Saturday, 28 March 2020 12:32

የእቴጌ መስቀል ክብራ ታሪካዊ ሥራ

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)
Rate this item
(0 votes)

     ቤተ አባ ሊባኖስ
በሀገራችን ከራቀው ዘመን ጀምሮ ወሳኝ የፖለቲካ ሥልጣን ጨብጠው አገር ሲያስተዳድሩ የነበሩት ጠንካራና ብልህ ንግሥታት (የሴት መሪዎች) ብዙ ናቸው:: ከንግሥታቱ መኻከል ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ1013- 982 ዓመተ ዓለም ለ31 ዓመታት የገዙት ንግሥት ማክዳ /ንግሥት ሳባ/፣ በ730 ኒካንታ ህንደኬ፣ በ333 ተካውላ ህንደኬ፣ በ233 ኒኮውሲስ ህንደኬ፣ በ88 ነግሠው ለ11 ዓመታት የመሩት አወሲና ንግሥት፣ በ24 ዓመተ ዓለም ነግሠው ለ10 ዓመታት አገር ያስተዳደሩት ደኮትሪስ ህንደኬ ንግሥት 6ኛ፣ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ደግሞ በ34 ዓመተ ምሕረት የነገሡት ንግሥት ህንደኬ 7ኛ፣ በ42 ዓ.ም. የነገሡት ገርሰምት ንግሥት፣ በ230 ዓ.ም.በትረ መንግሥት የጨበጡት ዋከና ንግሥት፣ በ299 ዓ.ም.መንግሥታዊ ሥልጣን የያዙት አሀየዋ ሶፍያ ንግሥት፣ በ369 ዓ.ም. መሪ የሆኑት አድኀና ንግሥት 1ኛ፣ በ412 ዓ.ም. አገር የመሩት አድኀና ንግሥት 2ኛ፣ ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡
በተመሳሳይ መልኩ በ850 ዓ.ም. ላይ ዮዲት ጉዲት፣ በ1909 ዓ.ም. ደግሞ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ወለቱ ለዳግማዊ ምኒልክ ቢነግሡም፣ የንግሥት ዘውዲቱ ሥልጣን በአልጋ ወራሹ በራስ ተፈሪ መኮንን ቁጥጥር ሥር ስለዋለ እንደነ ዮዲትና ሌሎች ንግሥታት ወሳኝ የፖለቲካ ሥልጣን ነበራቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በሞተበትና በተነሣበት ዘመን ገደማ ማለት በ34 ዓመተ ምሕረት በነበሩት በንግሥት ህንደኬ 7ኛ ዘመነ መንግሥት ከተከናወኑት ዐበይትና ታሪካዊ ተግባራት ውስጥ ዋነኛው የክርስትና እምነት ዜና በኢትዮጵያ ውስጥ በሰፊው መሰማቱ ነው:: አስቀድሞም ሆነ በንግሥት ህንደኬ 7ኛ ዘመን ኢትዮጵያና እስራኤል የሃይማኖትና የንግድ ግንኙነት ነበራቸው። እናም ንግሥት ህንደኬ በይበልጥም ሃይማኖታዊ ግንኙነቱን ለማጠናከር ሲሉ በሀብታቸውና በገንዘባቸው አዛዥና ናዛዥ የነበረውን ባለሟላቸውን /ጃንደረባቸውን ባኮስን/ በ34 ዓመተ ምሕረት ወደ ኢየሩሳሌም ሰደዱት (ታደለ፡1997፤ የንግሥታት ገድሎችና የፍቅር ታሪኮች)፡፡  
በንግሥተ ሳባ ዘመነ መንግሥት ታምሪን፣ በንግሥት ዕሌኒ ደግሞ ማቴዎስ፣ ታማኝ ባለሟሎች እንደነበሩ ሁሉ ባኮስም በንግሥት ህንደኬ ዘንድ ክብርና ሞገስ የነበረው ሰው ነው፡፡
