ የሚጠበቅብንን እናድርግ፤ የተረፈውን ግን ለፈጣሪ እንተወው፡፡ ህይወት ይቀጥላል በጣም መጨነቅ ተገቢ አይደለም፡፡ ስንወለድ ማመልከቻ አስገብተን አልተወለድንም፤ ስለዚህ ስንሞትም በማመልከቻ አንሞትም፤ ጊዜው ከደረሰ እንሞታለን ግን ደሞ ከልብ እንዳንሆን የምንችለውን እናድርግ፤ ሌላውን ለፈጣሪ እንስጥ፡፡ ሕይወት ይቀጥላል፡፡
ሕግን ማክበር
ሌላው ከሕግ አንጻር በወረርሽኝ ደረጃ የተፈረጀ በሽታን ወደ ሌሎች ሆን ብሎ ማስተላለፍ እስከ ሞት ሊያስቀጣ ይችላል:: በ1997 ዓ.ም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጄል ሕግ አንቀጽ 514 (1) ‹‹ማንም ሰው አስቦ በሰው ላይ ተላላፊ በሽታ ያሰራጨ ወይም ያስተላለፈ እንደሆነ ከአስር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ ነገር ግን በወረርሽኝ ደረጃ የተፈረጀ በሽታን ያስተላለፈ እንደሆነ ከሃያ ዓመት ጽኑ እስራት እስከ ሞት ሊያስቀጣ ይችላል፡፡›› ስለዚህ ማንኛውም በበሽታው ራሱን የሚጠራጠርና በሽታው አለብህ ተብሎ የተነገረው ሰው ራሱን በለይቶ ማቆያ ክፍል ማኖር ይኖርበታል፡፡
ካሳለፍናቸው ታሪኮች ትምህርት መውሰድ  
ኢትዮጵያ ብዙ ስቃዮችን አሳልፋለች:: አዲስ መከራም አዲስ ደስታም የለም፤ ስለዚህ የድሮ አባቶቻችን ወረርሽኝ ሲመጣ እንዴት አድርገው አለፉት ብሎ መመርመር መጠየቅ ይገባል፡፡ ለምሳሌ፡- ከ1911 ዓ.ም ወረርሽኝ ትምህርት መውሰድ፡፡
የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መሰራት አለበት
ኮሮና የማይመለከተው የለም፤ ሁሉም የድርሻውን ወስዶ መስራት ካልቻለ ልንቋቋመው አንችልም፡፡ ትልልቅ የዓለም ሀገራት ጠንካራ የጤና ፖሊሲና ቴክኖሎጂ ያላቸውም እንኳን በጣም እየተፈተኑ ነው፡፡ ‹‹እየሳቁ አለቁ›› እንዲሉ በሕመሙ መቀለድ አያዋጣም፡፡ ለቫይረሱ ሚዲያዎች ቋሚ የአየር ሰዓት መመደብ አለባቸው፡፡ ነጻ የስልክ መስመሮችን በመክፈትና በአግባቡ በማስተዋወቅም ሕብረተሰቡ ያልገቡትን ጉዳዮች እንዲጠይቅና ግንዛቤውን እንዲያሰፋ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አስፈላጊ ነው፡፡ በገጠሩም በከተማውም የሚዲያ አካላትና ሌሎችም በዕውቀት ላይ የተመሰረተ መረጃ መስጠት ይኖርብናል፡፡
የተያዙትን ሰዎች አለማግለል
አጋጣሚውን ተጠቅሞ የተያዙትን ማግለል ተገቢ አይደለም፡፡ ፈረንጅም ይሁን ሀበሻ ማንም ስለፈለገ አይያዝም፤ ስለዚህ ነግ በእኔም ነውና ማግለልን እናስወግድ፡፡
አጋጣሚውን ተጠቅሞ ገቢያን አለመጨመር
አጋጣሚውን ተጠቅሞ የዋጋ ንረቱን መጨመርም ተገቢ አይደለም:: የሚጨምረው አካል የተለየ ፕላኔት የለውም፤ ትርፉ ትዝብት ብቻ ነው፤ ስለዚህ ነጋዴዎች ብታስተውሉ መልካም ነው፡፡
ቅድመ መከላከሉ ላይ መስራት
ኮሮና የመተላለፍ አቅሙ /Contagious Rate/ ከፍተኛ ሲሆን ገዳይነቱ /Fatality Rate/ ግን ዝቅተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ቫይረሱን ለመከላከል የቅድመ መከላከል ስራ መስራት ይኖርብናል፤ መከላከሉም ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል፡፡
