Saturday, 28 March 2020 11:43

በኮሮና ጉዳይ አለም አፍሪካን እንዲደግፍ ጠ/ሚኒስትሩ ጥሪ አቀረቡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

   “ቫይረሱን በአፍሪካ መቆጣጠር ካልተቻለ መልሶ ሁላችንንም ያጠፋናል”


             ‹‹የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በአፍሪካ ምድር ካልተሸነፈ ተመልሶ ሁላችንንም ያጠፋናል›› ያሉት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ የአለም ሀገራት ቫይረሱን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት አፍሪካውያንን እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በ‹‹ፋይናንሻል ታይምስ›› ጋዜጣ ላይ ለንባብ በበቃው የጠ/ሚኒስትሩ ጽሑፍ፤ የቫይረሱ ስርጭት በአፍሪካ ላይ የደቀነው ስጋት ከሌላው አለም የከፋ መሆኑን ጠቁሞ ቫይረሱን ለመቋቋም ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአህጉሪቱ ሀገራት አቅሙ እንደሌላቸው አመልክተዋል - ዶ/ር ዐቢይ፡፡
ለዚህም የአለም ሃያላን ሀገራትና የአፍሪካ ጉዳይ የሚገዳቸው በሙሉ ቫይረሱን በመዋጋት በኩል ከአፍሪካ ጐን እንዲሰለፉ ጠይቀዋል:: ይህን ሲያደርጉም የራሳቸውን ህልውናና ደህንነት እያስጠበቁ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል ብለዋል - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በአለም ላይ የተለያዩ ስልቶች እየተተገበሩ እንደሆነ በማውሳትም፤ ሌላው አለም ዜጐቹን ለመጠበቅ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ልክ የአፍሪካ ሀገራት ትርጉም ያለው እንቅስቃሴ ለማድረግ የአቅም ውስንነት ጋሬጣ እንደሚሆንባቸው ጠ/ሚኒስትሩ በጽሑፋቸው አስገንዝበዋል፡፡
ፈጽሞ ድንበር የማይገድበው አደገኛ ወረርሽኝ መሆኑ የተረጋገጠው ኮሮና ቫይረስ በተናጥል የሃገራት ውሣኔና ጥንቃቄ ብቻ ከምድረ ገጽ የማይጠፋ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ዐቢይ፤ ‹‹ቫይረሱ በአፍሪካ ምድር ካልተሸነፈ በድጋሚ ነጥሮ ወደ ሌላው አለም ይመለሳል›› ብለዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የቫይረሱን ስርጭት መግታትና ማሸነፍ የሚቻለው አለማቀፋዊ የተቀናጀ አመራር  መተጋገዝ ሲኖር ነው፤ ከዚህ ውጪ ከሆነ ግን በአፍሪካ ዘግናኝ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፤ ተመልሶም ለአለም ይተርፋል” ብለዋል - በጽሁፋቸው፡፡
ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ባለፉት 20 ዓመታት ያስመዘገበችውን ስኬት ጠቅሰው፤ ይህ ስኬቷ ግን እንደ ኮሮና ያሉ ወረርሽኞችን ለመቋቋም የሚያስችላት እንደማይሆን ገልፀዋል - ሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራትም ተመሳሳይ ወይም ከኢትዮጵያ ያነሰ አቅም እንዳላቸው በመጠቆም::
‹‹ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት መልካም የሚባል እድገት በጤናው ዘርፍ አስመዝግባለች፤ ነገር ግን እንደ ኮሮና ያሉ በሽታዎችን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም አልገነባንም፤ በሽታውን ለመከላከል የሚመከረው የእጅ መታጠብ ተግባር እንኳ ለኛ ቅንጦት ይሆናል፤ ምክንያቱም ከአጠቃላይ ህዝባችን ግማሽ ያህሉ ንፁህ ውሃ አያገኝም›› ሲሉ ጽፈዋል፡፡