በመሆኑም ባኮስ ከኢትዮጵያ ንግሥት ህንደኬ በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት፤ ለብዙ ዓመታት የፀሐይ ሐሩርና የሌሊት ቁር ሳይበግረው በእግሩ ተራራ ወጥቶ፣ ቁልቁለት ወርዶ፣ ሜዳውን ተጉዞ፣ በረሃውን አቋርጦ፣ ባሕሩን ሰንጥቆ ወደ ኢየሩሳሌም የዘለቀው  እምነቱን የድካሙ ጽንዓት፣ የንግሥቲቱን መልእክት ደግሞ የሕይወቱ መሠረት አድርጎ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት የጃንደረባው ታሪክ የተለወጠው ወደ ኢየሩሳሌም ወርዶ በሚመለስበት ጊዜ ነው፡፡ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 20 ቁጥር 26 እንደተገለጠው፤ የንግሥቲቱ ጃንደረባ ባኮስ ወደ ኢየሩሳሌም ወርዶና ኢየሩሳሌምን ተሳልሞ ወይንም ለፈጣሪው ሰግዶ ሲመለስ በሰረገላ ላይ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብብ ነበር። ሐዋርያው ፊሊጶስም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ወደ ጃንደረባው ባኮስ ቀርቦ “ወንድሜ ሆይ ለመሆኑ የምታነብበውን ነገር ታስተውለዋለህን?’ ብሎ ጠየቀው። እርሱም የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል አለው፡፡ጃንደረባው ባኮስም ፊሊጶስ ሰረገላው ወጥቶ ይቀመጥ ዘንድ ለመነው። ያነብበው የነበረው የመጽሐፍ ክፍልም ይህ ነበር፡፡ “እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፣ የበግ ጠቦት በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል እንዲሁ አፉን አልከፈተም። በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፡፡ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና ትውልዱንስ ማን ይናገራል?”
የንግሥት ህንደኬ ጃንደረባ ባኮስም ለፊሊጶስ መልሶ “እባክህ ነቢዩ ይህ ስለማን ይናገራል? ስለራሱ ነውን? ወይስ ስለሌላ?” አለው። ፊሊጶስም አፉን ከፈተ። ከዚሀም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት፡፡ በመንገድም ሲሔዱ ወደ ውኃ ደረሱ። ጃንደረባው ባኮስም እነሆ ውኃ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድን ነው? አለው፡፡ ፊሊጶስም በፍጹም ልብህ ብታምን ተፈቅዶአል አለው፡፡ የህንደኬ ጃንደረባም መልሶ‘ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ’ አለ፡፡ ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ። ፊሊጶስና ጃንደረባው ባኮስም ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ። አጠመቀውም። ከውኃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊሊጶስን ነጠቀው፡፡ ጃንደረባው ባኮስም ሁለተኛ አላየውም፣ ደስ ብሎት መንገዱን ይሔድ ነበርና---፡፡ በዚህ ዓይነት የሥርዓተ ጥምቀቱ እምነት በነአቡነ ሰላማ /ከሣቴ ብርሃን/ ዘመን እንደተደረገው በስፋት ባይሰበክም በንግሥት ህንዴኬ ዘመን ጃንደረባዋ የክርስትና ሃይማኖትን ዜና አምጭና የመጀመሪያው ተጠማቂ በመሆኑ ለኢትዮጵያ አማንያን ባለውለታ ሆኗል ማለት ነው፡፡
