Tuesday, 31 March 2020 00:00

መጋቢት 28/1928 ዓ.ም ስናስብ

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

   ከአድዋ ጦርነት በኋላ ለአርባ ዓመታት ተኝተው እንቅልፋቸውን ሲለጥጡ የነበሩት ኢትዮጵያዊያን፣ ለትናንቱ መደፈር ምን እንዳጋለጣቸው ለማሰብ እና ከስህተታቸው ለመማር ተነስተዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ዛሬም ከአዚማቸው የተላቀቁ አይመስልም፡፡
ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ለመውረርና ማስገበር ማሰብ የጀመሩት በ1924 ዓ.ም ላይ ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ በጉዳዩ ገፍተውበት ወታደራዊ ዝግጅታቸውን አጠናከሩ፡፡
እጅግ በከፍተኛ ገንዘብ መድበው በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የጦር አይሮፕላኖች አመረቱ:: ልዩ ልዩ መጠን ያላቸው በሺህ የሚቆጠሩ የጦር ሜዳ መኪናዎች ሠሩ፡፡ መድፎች ታንኮችና መትረየሶች በገፍ ተፈበረኩ፡፡ የተለያዩ መጠን ያላቸው ከአየር ወደ ምድር የሚወረወሩ ቦምቦችና የመርዝ ጋዞችም አዘጋጁ፡፡ የመርዝ ጋዙ እንዲያስከትል የተፈለገውንና ያስከተለውን ጉዳት፤ “ጋዙ ዝም ብሎ ሞት አልነበረም፡፡ ጋዙ የማይታይና የማይዳሰስ፣ አይን እያየ የሰው ገላ በቁም የሚያፈርስ፣ ሽታው የሚሰነፍጥ፣ ሰተት ብሎ ወደ ሳንባ የሚገባ፣ ገላ ላይ ተጣብቆ እጅን የሚበጣጥስና እየቆራረጠ የሚጥል፣ ወታደሮቹን መሣሪያቸውን ዓይናቸው እያዩ መጠቆም እንዳይችሉ የሚያደርግ፣ እጅ በእጅ ፊት ለፊት መዋጋት በለመደው ጦር ላይ የወረደ መዓት ነበር” በማለት ቀይ አንበሳ ተብሎ በተረጐመው መጽሐፍ ላይ ኮሎኔል አሌክሳንድሮቮ ደል ባዬ ይገልጠዋል፡፡
ከጣሊያንና ከቅኝ ግዞት አገሮቻቸው ማለትም ከሊቢያ፣ ከጣሊያን፣ ከሶማሌ ላንድና ከኤርትራ ለአዘጋጁት አምስት መቶ ሺህ እግረኛ ጦራቸው በጣም የተሻሻለ የነፍስ ወከፍና የቡድን መሣሪያ ከማስታጠቃቸው በላይ፣ ከአንድ ቢሊየን ሰባት መቶ ሚልዮን በላይ ጥይት በመጋዘኖቻቸው ከምረዋል፡፡
በዚህ ላይ በልዩ ልዩ ሙያና በሃይማኖት መልዕክተኛነት ስም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ በመላዋ ኢትዮጵያ ከዳር እስከ ዳር ተሰማርተው የነበሩት የስለላ ሰዎቻቸው ያከማቹት መረጃ፣ ከዚያ መረጃ በመነሳት የተሠራ እያንዳንዱን ተራራ ወንዝና ሸለቆ የሚያሳይ በቁጥር የማይገለጥ በእያንዳንዱ የሠራዊት እጅ የገባ የጦር ሜዳ ካርታ አለ፡፡
እየቆየ ሲሄድ ቢከሸፍና እንዳለበት ባይሳካም ጣሊያኖች ኢትዮጵያዊያንን በዘርና በሃይማኖት ከፋፍለው አንደኛውን በሌላኛው ላይ ለማስነሳትም ሠርተዋል፡፡ መንግሥትና ሕዝብን ሆድና ጀርባ ለማድረግም ጥረዋል፡፡ ለጣሊያን የፕሮፖጋንዳ ሰለባ ከሆኑት ውስጥ የትግራይ ደጃዝማች ኃይለሥላሴ ጉግሣ እና የጐጃሙ ደጃዝማች ገሠሠ ባለው ለአይነት መጠቀስ ይኖርባቸዋል፡፡
