Saturday, 21 March 2020 12:45

ልብ መግዛት!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ምን አደረግንህ? እንደው ምነ በደልንህ?
አንድዬ፡— አሁን ደግሞ ምን አደረግኸን ልትሉኝ ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡— ይህን ሁሉ ቁጣ የምታወርድበን ምን ሀጢአት ብንሠራ፣ ምን ያሀል ብናስቀይምህ ነው!
አንድዬ፡— እኮ ምን አደረግኋችሁ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ይህንን መቅሰፍት ሀገራችን ላይ ያመጣህብን ምን ብናደርግሀ ነው? ያለን ችግር አልበቃ ብሎ ይህንን ትጨምርብናለህ!
አንድዬ፡— ስለምንድነው የምታወራው?
ምስኪን ሀበሻ፡— ይሄ ቫይረሱ…
አንድዬ፡— ቆይ፣ ቆይ ተረጋጋ፡፡ ረጋ… አሁን እያበዛችሁት ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ምን…
አንድዬ፡— ነገርኩህ እኮ፣ አሁን አበዛችሁት! ዓለም ሁሉ እየታመሰ እያለ፣ ከእናንተ በስንትና ስንት ዘመን ቀድመው የሄዱ ሀገራት መከራቸውን እየበሉ ጭራሽ ለናንተ  ብቻ የመጣ ይመስል ወቀሳው እኔ ላይ ሆኖ አረፈው!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ወቀሳ አይደለም እኮ!
አንድዬ፡— ይልቅ ስማ…ጣት ቀሰራ ውስጥ ከምትገቡ መቀናታችሁን ጠበቅ ብታደርጉ ይሻላል፡፡ ሀኪሞቻችሁ አድርጉ የሚሏችሁን አድርጉ፣ አታድርጉ የሚሏችሁን አታድርጉ፡፡ በቃ ይኸው ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ እኔ የሚመለከተኝ ነገር የለም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንተ ብቻ ነህ እኮ ያለኸን፡፡ አንተ አይመለከተኝም ካልክ ወደማን እንዞራለን!
አንድዬ፡— ወደ ራሳችሁ ነዋ፡፡ ወደ ራሳችሁ… ወደ ህሊናችሁ ዙሩ፡፡ ማድረግ ያለባችሁን ራሳችሁ እወቁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን እናድርግ አንድዬ፣ ምን እናድርግ!
አንድዬ፡— የምታደርጉትማ ምን መሰለህ፣ እስቲ እንደው ልብ ግዙና አንዳንዴ ጣቱን ወደ ራሳችሁ አዙሩት፡፡ የምትገርሙ ሰዎች ናችሁ እኮ! ጭራሽ በሽታ ያመጣችሁብን እናንተ ናችሁ እያላችሁ በእንግድነት ወደ ሀገራችሁ የመጡትን እንግዶች መተናኮል ምን ይባላል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እንደሱ የሚያደርጉት እኮ ጥቂት ምግባር የሌላቸው ናቸው፡፡ አብዛኛው ህዝብ እንዲህ አይነት ተግባር እንደማይፈጽም አንተም ታውቃለህ::
አንድዬ፡— ጥቂቶች ብሎ ነገር የለም:: አንድም ሰው ፈጸመው፣ ሁለትም ሰው ፈጸመው ሌላው ዓለም እንደሁ ድፍን ሀገር እንደፈመጸው ነው የሚያየው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ የሰዎች ባህሪይ ከተበላሸ እኛ ምን አቅም አለንና ነው!
አንድዬ፡— መጀመሪያ እኮ እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ አንዲመጣ ያደረጋችሁት እናንተው ራሳችሁ ናችሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንዴት አድርገን አንድዬ!
አንድዬ፡— ምንም ነገር ሲመጣ አወራሩን አታውቁበትም! ልክ ራሳችሁን የተለያችሁ አድርጋችሁ ስለምትቆጥሩ. በእናንተ ቤት ሁሉም ጠላታችሁ ነው፡፡ ይህን ነገር ከአእምሯችሁ ካላስወጣችሁ እኔ ምን ላድርጋችሁ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ግን እኮ አንድዬ፣ ጠላቶቻችን ብዙ ናቸው፡፡
አንድዬ፡— እንግዲህ ካላችሁ እኔ ምን ማድረግ እችላለሁ! ችግሩ ምን እንደሆነ ታውቃለህ፤ መልስልኛ፣ አንዱ ትልቁ ችግራችሁ ምን እንደሆነ ታውቃለህ ወይ እያልኩህ ነው እኮ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ የእኛ ችግር ምኑ ተነግሮ ያልቃል! ቀኑን ሙሉ ባወራልሀ ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡
አንድዬ፡— ጥሩ፤ ይህንን ማወቅማ አንድ ነገር ነው፡፡ ግን ብዙዋቻችሁ ስለ ራሳችሁ ያላችሁ አመለካከት አንድ  ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እንዴት አንድዬ?