በዚህ ዓይነት በሀገራችን የንግሥተ ሳባ፣ የንግሥት ህንደኬ 7ኛ ፤የዮዲት ጉዲት፣ የእቴጌ መስቀል ክብራ፣ የንግሥት ዕሌኒ፣ የእቴጌ ሰብለ ወንጌል፣ የእቴጌ ምንትዋብና የእቴጌ ጣይቱ ተጋድሏቸውና የድል ዝናቸው ለሀገራችን ሴቶች በምሳሌነት የሚታይ ሲሆን  ሥራቸው ከሌሎች የዓለም ንግሥታት ታሪክ ጋር ሲነጻጸር ከፍ ያለና የታሪክን ሂደትም የቀየረ ነው ለማለት ይቻላል፡፡
የአይሁድ ሃይማኖት ተከታይ ከነበረቺው ከዮዲት ጉዲት ዘመን በኋላ በቀጣዩ የዛጉየ ሥርው መንግሥት አገዛዝ / በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማብቂያና በ13ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ/ የኢትዮጵያ መሪዎች እንደገና የክርስትና እምነት ተከታዮች ለመሆን በቅተዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ከዮዲት ጋር በንጽጽር ሲታዩ የተለየ ጠባይና ሥነ ምግባር ያላቸው ንግሥት በኢትዮጵያ ታሪክ ብቅ ብለዋል፡፡ እርሳቸውም መንፈሳዊ ተግባራትን በእጅጉ የሚያስፋፉ፣ ለእግዚአብሔር ያደሩ ንግሥት መስቀል ክብራ ናቸው። ንጉሡ ላሊበላ  ለደብረ ሊባኖስ ገዳም በአበረከተውና በወርቅ በተለበጠው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተጽፎ እንደሚገኘው፤ ንግሥት መስቀል ክብራ ልክ ዓፄ ዐምደ ጽዮን ቀዳማዊ፤ ዓፄ ዘርዐ ያዕቆብና ልጁ ዓፄ በእደ ማርያም ከአንድ በላይ ላገቧቸው ሚስቶቻቸው የቀኝ ባልቲሐቤት፤ የግራ ባልቲሐት ብለው ይጠሯቸው  እንደነበረው ንጉሡ ላሊበላም እኒህኑ የመጀመሪያቸውም፤ የመጨረሻቸውም የሆኑትን ባለቤታቸውን እቴጌ መስቀል ክብራን በዐልተቢሐት (በልተ ቤት) እያሉ በክብር ስማቸው ይጠሯቸው ነበር፡፡ ማርየ ዴራትና ስታንሰላው ኩርየ በበኩላቸው እንደጻፉት፤ ይህ የክብር ስም ለንግሥት መስቀል ክብራ ብቻ በላሊበላ ዘመን ከተሰጠ በኋላ በሌሎች ነገሥታት ዘመን  አልቀጠለም ፡፡  
በማዕረግ ስማቸው በዐልተቢሐት (የቀኟ እመቤት) እየተባሉ ይጠሩ የነበሩት እቴጌ መስቀል ክብራ በዓለም የታወቀውን ቤተ መቅደስ ከቋጥኝ ፈልፍለው የሠሩት የቅዱስ ላሊበላ ባለቤትና አማካሪም ነበሩ። እቴጌ መስቀል ክብራ ጠንካራና የራሳቸው እምነትም ሆነ አስተሳሰብ ተቀባይነት እንዲኖረው በባለቤታቸው በቅዱስ ላሊበላ ላይ ከባድ ተጽዕኖ ለማሳደር የቻሉ ሴት ነበሩ፡፡ ታደሰ ታምራት እንደጻፉት፤ እቴጌይቱ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሪ፤  ጳጳስ ወይም ሊቀ ካህናት የራሳቸው ወንድም ኃይሩን በኋላ ተክለ ማርያም እንዲሆንና ግብጻዊው ጳጳስ አቡነ ሚካኤል የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የነበረቺውን አዳፋን  ለቅቆ ወደ ሀገሩ ግብጽ እንዲመለስ የወሰኑ ራሳቸው ናቸው፡፡ ጳጳሱም ወደ ግብጽ ከተመለሰ በኋላ የንግሥቲቱ የመስቀል ክብራ ወንድም ኃይሩን ሥራውን እንዳይሠራ መሰናክል እንደሆነበት ለወገኖቹ ግብጻውያንና ለወዳጆቹ ኢትዮጵያውያን አስረድቷል:: የወርወር ቄስ ወይም ካህን የነበረውና በክህነት ስሙ ተክለ ማርያም ፤ በዓለም ስሙ ኃይሩን የዓፄ ላሊበላንና የዓፄ ነአኵቶ ለአብን  ገድል እንደ ደደረሰ ስታንስላው ኩርየ እና ማርየ ዴራት  (በ1972) ግምታቸውን አስፍረዋል፡፡   