በየመልኩ እራሳቸውን ለወረራ ያዘጋጁት ጣሊያኖች መስከረም 21/1928 ዓ.ም የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው በሰሜን ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ አካባቢዎችን ያዙ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት መስከረም 22/1928 ዓ.ም የክተት ጥሪ ለሕዝቡ አደረገ:: የአካባቢው ደጃዝማቾች ከመሐል አገር ጦር እስከሚደርስላቸው ድረስም ጠላትን ለመከላከል አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ሲያደርጉ ቆዩ፡፡
ቀድሞ የደረሰው በራስ እምሩ፣ በራስ ሙሉጌታና በራስ ካሣ የሚመራው ጦር ከጣሊያኖች ጋር በተፋለመባቸው የጦር ሜዳዎች ከፍተኛ ድል ያስመዘገበ ቢቆይም፣ ንጉሠ ነገሥቱ ተከታትሎ እንዲያጠቃ በሰጡት ትእዛዝ ምክንያት በአገኘው አጋጣሚ እንዲያጠቀም ሆነ፡፡ ወደፊት አለመገስገሱ ለጣሊያኖች መልሶ መደራጀትና ማጥቃት በየጊዜው በማገልገሉ በአሸነፈበት የጦር ሜዳ ተመልሶ ተሸናፊ ለመሆን እና ወደኋላም ለማፈግፈግ ተገደደ፡፡
ከሁት ወር ላላነሰ ጊዜ ደሴ ላይ የቆዩት ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለሥላሴ በመኪናና በበቅሎ ተጉዘው መጋቢት 12/1928 ዓ.ም ሃይ ከተባለ ቦታ ደረሱ፡፡ ራስ ካሣና ራስ ስዩም የተረፈ ጦራቸውን ይዘው ከንጉሥ ተገናኙ፡፡ እነሱና ሌሎች የጦር መሪዎች በተገኙበት መጋቢት 19/1928 ዓ.ም በተደረገ ስብሰባ ጦርነቱ መጋቢት 21/1928 እንዲደረግ ተወሰነ፡፡ ራስ ጌታቸው አልተሰባሰበልኝም ስለአለና የዋጅራ ሰዎችም ከንጉሠ ሠራዊት ጐን ለመሰለፍ ቃል ስለገቡ እነሱን ለመጠበቅ የዚያን እለቱ ጦርነት ሳያደርግ ቀረ፡፡
ይህ መዘግየት ያበሳጨው አንድ የሐማሴን ሰው ለንጉሡም ሆነ ለጣሊያኖች እየመጡላችሁ ነው የሚል መረጃ ሰጥቶ ሁለቱም ለውጊያ እንዲንቀሳቀሱ አደረገ:: በእሱ የርችት ተኩስ ጦርነቱ ተጀመረ፡፡ ንጉሠ እንደ አንድ ወታደር ግንባር ውስጥ ገበታው የታሳተፉበት የማይጨው ጦርነት መጋቢት 22/1928 ዓ.ም ተጀምሮ በአንድ ቀን ተጠናቀቀ፡፡
በጦርነቱ ላይ ሃምሳ አንድ ሺህ ኡትዮጵያዊያን መሰለፋቸውን ንጉሠ ነገሥቱ በጦርነቱ ዋዜማ ላይ ለማግርማዊት እቴጌ መነን ባስተላለፉት መልዕክት ገልጠዋል፡፡
ይህን መረጃ ጣሊያኖች አስቀድመው ያገኙት በመሆኑ እራሳቸውን ለማዘጋጀት አገልግሏቸዋል፡፡ የንጉሡ የቴሌግራም ግንኙነት በጣሊያኖች የመረጃ ክፍል ያላቋረጠ ክትትል ውስጥ የወደቀ መሆኑ አሳዛኙ የጦርነቱ ገጽታ መሆኑም ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡
“መጀመሪያ የማይጨው ምሽጋችን እንደሌላው ጊዜ በሽቦ አልታሠራም፡፡ የፈንጂ መከላከያም አልቀበርንም፡፡ በጥሩ ሁኔታ ቆፍረን ግንድ ረብርበን ያበጀነው ምሽግ ነው:: ይህን ማድረግ የቻልነው ኢትዮጵያዊያን ምክር እየለዋወጡ ጦርነቱን ለመጀመር ስለዘገዩ ነው” የሚለውን የቶሊዘን ምስክርነት ይዘን፣ የኢትዮጵያ ጦር ያደረገውን ተጋድሎ እንይ እሱን የሚነግረን ደግሞ ኮሎኔል አሌካንድሮሽ ደል ባዬ ነው:: እንዲሁ ይላል:: “አቢሲኒያውያን ለሞትና ለአደጋ ፍራቻ የላቸውም:: ከጠላት ወደሚከሰተው ጥይት ያለረፍትና ያለ ማቋረጥ ከሚገደለው የሰው ብዛት በስተቀር ይህ ነው የሚባል ከጠላት ጋር የሚወዳደር ሌላ ነገር የላቸውም፡፡ የጥይት እርሳስ ያረግፋቸዋል፡፡