አንድዬ፡— ብነግርህ ደግሞ ሰደብከን ትሉኛላችሁ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን በወጣን አንድዬ፣ ምን በወጣን፡፡
አንድዬ፡— እንግዲያው እነግርሃለሁ፡፡ ከፊሎቻችሁ ስለ ራሳችሁ ያላችሁ አመለካከት ልክ ከእናንተ ጋር የሚስተካከል ሌላ ፍጡር እንደሌለ፣ ተራራ ይመስል ትቆለላላችሁ፡፡ ይሄ ነገር አልተው ብሏችኋል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ቢሆንም እኮ አንድዬ፣ ቢሆንም…
ምስኪን ሀበሻ፡— ቢሆንም ምን? ቢሆንም እኮ እኛ የተለየን ነን ልትለኝ ነው:: እንደዛ ካሰብክ ይሁንልህ፡፡ ሌሎቻችሁ ደግሞ ስለ ራሳችሁ ያላችሁ አመለካከት እዛ ታች የወረደ ስለሆነ ሁሉም ሰው እናንተን የሚያጠቃ ይመስላችኋል፡፡ ራሳችሁን ቀና ማድረግ ካቃታችሁ እኔ ምን ላደርጋችሁ እችላለሁ!
ምስኪን ሀበሻ፡— እሺ አንድዬ፣ ሌላ ምን መሰለህ… የዚህ የውሀ ነገር…
አንድዬ፡— የምን ውሀ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ አውቀህ ስታሾፍብን ነው፣ አይደል?
አንድዬ፡— እኔ ምን አሾፍባችኋለሁ:: ራሳችሁ ላይ እያሾፋችሁ ያላችሁት ራሳችሁ:: በቃ ይሄ ሁሉን ነገር ወስዶ ሌላው ላይ የመለጠፍ ነገር ላይተዋችሁ ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— እሺ አንድዬ፣ ይቅርታ:: ውሀ ያልኩህ ምን መሰለህ፣ የዚህ የዓባያችነ ጉዳይ…
አንድዬ፡— አሁን ገና ጥሩ ንግግር ተናገርክ፡፡ ዓባያችን አይደለም ያልከው?
ምስኪን ሀበሻ፡— አዎ፣ አንድዬ፣ አጠፋሁ እንዴ!
አንድዬ፡— አላጠፋህም፡፡ ዓባያችን ስትል ግን ልትጠቀሙበት ወስናችኋል ማለት ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እሱን ልልህ ነበር እኮ! ይህች ግብጽ የሚሏት ሀገር…
አንድዬ፡— ቆይ፣ ቆየኝ፣ ከእሱ በፊት እኔ ልል የፈለግሁት አንዴ “ዓባይም ሲሞላ፣” አንዴ “ዓባይ ሲጎድል፣” እያላችሁ መዝፈን ትታችሁ፣ ልትጠቀሙበት መወሰናችሁ ጥሩ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ስለምንወደው ነው እኮ የምንዘፍንለት፡፡
አንድዬ፡— እንኳን ወደዳችሁት፡፡ ለወደፊቱ ምን አድርጉ መሰለህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን እናድርግ አንድዬ?
አንድዬ፡— ለወደፊቱ የምትወዱትን ነገር ዘፈኑን ቀነስ አድርጉለትና ተጠቀሙበት፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እሱን ልልህ እኮ ነው አንድዬ! እኛ ዓባይን እንጠቀምበታለን ስንል ይህች ግብጽ የሚሏት ደንቃራ…
አንድዬ፡— ደንቃራ አልካት! ደንቃራ ብቻ ነች እንዴ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን ደንቃራ ብቻ! ጭራሽ እኮ ፉከራም እያሰኛት ነው፡፡ አንድዬ፣ አሁን ግብጽ ነች እኛ ላይ የምትፎክረው!
አንድዬ፡— ረጋ በል ግዴለህም፡፡ የረጋ ወተት ምን ይወጣዋል ነበር የምትሉት?
ምስኪን ሀበሻ፡— የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል ነው የምንለው፡፡
አንድዬ፡— እንኳን ነገርከኝ፡፡ የረጋ ወተት ሁኑና ቅቤ ሁኑ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እሺ አንድዬ፣ እንዳልክ::
አንድዬ፡— አየህ እንዲህ ሲሆን ጥሩ ነው:: በሆነ ባልሆነው ጭቅጭቁንና ክርክሩን ትታችሁ እንዲህ ምክር ስትሰሙ ሸጋ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— የአንተን ምክር መቼ ሳንሰማ ኖረን እናውቃለን!
አንድዬ፡— አየህ አይደል፣ አሁኑኑ ክርክር ልታስጀምረኝ ነው፡፡ ብቻ ለክፉም ለደጉም በሽታውን በተመለከተ ባለሙያዎች የሚሏችሁን ሁሉ አድርጉ፡፡ ግብጽን በተመለከተ እነሱ ዓለምን እየዞሩ ደጋፊ እየሰበሰቡ ስለሆነ እናተም እወቁበት፡፡ ዋናው ነገር ልብ መግዛት ነው፡፡ ልብ ግዙ:: ሰላም ግባ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አሜን አንድዬ፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2448 times