Monday, 02 March 2020 00:00

የሰብአዊ መብት ተሟጋቹና የ97 ምርጫ ቀውስ ውጤቶች (ፊልም የሚመስል እውነተኛ ታሪክ)

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

    ይህቺ አገር በእውነት ላይ የተመሰረተ፣ ፍትህን ማዕከል ያደረገ፤ እርቅ ትፈልጋለች

                     - የእኔ ትልቁ ዕቅድ ወጣት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ማፍራት ነው
                    - ከምርጫው በፊት ሀገሪቱ በእርቅና መግባባት ከማጥ ውስጥ መውጣት አለባት
                    - ብዙዎቹ ፖለቲከኞች ባለፈው ሥርዓት “ቶርቸር” ተፈጽሞባቸዋል


             አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ይባላል፡፡ በሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ለ7 ዓመት ተኩል ያህል በሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ በዋና መርማሪነት ሰርቷል፡፡ በ1997 ምርጫ ወቅት ታዛቢዎችን ያሰለጠነ ሲሆን የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለዓለም አቀፍ ተቋማት አጋልጧል:: ይሄን ተከትሎም በመንግስት ተይዞ ለእስር
ተዳርጓል:: በዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች ግፊት ከወህኒ ሲለቀቅ ለሥራ ወደ ኡጋንዳ አመራ:: ከዚያ በኋላ ላለፉት 15 ዓመታት ወደ አገሩ አልተመለሰም፡፡ ኑሮውን በአውሮፓ አደረገ:: አብዛኞቹን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ለዓለም አቀፍ ተቋማት ያጋለጠው ግን ከኢትዮጵያ ከወጣ በኋላ ነው፡፡ በሰኔ 1/97
እና በህዳር 1998 በዜጐች ላይ የተፈፀሙ ግድያዎችን የተመለከተ ምስክርነት ለአውሮፓ ፓርላማ ሰጥቷል፡፡
በህግና በፍልስፍና ትምህርት የተመረቀው የሰብአዊ መብት ታጋዩ አቶ ያሬድ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ በመጣበት ወቅት ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተገናኝተው ፊልም የሚመስል ከ97 ምርጫ ቀውስ ጋር የተገናኘ የሰብአዊ መብት ጥሰት የማጋለጥ ታሪኩን በስፋት አውግቶታል፡፡

             በምርጫ 97 ወቅት ያሳለፍከው አስቸጋሪ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?
እንግዲህ ምርጫ 97ን ተከትሎ የተፈጠረውን ብዙዎች የሚያውቁት ነው፡፡ ከሁሉም ግን በአዲስ አበባ ሠላማዊ ሰዎች የተገደሉበት ሰኔ 1 ቀን 1997 ተጠቃሽ ነው፡፡ በወቅቱ ደህንነቶች እኛን በእጅጉ ይከታተሉን ነበር፡፡ የሰኔ 1 ግጭት ከተከሰተ በኋላም ቀጥታ ትኩረታቸውን እኛ ላይ አደረጉ፡፡ ሁለት የኢሠመጉ ሠራተኞችም ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በመገኘት የተጐዱ ሰዎችን ጉዳይ በየደቂቃው ያጣሩ ስለነበር፤ የእነሱን እዚያ ሆስፒታል ውስጥ መኖር ካረጋገጡና ኢሠመጉ ስለ ጭፍጨፋው መረጃ እንደሰበሰበ ካወቁ በኋላ እኛን ማሳደድ ጀመሩ:: በዚያው በሰኔ 1 ምሽት እኔ ቤት መጥተው ቤቴን በረበሩ፣ ከዚያም ወላጆቼ ቤት ሄደው ቤታቸውን በረበሩ፡፡ እኔ ደግሞ በአጋጣሚ ቤት አልነበርኩም፡፡ እኔ ቤት ቁጭ ብሎ ያገኙትን ባልደረባዬን፣ ቸርነት ታደሰን ወስደው አሠሩት፡፡ እኔን እየተከታተሉኝም ቢሆን ስራዬን ለአንድ ሳምንት ያህል ቀጠልኩ፡፡ ከዚያ ሰኔ 8 ከኢሠመጉ የስታዲዬም ቢሮ ስወጣ፣ በፌደራል ሃይሎች ተከብቤ ታሠርኩ ተወሰድኩ፡፡ ሌላም አብሮኝ የነበረ ብርሃነ ጽጉ የሚባል ባልደረባዬም አብሮኝ ተወስዶ ታሠረ፡፡
የት ነበር የታሰራችሁት?