እንደ ሀገር የሚወሰኑ ውሳኔዎችን በማስተዋል መወሰን
ደግሞ ደጋግሞ የውሳኔው አስፈላጊነት ጉዳት እየታየ ውሳኔዎች ሊሰጡ ይገባል:: ለምሳሌ፡- ከቤት አትውጡ አይነት ውሳኔዎች እንደገና ሊታዩ ይገባል፡፡ በሽታው ደሃና ሃብታንም የማይለይ ቢሆንም ደሃን ግን የበለጠ ይጎዳል፡፡
ቅዱስ ሙሴ እንዳለን የእግዚአብሔርን ቃል ብንፈጽም ኖሮ ይህ ሁሉ መንጫጫት ባልነበር፡፡ ለእግዚአብሔር የሚበጀውን ብናደርግ ኖሮ፣ ይህ ሁሉ መንጫጫት ባልነበር፡፡ ትእዛዙን ሰምተን ብንፈጽም ኖሮ ይህ ሁሉ መንጫጫት ባልነበር፡፡ ሥርዓቱን ሁሉ ብንጠብቅ ኖሮ፣ ይህ ሁሉ መንጫጫት ባልነበር፡፡ አሁንም በንስሐ ሳሙና ታጥበን እግዚአብሔርን ብንለምነው የመጣው ቁጣ፣ በሽታ ይመለሳል እርሱ እግዚአብሔር ይመልሰዋል፡፡ ‹‹እርሱም አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ በፊቱም የሚበጀውን ብታደርግ ትእዛዙንም ብታዳምጥ ሥርዓቱንም ሁሉ ብትጠብቅ በግብጻውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና፡፡›› /ኦ.ዘፀ.15፡26/  እንዳለን፡፡
ኢትዮጵያ ሐገረ እግዚአብሔር ነች፤ ስለዚህ ይህን የአምልኮተ እግዚአብሔር ሥርዓት ተጠቅሞ በሽታውን መከላከል አዋቂነት እንጂ ቂልነት አይደለም፡፡ መልካም ተሞክሮውን ለሌሎች ሀገራትም ማስተላለፍም ይገባል፡፡
በግሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ቫይረሱ ሰዎችን ሊይይዝ ይችላል፤ ነገር ግን ብዙ ሰዎችን ግን አይገልም የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ ይህ የሚሆነው ግን ቤተ ክህነቱና ቤተ መንግስቱ ተናበው ተባብረው ከሰሩ ነው፡፡ አልያ ግን እንደ ልቦናችን ክፋት ብቻ ሳይሆን ‹ለኃጥአን የወረደው ለጻድቃን› እንዲሉ ሁላችንንም ያጭደናል፡፡ ስለዚህ ነብዩ ኢሳይያስ ከአንተ ጋር ነኝ አትፍራ እንዳለ፣ በእግዚአብሔር ካመንን ፍርሃቱን አስወግደን ወደ እግዚአብሔር እንጩህ፡፡
በሀገራችን አባባል ‹‹አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን ያዥ›› እንደሚባለው ሊመጣ እኮ ይችላል ብሎ በማሰብ አብዝቶ ሳይጨነቁ ቅድመ ጥንቃቄ መውሰድ አስፈላጊ ነው:: ስለዚህ ቫይረሱ በጣም ከባድ በመሆኑ በመንፈሳዊም በስጋዊም በርትቶ ቅድመ መከላከሉን መስራት ይኖርብናል፡፡ አፋሮች እንዲህ ይላሉ፡- ‹‹ግመሌንም አስራለሁ በእግዚአብሔርም አምናለሁ›› እንዲሉ ጤንነቴን እጠብቃለሁ፤ በእግዚአብሔርም አምናለሁ፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን እግዚአብሔር ዳሯን እሳት መሀሏን ገነት አድርጎ ይጠብቅልን፡፡ አቁራሪተ መዓት ድንግል ማርያም መዓቱን ታርቅልን፡፡
ዲያቆን ዘዐማኑኤል አንተነህ ይግዛው
 መጋቢት 15/2012ዓ.ም ጎንደር/ኢትዮጵያ

Read 2715 times Last modified on Saturday, 28 March 2020 16:11
Administrator

Latest from Administrator