Print this page
Saturday, 07 March 2020 13:15

የማስታወቂያ ሥራ ፈር ቀዳጁ ውብሸት ወርቃለማሁ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

    የማስታወቂያ ሥራ ፈር ቀዳጁና የአንበሳ ማስታወቂያ መሥራችና ባለቤት አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ባደረባቸው ህመም  በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል በህክምና ሲረዱ ቆይተው፣ ባለፈው የካቲት-2012 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን የቀብር ሥነሥርዓታቸውም፣ ምክትል ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና የቱሪዝምና ባህል ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ካሣሁን እንዲሁም አንጋፋና ዝነኛ አርቲስቶች፣ የማስታወቂያ ባለሙያዎችና ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት በቅዱስ ሥላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን በክብር ተፈጽሟል፡፡  
ጋሽ ውብሸት በጥቁር ካባቸው ተውበው፣ በአገራዊ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባልነት፣ በቻምበር ኦፍ ኮሜርስ ሃላፊነት እንዲሁም፣ በቀይ መስቀልና ደም ባንክ አምባሳደርነት አገልግለዋል።
ነፍስ ይማር!
ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው መጽናናትን እንመኛለን፡፡
***
“ከመንዝ እስከ አዲስ አበባ”
የኢትዮጵያ ማስታወቂያ ፈር ቀዳጅ መሆናቸው የሚነገርላቸው ጋሽ ውብሸት ወርቃለማሁ፤ ለእንግድነት ከተጠሩ በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት የተዋበ ነጭ ልብስ ያዘወትራሉ፤ ከዚያም አጠር ካለው ቁመናቸው ጋር የሚሄድ ካባ በላዩ ላይ ይደርቡበታል።
በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ የማስታወቂያ ስራዎች የእርሳቸው አሻራ አርፎባቸዋል። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ማስታወቂያዎችን ሰርተዋል። ለዛ ባለውና በሚያስገመግመው ድምጻቸው ይታወቃሉ። ለወጣት የማስታወቂያ ባለሙያዎች አርአያ በመሆናቸው ብዙዎችም ያከብሯቸዋል። በቀብር ሥነሥርዓታቸው ላይ የተገኙ የአገሪቱ ታዋቂ የማስታወቂያ ባለሙያዎችም ይህንኑ ነው በአንደበታቸው የመሰከሩት፡፡
“ከመንዝ እስከ አዲስ አበባ”
አቶ ውብሸት ወርቅአለማሁ የተወለዱት መንዝ በቀድሞው ይፋት አውራጃ፣ ማፉድ ገበያ፣ አንቃውሃ በተባለ አካባቢ ነው። የትውልድ ዘመኑን የሚያስታውሱት ከታሪክ ግጥጥሞሽ ጋር በማያያዝ እንጂ በስንት ዓመተ ምህረት እንደሆነ በውል አያስታውሱትም።  በወርሃ መስከረም ጃንሆይ ድል አድርገው ከገቡ በኋላ እንደተወለዱ ከእናታቸው መስማታቸውን ይገልጻሉ፡፡ የግለ ታሪክ መፅሐፋቸው ደግሞ በ1934 ዓ.ም እንደተወለዱ ይናገራል።
አባታቸው አለቃ ወርቃለማሁ ወልደየሱስ፣ ወንድ ከወለዱ እረኛ ሆኖ ያገለግለኛል ቢሉም፤ ሳይጠቀሙባቸው ለስራ ወደ አርሲ ይሄዳሉ። ለቤተሰባቸው የመጨረሻ ወይም ሰባተኛ ልጅ የሆኑት አቶ ውብሸት በተወለዱ በዓመታቸው አባታቸውን በሞት ይነጠቃሉ። በዚህም በእናታቸው ወይዘሮ ተናኜወርቅ አበሩና በአያታቸው ወይዘሮ ዘነበች እጅ አደጉ፡፡ እናታቸው ወይዘሮ ተናኜወርቅ፣ ልጃቸውን በቤት ውስጥ መምህር ቀጥረው ፊደል እንዲቆጥሩ አደረጓቸው። መምህር ሸዋለማ የተባሉት የቤተክህነት መምህር ደግሞ ቅስና፣ ዳዊት መድገም እንዲሁም ዜማን አስተማሯቸው።
የትምህርት አቀባበላቸው ጥሩ ነበርና እድሜያቸው አስር ሳይደርስ ማፉድ ደብረኃይል ቅዱስ ሚካኤል ደብር በዲቁና ማገልገል ጀመሩ። ዲያቆን እያሉ ግን አንድ ቀን በተወለዱበት አካባቢ ማፉድ ገበያ ያለው ክንውን ቀልባቸውን ይስበዋል። የገበያው ትርምስ፣ የሸማችና ሻጭ አለመገናኘት በአጠቃላይ የቀያቸው ንግድ ቀልባቸውን ቢስበው አንድ መላ ይዘይዳሉ። ረጅም ሰው በረዳትነት በማቆም ገዢና ሻጩን እያገናኙ ገንዘብ እንደሚያገኙ በማሰብ ስራውን ጀመሩት። አብሯቸው የሚሰራው ደግሞ ሁለት ሜትር ከአስር ሳንቲ ሜትር ርዝመት ያለው ቁመተ መለሎ ሰው ነበር። በማፉድ ገበያ አንድ ጠዋት፣ ረጅሙ ሰው ትከሻ ላይ ወጥተው «ይህን ያህል ሰንጋ፣ ይህን ያህል ጤፍ፣ ሁሉም በየአይነቱ ገብቷል» በማለት የመጀመሪያውን ማስታወቂያ በአየር ላይ አዋሉ። በማስታወቂያው የተሳበው ሸማች፣ የትነው ያለው እያለ፣ ከሻጭ ጋር እየተገናኘ ግብይቱ ሲጧጧፍ ዋለ። መጠነኛ ገቢም ከሻጮች በመቀበል፣ የዕለት የማስተዋወቅ ውሏቸውን አጠናከሩት።
አያታቸውና አንዳንድ የቤተሰብ አባላት ግን «እንዴት የጨዋ ልጅ በገበያ መሃል ይጮሃል» እያሉ የማስታወቂያ ስራቸውን እንዲተዉ መገሰፃቸው አልቀረም። እርሳቸው ግን ስራውን ከማቆም ይልቅ ይበልጥ ገፉበት። በድቁና ስራቸው በዓመት አምስት ማርትሬዛ የሚያገኙት አቶ ውብሸት፤ በማፉድ ገበያ የሆሳዕና ዕለት በሰሩት የማስታወቂያ ስራ ብቻ ከአጋራቸው ጋር አስር ማርትሬዛ ማግኘታቸውን ያስታውሳሉ። በወቅቱ ሲሸከሟቸው ለሚውሉት ቁመተ መለሎ የተወሰነውን ማርትሬዛ በመስጠታቸውና እርሳቸውም እኩል መካፈል አለብኝ በማለታቸው ትብብራቸው መፍረሱን ያስታውሳሉ።
ግን ለበጎ ነበር፡፡ ሰው ትክሻ ላይ ወጥተው ማስታወቂያ ከመስራት ይልቅ ወደ ጽሁፍ ማስታወቂያ እንዲሸጋገሩ አድርጓቸዋል። አጤፋሪስ እና የከሰል ድቃቂ አቀላቅለው ለሶስት ቀን በማቡካት ያገኙትን ቀለም የፍየል ቆዳ አስወጥረው መፃፍ ጀመሩ። በገበያው በሚገኝ ትልቅ ዛፍ ላይ ቆዳውን በአጋም እሾህ ይወጥሩትና የገባውን እህልና ሰንጋ ብዛት እየጻፉ ማስተዋወቁንም ተያያዙት።
ቆዳው በየሳምቱ ቅዳሜ ዕለት ይታጠብና ሌላ ማስታወቂያ ይጻፍበታል። እንዲህ እንዲህ እያሉ የማስታወቂያ ስራ ታዋቂነታቸውን በመንዝና ይፋት አካባቢዎች አሰፉት። ከዚያ ከገበያ በኋላ ለእንጨት መጫኛ ከባድ መኪና አስተዋዋቂ ሆነው መስራት ጀመሩ። መኪናው እንጨት ከጫነ በኋላ ወደ አዲስ አበባና ወደተለያዩ ቦታዎች የሚሄዱ ተሳፋሪዎችን ይጭናል። አቶ ውብሸት ደግሞ «መኪናው ለአደጋ የማያጋልጥ ጠንካራ ነው፤ አይገለበጥም ተሳፈሩበት» እያሉ ያስተዋውቃሉ። ይህ ስራቸውም ጋቢና ተቀምጠው በነጻ የፈለጉበት ቦታ ደርሰው እንዲመለሱ ረድቷቸዋል። አንድ ቀን ግን ገበያው የደራለት ሾፌር፣ አቶ ውብሸትን ከላይ ከህዝቡ ጋር ለመጫን ይወስናል። በድርጊቱ የተበሳጩት አቶ ውብሸትም ያኮርፉና የባለመኪናውን ስም እየጠሩ «የክብረት መኪና አይረባም፣ ይገለበጣል» በማለት አሉታዊ ማስታወቂያ በመስራት ተጠቃሚ እንዲያጣ እንዳደረጉት አይረሱትም። ከዚያ የመማር ፍላጎት ያደረባቸው አቶ ውበሸት፤ የማስታወቂያ ስራቸውን ትተው አዲስ አበባ ታላቅ ወንድማቸው ዘንድ ለትምህርት መጡ።