በመጀመሪያ ካዛንቺስ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል የተሠራበት አካባቢ በሚገኝ አንድ ምድር ቤት ያለው ቤት ውስጥ ነው ወስደው ያሠሩን:: ከዚያም ከሌሊቱ 6 ሰዓት ላይ 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ወስደውን፣ ከሌሎች እስረኞች ጋር እጅና እግራችንን በካቴና አስረው ፒካፕ መኪና ላይ አስተኝተውን፣ በሌሊት ወደ ዝዋይ ይዘውን ሄዱ፡፡ ዝዋይ ስንደርስ በሽብር ተከሰው የኦነግ አባላት የነበሩበት ጥብቅ እስር ቤት ውስጥ አስገቡን፡፡ በእስር ቤት ውስጥ ሌላ እስር ቤት ነበረው፡፡ እዚያ አስገብተው ዘጉብን፡፡ ለ8 ቀን ያህል ቤተሰብ የት እንደገባን አያውቅም ነበር:: 8 ሰዎች ነበርን አንድ ላይ የታሠርነው፡፡ ሶስቱ የራሳቸው የደህንነት ሰዎች ነበሩ፡፡ እኛን ለመሰለል ነበር የተመደቡት፡፡ በወቅቱ የቅንጅት ሰዎች አብረውን ታስረው ስለነበር፣ በቅንጅትና በኛ የኢሠመጉ ሰዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጥናት ፈልገው ይመስለኛል፡፡
እስቲ እስር ቤቱ ምን አይነት እንደነበር ይግለፁልን?
አንድ ትልቅ ቆርቆሮ በቆርቆሮ መጋዘን ነው:: በውስጡ ምንም አይነት ፍራሽም ሆነ ጐን ማሳረፊያ ነገር አልነበረውም፡፡ ዝም ብለው አስገብተው ነው የዘጉብን፡፡ አልፎ አልፎ ዳቦ በሻይ ያመጡልናል፡፡ ጠዋት ማንም ሳይነቃ ሽንት ቤት ይወስዱናል፤ ማታም በጨለማ ሽንት ቤት ወስደው ይመልሱናል፡፡ ለ8 ቀን ያህል በዚህ መልኩ ነበር ስምንታችንን ከሰው ሁሉ ነጥለው ሲያሰቃዩን የከረሙት፡፡ የምንተኛው የመጋዘኑን አንድ ጥግ አቧራ ጠርገን፣ የተበጣጠቁ ካርቶኖች ፈላልገን ነበር፡፡ ከቢሮ በወጣንበት ልብስ ነበር ሳንታጠብና ልብስም ሳንቀይር ለ8 ቀናት የሰነበትነው፡፡
ይሄ ምናልባት የከፋ የእስር ሁኔታ ሊሆን ይችላል፡፡ በወቅቱ ግን ያስተዋልኩት፤ ከዚህም በከፋ ሰቆቃ ስር የነበሩ ህፃናት ሳይቀሩ ታስረው እንደነበርን ነው፡፡ እንደውም እኛ ከነበርንበት ክፍል አጠገብ ከ200 በላይ የሚሆኑ ህፃናት ልጆችን ትልቅ መጋዘን ውስጥ ዘግተውባቸው ያሰቃያቸው ነበር፡፡ እነዚህ ልጆች እድሜያቸው በአማካይ ከ15 ዓመት አይበልጥም ነበር፡፡ ፀጉራቸውን ላጭተዋቸው፣ ሰው  እንዳያያቸው ደብቀው አስቀምጠዋቸው ነበር፡፡ ብዙዎቹ ህፃናት በተላላፊ በሽታዎች ሁሉ ይሰቃዩ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር የኛ ስቃይ ብዙም አይደለም ማለት ይቻላል፡፡
ከ8 ቀን በኋላ ከነበርንበት ክፍል ወደ ሌላ ክፍል ሲቀይሩን፣ ከአጠገባችን ያለውን ክፍል በቀዳዳ ስንመለከት፣ እነ እንዳርጋቸው ፅጌንና ቸርነት ታደሠን አየናቸው፡፡ እንደ ምንም ተንጠራርተን እዚያ መኖራችንን ነገርናቸው፡፡ ከዚያም ከ10 ቀን በኋላ ይመስለኛል… ቀን ቀን ወጥተን ፀሐይ እንድንሞቅ ተፈቀደልን፡፡ ፍ/ቤትም ወስደውን አያውቁም፡፡
ቤተሰብ በዚህ ሁሉ መሃል የት እንዳላችሁ ያውቅ ነበር?
