Saturday, 07 July 2012 09:26

የምናደንቀው፤ የአትሌቱን ብቃት ነው ወይስ ሃይማኖቱን?

Written by  አለሙ ከድር
Rate this item
(1 Vote)

ለፊዚክስ ትምህርት ጠርቶ ሃይማኖትን መስበክ ግን፤ ተገቢ አይደለም። ተማሪዎቹኮ የተለያየ ሃይማኖትን የሚከተሉ ናቸው። ፊዚክስ ለማስተማር ቃል ገብቼላቸው ፍቃደኛ ከሆኑልኝ በኋላ፤ ክፍል ውስጥ አስገብቼ የራሴን ሃይማኖት መስበክ ብጀምር፤ ቃል እንደማፍረስና እንደማጭበርበር አይቆጠርም? ህገወጥ መሆን አለመሆኑን እንርሳው። ግን፤ ቢያንስ ቢያንስ የስነምግባር ጉድለት ነው - የቅንነት እጦት። ለዚህም ነው፤ የሃይማኖት ነገር አለቦታው ሲነሳ ተገቢ የማይሆነው። “ፈጣሪ ያዳላል እንዴ? - ያልተፈለገ ጥያቄ” በሚል ርእስ ነበር ፅሁፌን ያቀረብኩት። ባለፈው ሳምንት የአዲስ አድማስ እትም ላይ የወጡ ሁለት ፅሁፎች በበኩላቸው፤ “ፈጣሪ መኖሩን እንመን” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። በእርግጥ አላስፈላጊ ስድብና ውግዘትም ጨምረውበታል። ያው፤ የተለመደ የአገራችን ባህል ነው። እንዲያም ሆኖ፤ ውይይት መፈጠሩ መልካም ነው። ችግሩ ምን መሰላችሁ? ምላሾቹ ከጥያቄው ጋር ብዙም አይገናኙም።

“ፈጣሪ ያዳላል እንዴ?” የሚል ጥያቄ ሲመጣ፣ “በፈጣሪ እንመን” ብሎ መናገር፤ ፈፅሞ ትክክለኛ ምላሽ ሊሆን አይችልም። “እኔ የፈጣሪ ተቆርቋሪ ነኝ፤ አንተ ግን በፈጣሪ አታምንም” በሚል የውግዘት ዳርዳርታ፤ ጥያቄውን ለ”መሸወድ” ተፈልጎ ከሆነ ጥቅም የለውም። የጥያቄውን አመጣጥ ታስታውሱ እንደሆነ፤ በየቦታውና አለቦታው የሃይማኖት ጉዳይ እየበዛና እየገነነ ከመምጣቱ ጋር የተያያዘ ነው። እየጎላ ላለው የአክራሪነት አደጋ ፊት እየሰጠነው እንዳይሆን በመስጋትም ነው፤ “ፈጣሪ ያዳላል እንዴ?” የሚለውን ጨምሮ ሶስት ዋና ዋና ጥያቄዎችን በፅሁፌ ያነሳሁት።

አዎ፤ አላስፈላጊ የሃይማኖት ክርክርና ውዝግብ፤ አሳሳቢ የሃይማኖት መቧደንና ፉክክር የመስፋፋቱን ያህል፤ በዚያው ልክ የሃይማኖት ስብከትና ፖስተር በጣም ተበራክቷል። በተገቢው ቦታ የሚካሄድ የሃይማኖት ስብከትና የሚለጠፍ ፖስተር ላይ አንዳችም ጥያቄ አላነሳሁም። የራስን ሃይማኖት መስበክም ሆነ ማዳመጥ፤ “ንክች ሊደረግ የማይገባ መብት” መሆኑንም ገልጫለሁ። አለቦታው የሃይማኖትን ነገር መደንቀርና ስብከት ማካሄድ ግን፤ ጥያቄ ሊነሳበት ይገባል እላለሁ። ምሳሌዎችንም ጠቅሻለሁ።

አትሌቶችና ሌሎች ስፖርተኞች ለሻምፒዮንነት በሚፎካከሩበት የኦሎምፒክ ወይም የእግርኳስ ድግስ ላይ፤ ምርጥ አርቲስቶች በሚሸለሙበት የኪነጥበብ ፌስቲቫል መሃል፤ የቢዝነስ ስኬት በሚወደስበት መድረክ ስር፤ የጎበዝ ተመራቂዎች ሽልማት በሚወሳበት ዘገባ ውስጥ... አለቦታው የሃይማኖት ወይም የእምነት ጉዳይ መነሳቱ ተገቢ ነው?