አዲስ አበባ ከተማ ተስፋ ኮከብ የተባለ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የጀመሩት አቶ ውብሸት፤ ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎን፣ ሙዚቃና ቴአትር መማር ጀመሩ። በወቅቱ ፈረንሳይ አገር ተምረው የመጡት የቴአትር ባለሙያው አቶ ማቴዎስ በቀለ ነበሩ የሚያስተምሯቸው። እናም አንድ ተውኔት ተዘጋጅቶ የሀብታም ልጅ ገጸባህሪን ተላብሰው እንዲጫወቱ ተመረጡ። በወቅቱ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት የሃረርጌ የሀገር ፍቅር ቴአትር ስላቋቋመ አቶ ውብሸት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ ወደ ድሬዳዋ እንዲሄዱ ተደረገ።
በሁለት ዓመት የሃረርጌ ሀገር ፍቅር ቆይታቸው ጭሮ፣ ገለምሶ፣ ኦጋዴንና ቀብሪደሃር የመሳሰሉ አካባቢዎችን በመዘዋወር በርካታ ቴአትሮች ላይ ሰሩ። ከቴአትር ስራቸው በተጓዳኝ መድረክ መሪም ነበሩ። በመድረክ ላይ ቀልድና እያዋዙ በሚያቀርቡት መልዕክት ታዳሚዎቹን ያስደምሙ ነበር። በዚህም ብዙዎች መድረክ በመምራት ሙያ እንዲገፉበት ያበረታቷቸዋል። የሃረርጌው ሀገር ፍቅር ከሁለት ዓመት በኋላ ሲፈርስ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው ዳግም ወደ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ተቀላቀሉ።
በዚህ ቴአትር ቤት በተለያዩ ቴአትሮች ላይ በመሳተፍ ከወጋየሁ ንጋቱና አንጋፋ ተዋናዮች ጋር የመስራት እድልን አግኝተዋል። በቴአትር ክፍሉም በተዋናይነት፣ በደራሲነትና በመድረክ አስተዋዋቂነት ሰርተዋል። በወቅቱ ግን አጎታቸው “አዝማሪ ቤት ስራ ገብተሃል” ብለው አቶ ውብሸትን እስከ ማሳሰር ደርሰው እንደነበር ያስታውሳሉ። በሀገር ፍቅር መድረኮች የአፄ ኃይለስላሴን ገጸባህሪ ወክለው በመተወን ከንጉሱ ጭምር አድናቆትን ያተረፉት አቶ ውብሸት፤ ቴአትሩን በሚሰሩበት ወቅት መልካቸውም ሆነ ሁለመናቸው ንጉሱን ስለሚመስል ታዳሚዎች ልክ እንደ ንጉሱ እጅ እየነሱ ሰላምታ ይሰጧቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ከሀገር ውጭም ቢሆን መድረክ የሚመሩበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር። የኢትዮጵያ የባህል ቡድን በቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ቴአትር ቤትና በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤቶች በሁለት ቡድኖች ሆኖ ቻይና እና የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ሲሄዱ እርሳቸውም ተጓዥ ነበሩ። በዚህም ለሁለት ወራት ያክል በየመድረኮቹ በመምራት ብቃታቸውን አስመስክረዋል። በዚያም ችሎታቸውን ይበልጥ ለማዳበር ሞስኮና ቻይና የቴአትር ትምህርት ለመከታተል ፍላጎት አደረባቸው። ሀገራቱ ኮሚኒስት በመሆናቸው ግን ውጣ ውረዱ ይበዛብኛል በሚል ስጋት ዕቅዳቸውን ሰርዘው ወደ አገራቸው ተመለሱ።