“ከወጪ አንፃር እርካሽ የሆነውን የማህበራዊ መራራቅ እንኳ በማህበረሰባችን ዘንድ ተግባራዊ ለማድረግ አዳጋች ነው” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የኛ ማህበረሰብ የአኗኗር ዘይቤ በእጅጉ የጋርዮሻዊነት የሚንፀባረቅበት በርካታ የቤተሰብ አባላት አብረው ክፉና ደጉን እየተካፈሉ የሚኖሩበት፣ በጋራ በአንድ ገበታ የሚመገቡበት ባህል ነው ያለን” በማለት አስረድተዋል፡፡
የግብርና ሥርዓቱም ያለዘመና ወቅትና ዝናብን ጠብቆ የሚከናወን እንደመሆኑም በሽታውን መቆጣጠር ካልተቻለ ሊፈጥር የሚችለው አደጋ የሚገመት አለመሆኑንም     ጠ/ሚኒስትሩ አውስተዋል፡፡
የቫይረሱ ስርጭት በኢኮኖሚ ላይ የሚፈጥረውን ጉዳት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያጋጠመውን ኪሣራ ጠቅሰው ያስረዱት          ጠ/ሚኒስትሩ፤ አየር መንገዱ ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝና ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት 3 በመቶ የሚሸፍን ገቢ የሚያስገባ እንደነበረ፣ አሁን ግን በረራዎች በመቋረጣቸው ሀገሪቱ ቀድሞ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ እንድታጣ አድርጓታል፤ ይህም ለመድሃኒት መግዣ የሚሆን የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲፈጠር የሚያደርግ አደጋ ደቅኗል ብለዋል:: ይህ አይነቱ አቅም ማጣትና የህልውና አደጋ በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ያንዣበበ መሆኑን ያወሳው የጠ/ሚኒስትሩ ጽሑፍ፤ በሁሉም የአለም ሀገራት ትብብርና እርዳታ በአፍሪካ ያንዣበበውን ስጋት መቅረፍ ካልተቻለና ጠቃሚ እርምጃዎች ካልተወሰዱ፤ የትኛውም የአለም ሀገር ዋስትና እንደማይኖረው ጠቁሟል፡፡
“ሃብታም ሀገራት ድንበራቸውን ቢዘጉ የጉዞ እቀባ ቢያደርጉ ምናልባት ጊዜያዊ ድልን ሊያስገኝላቸው ይችላል እንጂ ዘላቂ ውጤት አያመጣም፡፡ ዘላቂ ውጤት የሚያመጣው በሽታውን በአለም አቀፍ ደረጃ ተባብሮ ማጥፋት ሲቻል ነው” ብለዋል ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
በአሁኑ ወቅት አለም በኮሮና ቫይረስ ተሳስሯል፤ ይህም ሰው ሰራሽ ልዩነቶች፣ የቆዳ ቀለም፣ ፓስፖርት፣ እምነት ቢለያየንም በሰውነት አንድ መሆናችንን ያሳየ ነው ብለዋል፡፡
በኮሮና ቫይረስ የተነሳ የሚሊዮኖች ህይወት አደጋ ላይ መሆኑን በመግለጽም በተለይ የቡድን 20 አባል ሀገራት ለጉዳዩ በተጠናከረ አመራር የታገዘ ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቀዋል፤ ጊዜም እንደሌለ በማስገንዘብ፡፡
የቡድን 20 አባል አገራት ጉባኤም በአለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በኩል ከወዲሁ ቫይረሱን ለመዋጋት የሚያስችል አለማቀፍ ፈንድ ይፋ እንዲያደርጉም፣ ለአፍሪካ ሀገራት የተቀናጀ ድጋፍ የሚደርስበትን መንገድም እንዲቀይሱ ጠይቀዋል፡፡
ቫይረሱን ለመቆጣጠር የሚደረገው ድጋፍም የአለም ህዝብ እውነተኛ ሰብአዊነትና አጋርነት የሚገለጥበት አጋጣሚ ይሆናል ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩ “በፋይናንሻል ታይምስ” ባስነበቡት ጽሑፋቸው አመልክተዋል፡፡   

Read 12613 times