በፍፁም! ቤተሰብ ከሳምንት በላይ እኛን ፍለጋ ሲማስን ነበር፡፡ የት እንዳለን ፍንጭ እንኳ የሚሰጣቸው አልነበረም፡፡ በኋላ አንድ ገራገር የሆነ ጥበቃ ነበረ፡፡ ውሃ ያመጣልናል፤ ብቻ ጥሩ አይነት ሰው ነበር፡፡ 10 ብር ላይ ስማችንንና ስልክ ቁጥራችንን ጽፈን ሰጠነው፡፡ እሱም  ለኢሠመጉ ደውሎ ዝዋይ መሆናችንን ነገራቸው፡፡ ከ10 ቀን በኋላ ማለት ነው፡፡ በወቅቱ ኢሠመጉም የአውሮፓ ህብረትም ሌሎች ዓለማቀፍ ተቋማትም የኛን አድራሻ ሲያፈላልጉ ነበር፡፡ ዝዋይ ድረስ መጥተውም “እዚህ የሉም” ተብለው ተመልሰዋል፡፡ በኋላ ግን በዚያ ጥበቃ እርዳታ ያለንበት ታወቀ፡፡ አለማቀፍ ቀይ መስቀል፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ኢሠመጉ መጡ፤ ነገር ግን አሁንም የሉም ተብለው ተመለሱ:: ሌላ ምግብ የምታመጣልን ሴት ነበረች፡፡ ለሷ በአገልግል ስር ስልክ ጽፈን ሠጠናት፡፡ እሷ እንደገና ለቤተሰብ ደውላ አሳወቀች፡፡
በድጋሚ ቀይ መስቀሎች መጥተው “ሰዎቹን አምጧቸው፤ አስተማማኝ መረጃ ደርሶናል” ብለው አፋጠጧቸው፡፡ ወዲያውኑ የግቢው ጥበቃዎች ተቀየሩ፡፡ በኋላ ምንም ማድረግ አልቻሉም፤ ሻወር እንድንወስድ ተደርጐ እንድንታይ ተፈቀደ፤ ፍራሽ ሁሉ አምጥተው ሰጡን፡፡
ግን የታሠራችሁበት ምክንያት ተነግሯችሁ ነበር?
ዝዋይ ስንደርስ “አዲስ አበባ የተደረገውን አመጽ በጠቅላላ በስልክ አደራጅተው ሲመሩ የነበሩት፣ መርካቶ ቴሌ እንዲቃጠል ትዕዛዝ የሰጡት እነሱ ናቸው፣ ለሞተው ሰው ሁሉ ኃላፊነት ይወስዳሉ” ተብሎ ነው የተወነጀልነው:: እኛን ከእነ አንዳርጋቸው ፅጌ ጋር ቀላቅለው፣ የሐሰት ክሣቸውን አደራጁብን፡፡ ያ ሁሉ ቡድን አንድ ላይ ተቀናጅቶ አመፁን ይመራ እንደነበር የሚገልጽ ክስ ተመሠረተብን፡፡ የሚገርምህ ከጉራጌ አካባቢ መጥተው ድንጋይ በመጥረብ የቀን ስራ ላይ የተሠማሩ አዛውንት ሳይቀሩ፣ በማያውቁት ጉዳይ በዚህ ክስ ተከሰው ነበር፡፡
ሽማግሌው አይናቸውን ሊታከሙ ከገጠር መጥተው፣ ቀጠሮ ሲራዘምባቸው ከምቀመጥ ብለው ድንጋይ ጠረባ የገቡ የቀን ሠራተኛ ነበሩ:: እሣቸውን ከኛ ጋር ቀላቅለው የአዲስ አበባን አመጽ ይመሩ ነበር ብለው ነው የከሰሷቸው፡፡ እንዲህ ያሉ አስገራሚ ክሶች ነበሩ የሚቀርቡት:: ክሱ ሲመሰረትብን መሃላችን የነበሩትን የደህንነት ሰዎች አስጠርተው ወደ ቤታቸው ላኳቸው፡፡ ሰዎቹ ተልዕኮአቸውን ጨረሱ ማለት ነው፡፡
በወቅቱ የሰብአዊ መብት ምርመራዎችን ስታሠሩ ምን ያህል ጥንቃቄ ታደርጉ ነበር? ወይስ ፊት ለፊት ነበር የምትጋፈጡት?
