Saturday, 28 March 2020 11:35

“የህብረተሰቡ ቸልተኝነት ከፍተኛ ሥጋት ጥሎብናል”

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

   - እየመጣብን ያለው ታላላቅ አገራት ያልቻሉት ትልቅ መከራ ነው
       - በሽታው የሚያደርሰውን መከራ ከሌሎች አገራት እንማር
       - በሽታው ከቁጥጥራችን ከወጣ ልንቋቋመው አንችልም
                   
                በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የድንገተኛ ጽኑ ህመምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ወልደሰንበት ዋጋ ነው፤ ሀሳቡ የግል አቋማቸው መሆኑን ጠቁመው በሰጡት አስተያየት፤ ህብረተሰቡ ለበሽታው እያሳየ ያለው ቸልተኝነት ስጋት ላይ እንዲጣላቸው ይናገራሉ፡፡
“እኔ የሕዝቡን ሁኔታ አይቼ ፈርቻለሁ:: ሕዝቡ ልክ እንደ ቀድሞው እየኖረ ነው፡፡ የሚነገረው ነገር የገባውና የተረዳው ሕዝብ 30 በመቶው ብቻ ቢሆን ነው፡፡ ይህ እጅግ ሊያሳስበን የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ እኛ መስራት ያለብን መከላከሉ ላይ ነው፡። ከዛ አምልጦ የሚያዘውን የማከም ጉዳይ ላይ ነው ማተኮር ያለብን፡፡ ይህንን ሁላችንም በአግባቡ ልንገነዘበውና ልንረዳው ይገባናል:: በዚህ በሽታ መያዝ ማለት እንደ ቀላል ጉዳይ ልናስበው አይገባንም፡፡ ሰው ሞትን ባይፈራ አሟሟቱን እንኳን ማሰብና መፍራት መጠንቀቅ ይኖርበታል፡፡ በኮሮና መሞት በሌላ በሽታ እንደ መሞት ቀላል አይደለም፡፡ በባህላችን ለአስከሬን የሚሰጠው ክብር ሁሉ ለኮሮና ሟች አይሰጥም፡፡ ሞትና አቀባበራችን ሁሉ ወትሮ ከምናውቀው ለየት ያለ ነው፡፡ ሰው ከሰው ንኪኪ ርቆ በፕላስቲክ ሳጥን ተሸፍኖ ምንም አይነት ሃይማኖታዊ ስርዓት ሳይደረግለት በአንድ ወይም በሁለት ሰው ብቻ የሚቀበርበት ሁኔታ ነው የሚኖረው፡፡ ሞታችንን ባንፈራ እንኳ አሟሟታችንን እንፍራና በበሽታው ላለመያዝ እንጠንቀቅ” ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ሁላችንም በተጠነቀቅን ቁጥር የበሽታውን ስርጭት መጠን እንቀንሰዋለን፤ ያሉት ዶ/ር ወልደሰንበት ይህ ደግሞ የጤና ባለሙያዎችንም ለበሽታ ተጋላጭ የመሆን ቁጥር በእጅጉ ይቀንሰዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ለህብረተሰቡ በሚገባ ስለ ጉዳዩ መንገር፣ ማስተማርና ራሱን ከበሽታው እንዲጠብቅ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አገራችን እንዲህ አይነት ወረርሽኞችን በመከላከል ረገድ ባላት ልምድ ማነስ ሳቢያ የሚከሰተውን ችግር ለመቋቋም የሚያስችል አቅም ይኖራታል ብለው ያስባሉ ወይ? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ ዶ/ር ወልደ ሰንበት ሲመልሱ፤ በተለያዩ ጊዜያት በአገራችን በተወሰኑ ደረጃዎች እየመጡ የሚመለሱ የወረርሽኝ ችግሮች አጋጥመውን ያውቃሉ፡፡ በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ጉዳዮች ምክንያትም በአንድ ጊዜ ብዙ ሰዎች ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ጊዜም አጋጥሞን ያውቃል፡፡ ይህም ብዙ ሰዎች በአንድ ላይ ሲጎዱ በምን መንገድ ማስተናገድ እንደሚገባን ልምዱ እንዲኖረን አድርጎናል፡፡ የጤና ባለሙያዎቻችንም ባደጉ አገራት ካሉት በዚህ የተሻሉ ናቸው፡፡  አንድ ታማሚ ሲመጣ በሽታው ተላላፊ ሊሆን እንደሚችል ቀድሞ የማሰብ ነገር አለን፡፡ ይህ ሊጠቅመን ይችላል:: በአገሪቱ በሽታው ብዙ ሰዎችን በአንድ ጊዜ ቢያጠቃ መቋቋም ትችላላችሁ ወይ ከሆነ ጥያቄው፤ ጉዳዩ አሳሳቢ ነው የሚሆነው:: እንኳንስ እኛ የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ አቅሙ ያላቸው አገራትም አልቻሉትም ሲሉ ይመልሳሉ፡፡ የሕክምና ባለሙያዎች ዝግጁነት፣ ብቃትና፣ አቅምን አስመልክተው ሲናገሩም፤ “የህክምና ባለሙያ እንደ ወታደር ነው፡፡ ጦርነት መጣ ሲባል ወደ ግንባር ሄዶ ራሱን ከጠላት ጋር እያፋለመ የሚመጣውን ይቀበላል፡፡ አንድ ወታደር ጠላት መጣ ሲባል ፈርቶ አይደበቅም፤ ወጥቶ ይፋለማል እንጂ፡፡ ይህንን ለማድረግ ግን ትጥቁ ሊሟላለት ይገባዋል፤ ባዶ እጁን ወደ ጦር ግንባር አይሄድም፤ አልሄድም ብሎ ፈርቶ ሸሽቶ ቤቱ ቢቀመጥ ሞት ቤቱ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ጠላት የግንባሩን ሲጨርስ ወደየ ቤቱ መዝለቁ አይቀርምና፤ ስለዚህ የመጣበትን ጠላት ለመመከትና ህብረተሰቡን ከአደጋ ለመከላከል ይዘምታል፡፡ ሃኪምም በቃ እንዲህ ነው፡፡
እኔ አሁን ለምሳሌ በዚሁ በኮቪድ 19 ሕክምና ውስጥ እየሰራሁ ነው፤ የሚመጣውን ከወገኖቼ ጋር ሆኜ ለመቀበል ተዘጋጅቼ ነው እየሰራሁ ያለሁት፡፡ በዓለማችን እንደምንሰማው የሕክምና ባለሙያዎች ተጋላጭነታቸው የሰፋ ነው፡፡ ስለዚህም ህብረተሰቡ በሁለት ጉዳዮች ሊያግዘን ይገባል፡፡ አንደኛው በበሽታው እንዳይያዝ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ፤ ይህም የታማሚው ቁጥር እንዲቀንስ ያደርገዋል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የእኛም ለበሽታው ተጋላጭነት ይቀንሳል ማለት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ህብረተሰቡ በተለይም ባለሀብቱ፣ በዚህ አስከፊ ጊዜ ከመንግስት ጎን መቆም መቻል አለበት፡፡ አገሪቱ ያላት አቅም ውስን ነው፡፡ እንኳንስ እኛ ደካማ ኢኮኖሚ ያለን አገር ቀርቶ በበለፀጉት አገራትም ሁኔታው ፈታኝ ሆኖባቸዋል፡፡ ቻይናዊው ባለሀብት በዚህ ወቅት የሚያስፈልጉትን የሕክምና መርጃ ቁሳቁሶች ሊረዳን እጁን ዘርግቶልናል፡፡ ይህ ሁኔታ ለእኛ አገር ባለሀብቶች አስተማሪ መሆን ይኖርበታል፡፡ ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል፤ በሽታው ቢስፋፋ የሚተርፍ ሰው አይኖርም፡፡ በሽታው ሀብት፣ ዘር ቀለም ድንበር የማያሸንፈው ነው፡፡ እናም ማንም ከበሽታው ነፃ መሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ ባለሀብቶቻችን ለወገኖቻቸውም ለራሳቸውም ሲሉ ከጎናችን ሊቆሙ ይገባል፡፡ መንግሥትም ሕዝቡን የማስተባበር ሥራ መስራት አለበት:: ለዚህም ጊዜው አሁን ነው፡፡ በሽታው ወደ ሁሉም የአገራችን ክፍል ከተሰራጨ ልንቋቋው አንችልም፡፡ ታሪክ ሊረሳው የማይችለው አደጋ ሊከሰት ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡  
የውስጥ ደዌ ሀኪሙና የህብረተሰብ ጤና ባለሙያው ዶ/ር ተስፋሁን ዓለሙ በበኩላቸው፤ የበሽታውን የስርጭት ፍጥነት በሚገባ የተረዳነው አልመሰለኝም፣ አሁን በከተማው የምናየው ነገር ሁሉ የሚያስገነዝበኝ ይህንን ነው፡፡ ህብረተሰቡ በመንግስት የሚወጡትን መመሪያዎች ማክበርና መተግበር ይኖርበታል፡፡ ይህንን ማድረግ የማይፈልጉትን ደግሞ መንግስት በግድ መመሪያውን እንዲያከብሩ ማስገደድ አለበት፡፡ አሁን ነገሮችን አቅልለን የምናይበትና የምንቀልድበት ጊዜ አይደለም፡፡ እየመጣብን ያለው ነገር ታላላቅ አገራት ያልቻሉት ትልቅ መከራ ነው፡፡ እባካችሁ እንጠንቀቅ፣ ራሳችንን እንጠብቅ፣ ከሰዎች ጋር የሚኖረንን ርቀት በሚነገረን ልክ እናድርግ ብለዋል፡፡