መቼም ሰዎች በሃይማኖት ቢለያዩም፤ ብዙዎቹ እንደየዝንባሌያቸው አንድ ላይ ተደበላልቀው በስፖርትና በኪነጥበብ ይዝናናሉ፤ በትምህርትና በቢዝነስ መስክ ህይወታቸውን ለማሻሻል ይሞክራሉ። የሃይማኖት ወይም የእምነት ልዩነት ቢኖርም እንኳ፤ በየሙያውና በየመስኩ ስኬታማ ሰዎችን ስንመለከት አድናቆታችንን እንገልፃለን፤ በአርያነታቸው እንነቃቃለን - ለሃይማኖት ልዩነት ቦታ ሳንሰጥ። ታዲያ በዚህ መሃል፤ ኦርቶዶክስ ወይም ፕሮቴስታንት፤ ሱኒ ወይም ሱፊ የመሆን ጉዳይ ቢነሳ ይስማማችኋል? በአጭሩ፤ አለቦታው የሃይማኖት ነገር መነሳቱ ተገቢ ነው ወይ? ይሄ ሁለተኛው ጥያቄ ነው።

በየመስኩና በየሙያው ለምንመለከታቸው ስኬታማ ሰዎች፤ አድናቆታችንን ስንገልፅኮ የሃይማኖት ልዩነት አይገድበንም። ሃይማኖታቸውን ሳይሆን፤ ጥረታቸውንና ፅናታቸውን፤ ብቃታቸውንና ችሎታቸውን ነው የምናደንቀው። አድናቆታችንን ለመግለፅ በተሰበሰብንበት መድረክ፤ አንድ በአንድ እየተነሱ “የስኬቴ ሚስጥር የምከተለው ሃይማኖት ነው” እያሉ ለየራሳቸው ሃይማኖት ቢመሰክሩ ትርጉሙ ምን እንደሆነ አስቡት። “ጥረቴንና ብቃቴን ሳይሆን ሃይማኖቴን አድንቁ፤ ስኬታማ ለመሆን ከፈለጋችሁ የኔን አይነት ሃይማኖት ተከተሉ” እያሉን አይደለም ወይ? - ይሄ ነው ሶስተኛው ጥያቄ።

ሃይማኖትን - በቦታውና አለቦታው

የሃይማኖት ጉዳይ በተገቢው ቦታ መነሳቱ... ምንም አያከራክርም። የሃይማኖት ነገር አለቦታው ሲነሳ ግን፤ በዚያ ላይ እየተበራከተና እየገነነ ሲመጣ፤ ያሳስባል። “አለቦታው” ስል ምን ማለቴ ነው? ... ያው፤ ሳይፈቀድልኝ በጉልበትም ሆነ “በብልጣብልጥነት”፤ የሌላ ሰው ህይወት ላይ የኔን ሃይማኖት ለመጫን ብሞክር ተገቢ እንደማይሆን የምንስማማ ይመስለኛል። በዘፈቀደ የሌላ ሰው ህይወት ውስጥ ጣልቃ ለመግባት ብዬ ስለራሴ ሃይማኖት ካወራሁ፤ ያኔ የሃይማኖት ነገር አለቦታው ተነስቷል ማለት ነው። በፊዚክስ ክፍለ ጊዜ፤ አስተማሪው ስለ መፅሃፍ ቅዱስ ወይም ስለ ቅዱስ ቁርአን ተአማኒነት የሚያወራ ከሆነ፤ ሃይማኖትን አለቦታው እያነሳ ነው።

ሰዎችን ለስብከት በመጥራት ወይም በመጋበዝ፤ በጎዳና ላይም ሆነ በጠረጴዛ ዙሪያ፤ ዛፍ ጥላ ስርም ሆነ አዳራሽ ውስጥ ስብከት ማካሄድ አከራካሪ አይመስለኝም። አንደኛ፤ በማንም አካል በምንም ምክንያት ሊጣስ የማይገባው መብት ነው። አዳማጮቹ አውቀውና ፈቅደው መጥተዋል። ሁለተኛ፤ ሰባኪው ቃሉን አክብሯል - ለስብከት ጠርቶ ሰበከ።

