Monday, 16 March 2020 00:00

በጥረት የተገኘ ታላቅነት!

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)
Rate this item
(3 votes)

  «ታላቅ ነህ ሳልልህ ብቀር ሥራዎችህ ቀድመውኝ ይናገራሉ» - (ቀ.ኃ)
              
          በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ታላቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ደራሲ፣ ታሪክ አዋቂ፣ ዕውቅ  ዲፕሎማት፣ በቤተ ክህነት ትምህርትና በቋንቋ የተካኑ ባለቅኔ፣ ገጣሚ፣ የዘመናቸውን ዕውቀት የቀሰሙ ምሁር፣ በአኗኗራቸው በምሳሌነት የሚታዩና ሠርተው የማይደክሙ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ እኒህ ሊቅ ብላቴን ጌታ ኅሩይ  ወልደ ሥላሴ ይባላሉ፡፡ የተወለዱት ግንቦት 1 ቀን 1871 ዓ.ም ከአባታቸው ከአቶ ወልደ ሥላሴና ከእናታቸው ወይዘሮ ወለተ ማርያም ዜና፣ በቀድሞ አጠራሩ በመርሐ ቤቴ አውራጃ፣ በታች ቤት ወረዳ ረመሸት ቀበሌ፣ ደን አቦ ገዳም በተባለ ሥፍራ ሲሆን ያረፉት ደግሞ መስከረም 9 ቀን 1931 ዓ ም እንግሊዝ አገር ባዝ በተባለው ቦታ በስደት ላይ እያሉ ነው:: ብላቴን ጌታ ኅሩይ ለቤተሰቦቻቸው የመጀመሪያ ልጅ ሲሆኑ አባትና እናታቸው ከእርሳቸው ቀጥሎ በተከታታይ ሁለት ሴት ልጆችን ወልደዋል፡፡ ሲወለዱ የወጣላቸው ስም ገብረ መስቀል የሚል ነው፡፡ ምናልባትም የክርስትና ስማቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም የመስቀል ባሪያ አገልጋይ፤ ጽሙድ እንደ ማለት ነው (ካፕላን፡ 2007፤21)፡፡
ክቡር  ብላቴን ጌታ ኅሩይ  የተወለዱበትን የደን አቦ ገዳም ቤተ ክርስቲያን ያሠሩትና የበላይ ጠባቂ ሆነው ያስተዳድሩት የነበሩት የዳግማዊ ምኒልክ የቀድሞ ሚስታቸው ወይዘሮ ባፈና ነበሩ፡፡ በዚህ ረገድ ወይዘሮ ባፈና የብላቴን ጌታ ኅሩይን አባት አቶ ገብረ ሥላሴን የገዳሙ አስተዳዳሪና የቤተ-ርስት ሹም አድርገው አስቀምጠዋቸው ነበር:: አቶ ገብረ ሥላሴም ሸዋ ውስጥ በመርሐ ቤቴ፣ አገሪት በተባለች ቦታ መንዝ ውስጥ ቢያድጉም፣ ቤተሰቦቻቸው ከወሎ አማራ ሳይንት የመጡ ናቸው፡፡ እናም አባታቸው እናታቸውን ያገቡት የ40 ዓመት ጎልማሳ እያሉ ሲሆን ወይዘሮ አመተ ማርያም ዜና፣ በመንዝ ጠል በተባለው ቦታ የማደሬ ቤተሰብ ተወላጅ ናቸው፡፡ ከሸዋው ንጉሥ ከሣህለ ሥላሴ እናት ከወይዘሮ ዘነበወርቅ ጋርም  ይዛመዳሉ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አቶ ወልደ ሥላሴ፣ የገዳሙን ካህናትና ዲያቆናት ግብር ለማብላት ተዘጋጅተው ሳለ፣ የገዳሙ አለቃ ለጊዜው በቦታው ላይ ባለመገኘታቸው ካህናቱ በረሀብ ይንገላታሉ፡፡ ይህንን ያስተዋሉት የቤተ ርስቱ ሹም አቶ ወልደ ሥላሴ፤ የገዳሙ አለቃ የድርሻቸው ምግብ ተቀምጦላቸው፣ አገልጋይ ካህናቱ እንዲመገቡ ያደርጋሉ፡፡ በመሃል የደብሩ አለቃ፣ እየተበላና እየተጠጣ ከች ይላሉ:: በቁጣ ንግግርም፤ «በቃ የገዳሙ ባህል ፈረሰ? እንዴት እኔ ሳልመጣ ሌሎቻችሁ ማዕድ ትቆርሳላችሁ? ይህንን የሚያደርግ መቼም ወልደ ሥላሴ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ወይዘሮ ባፈና ያልተማረ ጨዋ ሾመው ይኸው ይጫወትብናል» አሉና፤ ወደ ካህናቱ ዞረው «እንዴትስ በሌለሁበት ግብር ትበላላችሁ?» በማለት ይገስጿቸዋል፡፡
አቶ ወልደ ሥላሴም ጠቡንና ክርክሩን ያበረድሁ መስሏቸው «ካህናቱ በደጅ ቆመው በፀሐይ ሙቀት ስለተጉላሉ እርስዎም እንደ ደረሱበት ገብተው ግብር እንዲቀመጡ ያደረግሁ እኔ ነኝ፡፡ የእርስዎም ፋንታ በክብር ተቀምጧል፡፡ እና እባክዎን ይቀመጡና ይጋበዙልን» በማለት በትሕትና ይለምኗቸዋል፡፡ የደብሩ አለቃ ግና ባለመረጋጋት ነገሩን አክርረው «ካልተማረ መሐይም ምን ይጠበቃል? ቆይ ለወይዘሮ ባፈና ነግሬ ከሹመትህ ባላሽርህ እኔ ሰው አይደለሁም» ብለው የተቀመጠላቸውን ምግብ መኮምኮምና ጠላቸውንም መጎንጨት ይጀምራሉ፡፡ አቶ ወልደ ሥላሴም በደብሩ አለቃ ንግግር ተበሳጭተው ነበርና «መቼም እኔ ከእንግዲህ ተምሬ አልደርስም፡፡ ልጄ እንደኔ እንዳይሰደብ እርሱን ማስተማር አለብኝ» በማለት ወሰኑ (ኅሩይ ኢትዮጵያ ታሪክ 1999፤10)፡፡
በዚህ ዓይነት ልጃቸው ገብረ መስቀል የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ለመማር እንዲችሉ  በሰባት ዓመታቸው  መርሐ ቤቴ ሥላሴ ወስደው፣ ከእነ ስንቃቸው ጭምር ለመምህራኑ ያስረክቧቸዋል፡፡ የመጀመሪያው መምህራቸውም ደብተራ ሥነ ጊዮርጊስ ይባላሉ፡፡ በሁለት ዓመት ውስጥ ግእዝ ለማንበብና ዳዊት ለመድገምም ችለዋል፡፡ ከችሎታቸው የተነሣም ኅሩይ ለአባታቸው ጠቃሚ ልጅ ሆነው ታዩ፡፡ በዚህም ልጃቸው የበለጠ እንዲማር ከፍተኛ ፍላጎት ስለአደረባቸው፣ ኅሩይ 10 ዓመት ሲሆናቸው፣ በዘመኑ ታላቅ ወደነበረው ስሬ መድኃኔ ዓለም መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ወስደው አስገቡዋቸው፡፡ በዚህ ዓይነት የቤተ ክህነቱን ልዩ ልዩ ከፍተኛ ትምህርት ሲማሩ ቆይተው፣ በዜማ ትምህርት እስከ መምህርነት ደረጃ አጠናቀቁ፡፡ የመጻፍንም ልምድ ከተለያዩ ዕፀዋትና ጥላሸት፣ ቀለም በጥብጠው ከሚገለብጡት ከብራና መጻሕፍት ቀለማት ለማወቅ ችለዋል፡፡ ስሬ መድኃኔዓለም በትምህርት ከሚያተጓቸው አባታቸው ጋር በነበሩበት የመጀመሪያ ዓመታት፣ ከፍተኛ የሆነ የምግብ ችግር ደርሶባቸዋል (ሞልቪየር 1997፡3)፡፡ በኋላ ግን ችግራቸውን የተረዱትና የስሬ መድኃኔ ዓለም የበላይ ጠባቂ የነበሩት ወይዘሮ ፀሐየ ወርቅ ዳርጌ፤ ቋሚ የሆነ ጥቂት የምግብ አቅርቦትና ጥቂት ዓመታዊ የኪስ ገንዘብ መድበውላቸው ነበር፡፡
ከባለቤታቸው ከክብርት ወይዘሮ ሐመረ እሸቴ ጋር
