Saturday, 14 March 2020 15:41

በሃሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

     ድሮ የሰማናት ቀልድ ነበረች፡-
ታላቁ መልዓክ ወደ ጌታው ቀርቦ እጅ ከነሳ በኋላ፡-
“ጌታዬ ሆይ”
“አቤት”
“ሌኒን መጥቷል” አለው፡፡
“ገሃነብ አስገባው”
“እሽ” ብሎ እንደ ታዘዘው አደረገ፡፡
ከአንድ ሳምንት በኋላ ገሃነብም አብዮት ተጀመረ፡፡ መልዓኩም የሆነውን ለጌታው ሪፖርት አቀረበ፡፡
ጌታውም፤ “ይኸ ሰውዬ እዚህም አላርፍ አለ?” ሲል አሰበና፤
‹‹ወደ ገነት አምጣው›› አለው፡፡… እንዳለው ቢሆንም ተመሳሳይ አመፅ በገነት መቀስቀሱ አልቀረም፡፡ ይህም ከጌታ ጆሮ እንደደረሰ ሌኒን ተጠርቶ እንዲመጣና አጠገቡ እንዲቀመጥ ተደረገ፡፡ በሲዖልና በገነት የነበሩት አብዮተኞች፣ እርምጃውን በመቃወም ላለቆቻቸው አንታዘዝም አሉ:: መልዓኩም ይህን ለጌታው ለማሳወቅ ወደ እልፍኝ እንደገባ፣ በተመለከተውና በሰማው ነገር ግራ ተጋባ፡፡… ምን ይሆን?
***
አለማመንን (atheism) ጨምሮ ሁሉም የዕምነት ተቋማት በሰበካቸውም ሆነ በቅዱሳን መፃሕፍቶቻቸው ገፆች ‹እዚህና እዚያ› የሰፈሩ ታላላቅና መሳጭ ትርጉም ባላቸው ቃላትና አረፍተ ነገሮች አሸብርቀዋል፡፡… ፍቅር፣ መቻቻል፣ መረዳዳት፣ ወንድማማችነት… በሚሉና በመሳሰሉት፡፡ እነዚህ አባባሎች የሰው ልጅ በጋራ የመኖሩንና በጋራ የመለወጡን ቅድስና የሚያጎናጽፉ፣ የልባዊነቱ ፀጋና የአንድነቱ ካስማ የቆመባቸው መሠረቶች ወይም መገለጫዎች ናቸው… እንደ ወርቃማው ሕግ!!
ቀደም ሲል በነበሩ ጨለማ ዘመናት፣ ሰዎች በሰበብ አስባቡ ጎራ እየፈጠሩ ሲዋጉ የነበሩት፣ አላዋቂና ኋላ ቀር በመሆናቸው እየተጠቀሙ፣ የገዥነትና የንብረት የበላይነትን በሚፈልጉ መሪዎች አሳሳች ቅስቀሳ በመወናበዳቸው መሆኑ ተጽፏል፡፡ ሰዎቹ የቅዱስ መጽሐፍት አስተምህሮቶቹን ትርጉም በማወላገድና ጥቅሶቻቸውን ከተጻፉበት አውድ (Context) ውጭ ያለ ቦታቸው በመደንቀር፣ ስሜታዊ ንግግር በማድረግ፣ ያልተረጋገጠና ያልነበረ ታሪክ በመፍጠር ተከታዮቻቸውን አስፈጅተዋል:: አይሁዶች፣ ካቶሊኮች፣ ፕሮቴስታንቶች፣ ሙስሊሞችና ኢ - አማንያን አንዱ ከሌላው፣ አንዳንዴም እርስ በርስ እየተከፋፈሉ ሲዋጉ እንደነበር በታሪክ ተመዝግቧል፡፡
ወዳጄ፡- በዚህ ዘመን ተመሳሳይ ስህተት ሊደገም እንዳማይቻል የተረጋገጠ ቢሆንም አልፎ አልፎ በሚታዩ የአጻጻፍ፣ የአተረጓጎም፣ ያለ ቦታቸው በሚጠቀሱ ምሳሌያዊ አነጋገሮችና መሰል ነገሮችን መጠቀሚያ በማድረግ፣ ምዕመኑ የአረዳድ ስህተት እያዳበረ፣ ከወንድሞቹ ጋር እንዲጋጭ የሚያመቻቹ ቅስቀሳዎች ስለሚታዩ፤ ማንኛውንም ነገር በግልጽ በመወያየት፣ በመመርመርና በማወቅ፣ አጓጉል ቀዳዳዎችን ለመድፈንና ከግንዛቤ ስህተት ያግዛል፡፡