የአቡነ ሚካኤልን ወደ ግብፅ መጋዝ አስመልክቶ የእስክንድርያው ፓትርያርክ  ለንጉሥ ላሊበላ በጽሑፍ ጥያቄ  አቅርቦለት ነበር፡፡ ላሊበላም በተቃራኒው አቡነ ሚካኤል ከቅርብ ወገኖቹ ውስጥ አንዱን ካህን እንደገደለና የቤተ መንግሥቱንም ሀብትና ንብረት እንደ ዘረፈ፤ ከዚህም የተነሣ ከሥልጣኑ እንደተወገደ መልስ ሰጥቷል:: አቡነ ሚካኤልን ነቅለው ወንድማቸውን ኃይሩንን የተከሉት እቴጌ መስቀል ክብራ ከቅዱስ ላሊበላ ይትባረክና አቱአብ ወይንም አናብ የተባሉ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወልደዋል፡፡ አቱአብ የሚለው ስም  ነአኩቶ ለአብ ከሚለው ስም ጋር ይወራረሳል፡፡ የሁለቱም ልጆች ታሪክ በግብጽ ፓትርያርኮች መጽሐፍ ውስጥ ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ እቴጌ መስቀል ክብራ ቅዱስ ላሊበላ ዙፋናቸውን ከአብራካቸው ለተገኙትናበጊዜው የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ ብቃት እንደሌላቸው ለተገመቱት ለልዑል ይትባረክ ወይም ለልዑል አቱአብ ከሚሠጡ ይልቅ የወንድማቸው የቅዱስ ሐርቤ ልጅ ለሆኑት ለልዑል ነአኩቶ ለአብ እንዲለቁላቸው መክረዋል። ይህንንም ያደረጉት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተመርተውና ራዕይ አይተው እንደሆነ በገድለ ላሊበላ ታሪክ ላይ ተገልጧል።ዓፄ ላሊበላ ግን የባለቤታቸውን የእቴጌ መስቀል ክብራን ምክር ባለመቀበል እኔ በሕይወት እያለሁ መንግሥቴን አሳልፌ እንዴት  ለወንድሜ ልጅ እሠጣለሁ  ብለው ቅር ቢሰኙም ከብዙ ምክር በኋላ መስቀል ክብራ አሳምነዋቸዋል። በመጨረሻም ነአክቶ ለአብ ተጠርተው ሥርዓተ ንግሥ ይፈጸምላቸው ዘንድ ይጠየቃሉ። እርሳቸውም “እኔ መንግሥት የማይገባኝ ሰው ነኝና አልቀበለውም ይቅርብኝ”  ብለው ሐሳብ ያቀርባሉ። ብዙ ምክክር ከተደረገ በኋላም  ልዑል ነአኩቶ ለአብ በእቴጌ መስቀል ክብራ አግባቢነት መንግሥቱን ከዓፄ ላሊበላ ይቀበላሉ።
ቅድስት መስቀል ክብራ በቅ/ሚካኤል እየተመሩ ሲጸልዩ
ዓፄ ላሊበላም ነአኩቶ ለአብን ባርከውና መርቀው ሠራዊት ሠጥተው ከእርሳቸው በታች  የአንድ አውራጃ ንጉሥ እንዲሆኑ ሾሟቸው። በዚያው ሳሉ የነአኩቶ ለአብ ወታደር የአንድ ገባር /ገበሬ/ ላም ቀምቶ ይወስዳል። ላሙን የተቀማው ገባርም “እግዚአብሔር ያሳይዎ ክርስቶስ ያመልክትዎ” ብሎ ለዓፄ ነአኩቶ ለአብ አቤት ቢላቸው ንጉሡ ለጉዳዩ ትኩረት ሳይሠጡ ይቀራሉ። ገባሩም ‘ የጌታም ጌታ አለው፡’ በሚል ወደ ሮሓ ክተማ ሔዶ ወደ ታላቁና ወደ በላዩ ንጉሠ ነገሥት ወደ ዓፄ ላሊበላ ቀርቦ በደሉን ያመለክታል። የደረሰበትን ችግርና በደል ዘርዝሮም በተለይ ለንግሥቲቱ ለእቴጌ መስቀል ክብራ ያስረዳል።እቴጌ መስቀል ክብራም ነአኩቶ ለአብን አስጠርተው  ላሚቱን ለባላገሩ ያስመልሱ ዘንድ አዘዙ። ነአኩቶ ለአብ ግን ነገሩን ችላ ብለውና አስተሐቅረው የንግሥቲቱን ሐሳብ ሳይቀበሉ ይቀራሉ። ዳግመኛም ዓፄ ላሊበላ በዚህ አዝነውና ነአኩቶ ለአብን አስጠርተው በብዙ ወቀሷቸው። በኋላ ነአኩቶ ለአብ የእቴጌ