በዚህ ዓይነት አባትና ልጅ አብረው ለሁለት ዓመታት ከቆዩ በኋላ፣ ወልደ ሥላሴ ወደ ታላቁ ገዳም ደብረ ሊባኖስ ሄደው በምንኩስና መኖር ጀመሩ፡፡ በኋላ በ53 ዓመታቸው እንደገና ወደ ልጃቸው ዘንድ ተመለሱ፡፡ ወላጅ እናታቸው፣ ልጃቸውን ኅሩይን አንድ ጊዜ የሚማሩበት ቦታ ድረስ ሄደው ቢጠይቋቸውም፣ በኋላ ግን ሊያገኙዋቸው አልቻሉም፤ ጠፉባቸው:: የአባ ወልደ ሥላሴም ጤና እየታወከ በመሄዱ እንደገና ወደ ደብረ ሊባኖስ ወርደው ጸበል ሲጠመቁ ከቆዩ በኋላ፣ ልክ ኅሩይ 13 ዓመት ሲሞላቸው ዐረፉና እዚያው ደብረ ሊባኖስ ተቀበሩ፡፡ ኅሩይ የአባታቸውን መቃብር ለማየት ወደ ደብረ ሊባኖስ በሄዱበት ሰዓት የአባታቸውን የንስሐ አባት አግኝተው፣ ያባታቸውን ኑዛዜ ነገሩዋቸው:: ይኸውም “ለኅሩይ በዚህ ዓለም ላይ ያለው ሀብት ትምህርት ስለሆነ ጠንክሮ ይማር፤ የማወርሰው ሀብትና ንብረት ስለሌለኝ ወደ ትውልድ ሀገራችን እንዳይመለስ” የሚል ነው፡፡ ከአባታቸው በተቀበሉት ኑዛዜ መሠረትም፤ ኅሩይ የቤተ ክህነቱን ልዩ ልዩ የትምህርት ዓይነት አጠናቅቀው፣ በዜማ ትምህርት እስከ መምህርነት ደረጃ ደርሰዋል፡፡ ከዚህ ደረጃ ላይ የደረሱትም ብዙ ችግሮችን በመቋቋም ነው፡፡
ቀደም ሲል ይረዱዋቸው የነበሩት ወይዘሮ ፀሐየ ወርቅ ዳርጌ፣ በሀገራችን በ1881 ዓ.ም የተከሠተውን የከብት እልቂት ተከትሎ ረሀብ ስለገባ፣ ለኅሩይ ይሰጡዋቸው የነበረውን የምግብና የኪስ ገንዘብ ድጋፍ ያቋርጡባቸዋል፡፡ ይሄኔ የግድ ራሳቸውን ለማኖር ሲሉ ባደረጉት ጥረት፣ ያያ በተባለው ቦታ የቤተ ክርስቲያን መሬት ያስተዳድር ከነበረ አርሶ አደር ድጋፍ ለማግኘት ቻሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ኅሩይ በዲቁና ማዕርግ ሲያገለግሉ የራሳቸው መተዳደሪያ የሆነች መሬትም አግኝተው ስለነበር፣ ኑሯቸው ከሞላ ጎደል ጥሩ ሆነላቸው፡፡ የተለያዩ የጽሕፈት ሥራዎችን በክፍያ ለሰዎች ይጽፉ ነበር፤ በዚህ ዓይነት ገቢያቸው እያደገ ስለሄደ ፈረሰኛ ባይሆኑም፣ አንድ ፈረስ ገዝተው ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ስማቸው እየታወቀ ስለሄደ የሰላሌው ገዥ ደጃዝማች በሻህ ውረድ፣ ጸሐፊ አስፈልጓቸው ነበርና ኅሩይን በጸሐፊነት ቀጠሯቸው፡፡ ብዙም ሳይቆዩ የራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል ዋና ጸሐፊ ለሆኑትና አዳበርጋ አጠገብ፣ ሲኖ ከተባለው ቦታ ለሚኖሩት  ቀኛዝማች መቅረጭ አገልጋይ ሆኑ፡፡ ኅሩይ በጸሐፊነት ባይቀጠሩም ቀኛዝማች መቅረጭ ችሎታቸውን ተመልክተው “የሆነው ፍሬ” እያሉ ይጠሯቸው ነበር፡፡ ከዚህም የተነሣ የመንግሥት ግብር በሚሰበሰብበት ሰዓት ኅሩይ ዋና ንብረት መዝጋቢ ሆነው ያገለግሏቸው ስለነበር፣ በቀኛዝማች መቅረጭ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ሆኑ  (ዝኒ ከማሁ 1997፡3)፡፡