ከስራቸው በኋላ ማታ ማታ መደበኛ ትምህርታቸውን የሚከታተሉት አቶ ውብሸት፤ በስራ ቦታቸው ላይ ደረጃቸውን እያሳደጉ በቴአትር ቤቱ እስከ ምክትል ዳይሬክተር ደረጃ ደርሰው እንደነበር ይናገራሉ። ቴአትር ቤቱን ለቀው ሲወጡም በብሔራዊ ሎተሪ ድርጅት የማስታወቂያ ባለሙያነት ተቀጠሩ። ከቴአትር ሙያቸው ጋር በተያያዘ «እኔና ሰባት ገረዶቼ፣ ማን መክቶት፣ 3 ለ1፣ የጥንቆላው መዘዝ፣ ውለታ በጥፊ፣ ሁለተኛ ምዕራፍ እና ባሻህ ዘመኑ» የተባሉ ድርሰቶችን አዘጋጅተዋል። ሰባት የቴሌቪዥንና ሁለት የመድረክ ስራዎችንም አቅርበዋል። «የክትነሽ» የሚል ፊልም ደግሞ በአሜሪካን ስቱዲዮ አቀናብረው ለእይታ አብቅተዋል።
የሙሉ ጊዜ ማስታወቂያ ሥራ
ብሔራዊ ሎተሪ ትኬቶቹን የሚያሻሽጥለትና ወደተሻለ ትርፍ የሚያመራው ሁነኛ የማስታወቂያ ሰው ይፈልግ ነበርና በመድረክ ስራቸው የሚታወቁትን አቶ ውብሸት ወርቃለማሁን ያገኛል። የብሄራዊ ሎተሪ ድርጅትን ኢ ቦኑሜር የተባሉ ስራ አስኪያጅ፣ አቶ ውብሸትን የማስታወቂያ ክፍል ሹም አድርገው ይሾሟቸዋል። በወቅቱ ዜጎች በሬዲዮ የሚነገረውን የሎተሪ ዕድል አላምን ብለው ነበርና፣ አቶ ውብሸት ሎተሪ የደረሳቸውን ሰዎች በእማኝነት ያቀርቡ ነበር። «ትከብራለህ ሎተሪ ግዛ!» እያሉም በራዲዮንና በድምጽ ማጉያ በከተሞች እየተዘዋወሩ ቅስቀሳ ያሰሙ ነበር።
በከተማዋ ለማስታወቂያ ስራ ሲዞሩ ግን አንድ ዘዴ ይመጣላቸዋል። ወዲያው ሰበታ ሄደው በ25 ብር አህያ ከገዙ በኋላ የብሄራዊ ሎተሪ ድርጅት ቀለብና ማረፊያዋን እንዲያዘጋጅ ያደርጋሉ። ከዚያም አህያዋ ላይ ብር በማዳበሪያ አድርገው ጠመንጃ በያዙ ጠባቂዎች እንድትታጀብ ያዛሉ። ማዳበሪያው ለይምሰል ከላይ የተወሰኑ የብር ኖቶች ጣል ይደረግበት እንጂ አብዛኛው በጭድ የተሞላ ነበር። አህያዋንም በከተማ እያዞሩ «ብሩ መጥቶልሃል ትኬትህን ቁረጥ» እያሉ የሎተሪ ማስታወቂያቸውን አጧጧፉት። አህያዋ በባቡር እስከ ድሬዳዋ፤ ጅማ ድረስ በመኪና ተጉዛ ማስታወቂያውን እንድትሰራ ያደርጉ ነበር።
በሌላ በኩል፤ በማስታወቂያ ስራቸው በእነ ምኒልክ ወስናቸውና ታዋቂ ሙዚቀኞች ጭምር የሚታጀብ ስለነበር በርካታ የሙዚቃና የንግግር እንዲሁም የማስታወቂያ ሥራዎችን በሬዲዮ እንዲያዘጋጁ እድል ተፈጥሮላቸው ነበር። በጊዜው ደመወዛቸው 400 ብር ሲሆን፤ ሎተሪ ድርጅቱም በእርሳቸው ዘመን ትርፋማነቱ ጨምሮ እንደነበር ያስታውሳሉ። ከሶስት ዓመት የሎተሪ አስተዋዋቂነት ሙያ በኋላ ደግሞ በተሻለ ደመወዝ ወደ ፊሊፕስ ኩባንያ ማስታወቂያ ባለሙያነት ተሸጋግረዋል።
ፊሊፕስ ኩባንያ ውስጥ በርካታ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን አስተዋውቀዋል፡፡ ሥራቸው የተቃና እንዲሆን ኩባንያው መኪና ሰጥቷቸዋል። ለማስተዋወቅ ስራቸው ለየት ያሉ ስራዎችን ይጠቀሙ የነበሩት አቶ ውብሸት፤ ለአብነት ፊሊፕስ ኩባንያ ቸርቸል ጎዳና የመንገድ መብራቶችን ግራና ቀኝ ተክሎ ስለነበር እርሳቸው ሌሊት ጭምር መብራቱ ስር ቆመው ጋዜጣ ያነባሉ። ይህም የመብራቱን ኃይል ለማስተዋወቅ አስበው ያደረጉት ነበር። ኩባንያው ገበያው እየደራለት ሲመጣ፣ አቶ ውብሸትን ለተጨማሪ ማስታወቂያ ትምህርት ሆላንድ አገር ላካቸው።
