Saturday, 29 February 2020 11:43

የጎዳና ሴቶች የስነተዋልዶ ጤና

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

    በጎዳና ላይ ሕይወታቸውን የሚገፉ ሴቶች በስነተዋልዶ ጤና አጠባበቅ ዙሪያ ያላቸው ልምድ እና ተጎጂነት ምን ይመስላል የሚለውን የምንመለከትበት ጥናት የረዳት ፕሮፌሰር በእውነቱ ዘውዴ ነው፡፡ ፕሮፌሰር በእውነቱ ይህንን ጥናት ያቀረቡት February 18, 2020 የኢትዮጵያ የማህጸ ንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር 28ኛ ጉባኤ በተከበረበት ወቅት ነው፡፡  
የጎዳናው ሕይወት የሚለመደው በተለያየ ምክንያት መሆኑ ይታወቃል፡፡ አንዳንዶች ከቤተሰ ቦቻቸው ጋር በተለያየ መንገድ ባለመስማማት ብቻ ቤታቸውን ጥለው ወደ ጎዳና ይወጣሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ቤተሰቦቻቸው ኑሮን ለማሸነፍ በመቸገራቸው ብቻ የራሳቸውን ሕይወት በቻሉት መንገድ ለመምራት ጎዳናውን ይያያዙታል፡፡ ባጠቃላይም ከሚደርስባቸው የተለያዩ ጫናዎች እና ምርጫቸው በመሆኑ ምክንያት ጎዳናውን ከሚለምዱት ውጪም በዚያው በጎዳናው ላይ ተወል ደው በጎዳናው ላይ የሚያድጉ ፤ የእኔ ቤተሰብ እዚህጋ አለ ብለው መናገር የማይችሉ ብዙ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ሕይወታቸውን በአሳዛኝ ሁኔታ ይመራሉ፡፡
በተለይም ወደ ሴቶቹ ሁኔታ መለስ ሲባል የሚደርስባቸው ችግር እጥፍ ድርብ መሆኑን መረዳት አያስቸግርም፡፡
በጎዳና ላይ የሚኖሩ ሴቶች ለተለያዩ ማህበራዊ፤ ስነልቡናዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ከጤና ጋር በተያያዘ ችግሮች ይደርሱባቸዋል፡፡
በጎዳና ላይ የሚኖሩ ልጃገረዶች በጎዳናው ላይ ለሚዘወተሩ ልማዶች የተጋለጡ ናቸው፡፡ ሲጋራ ማጤስ፤ የተለያዩ እጾችን መጠቀም፤ አልኮሆል መጠጣት፤ የንብረት መዘረፍ ወይንም በፍራቻ የተጠየቁትን የግላቸው የሆነ ንብረት መስጠት፤ ወሲባዊ ጥቃት፤ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ለአስከፊ የጤና ችግር የሚያጋልጣቸውን የወሲብ ስራን ከተለያዩ ወንዶች ጋር እንደደንበኞ ቻቸው ፍላጎት መፈጸም፤ ላልታቀደ እርግዝና መጋለጥ የመሳ ሰሉትን ችግሮች እንዲጋፈጡ ያደርጋቸዋል፡፡
በጎዳና ላይ የሚኖሩ ሴቶች በቤት ውስጥ ከሚኖሩት እጅግ በበለጠ ጥቃት የሚደርስባቸው ሲሆን የዚህም ልዩነት ሲገመት እንደሚደርሰው ጉዳት ምናልባትም ከ2-4 እጥፍ ሊባል የሚችል ነው፡፡  
በጎዳና ላይ ላሉ ሴት ልጆች ተገዶ መደፈር ከእለታት በአንድ ቀን የሚከሰት ድንገተኛ ነገር ሳይሆን እንደ ሚኖሩበት አካባቢ በየእለቱ ቀንም ሆነ ማታ በማንኛውም ወንድ አማካኝነት ሊደርስባቸው የሚችል በአስከፊነት ከሚገለጸው የህይወታቸው አካል አንዱ ነው ተብሎ ይታ መናል፡፡ የፕሮፌሰር በእውነቱ ጥናት እንደሚጠቁመው ከሆነ በኢትዮጵያ ደሴ ከተማ ቀደም ሲል የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው፡-