ከዚያም ወደ አዲስ አበባ እንጦጦ ራጉኤል ደብር መጥተው፣ የመጻሕፍትን ትርጓሜ፣ በዘመኑ ከነበሩ ሊቃውንት ዘንድ በመማር አጠናቀቁ፡፡ በእንጦጦ የነበሩ አንድ ሊቅ መምህራቸው ስማቸውን ሲጠይቋቸው፤ ገብረ መስቀል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሊቁም «ጎንደር በነበርሁ ጊዜ አስተማሪየ ስለወደዱኝ ኅሩይ እያሉ ይጠሩኝ ነበር፡፡ ወደ  አዲስ አበባ  ስመለስ ግን በቀድሞ ስሜ እየተጠራሁ ነኝ:: ስለዚህ አንተ የቀለም ቀንድ ስለሆንህና በምግባርህም የተወደድህ በመሆንህ ኅሩይ የተባለውን ስሜን ትጠራበት ዘንድ ሸልሜሃለሁ» ይሏቸዋል፡፡ በ1901 የራጉኤል የደብር አለቃና የዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ የጽሕፈት ሚኒስትር ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ ወልደ አረጋይ፣ ስለ ኅሩይ ዝና ከደብሩ ሊቃውንት ስለሰሙ፣ ኅሩይን በጣም አቀረቧቸው፡፡ ኅሩይንና ጓደኞቻቸውን፤ በምሁርነታቸውና በብሩህነታቸው፤ በትጋታቸውና በታማኝነታው እንዲሁም  በመልካም ሥነ ምግባራቸው ፈጽሞ ወደዷቸው፤ አከበሯቸውም፡፡
ከዳግማዊ ምኒልክ ፊት አቅርበውም አሸለሟቸው፡፡ ዳግማዊ ምኒልክም የኅሩይን ልጅነት አይተው፤ «እንዲያው ለቁጥር ማሙያ ከሊቃውንቱ ጋር አቅርበህ አሸለምከው እንጂ ገና ልጅ ነው፡፡ ምን ሊያውቅ ይችላል? ቢሏቸው ጸሐፌ ትእዛዝም፤ ‘ጃንሆይ ዕድሜው ነው እንጂ እውቀቱ ትልቅና ዘሊቅ ነው’ ብለው በመመስከር ንጉሠ ነገሥቱን አሳመኗቸው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኅሩይ በቤተ ክህነቱና በቤተ መንግሥቱ እየታወቁና እየገነኑ ስለመጡ፣ ተወዳጅነታቸው በሁሉም ሰው ዘንድ ታወቀ፡፡            
ብላቴን ጌታ ኅሩይ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የታወቁ ፖለቲከኛና በቤተክህነቱም ከፍተኛ ምሁር የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ ኅሩይ በጥንታዊና ዘመናዊ ትምህርት የተቀረጹ ሰው ነበሩ፡፡   ለዘመናዊ ትምህርትም ከአላቸው ጉጉት የተነሣ በኋላ ላይ አዲስ አበባ ስዊድን ሚሽን ትምህርት ቤት ገብተው፣ የውጭ አገር ቋንቋ ማለትም እንግሊዝኛ መማራቸው፣ ስለ ውጭ ሀገራት የነበራቸውን አሰተሳሰብ የበለጠ አሳድጎላቸዋል፡፡ በተጨማሪም ከዶክተር ቻርለስ ማርቲን ወይም ከሐኪም ወርቅነህ ጋር ግንኙነት መመሥረታቸው ስለ ውጭ ሀገር ያላቸውን ዕውቀት ከፍ አድርጎላቸዋል:: ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ በዐረብኛም የተለያዩ የትምህርት ዓይነቶችን ለመማር ጥረት አድርገዋል፡፡
