Saturday, 07 March 2020 12:15

ኮሮና ቫይረስ በመላው አለም መስፋፋቱን ቀጥሏል

Written by 
Rate this item
(4 votes)

     ከወደ ቻይና ድንገት ብቅ ብሎ መላውን አለም ስጋት ውስጥ የከተተውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተመለከተ እያደር አስደንጋጭ፣ አሳዛኝና ተስፋ አስቆራጭ እንጂ ይህ ነው
የሚባል በጎ ነገር ሳይሰማ ቀናትና ሳምንታት መፈራረቃቸውን ቀጥለዋል፡፡ ነጋ ጠባ መስፋፋቱን የቀጠለው ኮሮና ቫይረስ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ በ87 የአለማችን አገራትና ግዛቶች ውስጥ የሚገኙ 96 ሺህ 955 ያህል ሰዎችን ሲያጠቃ፣ ከ3 ሺህ 310 በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ለሞት መዳረጉ እየተነገረ ነው፡፡ ቫይረሱ በተቀሰቀሰባት ቻይና በኮሮና የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከ80 ሺህ 430 ማለፉንና የሟቾች ቁጥርም ከ3 ሺህ 13 በላይ መድረሱን አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ከትናንት በስቲያ ባወጧቸው ዘገባዎች አስነብበዋል፡፡ በፍጥነት በመስፋፋት ላይ የሚገኘውና
በመላው አለም ካጠቃቸው ሰዎች መካከል 3.4 በመቶ ያህሉን ለህልፈተ ህይወት እንደዳረገ የሚነገርለት ኮሮና ቫይረስ፤ በሳምንቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከገባባቸው አገራት መካከል ስሎቬኒያ፣ ቦስኒያ ሄርዜጎቪኒያና ደቡብ አፍሪካ ይገኙበታል፡፡ አርጀንቲናና ቺሊም በተገባደደው ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች የተገኙባቸውና በቫይረሱ የተጠቁ የአለማችን
አገራትን አጠቃላይ ቁጥር ወደ 86 ከፍ ያደረጉ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፣ በአለማቀፍ ደረጃ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በሳምንቱ ከወጡ ዘገባዎች መካከል የመራረጥናቸውን አቀናብረን እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡

             አፍሪካ
ከሁለት ሳምንታት በፊት ከጣሊያኗ ሚላን ወደ አልጀሪያ ርዕሰ መዲና አልጀርስ የበረሩት የ61 አመት ጣሊያናዊ አዛውንት ነበሩ፣ በአህጉረ አፍሪካ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ
የመገኘቱ የመርዶ ዜና ምክንያት፡፡ በአልጀሪያ የጀመረው የኮሮና ቫይረስ ክስተት ባለፉት ሳምንታትም በሌሎች የአፍሪካ አገራት የታየ ሲሆን እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ የኮሮና
ቫይረስ ተጠቂዎች እንደተገኙ የተረጋገጡባቸው የአፍሪካ አገራት አልጀሪያ፣ ሴኔጋል፣ ግብጽ፣ ሞሮኮ፣ ናይጀሪያ፣ ቱኒዝያና ደቡብ አፍሪካ መሆናቸውም ተነግሯል፡፡
በአልጀሪያ 17፣ በሴኔጋል 4፣ በግብጽ 2፣ በሞሮኮ፣ ናይጀሪያ፣ ቱኒዝያና ደቡብ አፍሪካ አንድ አንድ፣ በድምሩ 27 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ የተሟላ የጤናም ሆነ የሌሎች መሰረተ ልማት አውታሮች አቅርቦት ያለባቸው ያደጉ አገራት ሊቋቋሙት የተሳናቸው አደገኛው ኮሮና ቫይረስ፤ ወደ ድሆቹ የአፍሪካ አገራት በስፋት ቢሰራጭ ሊያደርሰው የሚችለው ጥፋት እጅግ የከፋ እንደሚሆን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት የውጭ ምርቶችን በብዛት የሚያስገቡት ከቻይና ከመሆኑ ጋር በተያያዘ
ኮሮና ቫይረስ በአፍሪካ አገራት ኢኮኖሚ ላይ የጎላ ተጽዕኖ ሳይፈጥር አይቀርም ተብሎ መሰጋቱን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡

             የአፍሪካ አየር መንገዶች ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጋር በተያያዘ በፈረንጆች አመት 2020 የሚያገኙት ገቢ በ40 ሚሊዮን ዶላር ያህል ሊቀንስ እንደሚችል መነገሩን የዘገበው ደግሞ
ሮይተርስ ነው፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ከጥቂት ቀናት በኋላ በአዲስ አበባ ሊያካሂድ የነበረውን የሚኒስትሮች ስብሰባ ጨምሮ ሌሎች ቀጣይ
የድርጅቱ ስብሰባዎችን በሙሉ ከኮሮና ቫይረስ ስጋት መባባስ ጋር በተያያዘ መሰረዙ ታውቋል፡፡ ከመጋቢት 10 እስከ 16 በአዲስ አበባ ሊካሄድ የታቀደው 53ኛው የአፍሪካ የፋይናንስ፣ ዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሮች አመታዊ ስብሰባ፣ የኮሮና ስጋት በማየሉና ለጉዳዩ ተጨማሪ ትኩረት ለመስጠት ሲባል መሰረዙን ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው በተመድ የአፍሪካ
ኢኮኖሚ ኮሚሽን፤ በቀጣይ ሊከናወኑ የታቀዱ የድርጅቱ ስብሰባዎች በሙሉ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘሙ መወሰኑን አስታውቋል፡፡
ከአውሮፕላን ማረፊያ በቀጥታ ወደ ተከለለ ማረፊያ ማዕከል በማስገባት ለሁለት ሳምንታት ያህል በጥበቃ ለማቆየት ማቀዷን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ከትናንት በስቲያ
ያስታወቁ ሲሆን፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ከኮሮና መስፋፋት ጋር በተያያዘ ወደሌሎች አገራት እንዳይጓዙ ለዜጎቿ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ማስተላለፏ ተነግሯል፡፡
የፍልስጤም ባለስልጣናት የውጭ አገራት ቱሪስቶች እንዳይገቡ ትናንት እገዳ የጣሉ ሲሆን በቤቴልሄም የሚገኘውና የእየሱስ ክርስቶስ የውልደት ቦታ እንደሆነ የሚነገርለት ቤተ
ክርስቲያንም እንዲዘጋ ተደርጓል፡፡ የዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ምናንግዋ፤ ኮሮና ቫይረስን ይዘውብኝ ሊመጡ ይችላሉ በሚል ስጋት የመንግስት ሰራተኞችን በሙሉ ወደ
ውጭ አገራት ጉዞ እንዳያደርጉ መከልከላቸውን የዘገበው ኦል አፍሪካን ኒውስ፤ የአገሪቱ ዜጎችን ደግሞ በተለይ ከአፍሪካ ውጭ ጉዞ እንዳያደርጉ አጥብቀው መምከራቸውን አመልክቷል፡፡ ከ53 በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ የተጠቁባትና አንድ ሰው የሞተባት የአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ግዛት ከትናንት በስቲያ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀች ሲሆን፣ በ16 ግዛቶች 150
ያህል ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባትና 11 ሰዎች የሞቱባት አሜሪካ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል 9 ቢሊዮን ዶላር መመደቧ ተነግሯል፡፡

            ከ290 ሚ. በላይ ተማሪዎች ትምህርት አቋርጠዋል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ እንዳለው፣ ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተያያዘ ትምህርት ቤቶች
በተዘጉባቸው 13 የአለማችን አገራት ውስጥ ብቻ ከ290 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ርቀው ይገኛሉ፡፡ ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ ከተሰራጨባቸውና ጥፋት እያደረሰ ከሚገኝባቸው ቀዳሚዎቹ የአለማችን አገራት አንዷ እንደሆነች የሚነገርላት ኢራን፣ ሁሉንም ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች እስከ መጋቢት ወር መጨረሻ የዘጋች ሲሆን፣ በህንድ መዲና ኒው ዴልሂ ሁሉም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ በግሪክ የተወሰኑ ግዛቶች ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው ተነግሯል፡፡ በአውሮፓ ከፍተኛው የኮሮና ቫይረስ ጥቃት የደረሰባት አገር እንደሆነች የሚነገርላትና በኮሮና የተጠቁ ዜጎቿ ቁጥር ከትናንት በስቲያ 3 ሺህ 89 መድረሱ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ የጣላት ጣሊያን፤ ሁሉንም ትምህርት ቤቶቿንና ዩኒቨርሲቲዎቿን
ለተወሰነ ጊዜ ለመዝጋት መወሰኗንም ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡

               የጉዞ እገዳ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጃፓን ከነገ በስቲያ ጀምሮ ከቻይና እና ከደቡብ ኮርያ የሚመጡ መንገደኞችን በሙሉ ከአውሮፕላን ማረፊያ በቀጥታ ወደ ተከለለ
ማረፊያ ማዕከል በማስገባት ለሁለት ሳምንታት ያህል በጥበቃ ለማቆየት ማቀዷን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ከትናንት በስቲያ ያስታወቁ ሲሆን፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ
ከኮሮና መስፋፋት ጋር በተያያዘ ወደሌሎች አገራት እንዳይጓዙ ለዜጎቿ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ማስተላለፏ ተነግሯል፡፡

      ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ

የኮሮና ቫይረስ መስፋፋት አለማችን በ2020 የፈረንጆች አመት የምታመርተውን አጠቃላይ ምርት ባለፉት አስር አመታት ታይቶ በማይታይ መልኩ ይቀንሰዋል ተብሎ እንደሚገመት
አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ አለማቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር አያታ ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ አልጀዚራ እንደዘገበው
ደግሞ፣ ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተያያዘ የአለማችን አየር መንገዶች፣ የ2020 የፈረንጆች አመት ገቢ በድምሩ በ113 ቢሊዮን ዶላር ያህል ሊቀንስ እንደሚችል ይገመታል፡፡ ታዋቂው አየር
መንገድ ሉፍታንዛ ከሚያደርጋቸው አጠቃላይ በረራዎች መካከል 20 በመቶ ያህሉን በኮሮና ቫይረስ ስጋት ምክንያት ለማቋረጥ መወሰኑን ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል::
የኮሮና ቫይረስ መስፋፋት በተለያዩ የአለማችን አገራት የህክምና ቁሳቁስና የመድሃኒቶች እጥረትና የዋጋ ውድነትን ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት መፍጠሩንና የምርቶችና መድሃኒቶች እጥረትና የዋጋ ውድነት መፈጠሩን የዘገበው ዴይሊ ሜይል፤ ይህን ተከትሎም መንግስታት የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ እንደጀመሩ ዘግቧል፡፡ ቫይረሱ በእጅጉ እየተስፋፋበት ያለችዋ የደቡብ ኮርያ፣ የቼክ ሪፐብሊክ፣ የጀርመንና የሩስያ መንግስታት የፊት ጭምብል፣ ጓንትና የመሳሰሉ ምርቶች እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ መባባሱን ተከትሎ፣ እነዚህ ምርቶች ወደ
ሌሎች አገራት ኤክስፖርት እንዳይደረጉ ጥብቅ ትዕዛዝ ያስተላለፉ ሲሆን፣ በደቡብ ኮርያ መሰል ምርቶችን ወደሌሎች አገራት ሲልኩ ወይም በድብቅ ሲከዝኑ የተገኙ አምራቾችና
አከፋፋዮች አደገኛ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ተነግሯል፡፡ የህንድ መንግስት ፓራሲታሞል በተባለው የማስታገሻ መድሃኒት ሽያጭ ላይ ከትናንት በስቲያ ገደብ መጣሏን የጠቆመው ዘገባው፣ የፊት ጭምብል የማታመርተዋና 10 ሚሊዮን ያህል የፊት ጭምብሎች የሚያስፈልጓት ጣሊያን ከደቡብ አፍሪካ 800 ሺህ ያህል ብቻ ማግኘት መቻሏንም አመልክቷል፡፡

             ከገንዘብ ድጋፍ እስከ ክትባት ፍለጋ ተቋማትና መንግስታት እንደ ሰደድ እሳት በመስፋፋት ላይ የሚገኘውን ኮሮና ቫይረስ በፍጥነት ለመግታት ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ
የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን፣ የአለማችን የህክምናው ዘርፍ ተመራማሪዎችና የምርምር ተቋማት ደግሞ መድሃኒትና ክትባት ለማግኘት ርብርብ ማድረጋቸውን እንደቀጠሉበት እየተነገረ
ነው፡፡ የጃፓኑ ኦሳካ ዩኒቨርሲቲ ከታዋቂው የአገሪቱ የመድሃኒት አምራች ኩባንያ አንጌስ ጋር በመተባበር ለኮሮና ቫይረስ ክትባት ለማግኘት በምርምር መጠመዱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የአለም ባንክ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ አገራትን ለማገዝ የሚውል የ12 ቢሊዮን ዶላር የመጀመሪያ ዙር አስቸኳይ የገንዘብ እርዳታ እንደሚሰጥ በሳምንቱ መጀመሪያ ያስታወቀ ሲሆን፣ አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ በበኩሉ በቫይረሱ ለተጠቁ አገራት የ50 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚሰጥ ከትናንት በስቲያ ይፋ አድርጓል፡፡
  ቻይና የኮሮና ቫይረስን ለመግታት ለሚደረገው ጥረት 16 ቢሊዮን ዶላር መመደቧን የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር ከትናንት በስቲያ ማስታወቃቸውም ተዘግቧል፡፡
  የአሜሪካ መንግስት በበኩሉ፤ በ25 የአለማችን አገራት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታትና ለመከላከል ለሚደረጉ ጥረቶች መደገፊያ የ37 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ
መወሰኑን ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ድጋፉ ከሚደረግላቸው 25 አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንደምትሆንም ተነግሯል፡፡

Read 14376 times