መስቀል ክብራንና የዓፄ ላሊበላን ምክር ተቀብለው ጉልበታቸውንም ስመው ወደ ግዛታቸው ከተመለሱ በኋላ ላሚቱን ከወታደራቸው ላይ ተቀብለው ለባላገሩ አስመለሱለት፡፡ በዚህ
የተናደዱት እቴጌ መስቀል ክብራ በቅዱስ ላሊበላ ላይ ተጽእኖ አድርገው  ዙፋኑን ዓፄ ላሊበላ ከወንድማቸው ልጅ ከነአኵቶ ለአብ ላይ ቀምተው ለልጃቸው ለይትባረክ እንዲሰጥ
አድርገዋል፡፡ ንጉሥ ላሊበላ ከንግሥት መስቀል ክብራ የወለዱት ይትባረክ በነአኩቶ ለአብ ቀጥሎ ነግሦዋል ማለት ነው፡፡
ዓፄ ላሊበላ ከዚሁ የንግሥናና የአስተዳደር ሥራቸው ጋር  አሥር አብያተ ክርስቲያናትን ከአለት እያስፈለፈሉ ሲያሳንፁ አሥራ አንደኛውን (ቤተ አባ ሊባኖስን) ለባላቸው ክብር ሲሉ ያሠሩት እቴጌ መስቀል ክብራ ናቸው፡፡ የቤተ አባ ሊባኖስ ቤተ ክርስቲያን ሦስት በሮች አሉት:: ዋናው ደጃፍ ከደቡብ ወደ ሰሜን የሚወጣ ሲሆን ሁለተኛውና ሦስተኛው ፊት ለፊት አይታዩም፡፡ በዚህ በቤተ ሊባኖስ ቅዱስ ላሊበላ ባለቤት ቅድስት መስቀል ክብራ ከዚህ ዐለም በሞት ከተለዩ በኋላ  ከቤተ ሊባኖስ በስተምሥራቅ በግምብ ቤተ መቅደስ በጥርብ ድንጋይ ተሠርቶላቸው ሲኖር ቤተ መቅደሱ በእርጅና ምክንያት ሰለፈረሰ ታቦተ መስቀል ከብራ በቤተ ሊባኖስ እንድትቀመጥ ተደርጓል፡፡ በአጠቃላይ የቤተ ሊባኖስ ቤተ ክርስቲያን ከውጭ ሆኖ ሚመለከተው ታቦት የተሸከመ መልካም ቄስ ይመስላል:: የቤተ አባ ሊባኖስ ታቦተ ሕግ ወደ ቤተ መቅደሱ የገባው ጥር ፫ ሲሆን ቅዳሴ ቤተ ክርስቲያኑም  በዚሁ ዕለት ተከብሮ ይውላል፡፡
በሌሎቹ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የጻድቃንና የሰማዕታት፣ የደናግልና የመነኮሳት፣ የቅዱሳንና የመላእክት፣ /የእነ ሚካኤልና የእነ ገብርኤል..../ የጌታችንና የእመቤታችን ሥዕላት ሲታዩ በቤተ አባ ሊባኖስ ግን በመካከል የንጉሡ የዓፄ ላሊበላ በቀኝና በግራ ደግሞ የእቴጌ መስቀል ክብራና የጻድቁ የአባ ሊባኖስ አባ መጣዕ መልኮች ተሥለው መታየታቸው እቴጌ መስቀል ክብራ ያደረጉትንና የፈጸሙትን ድንቅ ሥራ ያመለክተናል፡፡  
ንግሥቲቱ ላሊበላ ውስጥ በጥቂት አብያተ ክርስቲያናት ግንባታ ላይም ተሳትፈው የበኩላቸውን አሻራ አስቀምጠዋል፡፡ በሥጋዊውና በመንግሥታዊው አመራር ከባለቤታቸው ባልተናነሰ ሁኔታ፣ በመንፈሳዊውና በሃይማኖታዊው ሥራም ከቤተ ክርስቲያን አባቶች በላቀ ደረጃ ለሀገራቸው ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረጉት እቴጌ መስቀል ክብራ በተወለዱበት በላስታና በትግራይ አካባቢ ገዳም ቆርቁረዋል። ይህም ሥራቸው “የተከበሩ ንግሥት’’ አሰኝቷቸዋል። እንዲያውም መስቀል ክብራ ከኢትዮጵያ ቅዱሳት አንስት ጋር ተመድበው ይታያሉ። በዚህ ረገድ በሕይወት ታሪካቸው ዙሪያ የተፃፉና ገና