ከ97 በፊት ለሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራዎች በአንፃራዊነት ጥሩ ጊዜ ነበር:: ለምሣሌ በሰኔ 1 ግጭት ከየሆስፒታሉ የሠመጉ ሰዎች መረጃ ሲሰበስቡ ብዙም ጥቃት አይደርስባቸውም ነበር፡፡  በጥይት ተመተው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የገቡ ሰዎችን ሲከታተሉ የነበሩት ባልደረቦቼ፡- ማለትም አሁን ኢሣት ላይ የሚሠራው ወንድማገኝ ጋሹና ቸርነት ታደሰ እዚያው ሆስፒታል በመዋል፣ የሚነሳውን ሁሉ ቶሎ ቶሎ ፎቶ እያነሱ ወደ ቢሮ ይልካሉ፤ እኔ ደግሞ ከቢሮ በፍጥነት ለአለማቀፉ ማህበረሰብ፣ ለተባበሩት መንግስታትና ለመሳሰሉት እልክ ነበር፡፡
በምን ነበር የምትቀባበሉት? በወቅቱ ኢንተርኔት እንዳሁን አልነበረም…
አንዳቸው ሆስፒታል ሲቆዩ አንዳቸው መረጃውን ይዘው ቢሮ ይመጣሉ፤ በፍጥነት ነበር እየተቀያየሩ የሚመላለሱት፡፡ እኛ ፎቶውን ከዲጅታል ካሜራው ላይ ወደ ኮምፒውተር እንገለብጣለን፤ ካሜራውን እናፀዳላቸዋለን:: ወዲያው ተመልሰው ሄደው መረጃውን ይሰበስባሉ፡፡
በስልክም የሟቾችን፣ የተጐጂዎችን ማንነት ይነግሩናል፤ እኛ ቶሎ ቶሎ እንመዘግባለን:: በሰኔ 1 ግጭት ብዙ ሂደትን ሳንከተል ነበር መረጃ ስናስተላልፍ የነበረው፡፡ እኛም ላይ ችግር ከመምጣቱ በፊት ቶሎ ቶሎ ነበር ለእነ ኮፊ አናን፣ ለአምነስቲ የመሳሰሉት ተቋማት እንልክ የነበረው፡፡ በኋላ እነዚህን በሆስፒታል የሚሰሩ የኛ ሰዎች አንድ ነጭ ለባሽ የደህንነት ሰው ይይዛቸውና ለፖሊስ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፡፡ ነገር ግን ፖሊሱ ይለቃቸዋል፡፡ በኋላ መረጃው ሁሉ እጃችን ላይ እንደገባ ሲያውቁ ነው ማታውኑ እኛን ማሳደድ የጀመሩት፡፡ እስሩም የመጣው ይሄን ተከትሎ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ከሰኔ 1 ሂደት ትምህርት ወስደው ኋላ ላይ ማለትም ህዳር 98 በተፈጠረው ግጭት ላይ ጥንቃቄ ለመውሰድ ሞክረዋል፡፡ በሰኔው ግጭት የውጭ ሀገር ጋዜጠኞች ሳይቀሩ እንዳሻቸው ሆስፒታል ገብተው ጉዳዩን ይከታተሉ ነበር፡፡ በኋላ ላይ በተፈጠረው ግጭት ወቅት ግን ጋዜጠኞችን በሙሉ ነው ያባረሩት፡፡ በሰኔው ግጭት አስከሬኖች ይላኩ የነበረው በየሠፈሩ ወዳሉ ሆስፒታሎች ነበር፡፡ በህዳሩ ሁለተኛው ግጭት ግን የተጐዳ ሰውና አስከሬን የሚልኩት ወደ ፖሊስ ሆስፒታልና ጦር ኃይሎች ብቻ ሆነ፡፡
በጥቁር ላስቲክ አስከሬን እየተጠቀቀለ ነበር የሚላከው፡፡ በሆስፒታሎቹ የአስከሬን ክፍል ሞልቶ ኮሪደር ላይ ሁሉ አስከሬን ተከማችቶ ነበር፡፡ እንደውም ሰበታ አካባቢ፣ አስከሬኖችን በጅምላ ወስደው፣ አንድ ጉድጓድ ውስጥ ቀብረዋል፡፡
በወቅቱ የጅምላ መቃብር ተፈጽሟል ማለት ነው?
በትክክል፡፡ ይሄ ማስረጃ ያለው፣ በሚገባ የተፈፀመ ጉዳይ ነው፡፡ እንደውም አንድ አባት፣ ነርስ ልጃቸው፣ ቤተሰብ የለሽ ተብላ በጅምላ ከተቀበሩት አንዷ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡
በሁለተኛው የህዳር 98 ግጭት አንተ ከእስር ወጥተህ ነበር ማለት ነው?
አዎ! በዋስ ተለቀን ነበር፡፡ ግን ችግሩ ባጋጠመ ጊዜ እኔ ኡጋንዳ ለስራ ጉዳይ ሄጄ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ እኛን በዋስ የለቀቀን ዳኛ፣ ከባለስልጣናት ከፍተኛ ዛቻና ስድብ እንደደረሰበት አጫውቶናል፡፡ እዚያው ኡጋንዳ ስብሰባ ላይ ሆነን ስልክ ተደወለልን፡፡ ይሄን ያህል ሰው ተገድሏል፣ ከተማ ውስጥ ውጥረት አለ የሚል መረጃ ደረሰን፡፡ ፖሊስም ኡጋንዳ ለስብሰባ ከሄድነው ሰዎች ውስጥ ክፍሌ ሙላትና እኔን ጨምሮ 55 ሰዎች ተፈላጊ ተብለን ስም ዝርዝራችን ይፋ መሆኑን ሰማን፡፡ የአገር ክህደትና የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመዋል ተብሎ በሄራልድ ጋዜጣ ፎቷችን ታተመ፡፡ በቴሌቪዥን ማስታወቂያ ተነገረብን፡፡ ስለዚህ እንዳትመጡ ተባልን፡፡ እዚህ የነበሩት ግን ታሠሩ፡፡ እነ ዳንኤል በቀለ፣ ሲሳይ አጌና፣ ፕ/ር መስፍን ታሠሩ፡፡ ውጪ የነበርነው እዚያው ቀረን፡፡ የስደት ህይወት በዚያው ተጀመረ ማለት ነው፡፡
የህዳሩ 98 ግጭትን መረጃ ታዲያ እንዴት ነው ያገኛችሁት?
