Saturday, 07 March 2020 12:29

የካራማራ ድል ከ28 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ ተከበረ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

  ኢትዮጵያ የሶማሊያውን የዚያድ ባሬ ወረራ የመከተችበትና ድል የተቀዳጀችበት 42ኛ ዓመት የካራማራ ድል ከ28 አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ በአደባባይ ተከብሯል፡፡
ከ42 ዓመት በፊት በ1967 የሶሻሊስቷ ሶማሊያ መሪ ጀነራል ዚያድ ባሬ ታላቋን ሶማሊያ የመመስረት ህልምን እውን ለማድረግ “የታላቋ ሱማሌ ግዛት ከአዋሽ መልስ ነው” በማለት ወረራ መፈፀሙ ይታወቃል፡፡
ይህን ወረራም ከአብዮት ማግስት ገና አንደኛ አመቱን ላስቆጠረው የደርግ መንግስትም ኢትዮጵያውያንን በሙሉ አስተባብሮ ወራሪውን የዚያድ ባሬ ጦር በመግጠም የመጨረሻውን ድል የካቲት 26 ቀን 1970 ካራማራ ላይ በማስመዝገብ የወራሪውን ሃይል ጠራርጐ ከሀገሩ ሊያስወጣ ችሏል፡፡
በብዙ ጀብዱዎችና ገድሎች የታጀበውን የካራማራውን ድል ለማሰብም በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ “ድላችን ሃውልት” የቆመ ሲሆን ይህ ሃውልት ላለፉት 27 አመታት ትውልድ ምንነቱን እንኳ በውል ሳያውቀው መቆየቱን በካራማራው ጦርነት ከፍተኛ ጀብዱ የፈፀሙትና የላቀ ሜዳይ ተሸላሚ የሆኑት መቶ አለቃ በቀለ ማሞ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ይህ ድል ከአድዋ ድል የማይተናነስ፣ ኢትዮጵያውያን ሉአላዊነታቸውን ከውጭ ወራሪ ያስጠበቁበት ታላቅ ድል ነው የሚሉት መቶ አለቃ በቀለ፤ ድሉም በየአመቱ ሊታሰብና ሊዘከር ይገባዋል ብለዋል፡፡
ዘንድሮም ብ/ጀነራል ካሣዬ ጨመዳ፣ ብ/ጀነራል ዋሲሁን ንጋቱ፣ የላቀ የጦር ሜዳ ጀብዱ ኒሻን ተሸላሚው አሊ በርኪን ጨምሮ ጦርነቱን የመሩና የተሳተፉ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተገኙበት ተከብሮ ውሏል፡፡
በበዓሉ አከባበር ላይ ንግግር ያደረጉት ብ/ጀነራል ካሣዬ ጨመዳ በእብሪት ተነሳስቶ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በመዳፈር ወረራ የፈፀመውን የሶማሌ ጦር ለመመከት ሺዎች ወድቀዋል፤ ሺዎች ደምና አጥንታቸውን ገብረዋል፤ ይሄን ያደረጉት በሀገር ፍቅር ነው፤ ዛሬም ወጣቱ የአባቶቹን የሀገር ፍቅር ወኔ መላበስ አለበት” ብለዋል፡፡ አያይዘውም፤ “የካራ ማራ ድል የኢትዮጵያውያን ሁሉ ድል ነው፤ በየአመቱ በሰፋና በደመቀ መልኩ ሊታሰብ ይገባዋል” ብለዋል፡፡
በመጪው አመትም ከዘንድሮው በበለጠ ሰፊ ግንዛቤ ተፈጥሮ ቀኑን በድምቀት ለማክበር ጥረት መደረግ እንዳለበትም የበዓሉ ታዳሚዎች ተናግረዋል፡፡
የካራማራን 42ኛ ዓመት በዓል አስመልክቶ መልዕክት ያስተላለፉት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው፤ የዚያድ ባሬ ወረራና የኢትዮጵያውያን ምላሽ፣ ኢትዮጵያውያን እንደ ፍግ ተኝተው እንደ እቶን በተነሱ ጊዜ ምን እንደሚያደርጉ ያሳየ ነው ብለዋል፡፡
ወረራውን በአገር ፍቅር ወኔ መከላከልና ማሸነፍ እንደተቻለ ያስታወሱት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ‹‹መንግሥታት በአገር ውስጥ ክንዋኔያቸው በአንድም በሌላም ልንመዝናቸው እንችላለን፡፡ ነገር ግን የአገርን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር ለማስጠበቅ የሚከፈሉ መስዋዕትነቶች በየትኛውም ዘመን ቢፈፀሙ ለአገራችን ታሪክ ኩራት ናቸው›› ብለዋል፡፡
‹‹የደርግ መንግሥትም በአጭር ጊዜ ጥሪ አቅርቦ፣ አሰልጥኖና አደራጅቶ የአገርን ክብር ለማስመለስ ያደረገው ተጋድሎና ያስመዘገበው ድል የሁላችንም የኢትዮጵያውያን የአልበገር ባይነትና ለአገር መስዋዕትነትን የመክፈል ታሪካችን አካል ነው›› ብለዋል - ጠ/ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፡፡
‹‹ሁሌም በውስጣችን ክፍተት ሲኖር የውጭ ጠላት እንጋብዛለን›› ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ‹‹ስንጠናከር ግን የተፈራንና የተከበርን እንሆናለን›› ብለዋል፡፡
በወቅቱ ከኢትዮጵያ ጎን ሆነው የተዋጉትና ሕይወታቸውን የሰው የኩባና የየመን ወታደሮችም ታሪክ ሁሌም ሲዘክራቸው ይኖራል ብለዋል - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
 


Read 13479 times