ነገር ግን በወቅቱ “ኅሩይ እስላም ሆነ” የሚለውን አሉባልታ ስለሰሙ የዐረብኛ ትምህርታቸውን ለማቆም ተገድደዋል:: ከዚያም ከፈረንሳይ የከብት ሕክምና ባለሙያዎች፣ ፈረንሳይኛን ለመማር ችለዋል፡፡ በተለይ የኅሩይን ዕውቀት የበለጠ ያሳደገላቸው በተደጋጋሚ ወደ ውጭ ሀገራት ሲያደርጉት የነበረው ጉዞ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ለአብነትም እ.ኤ.አ በ1911 ከደጃዝማች በኋላ ልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ ጋር በእንግሊዙ ንጉሥ በጆርጅ 5ኛ በዓለ ንግሥ ላይ ለመገኘት መቻላቸውና  በተደጋጋሚም ከኢትዮጵያ መንግሥት  ልዑካን ጋር እንግሊዝ ሀገር ደርሰው መመለሳቸው፤ እ.ኤ.አ በ1949 በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ዘአሊያንስ ተብለው ይታወቁ የነበሩት  የቃል-ኪዳን (የኅብረት ኃይሎች) ስላሸነፉ አሜሪካንን እንኳን ደስ አለሽ ለማለት ወደዚያው መጓዛቸው፤ እ.ኤ.አ በ1920 እና በ1923 ወደ ኢየሩሳሌም ማቅናታቸው፤ እንደገና እ.ኤ.አ በ1924 እና 1931 ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጋር  አውሮፓና ቻይና ደርሰው ለመመለስ በመቻላቸው፤ ለጥቂት ጊዜያትም በጃፓን የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሙሉ ሥልጣን ሚኒስትር (አምባሳደር) ሆነው መሥራታቸው፤ ስለ ውጭ ሀገራት እድገትና ሥልጣኔ ይበልጥ ለማወቅ አስችሏቸዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ1914/15 የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሆኑ በር የከፈተላቸው፣ ራሳቸው የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ብለው ስም ባወጡለት መሥሪያ ቤት ዋና ጸሐፊና ኃላፊም ሆነው መሥራታቸው ነው፡፡ እ.ኤ.አ ከ1916 ጀምሮ በዳሬክተር ጀነራልነት ማዕርግ አግኝተው አገልግለዋል፡፡ እ.ኤ.አ ከ1920-21 ድረስ ደግሞ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ከንቲባ ሆነው ሠርተዋል፡፡ ቀጥሎ በዋና ኃላፊነትና በብላቴን ጌታ ማዕርግ የልዩ ፍርድ ቤት ዳኛ በመሆን አገልግለዋል፡፡ ልዩ ፍርድ ቤቱ ይመለከትና ይመረምር የነበረው ርእሰ ጉዳይ፣ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ዜጎችን ክስ ነው፡፡ «ብላቴን ጌታ» የሚለው ስመ ማዕርግ ፤ ኅሩይ ከሚለው ስማቸው ጋር ተወራራሽነት አለው፡፡ ብላቴን ጌታ ኅሩይ እ.ኤ.አ በ1927 በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዳሬክተር ጀኔራል ሆነው ተሹመዋል፡፡