ለፊዚክስ ትምህርት ጠርቶ ሃይማኖትን መስበክ ግን፤ ተገቢ አይደለም። ተማሪዎቹኮ የተለያየ ሃይማኖትን የሚከተሉ ናቸው። ፊዚክስ ለማስተማር ቃል ገብቼላቸው ፍቃደኛ ከሆኑልኝ በኋላ፤ ክፍል ውስጥ አስገብቼ የራሴን ሃይማኖት መስበክ ብጀምር፤ ቃል እንደማፍረስና እንደማጭበርበር አይቆጠርም? ህገወጥ መሆን አለመሆኑን እንርሳው። ግን፤ ቢያንስ ቢያንስ የስነምግባር ጉድለት ነው - የቅንነት እጦት። ለዚህም ነው፤ የሃይማኖት ነገር አለቦታው ሲነሳ ተገቢ የማይሆነው።

ፋብሪካ ውስጥ የስራተኞች ስብሰባ ላይ፤ ስለ ፈጣሪ ረድኤት፤ ስለ ኢየሱስ ጌታነት፤ ስለ ቅዱሳን አማላጅነት፤ ስለ ነብያት ፃድቅነት ከተሰበከ፤ ሃይማኖት አለቦታው ተነስቷል። ሰራተኞቹን የቀጠርኳቸው፤ የራሴን ሃይማኖት ስሰብክ እንዲያዳምጡኝ አይደለማ። በሙያችሁ እየሰራችሁ ክፍያ ታገኛላችሁ ብዬ ከተዋዋልኩና ፈቃደኛ ሆነው ከተቀጠሩ በኋላ፤ ሌላ ነገር ልጫንባችሁ ማለት... የቅንነት እጦት ነው። የሃይማኖት ነገር አለቦታው መነሳቱ ተገቢ አይደለም።

እንግዲህ ተመልከቱ፤ ያነሳሁት ጥያቄ “የሃይማኖት ጉዳይ ማንሳትና መስበክ ተገቢ ነው ወይ?” የሚል አይደለም። ጥያቄውን ልድገመው። “አለቦታው የሃይማኖት ነገር ማንሳትና መስበክ ተገቢ ነው ወይ?” - ይሄ ነው ጥያቄው። እኔ፤ ተገቢ አይደለም ብያለሁ። ሃሳቤን የተቃወሙ አቶ ጌታቸው አበበ ባለፈው ሳምንት የሰነዘሩትን ምላሽ ደግሞ ተመልከቱ። የሃይማኖት ነገርና የፈጣሪ ስም ሲነሣ ስለሚቆጭህ የጭቃ ጅራፍህን በአማኞች ላይ አውርደሃል በማለት ሃሳቤን ተቃውመዋል - አቶ ጌታቸው፡፡ ሌላኛው ፀሃፊ በበኩላቸው በሰጡት ምላሽ፤ “የሀይማኖት ነገር መስማት አልፈልግም ካሉ አማኝ ሕዝብ የሌለበት ፕላኔት ማፈላለግ ግድ ይልዎታል” ብለዋል፡፡

ሁለቱ ፀሃፊዎች የሰነዘሯቸው ምላሾች፤ እኔ ካነሳሁት ጥያቄ ጋር ግንኙነት የላቸውም - በፍሬ ነገር ይለያያሉ። ፍሬ ነገሩኮ፤ የሃይማኖት ስብከትን የመስማትና ያለመስማት ጉዳይ አይደለም። አለቦታው መስበክ ተገቢ መሆኑና አለመሆኑ ላይ ነው ፍሬ ነገሩ። የፈጣሪ ስም ይነሳ ወይስ አይነሳ የሚል አይደለም ጥያቄው። “አለቦታው፤ ለምሳሌ በፊዚክስ ክፍለጊዜና በፋብሪካ ሰራተኞች ስብሰባ ላይ፤ የራሴን ሃይማኖት ለመስበክና ሃይማኖታዊ ንግግር ለማሰማት ብሞክር ተገቢ ነው ወይስ አይደለም?” ይሄ ነው ጥያቄው።