በሆላንድ የሶስት ወራት ቆይታ ስለማስ ታወቂያ ቴክኒኮች፣ ድምጽ ቀረጻና አርት ኦት ተማሩ። ስድስት ዓመታትንም በፊሊፕስ ኩባንያ የራዲዮንና የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ማስታወቂያ ሰሩ። ከበርካታ ድርጅቶች ጋር ለመተዋወቅ ቻሉ። ከዚህ በኋላ የራሳቸውን ማስታወቂያ ድርጅት በማቋቋም ከሚወዷቸው እንስሶች መካከል አንዱ የሆነውን አንበሳን መጠሪያ በማድረግ፣ በ1656 ዓ.ም አንበሳ የማስታወቂያ ስራዎች ድርጀትን ከፈቱ። ከአንድ አርመናዊ ወዳጃቸው ያገኙትን ሁለት ሺ ብር እና ከሌላ ሰው አምስት ሺ ብር በመበደር መቅረፀ ድምፅና የተለያዩ መሳሪያዎች ገዝተው፣ ቢሮ ተከራይተው ስራ ጀመሩ።
ፊሊፕስ ኩባንያን ጨምሮ አምስት ድርጅቶችን ይዘው በአንድ ወር ውስጥ 10 ሺ ብር በመስራታቸው ብድራቸውን መለሱ። የማስታወቂያ ድርጅቱ አሁንም ድረስ በስራ ላይ ያለ ሲሆን፤ በስሩም 12 ቋሚ ሰራተኞች ይዟል። 10 በትርፍ ጊዜ የሚሳተፉ ሙያተኞች አሉት። አቶ ውብሸት በማስታወቂያ ድርጅታቸው በአቢሲኒያ ባንክና በመድን ድርጅት ማስታወቂያዎች በይበልጥ ይታወቃሉ፤ ለበርካታ ድርጀቶች ለዘመናት ማስታወቂያዎችን አዘጋጅተዋል። ይሁንና በደርግ ዘመን ይህ ሙያቸው ሊያስገድላቸው እንደነበር አይረሳቸውም። ለዚህ መንስኤውም የሰሩት የበረሮ ማስታወቂያ ነበር።
በራዲዮ «ቢንቢ የት ልትገቢ፣ በረሮ መጥፊያሽ ነው ዘንድሮ» የሚል የነፍሳት ማጥፊያ ማስታወቂያ ሰርተው ነበር። በአየር ላይ ከዋለ በኋላ በመኪናቸው ሜክሲኮ ላይ ሲዘዋወሩ አንድ የደርግ አባል ያስቆማቸዋል። ከዚያም ለጥያቄ እንደሚፈለጉ ይነግራቸዋል፤ ፖሊስ መኮንኖች አካባቢ በሚገኘው የደህንነቶች ቢሮ እንዲሄዱ ያዛቸዋል። ይሁንና ቤቱ በወቅቱ ሰዎች ይገረፉበት የነበረና ጭካኔ የሚፈጸምበት መሆኑን በወሬ ሰምተዋልና መንገድ አሳብረው ወደ ሌላ ቢሮ ይሄዳሉ።
ከብሔራዊ ቤተመንግስት አካባቢ ሲደርሱ ቀድሞ የሚያውቋቸው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ በኋላም ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ፍሰሃ ደስታ ቢሮ ዘው ብለው ገቡ። በማያውቁት ሁኔታ ሰዎች እንደሚያሳድዷቸው አስረዷቸው። የደርግ አባሉ ተከትሏቸው ኖሮ፣ ለአቶ ፍስሃ ደርግን የሚሳደብ ማስታወቂያ ሰርተዋል «ትጠፊያለሽ በረሮ ያለው ደርግን ነው» ብሎ ወነጀላቸው። ክሱ ተቀባይነት ባያገኝም አቶ ፍሰሃ «የማስታወቂያ ጽሁፉ ሳንሱር እየተደረገ ይለፍ» የሚል ትዕዛዝ ሰጥተው ያሰናብቷቸዋል። የተባለው ቢሮ ቢሄዱ ኖሮ ሊፈጠር የሚችለውን መከራ ሲያስቡ ሁሌም ይዘገንናቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ --
(ከጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን ገጽ የተወሰደ)

Read 2648 times
Administrator

Latest from Administrator