ብላቴን ጌታ ኅሩይ፤ በትዳር ሕይወታቸውም መልካም አርዓያ ስለነበሩ፣ ከባለቤታቸው ወይዘሮ ሐመረ እሸቴ ስድስት ልጆን ወልደዋል፡፡ በርካታ የልጅ ልጆችንም አፍርተዋል፡፡ ቤተሰባቸውንም በእግዚአብሔር ሕግ መሠረት በፍቅር ይመሩና ያስተዳድሩ ነበር፡፡ ሞልቪየር እንደጻፈው፤ ብላቴን ጌታ ኅሩይ በዚያች በድህነታቸው ዘመን ለማግባት የፈለጉት የጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴን ልጅ ነበር:: ግን አልፈቀዱላቸውም፡፡ ለዚህም ነው ወደ ትውልድ ሀገራቸው ሔደውና ቆንጆይቱን ወይዘሮ ሐመረን አፈላልገው ያገቡት:: በድርሰት ረገድ ከ21 በላይ የተደነቁ መጻሕፍትን ደርሰዋል፡፡ ሥራዎቻቸው ሁሉ ትሕትናን፤ ትክክለኛነትን፤ ምግባረ ሠናይነትንና  ሞራልን ከፍ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው፡፡
ብላቴን ጌታ ኅሩይ  ከጻፏቸው መጻሕፍት ውስጥ “ኢትዮጵያና መተማ የዓፄ ዮሐንስ ታሪክ ባጭሩ” (1910 ዓ.ም)፤ “ወዳጄ ልቤ” 1955 ዓ ም፤ “ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” 1955 ዓ.ም፤ “የልዕልት ወይዘሮ መነን መንገድ በኢየሩሳሌምና በምስር” 1915 ዓ.ም፤ “መጽሐፈ ቅኔ” 1918 ዓ ም፤ “ዋዜማ” 1926 ዓ ም፤ “በኢትዮጵያ የሚገኙ በግእዝና በአማርኛ ቋንቋ የተጻፉ የመጻሕፍት ካታሎግ” 1920፤ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥት ሳባ እስከ ታላቁ የዓድዋ ድል” 1999 ዓ.ም፤”ድርሳኖች” 1983፤ “ማኅደረ ብርሃን ሀገረ ጃፓን” 1924 ዓ.ም፤ “የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ታሪክ” 1871-1931 ዓ.ም በባሕሩ ዘውዴ የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ሥራዎቻቸው አብዛኞቹ በታሪክ፤ በግለ ታሪክ፣ በመዝገበ ቃላት፤ በጉዞ ማስታወሻዎችና በልቦለድ ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቻቸውም ዓለማቀፋዊ ዝናን አትርፈውላቸዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ1929 በስደት እንግሊዝ አገር ሳሉ፣የጀርመን ኦሪየንታል ማኅበረሰብ የክብር አባል እስከመሆን ደርሰው ነበር:: በኢጣሊያ ወረራ ምክንያት በስደት እንግሊዝ አገር እንደነበሩም፣ በኦሪየንታል ጥናትና ምርምር ተቋም (በኋላ የኦሬንታልና የአፍሪካ ጥናት ትምህርት ቤት በተባለው) የግእዝና የአማርኛ መምህር ሆነው ሠርተዋል፡፡ የአገልግሎታቸው ዋጋ ከፍ እያለ በመሄዱም እ.ኤ.አ ከሚያዚያ 19/1931 ጀምሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡ በተጨማሪም በ1937 ዓ.ም ለተቋቋመው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የመጀመሪያው ሊቀ መንበር በመሆን አገልግለዋል፡፡ ብላቴን ጌታ ኅሩይ፣ በኢጣሊያ ወረራ ወቅት፣ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ በማይጨው ጦርነት ስለተሸነፉ፣ ወደ ስደት መሄድ የለባቸውም ከሚሉት ወገኖች የነበሩ ሲሆን በኋላ ግን ንጉሠ ነገሥቱን ተከትለው ወደ እንግሊዝ ሄደዋል፡፡