እኔ እዚያው ኡጋንዳ ሆኜ በቀጥታ ፖሊስ ውስጥ ያሉ፣ አብረውኝ የሚሠሩ የውስጥ ሰዎች ነበሩኝ፡፡ ያለንም እድል በራሳቸው በፖሊሶች ውስጥ ሠርጐ መግባት ነበር፡፡ ስለዚህ ሁለት ሰዎችን በሌሎች ሰዎች አማካይነት አገኘን:: አንደኛው የአስከሬን ምርመራ ኤክስፐርትና ሌላኛው የሟቾች አሻራና ፎቶግራፍ አንሺ ባለሙያ ነበር፡፡ ግንኙነታችን በጥንቃቄ ነበር የሚካሄደው፡፡  በራሣቸው ስልክ አላወራቸውም ነበር፡፡ በዚህ ግንኙነታችንም ያለውን የፖሊስ መረጃ በጠቅላላ ሰብስበው አወጡልኝ፡፡ መረጃውን ሳየው በጣም ያስደነግጣል፡፡ ግድያው በጠቅላላ እጅግ ዘግናኝ የሚባል አይነት ነበር፡፡ ግማሽ ጭንቅላት የሌለው አስከሬን ፎቶ ሳይቀር ነው የላኩልኝ፡፡ መረጃው በጣም ያስደነግጣል፡፡ አሮጊት እናትን ጨምሮ ሁሉም ሰዎች የተመቱት በከባድ የአልሞ ተኳሽ መሣሪያ ከደረታቸው በላይ ነው፡፡ ያ መረጃ ደግሞ ፖሊስ ጋ ብቻ ነው የነበረው፡፡ የተመቱት ሰዎች ስም ዝርዝር ከእነ ፎቶግራፋቸው ማለት ነው፡፡  ያንን ሙሉ መረጃ ነው እነዚህ ሁለት ሰዎች የላኩልኝ፡፡ ፖሊስ የሚያውቀውን መረጃ በሙሉ ነበር እኔ የማውቀው፡፡
መረጃውን እጅህ እንዳስገባህ ምን ነበር ያደረግኸው?
ሲጀመር ለኔ ያየሁት ሁሉ በጣም የሚረብሽና ዘግናኝ ነበር፡፡ በወቅቱ ከአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ አና ጐሜዝ ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበረን፡፡ ለሷ ያለውን ነገር ፃፍኩላት:: የተወሰነውንም ላኩላት፤ በጣም ደነገጠች:: ወዲያውኑ በአውሮፓ ፓርላማ ውስጥ “የኤክስትራ ኦርዲነሪሴሽን” ተብሎ በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ያተኮረ፣ ሙሉ የፓርላማ አባላት የተገኙበት፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚደመጥበት መድረክ አዘጋጀችና ጠራችኝ፡፡ አሁን ያንን ነገር በአደባባይ ይፋ ካደረግሁት፣ እነዚያ ፖሊሶች አደጋ ላይ ሊወድቁ ሆነና፣ ያለኝ አማራጭ በመጀመሪያ እነዚያን ሰዎች ከሀገር ማስወጣትና ደህነነታቸውን ማስጠበቅ ነበር፡፡ ቀስ ብዬ ከሀገር የሚወጡበትን ሂደት ጀመርኩ፡፡ በኋላም በሞያሌ አድርገው ኬንያ፣ ከዚያ ኡጋንዳ እንዲገቡ አደረግሁ፡፡
በዚህ ሁሉ መሃል ችግር አልገጠማችሁም?
