Saturday, 21 March 2020 12:53

“እጅህን ባህሩ ውስጥ ክተት፡፡ ካገኘህ አሣ ትይዛለህ፡፡ ካጣህ እጅህን ታጥበህ ትወጣለህ”

Written by 
Rate this item
(10 votes)

  ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሰውዬ ሠፈር ውስጥ ሲዘዋወር አንድ መንገደኛ ያገኝና አብረን እንሂድ ይባባላሉ፡፡
“ወዴት ነው የምትሄደው ወዳጄ?” አለ የሠፈሩ ሰውዬ፡፡
“ዘመድ ለመጠየቅ ወደ ሩቅ አገር እየሄድኩ ነው” አለ መንገደኛው፡፡
“እኔም የምሄደው ቅርብ አይደለም”
“የተወሰነ ርቀት አብረን እንጓዛ?”
“ደስ ይለኛል”
አብረው መሄድ ጀመሩ፡፡
ሠፈር ውስጥ የሚዘዋወረው ሰው ጨዋታ ቀጠለ፡-
“ልጆች አሉህ ወዳጄ?”
“አዎን፤ ብዙ ልጆች አሉኝ”
“ታዲያ አንዳቸው እንኳን ለምን አብረውህ አልመጡም?”
“ምን እባክህ፤ የዛሬ ልጆች እነሱ የሚሄዱበትን እንጂ አንተ የምትሄድበትን አያደንቁም፡፡ እነሱ ወደሚሄዱበትም አንተ የመሄድ ፍላጐት ብታሳይ በቀላሉ አያበረታቱህም፡፡”
“ይሁን፡፡ መታገሥና ዕድገታቸውን መከታተሉ ይሻላል፡፡”
“አዎን ምርጫ የለንም፡፡”
ጥቂት እንደ ተጓዙ አጥር ላይ ያለ አንድ አውራ ዶሮ ይጫሃል፡፡
ይሄኔ አንደኛው መንገደኛ፤
“ወዳጄ፤ አሁን ይህ አውራ ዶሮ እዚህ አጥር ላይ ሆኖ ሲጮህኮ መንግሥተ ሰማይም ውስጥ ልክ ይሄንኑ የሚመስል አውራ ዶሮ ይጮሃል” አለ፡፡
ሁለተኛው መንገደኛም፤
“ወዳጄ ትቀልዳለህ እንዴ? እንደ ዶሮ አይነት ልክስክስ ቆሻሻ ነገር እንዴት ብሎ ነው መንግሥተ ሰማይን የመሰለ ንጹህ ቦታ የሚገባው?”
አንደኛው፤
“አይደለም ወዳጄ ይህ አውራ ዶሮ መንግሥተ ሰማይ ውስጥ ሲገባ ጭራውን ወደ ሲዖል አፉን ወደ መንግሥተ ሰማይ አድርጎ ነው! የሚጮኸው” አለው፡፡
ሁለተኛው መንገደኛም፤
“አዬ፤ ነገሩን እንዲህ በቀላሉ አትየው፡፡ የሲዖል እሳት የወዛ አይምሰልህ፡፡ እንኳን እሳቱ ወላፈኑም እንኳ ዶሮ ላባ አግኝቶ ደረቅ እንጨት ቢያገኝ ዝም አይልም››
አንደኛው ትዕግሥቱ አለቀና፤
“ዎዎ! እኔ ምን ቸገረኝ - የአባቴ ዶሮ አይደለ ቢያንበገብገው!” ብሎት ሄደ፡፡
*     *    *
ከማይሆን ተሟጋች ጋር ትክከለኛም ሙግት ቢሆን የምንሟገተው ከንቱ ድካም ነው:: ወደ ራሱ ስሜት እንጂ ወዴ ትክክለኛው አመክንዮ ስለማይወስደን በከንቱ ጊዜያችንን፣ መልካም አስተሳሰባችንና ስብዕናችንን ያባክንብናል፡፡ ከቶውንም በትግዕስት በጥሞናና በበሰለ አካሄድ ያልተቃና የአገር ነገር ታጥቦ ጭቃ የሚሆን ነው፡፡
ነገርን እንደ በቀቀን ስለደጋግምነው ብቻ ወደ ዕውነቱ መቀረቢያውን ቀንዲል ለኮስን ማለት አይደለም፡፡ ሞቅ ደመቅ እያደረግን የምናሰማምራቸው ጉዳዮች አንድም በሙያዊ ብቃት፣ አንድም በልባዊ ፅናት ካልታገዙ ደጋግመው ለእንቅፋት እንደሚዳረጉን ግልጽና ግልጽ ነው፡፡
“ትላንትና ማታ ወደ ቤትህ ስትገባ በርህ ላይ የመታህ እንቅፋት ዛሬም ከመታህ ድንጋዩ አንተ ነህ”  ይላሉ ቻይናዎች፡፡ በአገራችን እንቅፋት የሆኑ አያሌ ሳንካዎች አሉ፡፡ እንኳንስ ተነጣጥለን አንድና ህብር ሆነንም በቀላሉ ነቅለን የማንጥላቸው ያመረቀዙና አዲስ ያቆጠቆጡ ብዙ ችግሮች አሉብን፡፡ ዛሬም ደግመን ልንለው የምንሻው እንደ ተጠቃሽ አነጋገር አለ፡-
If Your plan is for a year, plant Teff.
If Your plan is for fire years plant  eucalyptus tree.
If Your plan is forever, educate your child.
ስንተረጉመው፤
“እቅድህ ለአንድ ዓመት ከሆነ ጤፍ ዝራ፡፡
እቅድህ ለአምስት ዓመት ከሆነ ባህር ዛፍ ትከል፡፡
እቅድህ ለዘለዓለም ከሆነ ልጅህን አስተምር!!”
ማለት ነው፡፡
ምንጊዜም ሕይወት አዳጊ እንቅስቃሴ፣ አዳጊ ሂደት መሆኑን አትዘንጋ፡፡ Life is an incremental Process  እንዲሉ፡፡ እኛ ብንቆምም አይቆም፡፡ እንሽሽህ ብንለውም አይሸሽም ሰልጠንና ጨከን ብሎ መጓዝ ብቻ ነው መድሀኒቱ፡፡ ኮስተር መረር ማለት ነው መፍትሔው፡-
“እረ ምረር ምረር፣ ምረር እንደቅል
አልመርም ብሎ ነው፣ ዱባ እሚቀቀል”
የሚለው የአገራችን ሰው ወዶ አይደለም፡፡ ያም ሆኖ ጊዜውን ጠብቆ ሊፈነዳ ያላጠነጠነ እንቡጥ በግድ ለቅቄ አፈካዋለሁ ብንል ውጤቱ ማፍካት ይለዋል መጽሐፉ፡፡
በዚህም አልን በዚያ የምንሄድበትን አቅጣጫ ለመወሰን ዋንኛው ዘዴ ሶስት መንገዶች ማስተዋል ነው!! መሞከር ነው፡፡ ሁለተኛውም መላ መሞከር ነው! ሦስተኛውም መላ መሞከር ነው!
“እጅህን ባህሩ ውስጥ ክተት፡፡
ካገኘህ አሳ ትይዛለህ፡፡
ካጣህ እጅህን ታጥበህ ትወጣለህ!!” የሚባለው ታላቅ ቁም ነገር በሙከራችን ተስፋ እንዳንቆርጥ የሚመክረን ይሄንኑ ነው!!



Read 14565 times