አሁን አገሪቱ ባላት አቅም በርከት ያሉ ህሙማን በአንድ ጊዜ ቢመጡብን፤ ምን ልንሆን እንደምንችል አላውቅም፡፡ በአጠቃላይ በአገሪቱ ለዚህ በሽታ ተብለው የተዘጋጁት የማከሚያ ስፍራዎች እጅግ አነስተኛ ናቸው፡፡ እዚህ በከተማችን አዲስ አበባና በደብረ ዘይት ባሉን ማግለያና ማከሚያ ቦታዎች ያሉን አልጋዎች በአጠቃላይ 500 አይሆኑም፤ በሽታው ትንፋሽ የሚያሳጣ በሽታ ነው፡፡ ለመተንፈስ የሚረዱ መሳሪያዎች ስንት አሉን? ብለን ስናስብ ቁጥሩ ያስደነግጣል፡፡ እኛ ያለን ብቸኛ መዳኛ ጥንቃቄ ነው፡፡ ይህ ጊዜ ለእኛ የማርያም መንገድ የሚባለው አይነት ነው፤ እባካችሁ በዚህ በተሰጠን ጊዜ እራሳችንን ከበሽታው እንጠብቅ እንጠንቀቅ፡፡ በሽታው የሚያደርሰውን መከራ ከሌሎች አገራት እንማር፡፡ አሁን በያዝነው ሁኔታ ከቀጠልን የሚደርሰው ጥፋት እጅግ ዘግናኝ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ለዚህ ጉዳይ ኃላፊነት አለበት፡፡ ራሱን ለሞት አሳልፎ የሚሰጠው የሕክምና ባለሙያም ጥንቃቄ ሊደረግለት ይገባል፡፡ ችግሩን ለማስቀረት ባንችል እንኳን የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ መጠንቀቅ ከሁላችንም የሚጠበቅ ጉዳይ ነው ሲሉ አሳስበዋል - የህክምና ባለሙያው፡፡
የህብረተሰብ ጤና ባለሙያው ዶ/ር ሰለሞን ወርቁ ደግሞ እንዲህ ይላሉ፡- በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡ ለበሽታው የሰጠው ግምትና እየወሰደ ያለው ጥንቃቄ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ህብረተሰቡ እየተነገረው ያለውን ነገር መተግበር ይኖርበታል፡፡ አትገናኝ፣ አትጨባበጥ፣ ተራራቅ፣ እጆችህን ታጠብ፣ ይህ በጣም ቀላልና ሁላችንም በቀላሉ ልንተገብረው የምንችለው ነገር ነው፡፡ ስለዚህ የግድ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ አላደርግም ያለውን ደግሞ መንግስት ማስገደድ ይኖርበታል:: ይህ የሕይወት ጉዳይ ነው፡፡ መከላከሉ ላይ አተኩረን ካልሰራንና አንዴ ከቁጥጥራችን ከወጣ ልንቋቋመው አንችልም፡፡ በእኛ ደካማ የጤና ስርዓት ይህንን ከባድ መከራ ማለፍ አንችልም፡፡ ይህ ማለት ግን አሁን እየተሰራ ያለው ነገር ትንሽ ነው ማለት አይደለም፡፡ ትልቅ ስራ እየተሰራ ነው ያለው፡፡ የጤና ባለሙያዎቻችን በዚህ ደካማ የጤና ሥርዓት ውስጥ ተፍጨርጭረው ለመስራትና ወገኖቻቸውን ለማዳን እያሳዩት ያለው ዝግጁነት እጅግ የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡ 200 አዳዲስ የጤና ባለሙያዎች ለዚሁ ወረርሽኝ አጋዥ ሆነው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ይህ ለእኛ መልካም ዜና ነው፡፡ ሁላችንም በአንድ ላይ ሆነን ይህንን ክፉ ጊዜ የምንወጣበትን መንገድ ማሰብ ይኖርብናል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በዓለማቀፍ ደረጃ በሽታው ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ የጤና ባለሙያዎች በደህንነት መከላከያ እጦት ለቫይረሱ ያላቸው ተጋላጭነት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣ ሲሆን እስካሁን ----ያህል ሀኪሞች ለሞት መዳረጋቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡             

Read 12611 times