ኬንያ ላይ በፖሊሶች ተይዘው ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከፖሊስ መኮንኑ ጋር ተነጋግሬ፣ ያው ትንሽ ጉርሻ ልኬለት፣ በሆነ መንገድ ሁለቱንም ሰዎች ወደ ኡጋንዳ አሻገረልኝ፡፡ ኡጋንዳ ካምፓላ ሲደርሱ ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ጋር አገናኘኋቸው፡፡ አሁን አንዱ ካናዳ፣ አንደኛው አሜሪካ ነው ያሉት፡፡ በዚያ መንገድ የእነሱ ደህንነት ከተጠበቀ በኋላ እኔ ወደ ብራስልስ ሄጄ የተፈፀመውን ነገር ለተሰብሳቢው ይፋ አደረግሁ፡፡ ወደ 97 ገፅ ሪፖርት ነበር ያዘጋጀሁት፡፡ ስም ዝርዝር፣ የግድያ ሁኔታ እንዲሁም የግድያውን አይነት ሁሉ የሚያሳዩ ፎቶዎች ነበር በስላይድ ያቀረብኩላቸው፡፡ የፓርላማው አባላት በጣም ነበር የደነገጡት:: በዚህ ምስክርነት ላይ አንዳርጋቸው ፅጌ፣ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፣ ኦባንግ ሜቶ ተገኝተዋል:: አራታችን ነበርን ምስክርነቱን ያቀረብነው፡፡ ወዲያው እዚህ መታመስ ተጀመረ፡፡ መረጃው ከየት መጣ፣ እንዴት እጁ ገባ ተብሎ ታመሰ፡፡ እኔ በወቅቱ መረጃውን ከፖሊስ ነው ያገኘሁት ብዬ በግልጽ አሳውቄ ነበር፡፡ ማን ነው ያወጣው ተብሎ ግምገማ ተደረገ፡፡ ሁለቱ ፖሊሶች የት ገቡ ተባለ፤ ግን ምንም ሊገኝ አልቻለም:: ከዚያ በኋላ እንግዲህ መንግስት የሞተውን ሰው መደበቅ እንኳ አልቻለም ነበር፡፡ 198 ሰው ሞቷል አለ - አጣሪ ኮሚሽኑ፡፡ እኛ ግን ከፖሊስ በቀጥታ ያገኘነውና ያቀረብነው ሪፖርት የ210 ሰዎችን ሙሉ መረጃ የያዘ ነበር፡፡
እንዴት የእናንተ ቁጥር ከፍ አለ?
የኛን ዝርዝር ከፍ ያደረገውና እነሱ የደበቁት፣ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ‹‹እስረኞች አመፁ›› ብለው የቆርቆሮ ቤት ውስጥ ቆልፈውባቸው፣ ወታደሮች ዙሪያውን ቆመው በጥይት ሩምታ የጨፈጨፏቸው አሉ፡፡ በዚያ የጅምላ ጭፍጨፋ 68 ሰው ነው የገደሉት፤ እነሱ ግን ስምንት ሰው ነው የሞተው ይላሉ፡፡ ያ እስር ቤት እንዳይጣራ ሁሉ ሲከለከል ነበር፡፡ የተገደሉት 68 ሰዎች ፖለቲከኛ ያልሆኑ፣ በተለያየ ወንጀል የተከሰሱ፣ ነገር ግን አምፀዋል የተባሉ ናቸው:: እኛ ባገኘነው የፖሊስ መረጃ ላይ፤ በጥይት የተበሳው ቆርቆሮ ቀዳዳ ሁሉ አለ፡፡ እነ አቶ በረከት ግን 8 ሰው ነው የተገደለው” ተብሎ ዜና እንዲሠራ አደረጉ፡፡ ነገር ግን 68 እስረኞች ናቸው የተገደሉት፡፡
ይሄ ሪፖርት ይፋ ከሆነ በኋላ ችግር አልገጠመህም?
ከዚያ በኋላ የእኔና የወያኔ ጠላትነት በይፋ ታወጀ፡፡ ወደ ኡጋንዳም መምጣት አልቻልኩም:: እዚያው አውሮፓ ቀረሁ፡፡ ከዚያ በኋላም አንድ አራት ጊዜ አውሮፓ ህብረት ቀርቤ ስለ ጉዳዩ አስረድቻለሁ፡፡ ያው ቤልጅየም ኑሮዬን አድርጌ ቆየሁ ማለት ነው፡፡ ብዙም የተለየ ችግር ግን አልገጠመኝም፡፡ እንግዲህ አሁን ከ14 ዓመት በኋላ ነው ወደ ሀገር ቤት የመጣሁት፡፡ የእነሱ ማስፈራሪያም ለኔ ብዙም አያስፈራኝም ነበር፡፡ ከአነ አቶ ጌታቸው አሠፋም ቀጥታ ማስጠንቀቂያ ደርሶኝ ነበር፡፡
አውሮፓ ውስጥ በሰብአዊ መብት ተሟጋችነት ነው የቀጠልከው?
