Saturday, 07 March 2020 13:12

“ከእኔ በላይ አዋቂ ለአሳር!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(8 votes)

        “አሁን ቦለቲካው ውስጥ ሁሉም ነጻ አውጪ ሆኖብን የለ! ኮሚክ እኮ ነው..መጀመሪያ ራሱን ከኋላ ቀር አስተሳሰብ ነጻ ሳያወጣ ሌላውን ነጻ ላውጣ የሚል ከመብዛቱ የተነሳ ‘ተረፈ ምርት’ በሽ፣ በሽ ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…”
           
            “እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…በቀደም በአድዋ በዓል አከባበር ላይ አንድ ወጣት በወረቀት ይዟት የነበረች መፈክር ነገር ምን የምትል መሰላችሁ… “ግብጽ ወዮልሽ!” ለጉልቤው አልሲሲ ኢንቦክስ አድርጉላቸውማ! 
ዘንድሮ ምን አይነት ነገር አለ መሰላችሁ…“ሁሉም ለእኔ፤ ለሌላው ምንም” አይነት ነገር የሁላችንም ባህሪይ እየሆነ ነው፡፡ ቦተሊካችን ቢያጥቡት አልጠራ፣ ቢኳኩለት አላምር ያለው እኮ ለዚሁ ነው፡፡ ከእለታት አንድ ቀን እዚህ አገር ላይ ‘ተካፍሎ መብላት’ የሚሉት ነገር ነበር፡፡ አይደለም የሚያውቁት ሰው፣ የማያውቁት ሰው እንኳን አካባቢያችን ካለ መጋበዝ የተለመደ ነበር፡፡ 
“እንብላ…”
“አመሰግናለሁ፣ አሁን ነው የበላሁት፡፡”
ሁሉም “እንብላ…” ባይ ከአንጀቱ መጋበዙ ላይሆን ይችላል፡፡ ግን በቃ አብሮ የመኖር አንዱ ልማድ ነው፡፡ ተጋባዡም ቢሆን ከተመገበ ሦስት ቀን ያለፈው ቢሆንም “በአንድ አፍ!” ብሎ ማእዱ ላይ አይሰፍርም:: ሞራል፣ ምግባር፣ አብሮ መኖር ምናምን የሚባሉ ነገሮች ከእለታት አንድ ቀን ነበሩዋ!
ዘንድሮ ‘ተሰለጠነና’ አይደለም “እንብላ…” ማለት ስንመገብ በአጠገባችን የሚያልፍ ሰው ከአፋችን ላይ የሚነጥቀን መስሎን ለመከላከል እናኮበኩብ እንደሆነ ነው እንጂ ግብዣ ብሎ ነገር እየጠፋ ነው፡፡ እንደውም ምን መሰላችሁ… የማናውቀው ሰው “እንብላ…” ካለን… አለ አይደል… ነቃ ነው የምንለው፡፡ “አላውቀው፣ አያውቀኝ እንዴት እንብላ ይለኛል!” በሚል ይጀመርና ምን አለፋችሁ የመላ ምቱ መአት ይደረደራል፡፡ 
“ያቺ ነገረኛ እኔ ላይ በጎን ጠላት መላኳ ነው!” ይልና ከአስራ አንድ ዓመት በፊት የተለያያት ሚስቱ ትመጣበታለች፡፡ “አጅሪት በእሷ ቤት ብልጥ መሆኗ ነው፡፡” ይላል:: እሷ እኮ እንደገና አግብታ፣ ማንም ሰው ከማይቀርባት አማሪካን ሄዳ ምናምን ስትሪት ላይ “ናፈቀኝ አገሬ” የሚል ሬስቱራንት ከፍታለች፡፡
ወይ ደግሞ… አለ አይደል… ዘንድሮ መቼም በየክንዱና በየምናምን የሰውነት ክፍሉ የሚነቀስና ቦተሊከኛ ነኝ የሚል በጸጉር ልክ ነውና አጅሬው ምን ይላል መሰላችሁ… “ምርጫ ሲቃረብ ደግሞ እንደማሸንፋቸው አውቀው በዚህ በኩል መጡብኝ! በእነሱ ቤት እኔ ሞኝ እነሱ ብቻ ብልጥ፡፡ ይህን ከእንትን አገር ሶስት ወር ሙሉ ያስደገሙበትን መድህኒት፣ በምግብ አስመስለው ሊሰጡኝ!” ምናምን ይላል፡፡