ሁለቱ ፀሃፊዎች፤ “አለቦታው ሲሆንማ ማንኛውም ነገር ተገቢ አይደለም” የሚሉ ከሆነ በሃሳብ ተግባብተናል ማለት ነው። “አይ፤ የትም ቦታ ቢሆን፤ አጋጣሚውን በመጠቀም የራስን ሃይማኖት መስበክ ተገቢ ነው” የሚሉ ከሆነ ደግሞ፤ ተገቢነቱን ለማስረዳት ይሞክሩ። ፍሬ ነገሩን በማዛባትና ጥያቄውን “በማስቀየስ”፤ ውግዘት ለማውረድ መሞከር ግን ጥቅም የለውም። አሃ... የፈጣሪ ስም ሲነሳ ስለማትወድ ነው፤ የሃይማኖት ጉዳይ መስማት ካልፈለግክ አማኝ ወደሌለበት ወደ ማርስ ውጣ ... እንዲህ የፈጣሪ ተቆርቋሪ ወይም የአማኞች ጠበቃ መስሎ መቅረብ ምን አመጣው - ለማስፈራራትና ዝም ለማሰኘት ካልሆነ በቀር።

ማድነቅ - የአትሌቱን ብቃት ወይስ ሃይማኖቱን

ሜዳሊያ ያጠለቀች የስፖርት ሻምፒዮን እና የወርቅ ሃብል የተበረከተላት “ሰቃይ” ተመራቂ፤ ምርጥ አርቲስት የሚል ማእረግ የተሰጠው ተዋናይ እና በድንቅ የቴክኖሎጂ ፈጠራው የተሸለመ ተመራማሪ ... በአጠቃላይ ስኬታማ ሰዎች ሲያጋጥሙን ውስጣችን በደስታና በአድናቆት ቢፍለቀለቅ ተገቢ ነው። ለስኬት የበቁበትን ሚስጥር (ማለትም የጥረትና የብቃት ሰብእናቸውን) ሲነግሩን ደግሞ ከአድናቆት ጋር መንፈሳችን ይነቃቃል። በየተሰማራንበት ሙያ የአቅማችንን እንድንጥር በአርአያነት ፈር ይቀዱልናል።

በጥረትና በስራ አማካኝነት ከፍተኛ ብቃትን መጎናፀፍና ትልቅ ስኬትን መቀዳጀት እንደሚቻል በቲዎሪ ብቻ ሳይሆን በእውንና በተግባር ስለሚያሳዩን፤ በብሩህ መንፈስ ተነቃቅተን እንበረታታለን። በዚህ መሃል፤ እነዚያ ጀግኖች፤ “ለዚህ ስኬት የበቃሁት በሃይማኖቴ ነው” ብለው ቢነግሩንስ? ደግሞም ብዙዎቹ ነግረውናል - በተለያየ አይነት መንገድ።

ስኬት በጥረትና በስራ የሚገኝ ከሆነ፤ ሁሉም የስራውንና የጥረቱን ያህል ይሳካለታል። ደግሞም ስኬት ይገባዋል። ጥረቱ ያገኘውን ስኬት ለመንጠቅና ለመዝረፍ የሚሞክር አካል መኖር የለበትም። ነፃነት የሰፈነበት የፖለቲካ ስርአት የሚያስፈልገንም በዚህ ምክንያት ነው። የነፃነት ስርአት ማለት፤ የፍትህ ስርአት ማለት ነው - ሁሉም የስራውን ያገኛል ወይም የስራውን ያገኛታል። ስራንና ጥረትን ከመረጥን፤ ስኬትን እንቀዳጃለን። አለመስራትንና አለመጣጣርን ከመረጥንም፤ ያው ውድቀትን እንቀምሳለን።

በሌላ አነጋገር፤ በዘርፊያና በቅሚያ ፍትህን ካላጠፋናት በቀር፤ ህይወታችን በእጃችን ውስጥ ነው - በራሳችን ምርጫና በራሳችን ተግባር የህይወታችንን አቅጣጫ እንመራለን። ለጊዜው ሳንሰራና ሳንጥር ስለቀረን ባይሳካልንና መንፈሳችን ቢዳከም እንኳ፤ የስኬታማዎቹን አርአያነት ተከትለን መንገዳችንን ማስተካከል እንችላለን። በዚህ ምክንያት ይሆን እንዴ፤ ስኬታማ ጀግኖችን የምናደንቀው?

