Saturday, 14 March 2020 11:11

የሀገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል ለምግብ እጥረት ሊዳረግ ይችላል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

     በሚቀጥሉት 8 ወራት ድረስ የምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ለምግብ እጥረትና ማህበራዊ ቀውስ እንደሚጋለጡ ያስታወቀው የአለም የምግብ ፕሮግራም፤ መንግስት ከወዲሁ ችግሩን ተረድቶ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ መክሯል፡፡
በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል በዋናነት በ2011 ክረምት የዝናብ ስርጭት ለሚፈጠረው የምግብ እጥረት ትልቁን ድርሻ ይይዛል ያለው ሪፖርቱ፣ ከዚህ ባሻገር ጐርፍ፣ ግጭቶችና መፈናቀል እንዲሁም የአንበጣ መንጋ ወረራ ለችግሩ በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡
በአካባቢዎቹ ከወዲሁ የእለት ምግብ ዋጋ እያሻቀበ መሆኑን፣ አካባቢዎቹ በስፋት አርብቶ አደር እንደመሆናቸውም ለእንስሶቻቸው የምግብ አቅርቦት እጥረት እየተፈጠረባቸው መሆኑንም ሪፖርቱ አትቷል፡፡
በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተው የዝናብ ስርጭት መዛበት ለቀውሱ ምክንያት ከመሆኑ ባሻገር በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም ዋነኛ ሰብል አምራች በሆኑ አካባቢዎች የአንበጣ መንጋ ያደረሰው ጉዳት በብሔራዊ የሀገሪቱ የሰብል ምርት መጠን ላይ መቀነስ ይፈጥራል፤ ይህም ቀውሱን ሊያባብስ ይችላል ተብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በሀገሪቱ ሰሜን ክፍል ደጋማ አካባቢዎች እንዲሁም ምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ክፍሎች የሚደርሰውን የአንበጣ መነጋው ጥቃት እንደቀጠለ መሆኑም በሰብልና በከብቶች ግጦሽ ላይ ጉዳት ያባብሰዋል ብሏል - ሪፖርቱ፡፡
ቀጣዩ የበልግ አዝመራ ወቅት ከመድረሱ በፊትም የአንበጣው ጉዳይ መላ ሊባል እንደሚገባው የአለም የምግብ ፕሮግራም አሳስቧል፡፡
ግጭት፣ የብሔር ጠብና የሠላም ደህንነት መታጣት ደግሞ በምዕራብና በደቡብ ኦሮሚያ አካባቢዎች እስካሁንም ድረስ የዘለቀ ችግር ሆኗል፤ በዚህም አርሶ አደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ የተቃወሰ ህይወት ለመግፋት ተገድዷል ያለው ሪፖርቱ፤ ውጥረቱ በጊዜ እልባት ካልተሰጠው በተለይ በቀጣዩ የክረምት ወቅት በአካባቢዎቹ ሰብል ማምረት ሊያስቸግር ይችላል ብሏል፡፡  


Read 855 times