እንደውም በኮንዶሚኒየም ኑሮ እናሳብባለን እንጂ ገና በየኮንዶሚኒየሙ ያልሰፈረውም ሰው እንደ ቀድሞው ቡና መጠራራት እየተወ ነው፡፡ አይደለም “እትየ እንትና፣ ኑ ቡና ጠጡ” ብሎ መጠራራት “አንቺ፣ እስካሁን ቡናው አልደረሰም እንዳትዪኝ!” ብለን ሰተት ብለን የምንገባበት ዘመን ቅርብ ነበር እኮ! 
እናላችሁ… ብዙዎቻችን ለራሳችን የምንሰጠው ግምት ጣራ እየነካ፣ ሰውነት ማሳረፊያ በሌለበት ባዶ አየር ላይ ተንሳፈን “ረጅም እድሜ ለንጉሣችን!”” እየተባለ እንዲዘመርልን እንፈልጋለን፡፡ አሁን ቦለቲካው ውስጥ ሁሉም ነጻ አውጪ ሆኖብን የለ! ኮሚክ እኮ ነው..መጀመሪያ ራሱን ከኋላ ቀር አስተሳሰብ ነጻ ሳያወጣ ሌላውን ነጻ ላውጣ የሚል ከመብዛቱ የተነሳ ‘ተረፈ ምርት’ በሽ፣ በሽ ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… እናላችሁ…“ሰዉን በፈለገው ስፍራ ተዘዋውሮ እንዲሠራና እንዲኖር አደርጋለሁ” የሚለው ‘የዘመኑ ሌኒን’ እኮ ሚስቱን… “ከሥራ ከወጣሽ በኋላ ቀጥ ብለሽ ቤት ትመጫለሽ እንጂ ወዲህ፣ ወዲያ ውልፍት እላለሁ ብትይ አንቺን አያድርገኝ!” የሚል አይነት ነው፡፡
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የመፈላሰፍ ወይ ካልተፈላሰፍን የምንል አልበዛንባችሁም፡፡ የምር እኮ በተለይ ካሜራ ፊት ከተቀመጥን፣ ወይም ማይክ አፋችን ስር ከተደረገልን፣ ካልተፈላሰፍን እያልን ነው፡፡
“በአሁኑ ጊዜ ላለው የኑሮ ውድነት ዋናው ምክንያት ምንድነው ይላሉ?”
“እ….ዌል፣ ምን መሰለሽ… መቼም የሰው ልጅ ካልበላ፣ ካልጠጣ ፈንክሽን ማድረግ…”
ይሄን ጊዜ… አለ አይደል….ጋዜጠኛዋ በሆዷ “አቦ፣ ወደ ጉዳይህ ግባ! ትረካ አንብብልኝ አልኩህ እንዴ!” ሳትል አትቀርም:: ጮክ ብላ ግን “ይቅርታ፣ በቀጥታ ወደ ጉዳዩ ይገቡልኛል!” ማለት ሲገባት…አለ አይደል… “በእርግጥ እርሶ እንዳሉት በተለይ የተመጣጠነ ምግብ ለሰው ልጅ አካላዊና አእምሯዊ እድገት…” ምናምን እያለች እንትና የሚባል ፈላስፋ ‘ህጋዊ ወራሽ’ ዓይነት ሆና ቁጭ ትላለች፡፡
እናማ…እንዲህ አይነት በትንሽ ትልቁ ነገር በአስር ቃላት ተናግረን የምንጨርሰውን ነገር ወደ መቶ አንድ ቃላት የምናበዛ ሰዎች፣ አንዱ ችግራችን ምነ መሰላችሁ፣ ሌላው ሰው ዝም ብሎ ስለሚያዳምጠን እኛ ብቻ አዋቂ የሆንን ይመስለናል፡፡ ስለ ፖለቲካው የምናውቅ እኛ ብቻ፣ ስለ ኤኮኖሚ የምናውቅ እኛ ብቻ፣ ስለ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች የምናውቅ እኛ ብቻ…
“የቱርክ ጦር በአፍጋኒስታን ላይ እያደረገ ያለው የአውሮፕላን ድብደባ…”
ኸረ በህግ!
 “ሁሉን አውቃለሁ” የምንል ሰዎች ግትር የሚለው ቃል ብቻ አይገልጸንም፡፡ ያቺ አሁን፣ አሁን ያቺንም፣ ይህንንም እያሳበጠች ያለች እብሪት የሚሏት ነገር አለች፡፡ የምር የአንዳንዱ እብሪት እኮ…አለ አይደል…የሆነ ኮሜዲ ነገር ሊሆን ምንም አይቀረው:: “መግቢያ በነጻ” እንደሚባል ኤግዚቢሽን ምናምን ነገር ሁላችንም “እኔ ነኝ ፊታውራሪ” እያል ያለንበት የዘንድሮ ‘ቦተሊካ’ የማያሳየን ጉድ የለም፡፡ ግንድ የሚያካክል ስልጣን ያለው፣ ግንድ የሚያካክል አካዳሚያዊ ማእረግ ያለው፣ ግንድ የሚያካክል የእምነት ስልጣን ያለው ሰው ሁሉ አደባባይ እየወጣ… አለ አይደል… ጥንድ ድርብ ጋቢ ነው ያልነው ሁሉ ትንሽ ጠንከር ያለ ነፋስ የሚሸረክተው በቀሺም ሸማ የተሠራ ነጠላ እየሆነብን ተቸገርን፡፡ (ምሳሌያችንን በአገር በቀል ምርቶች ለማድመቅ ያህል ነው!)