አዎ፤ በተለያዩ ድርጅቶች በኩል በርካታ ስራዎችን ስሰራ ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ጉዳይ በተመለከተ ከአንዳንድ ድርጅቶች ጋር እሠራ ነበር፡፡ ሪፖርቶችን እናወጣ ነበር፡፡ አሁን እኔ በሊቀ መንበርነት የምመራውንና ‹‹ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ›› የሚለውን ተቋም እ.ኤ.አ በ2013 ሃሳቡን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ጀመርን፡፡ ድርጅቱን መጀመሪያ ሆላንድ አስመዘገብነው፡፡ ከሁለት አመት በኋላ ደግሞ በጄኔቭ ተመዘገበ፡፡ እሱን እየመራሁ ነበር የቆየሁት፡፡ ዋነኛ ስራው እዚህ ሰው ሲበደልና ሲታሠር በፍጥነት ለአለማቀፍ ማህበረሰብ ማሳወቅ ነበር፡፡ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮች… ችግር ሲገጥማቸው ለእነሱ ድምጽ የማሰማት፣ ከሀገር መውጣት ሲኖርባቸው ከሀገር እንዲወጡ መርዳት፣ ከሀገር ከወጡ በኋላ ገንዘብ እንዲያገኙ መርዳት፣ አንዳንዶቹም እዚሁ ሀገር ውስጥ ሆነው ደህንነቱ የተጠበቀ ቤት እንዲከራዩ በገንዘብ መርዳት… የመሳሰሉትን በጥንቃቄ ስንሰራ ቆይተናል፡፡ ምርምሮችንም እንሠራ ነበር:: በተለይ በኢትዮጵያ ያለውን የእስረኞች አያያዝ በተመለከተ ምርምር እንሠራ ነበር፡፡ “የእስረኞች ምስክርነት በፍ/ቤት” በሚል ርዕስ መጽሐፍ አሳትመንም ለአለም ህብረተሰብ አሳውቀናል፡፡
ሀገሪቱ በሰብአዊ መብት አያያዝ ለውጥ አሳይታለች ይላሉ?
እኔ ሁሌም ተስፈኛ ነኝ፡፡ በፖለቲካ ረገድ የሚደረገው ማሻሻያ፣ ለሰብአዊ መብት መሻሻሎች ወሳኝ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ይሄን የማሻሻል ሂደት የሚረዱ ህጐች በፓርላማ እየወጡ ነው፡፡ በመንግስት በኩል፣ የሀገሪቷን የሰብአዊ መብት ይዞታ ለማሻሻል ፍላጐትና ጥረት እንዳለ ይታያል፡፡ የእነ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ወደ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን መምጣትና የፍትህ ተቋማት ላይ የሚደረጉ ሪፎርሞች፣ ምርጫ ቦርድ ላይ እንደነ ብርቱካን አይነት ሰዎች መምጣታቸው፣ ሲቪክ ማህበረሰቡ አንደ አዲስ መደራጀት መጀመራቸው፣ ሚዲያውም እያበበ መምጣቱ… ለሰብአዊ መብት ይዞታ መሻሻል ተስፋ የሚሰጡ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ ሆና… ለውጥ እያካሄደች ነው፡፡ ለውጡ የተሳካ እንዲሆን ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ሀገሪቱ አሁንም ምጥ ላይ ነች፡፡ ይህ ምጥ ከእነ ሙሉ ጤንነቱ “እናት ደህና፣ ልጅም ደህና ሆኖ ይወለዳል” የሚለው የሚወሰነው እንደ አዋላጁ ጥንቃቄ ነው፡፡ ስለዚህ አዋላጁ ብዙ መጠንቀቅ አለበት፡፡ በሌላ በኩል፤ ለጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ የማስተላልፈው መልዕክት፤ ይህቺ ሀገር ብዙ ቁስሎች የያዘች ናት፡፡ የተጐዱ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት የተፈፀመባቸው፣ የተከፉ ብዙ የማህበረሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ እነዚህ የስነልቦና ቀውስ የደረሰባቸው ዜጐች ከቀውሱ ወጥተው የሚታደሱበት የማገገሚያ ማዕከል ያስፈልጋል:: ልክ ደቡብ አፍሪካ እንደነበረው፣ በእውነት ላይ የተመሰረተ፣ ፍትህን ማዕከል ያደረገ እርቅ ይህቺ ሀገር ትፈልጋለች፡፡ ለውጡ ከመጣ በኋላ እንደገና ወደ ስጋት ያመራነው፣ እነዚያ የቆዩ ቁስሎች ባለመታከማቸው ነው፡፡
በእንዲህ ያለ ግጭት ውስጥ ያለፈ ማህበረሰብ፣ ቁስሎቹን ማከም የሚችለው፣ በእውነት ላይ የተመሰረተ፣ ፍትህን ማዕከል ያደረገ የእርቅ ሂደት ነው፡፡ የከፋ የሰብአዊ መብት የፈፀሙትን ለፍርድ አቅርቦ፣ ተሳትፎአቸው ትንሽ የሆነውን በይቅርታ አልፎ መሄድ ካልተቻለና እርስ በእርሱ በቁርሾ የተጨማለቀ፣ ቂምና በቀል በልቡ ይዞ ሚዲያ የከፈተ ጋዜጠኛ፣ ፓርቲ ያቋቋመ ፖለቲከኛ… እርስ በእርስ የሚናደፍ ማህበረሰብ ይዞ፣ ስለ ብልጽግና ወይም ሌላ ነገር ቢወራ፣ ወገብ ድረስ በማጥ ተይዞ እሽኮኮ እንዲደረግ እንደማለት ነው፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ ደረጃ፣ የነበርንበትን የማጥ ልክ አጥንቶ፣ የምንወጣበትን መንገድ ማቀድ፣ ከዚያ ጭቃው ታጥቦ ከማጡ ፀድቶ ንፁህ ሜዳ ላይ በማረፍ ስለ ብልጽግናና ስለ መደመር ማውራት ይቻላል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ አሁን ብልጽግናን፣ መደመርን እያወሩ፣ እየፃፉ ያሉት፣ እስከ ወገባቸው ድረስ ማጥ ውስጥ ሆነው ነው፡፡
የእርቅና ብሔራዊ መግባባት ኮሚሽን ተቋቁሟል፡፡ ኮሚሽኑ እርስዎ የሚሉትን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ብለው ያምናሉ?
