Saturday, 29 February 2020 12:04

ኦኤምኤን ቤተክርስቲያኒቱን ይቅርታ እንዲጠይቅ፣ ዘገባውንም እንዲያርም ማሳሰቢያ ተሰጠው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

   ኦኤምኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን አስመልክቶ የሠራውን ፕሮግራም ይቅርታ ጠይቆ እንዲያስተካክልና ቤተ ክርስቲያኒቱን ይቅርታ እንዲጠይቅ ብሮድካስት ባለስልጣን አሳሰበ፡፡
ጴጥሮሳውያን የቤተክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ህብረት ያቀረቡለትን አቤቱታ ተቀብሎ ማጣራት ማድረጉንና አቤቱታ የቀረበበት ኦኤምኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ የሰጠውን ምላሽ ማገናዘቡን የገለፀው ብሮድካስት ባለስልጣን፤ በቀረበው ቅሬታ መሠረት የቴሌቪዥን ጣቢያው ጥፋተኛ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል፡፡
የቴሌቪዥን ጣቢያው ጥር 9 ቀን 2012 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡00 እስከ 3፡30 ድረስ ኦፌኮ በገብረ ጉራቻ ከተማ ያካሄደውን ህዝባዊ ስብሰባ አስመልክቶ በሠራው ፕሮግራሙ ላይ አቶ ኃይለሚካኤል ታደሰ የተባሉ ግለሰብ ያደረጉት ንግግር ይዘት፤ የቤተክርስቲያኒቱን መብት የተጋፋና የብሮድካስት አዋጁንም የጣሰ ነው ተብሏል፡፡
አቶ ኃይለሚካኤል በፕሮግራሙ ላይ “እናንተ የኦሮሞ ወጣቶች በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንግዶች ሆናችኋል፣ ለምንድነው እንግዶች የሆናችሁት? ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን መስቀል አሳልማ፣ ፕ/ር መረራ ጉዲናን የምታገል ቤተ ክርስቲያን አንፈልግም፤ በሌሎች መርሃ ግብር ላይ ተገኝቶ የጃዋርን መርሃ ግብር የምትጠላ ቤተ ክርስቲያን አንፈልግም፤ በሃይማኖት የምትከፋፍለን ቤተ ክርስቲያን አንፈልግም፤ ኦሮሞን በጐሣ የምትከፋፍል ቤተ ክርስቲያን አንፈልግም…በቤተ ክርስቲያን ላይ እንደ ባዳ፣ እንደ ሽፍታ አልታያሁም” የሚሉ ትክክለኛነታቸው ያልተረጋገጡና ምንጫቸው የማይታወቁ መረጃዎች መቅረባቸው በብሮድካስት አዋጁ “ማንኛውም ለስርጭት የሚቀርብ ፕሮግራም ይዘቱና ምንጩ ትክክለኛ መሆኑ መረጋገጥ አለበት” የሚለውን ድንጋጌ ይጥሳል ብሏል - ብሮድካስት ባለስልጣን፡፡
በዚሁ የአቶ ኃይለሚካኤል ንግግር ላይ ቤተክርስቲያኗን “የፊውዳሎች የፖለቲካ ኤምባሲ መፍረስ አለበት” በማለት “ማንኛውም ለስርጭት የሚቀርብ ፕሮግራም የሰው ልጆችን ሰብዕና፣ ነፃነት ወይም ስነ ምግባርን የሚፃረር ወይም የሌሎችን እምነት የሚያንቋስስ መሆን የለበትም” የሚለው ድንጋጌም መጣሱን ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡
የአማኞችን ቤተ እምነት ከአምልኮ ስፍራነት በማውጣት ጨቋኝ የፖለቲካ ተቋም አድርጐ ማቅረብ የሌሎችን እምነት የሚያንኳስስ መሆኑንም ብሮድካስት ገልጿል፡፡
በተጨማሪም በእለቱ የተላለፈው ፕሮግራም ላይ ብሔርን በብሔር፣ ህዝቦችን እርስ በእርስ የሚያጋጩ መልዕክቶችም መተላለፋቸውን ባለስልጣኑ አረጋግጧል፡፡
“በቤተ ክርስቲያን ሰብራችሁ ግቡና ከእጃቸው ተቀብላችሁ እጃችሁን አስገቡ፤ ኦሮሞን ነፃ እናወጣለን፤ ደብረሊባኖስ የእናንተ ነው፤ አሁን በኋላ ደብረ ሊባኖስ ላይ የምታዝዙት እናንተ ናችሁ፤ ካሁን በኋላ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ የምታዝዙት እናንተ ናችሁ፤ እኛ ሰላሌ ላይ ቤተ ክርስቲያንን ነፃ ማውጣት አለብን” በማለት ብሔርን ከብሔር የሚያጋጭ፣ የእርስ በእርስ ግጭትን የሚያነሳሳ፣ ሠላምን የሚያደፈርስ ተንኳሽ መልዕክቶች መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል - ባለስልጣኑ፡፡
እነዚህ የጣቢያው ስህተቶች በህግ ሊያስጠይቁ ብሎም የጣቢያውን የብሮድካስት አገልግሎት ፍቃድ ሊያሰርዝ የሚችል ነው ተብሏል፡፡
ጣቢያው በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ በተጠየቀበት ወቅትም ቅሬታ የቀረበባቸው ፕሮግራሞች ሚዛናዊ ያልሆኑ፣ ትክክለኛነቱ ያልተረጋገጠ፣ የሌሎችን እምነት የሚያንኳስስ፣ ስም የሚያጠፉና በሐሰት የሚወነጀል እንዲሁም ግጭትን የሚያነሳሳና ጦርነትን የሚቀሰቅስ መልዕክት ሆኖ ሳለ “ቅሬታ አቅራቢው አካል በማይመለከተውና መብቱን በማይጋፋ ጉዳዮች ላይ ያቀረበው ቅሬታ ተቀባይነት የለውም” በማለት የሰጠው ምላሽ የህግ መሠረት የለውም ብሏል -  ብሮድካስት ባለሥልጣን፡፡
ጣቢያው ለፈፀመው የህግ መተላለፍ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ይቅርታ እንዲጠይቅ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ተመጣጣኝ ምላሽ የማቅረብ መብት አክብሮ እንዲያስተናግድና ይህንን ስለመፈፀሙም ለብሮድካስት ባለስልጣን ሪፖርት እንዲያደርግ ተወስኗል ተብሏል ባለሥልጣን መ/ቤቱ፡፡
ለወደፊት በሚያቀርባቸው ፕሮግራሞችም ጣቢያው ጥንቃቄ እንዲያደርግ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል፡፡

Read 13545 times