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ
       ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ በጀኔቫ የዓለም መንግሥታት ማኅበር፣ ስለ ኢትዮጵያ የግፍ ወረራ ሲገልጹ፤እርሳቸውም ከንጉሠ ነገሥቱ ጎን ሳይለዩ የመከራውና የስደቱ ተካፋይ ነበሩ፡፡ እዚያም የሕይወታቸው ፍጻሜ ሆኗል፡፡ መስከረም 9 ቀን 1931  ዐርፈው፣ መስከረም 10 ቀን 1931 ዓ ም በባዝ ከተማ ሉግዘምበርግ በተባለው ቦታ በተከናወነው የቀብራቸው ሥነ ሥርዓት ላይ፤ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ «ታላቅ ነህ ሳልልህ ብቀር ሥራዎችህ ቀድመውኝ ይናገራሉ» ብለዋል፡፡ ቀጥለውም፤ «ይህ የአዳም ልጆችን ወግ ሲቀበል የምታዩት ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ በሀገራችን ሥርዓት በመልካም አያያዝ ያደገ፤ ከኢትዮጵያም ከፍ ካሉት ሊቃውንት የሚቆጠር ነው፡፡ ብልኃቱንና ትጋቱንም ለመልካም ሥራ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች ስለአደረጋቸው በመንግሥታችን ሥራ ለመመረጥና ወደ ታላቁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ለመድረስ ችሏል፡፡ በጊዜውም የጻፋቸው መጻሕፍት ከፍተኛ ባሕርዩን የሚገልጹ ይልቁንም በቤተ ክህነትና በታሪክ ዕውቀት፣ በዓለም ሊቃውንት ዘንድ የታወቀና የተከበረ አደረጉት፡፡ ለምታውቁት ሰው ከታሪኩ ከዚህ የበለጠ ልነግራችሁ የሚያስፈልግ አይመስለኝም» የሚል ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡
የእግዚአብሔር መልካም ፈቃዱ ሆኖ ሀገራችን ለነጻነት ከበቃች፣ ዐፅሙን ለሀገሩ ዐፈር እንደሚያበቁ ንጉሠ ነገሥቱ ቃል የገቡ ሲሆን በቃላቸው መሠረት፣ ከነጻነት በኋላ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ዐፅም ከባዝ የመቃብር ቦታ ፈልሶና በመስከረም 11 ቀን 1940 ዓ.ም አዲስ አበባ ገብቶ፣ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን በክብር እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ለሀገራቸው ዕድገትና መሻሻል የራሳቸውን አሻራ ጥለው ያለፉ ታላቅ ምሁር ስለነበሩ በትውልድ ዘንድ ለዘለዓለም ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡ ለስማቸው ማስታወሻ እንዲሆንም መኖሪያ ቤታቸው የሳይንስ አካዳሚ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡              



Read 10559 times