በስፖርትም ሆነ በኪነጥበብ፤ በትምህርት ሆነ በቢዝነስ፤ በእጅጉ የምናደንቃቸው የስኬት ሰዎች፤ የተለያየ ሃይማኖትና እምነት ሊኖራቸው ይችላል። ይህንን እንደ ችግር እንቆጥረዋለን እንዴ? እኔ አልቆጥረውም። ይህንን ወይም ያንን ሃይማኖት የሚከተሉ መሆናቸው ለውጥ የለውም። ዋናው ነገር፤ በጥረታቸውና በብቃታቸው ስኬታማ መሆናቸው ነው። የአድናቆት ስሜት የሚፈጠርብንም በሌላ ምክንያት አይደለም። ስኬታቸውና ውጤታቸው፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የጥረታቸውና የብቃታቸው ማረጋገጫ ስለሆነ ነው የምናደንቃቸው።

በውርስ ቢሊዮነር የሆኑ ሰዎች፤ አልያም በእጣ ኮንዶምኒየም የደረሳቸውና በሎተሪ ሚሊዮን ብር ያገኙ ሰዎች ሲያጋጥሙን ያን ያህልም የአድናቆት ስሜት የማይፈጠርብን ለምን ይሆን? በሌላ ምክንያት አይደለም። ውርስና ሎተሪ፤ ያን ያህልም የጥረትና የብቃት ጉዳይ ስላልሆኑ ነው።

በአጭሩ፤ ጀግኖችን ማድነቅ የሚገባን፤ ሃይማኖታቸው ምንም ሆነ ምን፤ በራሳቸው ጥረትና ብቃት የተቀዳጁትን ስኬትና ውጤት በማየት ነው - ሃይማኖታቸውን ነው የምናደንቀው ካልተባለ በቀር። እንደ ስኬታማዎቹ ሰዎች ሁሉ፤ አድናቂዎቹም የተለያየ የሃይማኖት አይነት እንደሚከተሉ አትዘንጉ። ግን የሃይማኖት ልዩነት ምንም ለውጥ አያመጣም - ምርጥ አትሌቶችንና አርቲስቶችን የምናደንቀው ሃይማኖታቸውን እያየን ነው ካልተባለ በቀር።

ታዲያ በሃይማኖት ተከታይነት ሳይሆን፤ በጥረትና በብቃት የሚገኝ ስኬትን ለማድነቅ ብዙ ሰዎች በተሰባሰቡበት አዳራሽ ወይም ሚዲያ ላይ፤ የሃይማኖት ጉዳይና የእምነት ልዩነት መነሳት ይገባዋል? “ለስኬት፣ ለሽልማት፣ ለሻምፒዮንነት የበቃሁት፤ በሃይማኖቴ ምክንያት ነው” የሚል ሃሳብ ከስኬታማዎቹ ሰዎች አንደበት መውጣቱ ተገቢ ነው? እንግዲህ አንዱን መምረጥ ይኖርብናል።

በአንደኛው አማራጭ ከሄድን፤ የአትሌቱን ወይም የአርቲስቱን ጥረትና ብቃት እናደንቃለን - እዚህ ላይ የሃይማኖት ልዩነት ቦታ አይኖረውም - ሃይማኖቱ ምንም ሆነ ምን የጥረቱንና የብቃቱን ያህል እንደሚሳካለት የምንገነዘብ ከሆነ።

በሁለተኛው አማራጭ ከሄድን ደግሞ፤ አትሌቱና አርቲስቱ የሚከተሉትን የሃይማኖት አይነት እያጣራን ማድነቅ ይኖርብናል - እዚህ ላይ የጥረትና የብቃት ጉዳይ ቦታ አይኖረውም - የስኬቱ መንስኤ ሃይማኖት እንደሆነ ካመንን። ከሁለቱ ተቃራኒ አማራጮች መካከል አንዱን ስንመርጥ፤ ወደ መጨረሻው ጥያቄ እንሸጋገራለን።

“ፈጣሪ ያዳላል ወይስ አያዳላም?”