እነሱ ግን የወደቀው ወድቆ የተረፈው ሳይቆም በቀጥታ ወደ ጥይቱ መውጫ አፈሙዝ ይገሰግሳሉ:: ይጠርጋቸዋል፤ የውስጥ አካላቸውን ይበጣጥሰዋል ወይም ጭንቅላታቸውን በመቶ ቁርጥራጭ ይበትነዋል፡፡ እነሱ ግን የወደቀው ወድቆ የተረፈው ሳይቆም ወደፊት ይገሰግሳል:: በወንድሞቻቸው ሬሳ እየተረማመዱ ወደፊት ይሄዳሉ:: ምንም አይነት ጥይት ይህንን ህልም የሚመስል ሩጫ ይህን እልህ የተሞላበት ግስጋሴ አንድ ስንዝር እንኳ ወደኋላ ሊያስቀረው አይችልም፡፡”
በዚህ መንገድ የጐረፈው ጦር ከአምስት ያላነሱ የጣሊያኖች ምሽጐች ሰብሮ ገባ፡፡
ዘመናዊ ስልጠና ያገኘው የክቡር ዘበኛ ጦር ደግሞ በወገን ጦር የተኩስ ሽፋን የታገዘ ተጠግቶ የጣሊያኑን 10ኛ ባታሊየን በመግደልና በማቁሰል ከጥቅም ውጭ እንዳደረገው በማለት ጄኔራል ቦይለዮ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡
ጦሩ እዚህ ውጤት የበቃው ከላይ 150 የጦር አይሮፕላኖች እየተመላለሱ ከአየር የሚዘንቡበትን የመርዝ ጋዝ ቦንብና የመትረየስ ተኩስ ከምድር የሚወርድበትን እግርኛ ጦር መድፍና መትረየስና የነፍስ ወከፍ ተኩስ ጥይት አካለን በመገበር ተቋቁሞ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
እንዲህ የኢትዮጵያ ጦር ሙሉ ሕይወቱንና አካሉን ገበሮ ለማሸነፍ ቢዋደቅም ጦርነቱ በሚፈለገው ሳይሆን በማይፈልገው መንገድ ተደምድሟል፡፡ የማይጨውን ጦርነት ፍፃሜ ለመንገር ደግሞ ከአበሻ ጀብዱ ፀሐፊ ከአዶልፍ ፐርክሰን፣ የተሻለ ሰው የሚጠቀስ አይኖርም፤ እጠቅሳለሁ፤
“እድሜ ለአራተኛ ረድፈኞች (አብቹንና የወላይታን ጦር ማለቱ ነው) የጣሊያንን ጦር ወገቡ ላይ ሰብረው የሚገባበት አሳጡት፡፡ የሶስቱ ራሶች (ራስ ስዩም ራስ ካሣና የራስ ጌታቸው ማለቱ ነው) ጦር የጣሊያንን ዋና ምሽግ ሰብሮ ገባ:: ድል በኢትዮጵያ እጅ የገባች መሰለች፡፡ በዚያች ቅጽበት አድዋ ሊደገም የሰዓታት ልዩነት ሲቀረው፣ እነዚያ ከሃዲዎች ሪያዎችና አዘቦዎች ድሉን በእጅ  ሊያስገባ የተቃረበውን የገዛ ወንድማቸውን ከጀርባ ወጉት ጨፈጨፉት፡፡
ድል በእጁ ለመጨበጥ ወደፊት የገሠገሰውን የእናታቸውን ልጅ ድል ነሱት::”
አዎ የኢትዮጵያ ጦር በዚህ አውደ ውጊያ በገዛ ወገኑ ተጠቅቶ ድል እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈሉን ማንም ሊክደው አይገባም፡፡
ለኢትዮጵያዊያን መሸነፍ ዋና ምክንያት መከፋፈልና በአንድ አለመቆም መሆኑ ሊሠመርበት ያስፈልጋል፡፡ እንደኔ የዛሬው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፀሎት ከወገን ጠላት ሰውረኝ መሆን አለበት፡፡
ሌላም አለ መሠልጠንን የሚመኝ ልቦና መንፈስ ስጠኝ፡፡
ሁሉንም መጋቢት 22/1928 ዓ.ምን እያሰብን፡፡  

Read 7896 times