እናላችሁ…. እብሪት ደግሞ ክፋቷ የማወቅ ምልክት አለመሆኗ ነው፡፡ የአእምሮ ስፋት፣ የአስተሳሰብ ጥልቀት ማስመስከሪያ አይደለችም፡፡ ይልቁንም አእምሮ እየጠበበ መሄድን የምታሳብቅ ነች፡፡ (አሀ…እኔስ መፈላሰፍ ይጠላብኛል!) በአጭሩ ‘ኢቮሊዩሽኑን’ ያልጨረሰ አእምሮ ውጤት ነች፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… ሰዋችን እኮ ዝም የሚለው ስለማያውቅ፣ ወይም ስላልገባው፣ ነገሩ ከአእምሮው የማመዛዘን ብቃት በላይ ስለሆነበት አይደለም፡፡ እጁን አጣምሮ፣ በእጁ አገጩን ደገፍ አድርጎ ሲያዳምጥ እኮ እየታዘበ ነው፡፡ “ሂድና መንገድ የጠፋበት አርመን ቱሪስት ብላ!” እያለ ነው፡፡
እንደው እነኚህ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የእኛን ደግ ደጉን አላይልን እያሉን አስቸገሩን እንጂ ራሳችንን በሾምን አዋቂዎች ብዛት ዓለም ላይ የሚወዳደረን ይኖራል? የምር እኮ…የሆነ ነገር “ይህን ነገር አላውቀውም” ማለት የዓለም ፍጻሜ የሚመስለን አለን:: ካላወቅነው አላወቅነውም ማለት ነው:: “ይህንን ጉዳይ ብዙም ስለማላውቀው የምታውቂውን ብታስረጂኝ” ማለት የዓለም ፍጻሜ ማለት አይደለም፡፡ “አላውቀውም” ማለት የሆነ እድሜ ይፍታህ እየመሰለን፣ በግድ አዋቂ ለመሆን ስንሞክር፣ ይበልጡኑ ራሳችንን እያጋለጥን ነው፡፡
ለምሳሌ በየጊዜው የምንሰማውን የመግለጫ ጋጋታ ነገሬ በሉልኝማ፡፡ መጀመሪያ ነገር በሆነ ህብረተሰብ ስም መግለጫ የሚሰጡ ክፍሎች፣ በተባለው የህብረተሰብ ክፍል ስም ኦፊሴላዊ መግለጫ ለመስጠት ምን ያህል ህጋዊ መሰረት አላቸው ማለት ግድ ነው፡፡ ራሱ ተመራጭ፣ ራሱ መራጭ፣ ራሱ ድምጽ ቆጣሪ አይነት ሰው በዝቶብናል:: እንዲህም ሆኖ ግን አንዱ ጥቁር ያለውን ሌላው ነጭ እያለ፣  አንዱ ወደቀ፣ ተሰበረ ያለውን አንዱ ቀና ብሎ ቆሟል እያለ እንደ ማዳወሪያ ወዲህና ወዲያ የምንወረወረው የማወቅ ምልክት አይደለም፡፡
የሀገር ችግር ተናጋሪው፣ ዲስኩረኛው መብዛቱ ብቻ አይደለም፡፡ ታሪክ የማናውቅ ታሪክ ተንታኞች፣ ፖለቲካ የማናውቅ ፖለቲከኞች፣ ዘፈን የማናውቅ ዘፋኞች (ቂ…ቂ…ቂ…) መብዛታችን ነው፡፡
“ከእኔ በላይ አዋቂ ለአሳር!” ብሎ ነገር አገርንም፣ እኛንም የትም እያደረሰን አይደለም፡፡
በነገራችን ላይ… የቢራው ሂሳብ ነገር እንዴት ይዟችኋል?!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1916 times

Follow us on twitter

Due to an error, potentially a timed-out connection to Twitter, this user's tweets are unable to be displayed.