ለግብረስጋ ግንኙነት ከደረሱት በጎዳና ላይ ከሚኖሩት ሴት ወጣቶች 25% የሚሆኑት ያልተፈለገ እርግዝና እንደገጠማቸው ይጠቁማል፡፡
በኢትዮጵያ ዋና ዋና ከተሞች በጎዳና ላይ ያሉ ሴቶች አንድ ወይንም ከዚያ በላይ ህጻን ልጅ ታቅፈው ወይንም አዝለው መንገደኛን ዳቦ መግዣ ሲለምኑ ማየት የተለመደ ነው፡፡
የጎዳና ሴቶች በሚደርስባቸው ተገዶ የመደፈር ጉዳት ምክንያት የሚከተለው ያልተፈለገ እርግዝና ለሌላ የስነተዋልዶ ጤና መቃወስ እና በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት ለሚተ ላለፉ በሽታዎች መጋለጥ እንዲሁም ደህንነቱ ያልተጠበቀ የጽንስ መቋረጥን ሊያስከትል እንደሚችል …ወዘተ የተለያዩ መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡
የተለያዩ ጥናቶች እንደሚጠቁሙትም በጎዳና ላይ የሚኖሩ ሴቶች በተገቢው መንገድ የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት ከሚሰጥባቸው የጤና ተቋማት ሄደው የመገልገላቸው ነገር ብዙም የማይታሰብ መሆኑን እና ኑሮአቸውና በአካባቢያቸው ያለው ህብረተሰብ የኑሮ ዝቅተኛነት ወደሚመራቸው በመሄድ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የፕሮፌሰር በእውነቱ የጥናት ወረቀት ያሳያል፡፡ይህንንም ምክንያት በማድረግ ጥናቱ በተለይም በሻሸመኔ  ከተማ ያሉ የጎዳና ላይ ሴቶች ምን ያህል የስነተዋልዶ ጤናቸው ይቃወሳል ? ምን ያህል ጉዳት ይደርስባቸዋል የሚለውን ለመመልከት የታቀደ መሆኑን ጥናት እቅራቢው ይገልጻሉ፡፡
1-ወሲብ መፈጸምና ኤችአይቪ ኤይድስ በጎዳና ሴቶች፤
ጥናቱ በተደረገበት ሻሸመኔ ከተማ ጎዳና ላይ የሚኖሩ ሴቶች ኤችአይቪ ኤይድስን በሚመለከት ጥሩ ንቃተ ህሊና አላቸው፡፡ ቫይረሱ በምን መንገድ ከሰው ወደሰው እንደሚተላለፍም ያውቃሉ፡፡ጥንቃቄ የጎደለው ግብረስጋ ግንኙነት ምን ያህል ለበሽታው እንደሚያጋልጥም ብዙዎቹ ያውቃሉ፡፡ በሻሸመኔ ጎዳና ላይ ይሉ ሴቶች ጤናቸውን ለመጠበቅ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ሲሆን በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ተመርምሮ እራስን ማወቅን አምነውበት ፈጽመውታል፡፡በእርግጥ በጥናቱ ተሳታፊ በነበሩት መካከል ቫይረሱ በደማቸው ያላቸው ሴቶች ቁጥር ቀላል የማይባል ነው፡፡   
2-ጽንስ የማቋረጥ ድርጊት በጎዳና ላይ በሚኖሩ ሴቶች፤
በእርግጥ ጥናቱ በተካሄደበት አካባቢ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥን እንደማይደፍሩት የሚገልጹ አሉ፡፡ እንዲያውም ወደ 90.5 % የሚሆኑት መላሾች ጎዳና ላይ መኖር ከጀመሩ ጀምሮ ፈጽመውት እንደማያውቁ ገልጸዋል፡፡
አብዛኞቹ መላሾች ግን ጽንስን ማቋረጥን በህክምና ተቋም እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች እንደሚ ፈጽሙት ተናግረዋል፡፡ በጥናቱ ከተካተቱት መላሾች (35.7%) ያህሉ በጤና ተቋም ሳይሆን ድርጊቱን በሚፈጽሙ ሰዎች ቤት (21.4%) ጎዳናው ጥጋጥግ ከለል ያለ ቦታ (21.4%) ዛፎች ካለባቸውና ሰው እንደልብ ከማያሳዩ ቦታዎች በመሄድ (7.1. %)ጽንስ ማቋረጥን ከሚሰሩ አካባቢዎች በመሄድ እንደሚፈጽሙት ተናግረዋል፡፡  