ያልታተሙ ሁለት ሥራዎች እንደሚገኙ ሲታወቅ፣ አንደኛው ጽሑፍ ላሊበላ አጠገብ በሚገኘው በገነተ ማርያም ቤተክርስቲያን ውስጥ፤ ሁለተኛው ደግሞ በአክሱም ጽዮን እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ:: ለመልካም ሥራቸውና ስማቸው መታሰቢያ እንዲሆን በማሰብ በትግራይ ሽሬ አውራጃ መደባይ ታብር በተሰኘ ቦታ ቤተክርስቲያን ታንፆላቸዋል፡፡ ፅላትም በስማቸው ተቀርጾላቸዋል፡፡ ንግሥቲቱ በመስቀል ጦርነት ምክንያት ሙስሊሞች ከውጭ አገር እየፈለሱ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በእግዚአብሔር ስም እየተቀበሉና በፍቅር እያስተናገዱ በሰላም እንዲቀመጡ አድርገዋል። የመጨረሻ ዘመናቸውን ያሳለፉትም ዓለምን ንቀው፣ መንነው፣ ገዳም ገብተው በጾምና በጸሎት በቀኖና በመፅናት ነው፡፡ የዕረፍት በዓላቸውም ሐምሌ 27  ቀን በየዓመቱ በታላቅ ድምቀት ይከበርላቸዋል፡፡
እቴጌ መስቀል ክብራ በዓለማዊ ሕይወት ፖለቲካን፤ በመንፈሳዊ ሕይወት ደግሞ ሃይማኖትን አጣምረው የያዙ ጠንካራ የሴት መሪ ነበሩ። መስቀል ክብራ ማለትም መስቀል ክብሯ ሞገሷ ነው ማለት ነው:: ለባለቤታቸው ለዓፄ ላሊበላ ታማኝ ሴት እንደነበሩ መልካም ሥራቸውን በሚዘክርላቸውና ለመታሰቢያቸው በተደረሰላቸው ገድልና በላሊበላ የመንበረ መቃብር ታሪክ  ላይ ተጽፎ  ይገኛል፡፡ ስለ መስቀል ክብራ የሚተርከው ገድልና ስለ ናዖድ ሞገሳ የሚያትተው ግለታሪክ፣ ለቤተ መድኃኔ ዓለም በተሰጠው ቅዱስ ወንጌል መጽሐፍ ላይ ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ የመስቀል ክብራ ግለ ታሪክ በ16ኛው ክፍለ ዘመን መኻከል ላይ እንደተደረሰም ይገመታል፡፡
 የመስቀል ክብራ ግለ ታሪክ  ስለ ሕይወታቸው፤ የተወሰነ ነገር ይፈነጥቃል:: ነገር ግን ጸሑፉ ስለ መስቀል ክብራ ቤተሰብ ሁኔታ ማለት ስለ ዘመዶቻቸው  ማንነት፤ከማን እንደተወለዱ፤ የየት አካባቢ  ተወላጅ እንደሆኑ ወይም ስለ ሕይወታቸው  ፍጻሜ፤ ስለ አሟሟታቸው አይገልጥም:: ጽሑፉ የሚያትተው መስቀል ክብራ ላሊበላን በስደት ዘመናቸው እንዴት እንዳገቧቸው፤ ላሊበላም በስደት ወደ ኢየሩሳሌም ሔደው እንደነበረ ብቻ ነው:: መስቀል ክብራ በዚህ ውስጥ ብቻቸውን በረሃ ውስጥ ሆነው ላሊበላ በናዝሬት ማርያም ስለ አዩት ባህላዊና ሃይማኖታዊ አኗኗር በማሰብ ነበር:: በ19ኛው ክፍለ ዘመን በተጻፈው በዜና ላሊበላ ገለጻ መሠረት ደግሞ እቴጌ መስቀል ክብራ ቅዱስ ላሊበላን ይጠብቋቸው የነበረው መደባይ በተባለው አካባቢ ሆነው ነው፡፡ መደባይ ትግራይ ውስጥ የሚገኝ ቦታ ነው:: ቅዱስ ላሊበላ ዘውድ ጭነው ከነገሡ በኋላ ደግሞ ታሪኩ የበለጠ እየተቆራረጠ ይነገር ጀመር፡፡ በዚያ ዘመን ደራሲው የቅዱስ ላሊበላንና የእቴጌ መስቀል ክብራን ታሪክ ከዓፄ ነአኩቶ ለአብ ታሪክ ጋር እያዛመደና እያዛነቀ፤እየቀነጫጨበ  ጽፏል፡፡ ንግሥት መስቀል ክብራ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅድስና ማዕርግ ስለአገኙ ‘ቅድስት’ ተብለዋል፡፡


Read 819 times