ይሄ ኮሚሽን ሲቋቋም በራሱ ትክክለኛ አልነበረም፡፡ አንዳንዶቹ የኮሚሽኑ አባል የሆኑ ሰዎች ራሳቸው እርቅ የሚያስፈልጋቸው ናቸው:: እነዚህ ሰዎች ምናልባት የታራቂ ቡድን ውስጥ ሊገቡ የሚገባቸው ናቸው:: በእነሱ የተከፋ ሌላ ማህበረሰብ አለ፡፡ ስለዚህ በየትኛውም ግጭት ውስጥ ተሳትፎ ያልነበራቸው፤ ቅሬታ የማይቀርብባቸው አይነት ሰዎችን ነው መምረጥ የሚገባው፡፡ ኮሚሽኑ እስካሁንም ምንም መስራት አልቻለም፡፡ ከምርጫው በፊት መስራት ያለበትን አልሰራም፡፡ የፖለቲካ ሃይሎችም፣ ህዝቡም፣ ሁሉም ከማጥ ሳይወጣ ነው ምርጫው የደረሰው፡፡ ምርጫ ደግሞ በተፈጥሮው ግለት አለው፡፡ ከምርጫው በፊት ሀገሪቱ በእርቅና መግባባት ከማጥ ውስጥ መውጣት ነበረባት፡፡
አሁንስ ባለው ጊዜ ውስጥ ማድረግ አይቻልም?
ከቀረ ነገር የዘገየ ይሻላል ይባላል፡፡ አሁንም ቢዘገይም ከምርጫ በፊት ይሄን ሂደት ማከናወኑ ወሳኝ ነው፡፡ የተፈፀሙ በደሎች አደባባይ ወጥተው፣ እያንዳንዱ አጥፊ (ተጠያቂ) ይቅርታ መጠየቅ አለበት፡፡ ማን ምንድነው የፈፀመው? ማን በምን ተጠያቂ ነው? የሚለው በዝርዝር መውጣት አለበት፡፡ ይሄ ደግሞ ብዙ ጊዜ የሚፈጅ አይደለም፡፡  
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ክስ ዶክመንቶች አሉት፡፡ ከማህበረሰቡ የተሰወረ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሂደቱን ማከናወን ቀላል ነው፡፡ እያንዳንዱ ጥፋተኛ በግልጽ ይታወቃል:: በተለይ ደግሞ ቶርች የተፈፀመባቸው ሁሉ በግልጽ በጀት ተመድቦ መካስ አለባቸው:: ትልቅ የማገገሚያ ማዕከል ተቋቁሞ፣ የሥነ ልቦና ህክምና ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ነፃ ህክምና ማግኘት አለባቸው፡፡ ለታሠሩበት ዘመን፣ ላጡት ኢኮኖሚ፤  ቢያንስ መኖሪያ ቤት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ እነዚህ ሰዎች ቂም ይዘው መቀመጥ የለባቸውም፡፡
በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙዎቹ የዛሬ የፖለቲካ ተዋናዮች፣ በአንድም በሌላም ባለፈው ስርዓት ቶርቸር የተፈፀመባቸው ናቸው፡፡ ሁሉንም አንድ በአንድ ብንቆጥር፤ ጋዜጠኞቹም፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾቹም፣ ፖለቲከኞቹም በዚያ ቁስል ውስጥ ያለፉ ናቸው:: ዛሬ እንዲህ መግባባት ያቃተንም ከዚህ የስነ አዕምሮ ችግርና ቁርሾ የተነሳ ነው፡፡ ያንን ቁስል ማከም የፖለቲከኞችን፣ ጋዘጠኞችን፣ ሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ባህሪ ያሻሽላል:: ንፁህ ማህበረሰብ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ መካስ አለባቸው፤ ቂማቸው በህክምና መሻር አለበት፡፡ ይሄ ባልሆነበት ስለ እርቅ፣ ብሔራዊ መግባባት፣ ሀገራዊ አንድነት መነጋገሩ ዝም ብሎ መደነቋቆር ነው የሚሆነው፡፡ ሁሉም አሁን ውስጡ እሣት እየተቀጣጠለ ነው፤ እርስ በእርሱ የሚነጋገረው፤ ስለዚህ ያንን የሚያክም ስርዓት በሀገሪቱ ሊዘረጋ ይገባል፡፡

Read 10514 times