ወዳጄ፡- ባለፈው ሰሞን በጉራጌ ዞን፣ በቀደምለት ደግሞ በሞረትና ጅሩ ወረዳ እነዋሪ ከተማ በሚገኙ የሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያንና ተከታዮቻቸው ላይ የንብረት ቃጠሎና ሰብዓዊ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ከውጭ አገር ለሕክምና ዕርዳታ በመጡ ወገኖችም ላይ ሰብዓዊነት ጉዳት፣ ከዚህም ጋር አያይዞ ከውጭ አገር ለሕክምና ዕርዳታ በመጡ ወገኖች ላይ አሳዛኝ ጥቃት ተፈጽሟል፡፡ ይህ የሰብዓዊ መብት ጉዳት፣ የእምነት ነፃነት መጋፋትና ኢ ፍትሃዊነት የፖለቲካ ወንጀል ቢኖርበትም፣ ስረ ምክንያቱ ግን እምነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ያለ መረዳት ወይም የግንዛቤ ስህተት ይመስለኛል፡፡
ወዳጄ፡- በዚህ አጋጣሚ ግንዛቤን የሚመለከት አንድ ምሳሌ እንዳነሳ ፍቀድልኝ፡- ‹ጎድ› የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል የመጀመሪያውን ፊደል በካፒታል ሌተር ስንፅፍ (Goad) የምናገኘው ትርጉም፣ በትንሽ ፊደል (Small letter) ስንጽፈው (goad) ከምናገኘው ትርጉም ይቃረናል:: በቅዱስ መጽሐፍ ከተጠቀሰው (ሱራህ 23፡116-117) አምስቱ የእስልምና ዕምነት ምሰሶዎች የመጀመሪያው፡- ‹‹ከአላህ በቀር ማንም የለም፣ ሞሃመድም የሱ መልዕክተኛ ነው›› (La illah illa Allah, Mohammed rasula Allah) የሚለው እምነት ቃል ነው:: የእንግሊዝኛው ትርጉም ‹‹There is no ጎድ,  but Allah, Mohammed is his mesenger›› ይላል፡፡ ቅድም እንዳልነው፤ ‹ጎድ› የሚለው ቃል የመጀመሪያ ፊደል በካፒታል ከተጻፈ (Goad) የሚወክለው ክርስትናና ተመሳሳይ እምነቶች ‹‹እግዜር፣ ፈጣሪ አምላክ›› የሚሉትን ባህሪ መንፈስ ነው፡፡ ‹ goad› ተብሎ ሲፃፍ ግን የሚወክለው ነቢዩ ሞሃመድ የሰባበሯቸውንና ያቀጠሏቸውን ጣዖታትና ግዑዝ አማልክትን ይሆናል፡፡ እኔም አንድ ቀን በዚህ ዓምድ ላይ “ክላውዴዎስ አምላክ /Cloudios the god) የሚለውን መጽሐፍ ስጠቅስ (ጥቅምት 22/1912 አዲስ አድማስ)፤ “ጎድ” የሚለውን ቃል መጀመሪያ በትንሽ ፊደል በመፃፌ፣ እህቴ የተሳሳትኩ መስሏት በካፒታል ፊደል አስተካክላ ጽፋዋለች፡፡
የፃፍኩት ሴት ጣዖታትና አማልክት የሚወክሉበትን ቃል (godess) ቢሆን ኖሮ፣ ምን ልታደርገው ነበር? ብዬ ሳስብ ሳቄ መጣ:: ለማለት የፈለግሁት “ትንሽ” የሚመስሉ የቃላት ግድፈቶች ትልቅ የግንዛቤና የአረዳድ ስህተት በታዳሚው ላይ ይፈጥራሉ ለማለት ነው፡፡ እዚች ጋ አንድ የድሮ ቀልድ ትዝ አለችኝ፡፡
ሰውየው አንዳንድ ሰዎች ከፊታቸው ወዳለው ሰው ለመጠቆም እንደሚያደርጉት አገጫቸውን የመነቅነቅ ልማድ አለባቸው:: ታዲያ አንድ ቀን “በል” ይላቸውና ቢንጐ ሲጫወቱ ሶስት መቶ ብር ያሸንፋሉ፡፡ ከሰፈር ጠጅ ቤት ጉብ ብለው፣ ፉት እያሉ፣ ፊት ለፊታቸው ከተቀመጠው ሰፈርተኛ ጋር ሲጨዋወቱ፣ አመል ነውና፣ አገጫቸውን ወደ ሰውየው ይጠቁማሉ፡፡ አዲሱ ጠጅ ቀጅም “ለሱም ቅዳ” የተባለ መስሎት የሰውየውን ብርሌ ይሞላል፡፡ እሳቸው ሲደግሙ ለሰውየውም ደገመው፡፡ አጅሬው ወደ ቤታቸው ለመሄድ ሂሳብ ሲከፍሉ፣ አስተናጋጁ የሁለቱንም እዳ ቆርጦ መልስ ሰጣቸው፡፡
“ምነው?”
“ምነው?”