3-ተገዶ መደፈር ከጎዳና በሚኖሩ ሴቶች ላይ፤
በሻሸመኔ ጎዳና ላይ የሚኖሩ ሴቶች ተገዶ መደፈርን እንደችግር የማያዩትና አጋጣሚውም ብዙም እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ ለጥናቱ መልስ ከሰጡት (88.5%) የሚሆኑት በጎዳና ላይ በኖሩባቸው ጊዜያት በጭራሽ ተገደው ተደፍረው እንደማያውቁ መስክረዋል፡፡ ነገር ግን ጎዳና ላይ በሚኖሩ ሴቶች ሕይወት ውስጥ ይህ ተገዶ መደፈር እንደ አንድ አስቸጋሪ ነገር በተለምዶ የሚቆጠር መሆኑንና አንዳንድ ጊዜ ከሚያርፉባቸው ቦታዎች ጋር የሚያያዝ መሆኑን ይጠቅ ሳሉ፡፡ ለምሳሌም በጎዳናው ጥጋጥግ ብርሀን በሌለባቸው ወይንም አቋራጭነታቸው በሚያስፈሩ እና ሰው በማይመላለስባቸው ቦታዎች የሚያርፉ፤ ወይንም ደግሞ በእምነት ተቋማት አጥር ግቢ ውስጥ የመሳሰሉት ቦታዎች የሚተኙ ሴቶች ተገዶ ለመደፈር ሊያጋልጣቸው ይችላል ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ወለል ያለውን ጎዳና እንደመኖሪያ የሚጠቀሙ ወይንም በመጠኑ ማረፊያ የሚሆኑ ቦታዎችን ተከራይተው የሚኖሩ በጭራሽ ተገደው አይደፈሩም ብለዋል፡፡  
አንዲት የጎዳና ሴት በሻሸመኔ ከተማ የሚከተለውን መልስ ሰጥታለች፡፡
‹‹……እኔ ሁልጊዜም የምተኛው በኬሻ ቤት ውስጥ በቀን አስር ብር እየከፈልኩ ነው፡፡በኬሻው ቤት ወንዶችና ሴቶች የሚያርፉባቸው የተለያዩ ናቸው:: የኬሻው ቤት ለእኔ ደህንነቴን ለመጠበቅ በጣም ረድቶኛል፡፡ ወንዶች በዚህ መንገድ እራሳቸውን የሚጠብቁ ሴቶችን በጭራሽ አይዳፈሩም፡፡ በቀን ተሯሩጬ ከማገኘው ውስን ገንዘብ ይህን ያህል ኪራይ በቀን የምከፍለው ለደህንነቴ ስል ነው፡፡ ስዚህም እኔ ደህና ነኝ፡፡›› ብላለች፡፡
ከዚህ መረዳት የሚቻለው በጎዳና ላይ እየኖሩ ያገቡ ሴቶች ሌሎች ለችግር እንዳይጋለጡ መንገድ የሚያሳዩ መሆኑ እና በጎ የሆነውን ልምዳቸውን በማካፈል የጎዳና ሴቶች እራሳቸውን ከአደጋ እንዲከላከሉ ማስቻላቸውን ነው፡፡ በአካባቢው የሚኖሩ የጎዳና ወንዶች በሚያስከትሉ ዋቸው ችግሮች ምክንያትም የሚነሳውን ጩኸት በመከተል እርዳታ የሚደረግበት የጉርብትና አይነት አብሮ መኖርም ይስተዋላል፡፡  
በጥናቱ እንደተረጋገጠው በጎዳና ላይ የሚኖሩ ሴቶች የስነተዋልዶ ጤና ችግርን የመከላከል ስራ አነስተኛ መሆኑን እና ሴቶቹ ግን በአኑዋኑዋራቸው የተነሳ በሚደርስባቸው የጤና እውክታ የሚጎዱ መሆኑን ነው፡፡ ኤችአይቪን በሚመለከት የመተላለፊያ መንገዱን በሚመለከት ያለው ንቃተ ሕሊና ከፍ ያለ ቢሆንም እራስን ተመርምሮ የማወቅ እና የምክር አገልግሎት የማግኘቱ ጉዳይ ዝቅተኛ ነው፡፡ ባጠቃላይም በጎዳና ላይ ያሉ ሴቶች የስነተዋልዶ ጤና ሁኔታ መንግስታ ዊም ይሁን መንግስታዊ ያልሆኑ እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሊያደርጉበት የሚገባ እንዲሁም የስነልቡናና ማህበራዊ እገዛ በተለይም ለጎዳና ላይ ሴቶች የስነተዋልዶ ጤናን አገልግሎት በተገቢው ማቅረብ የሚገባ መሆኑን ጥናቱ ያብራራል፡፡     Read 11650 times