የስኬት መንስኤ ጥረትና ብቃት አይደለም የምንል ከሆነና፤ የስኬት ምንጭ መለኮታዊ ሃይል እንደሆነ የምናምን ከሆነ፤ “ፈጣሪ ያዳላል እንዴ?” ከሚለው ጥያቄ ጋር መፋጠጥ አይቀርልንም። “በፈጣሪ እንመን” ብሎ መናገር፤ ለጥያቄው ምላሽ አይሆንም። ጥያቄም፤ “በፈጣሪ ታምናለህ ወይስ አታምንም?” የሚል አይደለማ።

ምናልባት፤ “ፈጣሪ ያዳላል ወይስ አያዳላም?” በሚል ጥያቄውን ብናሻሽለው መልካም ሳይሆን አይቀርም። “ፈጣሪ የሚያዳላ ከሆነ፤ ለየትኞቹ የሃይማኖት ተከታዮች ያዳላል? ከእነዚሁ ውስጥስ ለየትኞቹ ሰዎች ያዳላል?” የሚሉ ተደራራቢ ጥያቄዎችንም ማንሳት ይቻላል።

“ፈጣሪ አያዳላም፤ ሁሉም ሰው የስራውንና የጥረቱን ያህል ይሳካለታል” የሚሉ ሰዎች ካሉ፤ ሃሳባቸውን ያስረዱን። “ፈጣሪ ያዳላል” የሚሉ ሰዎችም ሃሳባቸውን ያብራሩልን። “በፈጣሪ እንመን፤ 70 ሚሊዮን ህዝብ አማኝ ነው” ብሎ መናገር ግን፤ ለጥቄው መልስ አይሆንም።

በእርግጥ ለጥያቄው ቀጥተኛ ምላሽ አገኛለሁ ብሎ መጠበቅ ትንሽ ያስቸግራል። ከመነሻውምኮ፤ “ያልተፈለገ ጥያቄ” ነው የቀረበው። እናም፤ “ጥያቄው ወዲህ፤ ምላሹ ወዲያ” ተለያይተው በፍሬ ነገር መራራቃቸው ሲታይ፤ “እውነትም ያልተፈለገ ጥያቄ” ያስብላል።

ምናልባት ውይይቱ፤ ከስድብና ከውግዘት በፀዳ መልኩ፤ በጨዋነትና በቅንነት እንዲቀጥል ቢደረግ፤ በፍሬ ነገር ሳንራራቅ ቁምነገረኛ ሃሳቦችን መለዋወጥ እንችል ይሆናል። ለዚህም ነው ውይይት መፈጠሩ መልካም ነው ያልኩት። ደግሞስ፤ በስድብና በውግዘት ጠያቂ አእምሮዎችን ለማፈን መሞከር ምን ይረባል? አፈና ለመንግስትም አልጠቀመው - ሁሌም ዜጎቹን በጥርጣሬ እያየ ይደናበራል። አፈና ለአገሪቱ አልጠቀማትም፤  በድህነትና በፍርሃት ትደነዝዛለች። ከጥያቄዎች ያመለጥን እየመሰለን፤ አራምባና ቆቦ የሚረግጥ ምላሽ ብንሰጥ፤ ራሳችንን ከ”መሸወድ” ያለፈ ጥቅም የለውም።

“ፈጣሪ ያዳላል እንዴ? - ያልተፈለገ ጥያቄ” በሚል ርእስ ነበር ፅሁፌን ያቀረብኩት። ባለፈው ሳምንት የአዲስ አድማስ እትም ላይ የወጡ ሁለት ፅሁፎች በበኩላቸው፤ “ፈጣሪ መኖሩን እንመን” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። በእርግጥ አላስፈላጊ ስድብና ውግዘትም ጨምረውበታል። ያው፤ የተለመደ የአገራችን ባህል ነው። እንዲያም ሆኖ፤ ውይይት መፈጠሩ መልካም ነው። ችግሩ ምን መሰላችሁ? ምላሾቹ ከጥያቄው ጋር ብዙም አይገናኙም።

Read 3925 times Last modified on Saturday, 07 July 2012 09:34