“ጠጅ ጨመረ እንዴ?”
“ኧረ አልጨመረም”
“መልሱ ልክ አይደለማ”
“ከጋበዙት ሰውዬ ጋር !ኮ ነው”
“ማንን ጋበዝኩ?”
….ጠጅ ቀጂው እሳቸው እንዳደረጉት አገጩን እየጠቆመ፤ “እንዲህ ሲሉኝ አልነበረም እንዴ?” በማለት አስረዳቸው፡፡ ሰውየውም አገጫቸውን እየነቀነቁ፤ “እንዲህ ባልኩኝ ፊት ለፊቴ ለተቀመጠ የቀዳህ እንዲህ ብልማ ኖሮ” (አንገታቸውን እያዟዟሩ) ቤቱን ሙሉ ልታንበሸብሽ ነበር ማለት ነው” አሉት አሉ፡፡ ይቺም የግንዛቤ ችግር ናት፡፡
ሰውየው ገንዘብ ባይኖራቸው የሚፈጠረውን ጭቅጭቅ አስቡት፡፡ …ዕድሜ ለቢንጐ!!
ወዳጄ፡- ሳያስበው እንደተጋበዘው ሰውዬ፣ የተፃፈልህ ወይም የታዘዙልህ ነገር (ክፉም ሆነ ደግ) መምጫው አይታወቅም፤ ሱፊዎች “Maktub” እንደሚሉት፡፡ ሌላ የህዝብ ቀልድ ልጨምርልህ፡-
ሰውየው ኑሮውን ለማሻሻል ይጥራል:: አልሆነለትም፡፡ ወደ መጽሐፍ ገላጭ (Fortune teller) ሄዶ አማከረ፡፡ መዝገቡ ተገልጦ ዕድሉ ተነበበ፡፡ አዋቂው እራሱን እየነቀነቀ፤
“በድካሜ ያልፍልኛል ብለህ አታስብ” አሉት፡፡ በዕድሉ ጠማማነት እየዘነ ተመለሰ:: ብዙም ሳይቆይ አጋር አጋጠመውና አገባ:: ባመቱ ሚስቱ ወለደች፡፡ ሌላ ጉሮሮ ተጨመረ፡፡ “ልጄን “በዕድሉ” እለዋለሁ” እያለ፣ እያሰበ ዕንግዴ ልጁን ለመቅበር ወደ ጓሮው ዞረ፡፡ ጉድጓዱን ሲቆፍር በወርቅ የተሞላ ትንሽ ማሰሮ አገኘ፡፡ ድንጋጤው ሲበርድለት፣ አዋቂው እንደተሳሳተ ሊነግረው ገሰገሰ፡፡ ሲገናኙ፡-
“ተስፋ ቆርጬ ብሞት ኖሮ… ምን ትጠቀማለህ?” ሲል ጠየቀው፡፡
“ምነው ምን ሆንክ?”
“በድካምህ አያልፍልህም አላልከኝም?”
“ብዬሃለሁ”
“ተሳስተሃል!”
“እንዴት?”
በኩታው ስር ከያዘው ወርቅ አፍሶ፤
“ይኸ የማን ይመስልሃል?” አለ እየተኩራራ፡፡
“እንዴት አገኘኸው?” አለ መጽሐፍ ገላጩ፤ መዝገቡን እያነሳ፡፡
“ከጓሮዬ ተቀብሮ”
“በምን አውቀህ ቆፈርክ?”
“ሚስቴ ወልዳ እንግዴ ልጁን ለመቅበር ስቆፍር አገኘሁት”
መጽሐፍ ገላጩም መዝገቡን እየገለበጠ፤ “ለማንኛውም እንኳን ደስ ያለህ” አለው፡፡
“አልተሳሳትኩም ማለትህ ነው?” ብሎ ሲቆጣ፣ አዋቂው መዝገቡን አሳየው፡፡
የማሰሮው ወርቅ የተመዘገበው በተወለደው ሕጻን ዕድል ውስጥ ነበር፡፡ ወዳጄ፡- ማክቱብ የዲተርምኒዝም ነፍስ ናት::
***
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- ታላቁ መላዕክ አብዮተኞቹ “ሌኒን ካልተፈታ አንታዘዝም” ያሉትን ለመናገር ከጌታው እልፍኝ ሲደርስ፣ ጌታውና ሌኒን እያወሩ ይስቁ ነበር፡፡ ጐንበስ ብሎ እንደተለመደው፤
“ጌታ ሆይ” በማለት ሲጀምር…
“ካሁን በኋላ ጌታ ሆይ እንዳትለኝ፤ ጓድ በለኝ” አለው፤ ጌታው ኮስተር ብሎ:: “ጊዜው የጌታና የሎሌ አይደለም”…እንደ ማለት፡፡
ወዳጄ፡- የግንዛቤ ስህተት አለ?
ሰላም!!    

Read 1477 times